Friday, July 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አየር መንገድንና ኤርፖርቶች ድርጅትን ለማዋሀድ ሐሳብ ቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድንና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትን ለማዋሀድ ለመንግሥት ሐሳብ ቀረበ፡፡

ታማኝ የዜና ምንጮች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አየር መንገዱ በፍጥነት በማደግ ላይ በመሆኑ የሚጠይቀው የተቀላጠፈ የኤርፖርት አገልግሎትና መሠረተ ልማት እያደገ በመምጣቱ፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የአየር መንገዱን ፍላጎት ለማሟላት ባለመቻሉ ሁለቱን ተቋማት ለማዋሀድ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች በአዲስ አበባና በክልል በሚገኙ ኤርፖርቶች መሠረታዊ የሆኑ የኤርፖርት መሠረተ ልማቶች መጓደልና የተቀላጠፈ አገልግሎት ችግር ላይ ምሬታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በበኩሉ የአየር መንገዱን ፍላጎት ማሟላት ያልቻለው በረዥም የመንግሥት የግዥ ሒደት መመርያ እንደሆነ ሲያስተባብል ቆይቷል፡፡

የአየር መንገዱ ፈጣን ዕድገት እንዳይደናቀፍ በማሰብ ሁለቱን ተቋማት በአንድ አስተዳደር ሥር ለማድረግ የሚያስችል ጥናት እንደተሠራና በቅርቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በቀረበው ጥናት ላይ ተመርኩዞ ምክር ቤቱ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጀት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ዳዊት ጉዳዩን በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ከመንግሥት የደረሳቸው ደብዳቤ ስለሌለ ምንም እንደማይሉ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድም ተክሉ ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸው፣ ድርጅታቸው አዲስ የኩባንያ የንግድ ምልክት በማዘጋጀት ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ስለተጠቀሰው የሁለቱ ተቋማት ውህደት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ሪፖርተር ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንደሚሰጠው የተገለጸ ቢሆንም፣ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ዓርብ ሐምሌ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ሌሊት ድረስ ምላሹ አልደረሰም፡፡

ምንጮች ግን ሁለቱን ድርጅቶች የማዋሀድ ሐሳብ ለመንግሥት ቀርቦ ይሁንታ ማግኘቱና የጥናቱ ሐሳብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ለማፀደቅ በሒደት ላይ እንደሆነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈቀዱ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈጣን ዕድገት በአየር መንገዱ በራሱ ላይ፣ በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትና በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ላይ ከፍተኛ ጫና እንደፈጠረ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት መጠነ ሰፊ አዳዲስ የኤርፖርቶች ግንባታና የነባር ኤርፖርቶች ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች እያካሄደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አሠራሩንም በማዘመን ላይ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ መሠረተ ልማቶችን አየር መንገዱ በሚፈልግበት ፍጥነት ለማሟላት የሚቸገረው መከተል የሚገባው ረዥም የመንግሥት የግዥ መመርያ በመኖሩ ነው ብለዋል ኃላፊዎቹ፡፡

የሁለቱን ተቋማት ውህደት አስመልክቶ ሪፖርተር ለትራንስፖርት ሚኒስቴር ያቀረበው ጥያቄም በወቅቱ ምላሽ አላገኘም፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የመዋሀድ ሐሳብ ሌሎች አየር መንገዶችን ሥጋት ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከሚበሩ የውጭ አየር መንገዶች መካከል የአንዱ አየር መንገድ ሥራ አስኪያጅ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኤርፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋምና አየር መንገድ የተለያዩ መሆን ይገባቸዋል ይላሉ፡፡ ‹‹የሁለቱ ድርጅቶች መዋሀድ የጥቅም ግጭት ያስከትላል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤርፖርቱን ካስተዳደረው ሁሉንም አየር መንገዶች በእኩል ያስተናግዳል ወይ የሚል ሥጋት ጭሮብናል፡፡ ተፎካካሪዎቹን በሚገባ ያስተናግዳል ወይ የሚል ጥያቄ ይነሳል፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው ሥጋት የገባቸው መደበኛ ያልሆኑ የበረራ አገልግሎት የሚሰጡ የግል አየር መንገዶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ የግል አየር መንገዶች አንዱ ባለቤት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብሔራዊ አየር መንገድ በመሆኑ በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትም ሆነ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከፍተኛ ድጋፍ ይደረግለታል፡፡ ‹‹በተለይ በኤርፖርት አካባቢ እኛ ላይ አድልኦ እንደሚፈጸምብን ስናመለክት ቆይተናል፡፡ አሁን አየር መንገዱ ኤርፖርቶችን የሚያስተዳድር ከሆነ እኛን ያጠፋናል፤›› ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አንድ አካል የነበረ ሲሆን፣ በ1995 ዓ.ም. ራሱን ችሎ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት 23 ኤርፖርቶችን የሚያስተዳድር ሲሆን፣ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች መጠነ ሰፊ የኤርፖርቶች ግንባታ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ ከ1,600 በላይ ሠራተኞች ያሉት በመሆኑ፣ ከአየር መንገዱ ጋር ከተቀላቀለ ከሥራ እንቀነሳለን የሚል ሥጋት በሠራተኞች ዘንድ እንደተፈጠረ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች