ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና 16 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመጪው ሐምሌ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ድርድር ለመጀመር ተስማሙ፡፡
ፓርቲዎቹ ዓርብ ሐምሌ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ለመደራደር በዘረዘሯቸው 12 ርዕሶች ላይ አምስት ሰዓታት የፈጀ ውይይት አካሂደዋል፡፡
ለድርድር ከዘረዘሯቸው 12 ነጥቦች የትኛው ቅድሚያ ይሰጠው በሚለው ላይ ታዛቢዎችን ያሰለቸ ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ በመጨረሻ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ቅድሚያ ተሰጥቶት ለድርድር እንዲቀርብ ወስነዋል፡፡
በቀጣይነትም የምርጫ አዋጅ ቁጥር 532/2000 ለድርድር እንዲቀርብ፣ በሦስተኛነት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥነ ምግባር አዋጅ፣ በአራተኛነት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ በቅደም ተከተል ውይይት እንዲደረግባቸው ተስማምተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ተሻለ ሰብሮ የመጀመሪያ የድርድር ርዕስ እንዲሆን በከፍተኛ ደረጃ የሞገቱበት ብሔራዊ መግባባት የሚለው ርዕስ፣ በመጨረሻ የድርድር አጀንዳነት እንዲቀመጥ በአብላጫ ድምፅ ተወስኗል፡፡
ድርድሩ ሐምሌ 17 ቀን ከመጀመሩ በፊት በሚውለው ሳምንት ማለትም ከሰኞ ሐምሌ 10 ቀን እስከ ዓርብ ሐምሌ 14 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ በፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ ላይ ሊሻሻሉ ይገባል የሚሏቸውንና የመፍትሔ ሐሳቦቻቸውን ዘረዝረው በጽሑፍ ለአደራዳሪ ኮሚቴ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
አደራዳሪ ኮሚቴው በጽሑፍ የቀረቡለትን ዝርዝር ነጥቦች ለኢሕአዴግ በማቅረብ፣ ከሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ መልስ በመስጠት ድርድሩን ለመጀመር ቀጠሮ ተይዟል፡፡