- የሕግ ሰነዱ የክልሎችን ሥልጣን ይጥሳል ብሏል
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የትራንስፖርት ቢሮ በቅርቡ ለፓርላማ በቀረበው የመንጃ ፈቃድ (የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ) ረቂቅ አዋጅ እርማት ሳይደረግበት እንዳይፀድቅ አሳሰበ፡፡
የክልሉ የትራንስፖርት ቢሮ ረቂቅ ሕጉን ላመነጨው የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን በዋናነት፣ እንዲሁም በግልባጭ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ ከክልሎች ሥልጣን ጋር የሚጋጩ የረቂቅ አዋጁ አንቀጾችን በመጥቀስ ማስተካከያ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡
ሰኔ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ አዋጅ የተፈጻሚነት ወሰን በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ በረቂቅ ሰነዱ አንቀጽ ሁለት ንዑስ አንቀጽ 18 ላይ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ የመስጠት ሕጋዊ መብት የሚኖረው፣ በኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለሥልጣን የዕውቅና ሠርተፊኬት የተሰጠው የመንግሥት አካል እንደሚሆን ይገልጻል፡፡ ይህንን ረቂቅ አዋጅ በመጀመሪያ ንባብ የተመለከተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዝርዝር ዕይታ ለሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ይህንን ያስተዋለው የኦሮሚያ ክልል የትራንስፖርት ቢሮ ረቂቅ አዋጁ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ያላገናዘበና የክልሎችን መብት የሚጥስ መሆኑን በመጥቀስ ማስተካከያ እንዲደረግበት፣ አዋጁን ላመነጨው ባለሥልጣንና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሳሰቢያ ጽፏል፡፡
‹‹በሕገ መንግሥቱ መሠረት የፌዴራላዊ መንግሥት አወቃቀር እየተከተልን እንገኛለን፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50 ላይም የመንግሥት ሥልጣን በፌዴራልና በክልል መንግሥታት የሕግ አውጭነት፣ የሕግ አስፈጻሚነትና የዳኝነት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህንንም መሠረት በማድረግ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት የሕግ አውጪ አካላት በርካታ ሕጎች ወጥተው በመተግበር ላይ ናቸው፤›› በማለት የክልሉ የትራንስፖርት ቢሮ የላከው ደብዳቤ ያስታውሳል፡፡
ይሁን እንጂ የተጠቀሰው ረቂቅ አዋጅ በክልሎች ሊሠሩ የሚገባቸውን ሥራዎች ከግምት ያላስገባና ለመተግበርም አስቸጋሪ ሆኖ የተዘጋጀ በመሆኑ ማስተካከያ እንዲደረግበት ጠይቋል፡፡
በማሳያነትም የተለያዩ የረቂቅ አዋጅ አንቀጾችን ጠቅሷል፡፡ ለአብነት ያህል የረቂቁ አንቀጽ 2(18) የፈቃድ ሰጪ አካላትን ትርጓሜ ሲያስቀምጥ በባለሥልጣኑ የዕውቅና ሠርተፊኬት የተሰጠው የመንግሥት አካል ማለቱ፣ በአንቀጽ 6(2) (3) ባለሥልጣኑ የዕውቅና ፈቃድ ሰጪ አካል ማሟላት የሚገባውን መሥፈርት እንደሚያወጣ መግለጹ፣ የፈቃድ ሰጪ አካላትን ስለማገድና ስለመሰረዝ መግለጽ፣ የታክሲ አገልግሎት አሽከርካሪ ሥልጠና ባለሥልጣኑ የሚያዘጋጀውን ልዩ ሥልጠና በመውሰድ የምስክር ወረቀት መያዝ ያስፈልጋል ማለቱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
የየትራንስፖርት ባለሥልጣን የሥራ ኃላፊዎችን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች በኦሮሚያ በኩል እንደተነሳ የተገለጸው ቅሬታ ተገቢነት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ ጉዳዩ የክልሎችን የአስተዳደር ሥልጣን የሚነካ በመሆኑ፣ ከዚህ ቀደም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሁንታ እንደፀደቀው የሊዝ አዋጅ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥር አልፎ ክልሎች ተመሳሳይ ሕግ በማውጣት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ሊፈቀድላቸው ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡