Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየላስታ ላሊበላ ቅኝት

የላስታ ላሊበላ ቅኝት

ቀን:

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ላሊበላ ውስጥ በሚገኝ አንድ አዳራሽ በቅርስ ጥበቃ ዙሪያ የተዘጋጀ ውይይት ለማካፈል የተገኙ ታዳሚዎች ሙሉ ትኩረታቸውን መድረኩ ላይ አድርገዋል፡፡ በአማራ ክልል ባህላዊ አልባሳትና ጌጣ ጌጦች የተዋቡ ወጣቶች መድረኩን ተቆጣጥረውታል፡፡ ሴት ተወዛዋዦችና በአንድ ወገን ወንዶቹ በተቃራኒያቸው ሆነው እስክስታውን ተያይዘውታል፡፡ ከበስተኋላቸው መሰንቆ፣ ከበሮ፣ ዋሽንትና ክራር በስሜት የሚጫወቱ ወጣቶችና ድምፃዊው አጅቧቸዋል፡፡ መድረኩ ላይ የተሰጣቸው ጊዜ ሲጠናቀቅ በደመቀ ጭብጨባ አድናቆቱን የገለጹላቸውን ታዳሚ እጅ ነስተው ወደ መልበሻ ክፍል አመሩ፡፡

ቁና ቁና እየተነፈሱ፣ እርስ በርስ እየተደጋገፉ መልበሻ ክፍሉ ውስጥ ተሰባሰቡ፡፡ አልባሳቱና ጌጣ ጌጣቸውን አውልቀው ለአስተባባሪያቸው እያስረከቡ ስላቀረቡት ትርዒት ያወጉ ነበር፡፡ ሳቅና ጨዋታቸው በአንድ የባህል ቡድን አብሮ ከመሥራት ባለፈ ወዳጆች መሆናቸውንም ያሳብቃል፡፡ ቡድኑ 24 አባላት ያሉት የላስታ ላሊበላ የባህል ቡድን ሲሆን፣ ሮማን ቢሆነኝና ውበት ጤናው ከአባላቱ መካከል ናቸው፡፡

ላሊበላ ተወልዳ ያደገችው ሮማን 21 ዓመቷ ሲሆን፣ ውዝዋዜ የጀመረችው የቅርብ ጓደኛዋን በመመልከት ነበር፡፡ አባቷ ተወዛዋዥ እንድትሆን ባይፈቅዱም የሙያው ፍቅር ስላሸነፋት የኪነ ጥበብ ቡድን ተቀላቅላ ችሎታዋን ታዳብር ጀመር፡፡ ላስታ ላሊበላ የባህል ቡድን በ2006 ዓ.ም. የሥራ ማስታወቂያ ሲያወጣ ለሮማን መልካም አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ መግቢያ ፈተናውን አልፋ ቡድኑን ከተቀላቀለች ሁለት ዓመት አስቆጥራለች፡፡

ላስታ ላሊበላ የባህል ቡድን የተቋቋመው በ2004 ዓ.ም. 14 ወጣቶችን በማሰባሰብ ነበር፡፡ በወቅቱ በተወዛዋዥነት፣ በሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችነትና ድምፃዊነት የተቀጠሩ የቡድኑ አባላት ወርኃዊ ደመወዝ 450 ብር ብቻ ነበር፡፡ ለመድረክ የሚጠቀሙባቸው መሣሪያዎች እምብዛም ካለመዘመናቸው በተጨማሪ አባላቱ ሙያቸውን የሚያዳብር ሥልጠና ለማግኘት ይቸገሩም ነበር፡፡ አሁን ነገሮች መሻሻል እያሳዩ ሲሆን፣ በቡድኑ 12 ተወዛዋዦች፣ ስድስት ድምፃውያንና ስድስት የሙዚቃ መሣሪያ  ተጫዋቾች አሉ፡፡ አባላቱ ከ1,600 እስከ 2,500 ብር የሚከፈላቸው ሲሆን፣ አልፎ አልፎም ቢሆን ሥልጠና የሚያገኙበት ዕድል ተመቻችቶላቸዋል፡፡

ሮማን እንደምትናገረው፣ የባህል ቡድኑ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እየተጋበዘ ሥራዎቻቸውን ማቅረባቸው በሙያው ከብዙዎች እንዲተዋወቁ መንገድ ፈጥሮላቸዋል፡፡ ቡድኑ እያተረፈ የመጣው ዕውቅና በሙያው የምትፈልግበት ቦታ እንድትደርስ እያገዛትም ነው፡፡ ‹‹በቅርቡ ወልዲያና ቆቦ ሄደን ነበር፡፡ ቆቦ የባህል ፌስቲቫልና ውድድር ለመሳተፍ ነበር የሄድነው፡፡ ጉዞዎቹ ከሌሎች የባህል ቡድኖች ጋር ተገናኝተን ልምድ እንድንለዋወጥ መንገድ ይከፍታል፤›› ትላለች፡፡

በአካባቢው ከሚዘወተሩ ባህላዊ ውዝዋዜዎች መካከል ሶራ ስትጫወት ደስ እንደሚላት ተወዛዋዧ ትገልጻለች፡፡ ‹‹ሶራ ስመታው ይቀለኛል፡፡ ሰው ሲመለከተው ደስ ስለሚለውም እወደዋለሁ፤›› ትላለች፡፡ ትርዒት ሲያቀርቡ በርካታ ታዳሚዎች ባውሽ የሚባለውን ውዝዋዜ እንዲያሳዩዋቸው ይጠይቃሉ፡፡ በብዙዎች ዘንድ ዕውቅና እያተረፈ ያለውን ባውሽ ሮማንና ጓደኞቿ ሲጫወቱም በደስታ ነው፡፡ ‹‹በአማራ ክልል ከሚዘወተሩ ውዝዋዜዎች መካከል በጣም የሚወደዱትን ለታዳሚዎች እናሳያለን፤›› ስትል ታስረዳለች፡፡

የባህል ቡድኑ አባላት ልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች ሲካሄዱ ተፈላጊ መሆናቸው ቢያስደስትም፣ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ነው ለማለት ትቸገራለች፡፡ በቤተሰቦቻቸውና በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድም ሙያው ተገቢውን ክብር አለማግኘቱ ይፈታተናቸዋል፡፡ ‹‹በተለይም ሴት ተወዛዋዦች ላይ ፈተናው ይበረታል፡፡ ሙያውን ስለምወደው ግን ፈተናዎቹ አላገዱኝም፤›› ትላለች፡፡ በቡድኑ የሚከፈላቸው ገንዘብ በቂ እንዳልሆነና በሚፈለጉት መጠን ሥልጠና እንደማያገኙም ታክላለች፡፡

ሮማን በውዝዋዜው ዘርፍ ዕውቅ ባለሙያ የመሆን ህልም አላት፡፡ በተለይም ላስታ ላሊበላና ሌሎችም የባህል ቡድኖች ያፈሯቸው ታዋቂ ባለሙያዎችን ስትመለከት ተስፋዋ ይለመልማል፡፡ የላስታ ላሊበላ የባህል ቡድን ማሲንቆ ተጫዋችና ድምፃዊ ሰጠ ዘበኛ ‹‹ባውሽ ላስታ›› የተሰኘ ነጠላ ዜማውን እንደለቀቀ ነበር ዘፈኑ ተወዳጅነት ያገኘው፡፡ ድምፃዊው በተለያዩ መድረኮች ሥራውን የማቅረብ ዕድል ሲያገኝ የባህል ቡድኑ አባላትም አብረውት ይጓዛሉ፡፡ ሮማን በሙያው መድረስ የምትፈልግበትን ያሳዩኛል ከምትላቸው ወጣቶች መካከልም ሰጠ ይጠቀሳል፡፡

ሌላው የቡድኑ አባል ውበትም ሐሳቧን ይጋራል፡፡ እንደ ላስቱ ሞላ (በካሳሁን ታዬ ሶራ ዘፈን ታዋቂ የሆነችው) እና ሶሪት በተባለ ዘፈኑ የሚታወቀውን ጋሻው ምሥጋናውን እንደ ምሳሌ ይጠቅሳል፡፡ ከላስታ ላሊበላ የባህል ቡድን ወጥተው አገር አቀፍ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ያተረፉ ወጣቶች ተስፋ እንደሚሰጡት ይናገራል፡፡

ላሊበላ የተወለደው የ22 ዓመቱ ውበት፣ አብዛኛውን ልጅነቱን ያሳለፈው፣ ሠርግ ባለበት ቤት እየሄደ በመወዛወዝና በየዓመቱ ለጥምቀት በዓል በመጨፈር እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ውዝዋዜን በሙያነት የያዘው ከአምስት ዓመት በፊት ጀንበር ባህልን  ጠብቅ የተባለ የባህል ቡድን ከጓደኞቹ ጋር ሲያቋቁሙ ነበር፡፡ ቡድኑ በቂ የሙዚቃ መሣሪያና አልባሳት ባይሟሉለትም ባላቸው ነገር እየተጠቀሙ ትርዒት ከማሳየት ወደ ኋላ አላሉም፡፡ በአካባቢው ከጀንበር በተጨማሪ አድማስ የተባለ የባህል ቡድንም እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር፡፡ ላስታ ላሊበላ የሁለቱን ቡድኖች አባላት አጣምሮ መሥራት ከጀመረም አራት ዓመታት አገባዷል፡፡

‹‹ወረዳው አድማስና ጀንበር ቡድኖችን በመጠኑ ቢደግፍም በቂ አልነበረም፡፡ የየግላችንን አልባሳትና ቁሳቁስ ተጠቅመን በየቀበሌው እየሄድን ድራማ እናሳይ ነበር፡፡ ላስታ ላሊበላ የተሻለ ግብዓት አቅርቦልናል፤›› ይላል፡፡ ከቀደሙት ዓመታት አንፃር በባህል  ፌስቲቫሎችና ውድድሮች የመሳተፍ ዕድል ማግኘታቸውንም እንደ ለውጥ ይጠቅሳል፡፡ በወረዳ፣ በዞንና በክልል ደረጃ ባሉ ውድድሮች ማሸነፍ የገንዘብና የቁሳቁስ ሽልማት ለማግኘት ያስችላል፡፡ ሆኖም ሙያውን ከዘልማዳዊ መንገድ በዘለለ በትምህርት በመደገፍ ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን ይገልጻል፡፡ የባህል ቡድኑ አባላት በተወሰነ ጊዜ ኮንትራት ብቻ ሳይሆን በቋሚነት የሚቀጠሩበት አሠራር ቢኖር መልካም መሆኑንም ያክላል፡፡

‹‹የአካባቢዬን ባህል አስተዋውቄ እኔም ብታወቅ ደስ ይለኛል፤›› የሚለው ውበት፣ ቱባ ባህሉን በማስተዋወቅ ወደ ገቢ ማግኛነት መለወጥ እንደሚቻል ያምናል፡፡ ሁሌም መድረክ ላይ ሆኖ ሲጨፍር የሚሰማውን ሐሴት ለመግለጽም ይቸገራል፡፡ ከላስታ ላሊበላ የባህል ቡድን በተጨማሪ ላሊበላ ከተማ ውስጥ ታዋቂ በሆነው ቶርፒዶ ጠጅ ቤት ምሽት ላይ ይሠራል፡፡

እንደ ቶርፒዶ ባሉ ባህላዊ የምሽት ክለቦች መሥራት፣ የባህል ቡድኑን አባላት ዕውቅና እንደሚጨምረው የሚናገረው የላስታ ላሊበላ የባህል ቡድን የሙዚቃና የውዝዋዜ ኃላፊ አቶ ተስፋ ቀለሙ ነው፡፡ ቱሪስቶች ላሊበላን ከጎበኙ በኋላ ምሽት ላይ ወደ ቶርፒዶ ጎራ ማለታቸው ስለማይቀር፣ የቡድኑ አባላት በክለቡ መሥራታቸው በገንዘብም ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ያስረዳል፡ ‹‹አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ዕውቅናም የሚያገኙት ከሕዝብ ጋር የሚገናኙባቸው መድረኮች ሲበራከቱ ነው፤›› ይላል፡፡

ጎብኚዎች ወደ ላሊበላ ሲሄዱ ከሚያገኟቸው ግዙፍ ታሪካዊ ቅርሶች  ጎን ለጎን የአካባቢው ማኅበረሰብ መገለጫ የሆኑ ባህላዊ እሴቶችንም የሚመለከቱበት መድረክ እንደሚያስፈልግ ይናገራል፡፡ ‹‹ከቅርሶቻችን በተጨማሪ የአካባቢያችን ቱባ ባህላዊ እሴቶች ባውሽ፣ ሶራ፣ ጀልጅሉ መተዋወቅ ይችላል፤›› ሲል ያስረዳል፡፡

ቡድኑ ዘላቂ የቱሪዝም ልማት በተባለ ፕሮጀክት የሙዚቃ መሣሪያዎችና ለአባላቱ የሥልጠና ድጋፍም አግኝቶ ነበር፡፡ ሆኖም ተከታታይነት ያለው ሥልጠና አለመኖሩ ሙያው ከልምድ ባለፈ በንድፈ ሐሳብ እንዳይደገፍ ማገዱን አቶ ተስፋ ይናገራል፡፡ የሙዚቃና ውዝዋዜን ንድፈ ሐሳብ ለአባላቱ በማስተማር ሥራቸውን በሳይንሳዊ መንገድ እንዲያከናውኑ ለማስቻል ይሞክራል፡፡ በሙያው የበቁ ተጨማሪ አሠልጣኞች ለማግኘት ያለውን ውጣ ውረድ ሳይጠቅስ ግን አያልፍም፡፡

የላስታ ላሊበላ የባህል ቡድን የሙዚቃ መሣሪያዎችን ይዞ በአባጣ ጎርባጣ በተሞላ አካባቢ ትርዒት ማሳየት ፈታኝ ነው፡፡ የመለማመጃ ቦታ ማግኘትም የሚያዳግትበት ወቅት አለ፡፡ ‹‹የኛ አካባቢ ጭፈራ አቅም ስላለው በዞንና በክልል መድረክም በብዛት እንጋበዛለን፡፡ ይህም ልጆቹን ያበረታታል፤›› ሲል ሁኔታውን ይገልጻል፡፡ ከሙዚቃና ውዝዋዜ በተጨማሪ በሥነ ጽሑፍና ቴአትር ዘርፍ እንዲሠሩ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ያክላል፡፡

በእርግጥ በማኅበረሰቡ ዘንድ ሙያው ተገቢ ክብር ባይሰጠውም፣ ወጣት ባለሙያዎችም የሚጠበቅባቸውን ያህል ጠንክረው እንደማይሠሩ አቶ ተስፋ ይናገራል፡፡ ‹‹የአሁኑ ትውልድ አማተር ማኅበራት ገንዘብ ተኮር ናቸው፡፡ ከቀድሞዎቹ ጋር ሲነፃፀሩ የሙያው ፍቅር ፈንቅሏቸው ራሳቸውን ለሙያው አሳልፈው የሚሰጡ ብዙ አይደሉም፤›› ይላል፡፡

ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ወጣቶቹ ሙሉ በሙሉ ለሙያው ተሰጥተው እየሠሩ፣ ቤተሰቦቻቸው፣ ማኅበረሰቡና መንግሥትም ሊደግፋቸው እንደሚገባ ያመለክታል፡፡ አልባሳትና ቁሳቁስ በማሟላት፣ መለማመጃ ቦታ በመስጠት፣ ወጣቶቹ ዘላቂነት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ በማስቻል ረገድም መሠራት አለበት፡፡ ወጣቶቹ አካባቢያቸውንና ራሳቸውንም የሚያስተዋወቁባቸው መድረኮች ተስፋፍተው በሚወዱት ሙያ ስኬታማና ትርፋማ እንዲሆኑም በሮች ሊከፈቱላቸው የግድ ይላል፡፡

በክልሉ እንደ ላስታ ላሊበላ ሁሉ በባህሉ ዘርፉ እየሠሩ ካሉ ቡድኖች ወሎ ላሊበላ በዋነኛነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ጉባ ላፍቶ፣ ወሎ ባህል አምባ፣ ራያ ቆቦ፣ ሰባቱ ዋርካና ፋሲለደስም ይገኙበታል፡፡ ፋሲለደስ የባህል ቡድን በአዲስ መልክ የተቋቋመ ሲሆን፣ ተመሳሳይ መጠሪያ ያለውን የቀድሞ የባህል ቡድን ያስታውሳል፡፡ በ1969 ዓ.ም. የተመሠረተው የቀድሞ ፋሲለደስ ኪነት ዝነኞቹን እንዬ ታከለና ይርጋ ዱባለ ያፈራ ነበር፡፡ ዛሬም በየአካባቢው ችሎታ ያላቸው ወጣቶችን ያሰባሰቡ እንደ ላስታ ላሊበላ ያሉ የባህል ቡድኖች እየተበራከቱ ሲሆን፣ ምን ያህል እንቁ ባለሙያዎችን ያፈራሉ? የሚለውን ጥያቄ ጊዜ ይመልሰዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...