Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበችግሮች የሚፈተነው የግብርና ምርምር

በችግሮች የሚፈተነው የግብርና ምርምር

ቀን:

ወደ ክፍሉ ሲገቡ ከበር የሚቀበልዎት የኬሚካል ጠረን ነው፡፡ በተለያዩ የላቦራቶሪ ቁሳቁሶች በተሞላው በዚህ ክፍል፣ ማይክሮ ባዮሎጂ በተለይም በምግብ፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ ዌስት ዩትላይዜሽን ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ የምርምር ስራዎች ይሰራሉ፡፡ በክፍሉ በአንደኛው ጥግ በአንድ መሳሪያ ላይ ሆነው በተመሳሳይ ፍጥነት የሚንቀሳቀሱት አራት በውኃ የተሞሉ ጠርሙሶች ትኩረት ይስባሉ፡፡

በጠርሙሶቹ ውስጥ ጥቃቅን ህዋሳት መኖራቸውን የተረዳነው ቆይተን ነው፡፡ ለጥቃቅን ህዋሳት (ማይክሮ ኦርጋኒዝሞች) እድገት የኦክስጅንና የንጥረ ነገሮች መኖር ግድ ይላል፡፡ በዚህ መሰረትም በጠርሙሶቹ ውሥጥ የተሞላው ውኃህዋሳቱ እንዲያድጉ የሚረዳቸውናበፈሳሽ መልክ የተዘጋጀ ምግብ ወይም የኦክስጅንና የንጥረ ነገር ክምችት ነው፡፡ በተመሳሳይ ፍጥነት የሚንቀሳቀስበት ሚስጠር ደግሞ በውስጡ ያለው ምግብ በአንድ ቦታ ላይ ተወስኖ እንዳይቀርና ለሁሉም ህዋሳት እኩል እንዲዳረስ ለማስቻል መሆኑን የሆለታ ግብርና ማዕከል የምርምር ባለሙያው አቶ ቤተማሪያም ከበደ ይናገራሉ፡፡

‹‹ጠርሙሶቹ ለሴሎቹ እንደ አገር ናቸው፡፡ በእኩል መጠን እንዲንቀሳቀሱ የሚደረገው ደግሞ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ ነው›› ይላሉ፡፡

ሴሎቹ እንደ አተርና ባቄላ ባሉ ጥራጥሬዎች ስር የሚገኙ ራይዞቢያ የተባለ የባክቴሪያ ዝርያ አካል ናቸው፡፡ ይህ ባክቴሪያ በጥራጥሬዎቹ ተክል ስራስሮች ላይ ጥገኛ ሆኖ በመቀመጥ ከአየር የሚመጣውን ናይትሮጅን ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት ሊጠቀሙበት ወደ ሚያስችለው የኬሚካል ፎርም እንዲለወጥ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ባክቴሪያ ተባዝቶና የከሰል አመድ ውስጥ ተደርጎበማዳበሪያነት እንዲጠቀሙት ለገበሬዎች ይሸጣል፡፡ ባክቴሪያውን ለማብዛትም ሴሎቹን ከማሳደግ ጀምሮ የተለያዩ ሂደቶች አሉ፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል፡፡ በብዙ ልፋት ከዳር ሊደርሱ ጥቂት የቀራቸው ምርምሮች በኤሌክትሪክ መቋረጥ ምክንያት እንዳልሆኑ የሚሆኑበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች የቱንም ያህል ሄደው የነበረ ቢሆንም ሁሉንም እንደገና እንደ አዲስ ለመጀመር ይገደዳሉ፡፡ በዚህ ረገድ አቶ ቤተማሪያም በአንድ ወቅት ያጋጠማቸውን እንዲህ ያስታውሳሉ፡፡

ለአንድ የምርምር ስራ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውረው ወደ 400 የሚሆኑ ሴሎችን ሰብስበው ነበር፡፡ ጥቂት የማይባሉ የምርምር ሂደቶችም አከናውነዋል፡፡ በሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ያለው ጀነሬተር በመበላሸቱ ኤሌክትሪክ ሲጠፋ የሚተካው ሌላ ሀይል ማግኘት የማይታሰብ ነው፡፡ የተጀመረው የምርምር ሂደት ከዳር ሳይደርስ በተደጋጋሚ ኤሌክትሪክ ይቋርጣል፡፡ ነገር ግን እንደከዚህ ቀደሙ ከአፍታ በኋላ አልተመለሰም፡፡ ሳይመጣ ሰአታት አለፉ፣ ቀናት ተቆጠሩ፡፡ በዚህ መካከል ሴሎቹን በህይወት የሚያቆያቸው ሀይል ባለመኖሩ አብዛኛዎቹ ሞቱ፡፡

‹‹እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ ስራውን እንደገና ሀ ብለን ነው የምንጀምረው፡፡ የሞቱትን ካሉት ለመለየት የሚደረገው ጥረትም ብዙ ልፋት የሚጠይቅ ነው፡፡ ጥሩ ስራዎች እንሰራለን ግን እንዲህ ባሉ ተልካሻ ምክንያቶች ልፋታችን ከንቱ ይሆናል፡፡ ሞራላችንም አብሮት ይሞታል›› የሚሉት ተመራማሪው ሌሎችም ችግሮች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡

ግብርና መር በሆነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጠቅላላ አመታዊ ምርት በግብርና የሚገኘው ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ አገሪቱ ከምታገኘው አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪም86 በመቶ የሚሆነው ከግብርናው ዘርፍ የሚገኝ ነው፡፡ የአመዛኙ ኢትዮጵያዊ ኑሮ የተመሰረተውም በዚሁ ግብርና ላይ ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዋልታ የሆነውን የግብርና ዘርፍ ማዘመንና በምርምርና በሳይንስ  ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማድረግ ለኤኮኖሚው እድገት ወሳኝ መሆኑም አያጠያይቅም፡፡

በአገሪቱ በተበታተነ መልኩም ቢሆን ከ1920ዎቹ ጀምሮ ነበር የግብርና ምርምር እንቅስቃሴዎች የተጀመሩት፡፡ በ1940ዎቹ በቀድሞው በአለማያ እርሻ ኮሌጅ፣ በጅማ እርሻ ኮሌጅ፣ በአምቦ እርሻ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት፣ በ1950ዎቹ ደግሞ በግብርና ሚኒስቴር ስር ግብርና ላይ ያተኮሩ የምርምር ስራዎች ሲከናወኑ ቆይቶ የካቲት 18 ቀን 1958 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ራሱን ችሎ ተቋቋመ፡፡ከተቋቋመ 50 አመታትን ያስቆጠረው ኢንስቲትዩቱ እስካሁን የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን ለማህበረሰቡ አቅርቧል፡፡ እያቀረበም ይገኛል፡፡

 የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር ዶክተር እንዳለ ገብሬ እንደሚሉት፣ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ሌሎችም ድርጅቶች የግብርና ምርምር ስራዎች ይሰራሉ፡፡ እስካሁንም በርካታ የምርምር ስራዎች ለውጤት ማብቃት ችለዋል፡፡ አስራ ሰባት ማዕከላት ያሉት የፌደራል የምርምር ተቋሙ ጠንከር ያሉ የምርምር ስራዎችን መስራት የጀመረው በዚህ አምስት አመታት ውስጥ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በመንግስት ብቻ የሚደገፉ፣ ትኩረታቸውን በእንስሳትና ዕፅዋት ላይ ያደረጉ ከ70 የሚበልጡ የባዮቴክኖሎጂ ምርምር ፕሮጀክቶችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

የሰብሎችን የምርት ጥራት ከመጨመር፣ በሽታን የመከላከል አቅሙን ከማሳደግና ሌሎችም የዝርያ ማሻሻያዎችን ከማድረግ አኳያ የተለያዩ የምርምር ስራዎች ይሰራሉ፡፡ በቲሹ ካልቸርም እንደዚሁ የሰብሎችን ዘር በማባዛት፣ በተለይም በከፍተኛ ደረጃ ለበሽታዎች የመጋለጥ ችግር ያባቸውን በሽታን የሚያስተላልፉ ዝርያዎችን የማፅዳት ስራ ይሰራል፡፡

እንስሳትን በተመለከተም ፈጣን ስነ-ተዋልዶ እንዲኖራቸው የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን በመስራት ረገድጥሩውጤት ማግኘት ችሏል፡፡  የአገር አቀፍ እንስሳት ማሻሻያን በስፋት መጠቀም የሚያስችል እስትራቴጂ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ካውንስል ሴክሬቴሪያት ተዘጋጅቶ ወደስራው ለመግባት የተለያዩ የዝግጅት ስራችን በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውንም ዶክተሩ ተናግረዋል፡፡

መሰል የምርምር ስራዎች በግብርና ላይ የተመሰረተውን የአገሪቱ ኤኮኖሚ አንድ እርምጃ ለማስኬድ ያላቸው ፋይዳ የጎላ ነው፡፡ አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ልገሳና ድጋፍ ወጥታ ራሧን እንድትችል የግብርናውን ዘርፍ ማዘመንና በምርምር ላይ የተመሰረተ  ማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ቁልፍ ነው፡፡ በየጊዜው በሚከሰተው ረሀብ የሚሰቃየውን አርሶ አደርና አርብቶ አደር ህይወትም መታደግ ነው፡፡

‹‹አገሪቱ በባዮቴክኖሎጂ ያላትን አቅም በመገንባት ሂደት ላይ ስለሆነች በርካታ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ›› የሚሉት ዶክተር እንዳለ፣ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት የተለያዩ ተግዳሮቶች እናዳሉበት ይናገራሉ፡፡ በቂ የሰው ሀይል አለመኖር ዋናው ሲሆን በአገር ውስጥና በውጪ የተሸለ የስራ እድል የሚያጋጥማቸው ተመራማሪዎችም በየጊዜው መስሪያ ቤቱን ለቀው እንደሚሄዱ ተናግረዋል፡፡

ይህ የስራ መስክ በሌሎች አገሮችም የሚሰራበትና ሰፊ የስራ እድል ያለው መሆኑ ተመራማሪዎች የተሻለ ደመወዝ ወደሚከፍላቸው ድርጅት ወይም አገር የመሄድ እድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ሌሎችም በስራ ሂደት የሚያጋጥሙናየምርምሮችንየሚያስተጓጎሉ  ችግሮች እንዳሉ አልሸሸጉም፡፡

የምርምር ስራዎቹ የሚሰሩባቸው አብዛኛዎቹ ግብአቶች የሚገቡት ከውጭ ነው፡፡ የግዢ ሂደቶች ረዘም ያሉ ጊዜያት የሚወስዱበት ሁኔታ መኖሩና የውጭ ምንዛሬ እጥረትአስፈላጊውን ኬሚካል በወቅቱ ለማግኘት እንዲቸገሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ሂደቱም ከአመት በላይ እንደሚፈጅ ዶክተሩ ተናግረዋል፡፡ ይህም አንድ ተመራማሪ የምርምሩ ውጤት እንዲዘገይ፣ የመስራት ፍላጎቱም እንዲቀንስ እያደረገው ይገኛል፡፡

‹‹በዋናነት ብዙ ልናቆያቸው የማንችላቸው፣ በጣም አጭር ዕድሜ ያላቸው፣ በማቀዝቀዣ ተጭነው የሚመጡና በቅዝቃዜ ተጠብቀው ጥቅም ላይ መዋልና ቶሎቶሎ መገዛት ያለባቸው የሆርሞን፣ የኢንዛይም፣ የፕራይመርስ አይነት ያሉ ግብአቶችን ለማግኘት ብዙ እንቸገራለን፡፡ ተመራማሪው ጊዜውን ምርምር ላይ ያጥፋ ወይም ግብአቱ ደረሰ አልደረሰም እያለ ይከታተል፡፡ ሁኔታው ተመራማሪዎች እንዲለቁ ምክንያት እየሆነም ይገኛል›› በማለት ከግዢ ጋር የተያያዙ ችግሮች ብዙዎችን እያማረረ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

የምርምር መሰረተ ልማቶች በተገቢው መጠን አለመሟላትም ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንድ ነገሮችን ከውጭ እየለመንን እንሰራለን የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ሌሎችን እርዱን በማለት የአገር አቅም እንደማይገነባ፣ ዘላቂነትና ቀጣይነት ያለውን የምርምር ግብአት ሊኖር እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡

ከአስራሰባቱ ማእከላት መካከል አንዱ የሆነውን የሆለታ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በጎበኘንበት ወቅት ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስተውለናል፡፡ ከዚህ ባሻገር በውድ ዋጋ የሚገዙ ነገር ግን ሊያንቀሳቅሳቸው የሚችል ባለሙያ ባለመኖሩ ተገትረው የቀሩ የላብራቶሪ መሳሪያዎችም አሉ፡፡  አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉ ቢኖሩም፣ ስለሙያው በቂ ዕውቀት የሌላቸው መሳሪያዎቹን ከፅንሰ ሀሳብ ውጪ በተግባር የማያውቁ እንደሚሆኑ ስማቸውን ያልገለፁ የላቦራቶሪ ባለሙያ ተናግረዋል፡፡

በላቦራቶሪው ጄንዶክ የተባለ የዘረመል ምስል የሚያሳዩ እያንዳንዳቸው በ250000 ዶላር የተገዙ አምስት ማሽኖች አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው አንዱ ብቻ ሲሆን አራቱ መበላሸታቸውን ይገልፃሉ፡፡ እሱም ቢሆንተበላሽቶ መቆየቱን፣ጥገና እስኪደረግለትም ለአራት ወራት ያህል ስራ ተቋርጦ መቆየቱን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞ ባለሙያዎች ከኬንያ መተው እንደሰሩትም ያስታውሳሉ፡፡ ማሽኖችን መጠገን የሚችል ባለሙያ ካለመኖሩ ባሻገር መለዋወጫ ዕቃዎችን በአግባቡ በማቅረብ ረገድም ክፍተት አለ፡፡

‹‹ጄንዶክ የሚባለው መሳሪያን ተበላሽቶ ለመጠገን ረዘም ያለ ጊዜ ፈጅቶብኛል፡፡ በእኛ አገር መሳሪያውን መጠገን የሚችል ባለሙያ ባለመኖሩ ጥገናውን ለማድረግ ውጭ አገር ካሉ ባለሙያዎች ጋር በኢሜይል ማውራት ነበረብኝ፡፡ በጣም ከባድ ነበር፡፡ ለመጨረስም አምስት ወራት ፈጅቶብኛል›› ይላሉ፡፡

በሆለታ፣ በመልካ ወረርና በጅማ መልኮ የምርምር ጣቢያዎች ከአመታት በፊት ስራውን የጀመረው ኢንስቲትዩቱ በአሁኑ ወቅት የሚሰራበትን የምርምር አድማስና የማዕከላቱን ቁጥር ጨምሯል፡፡ እስካሁንም 3000 የሚሆኑ የምርምር ውጤቶችን ማብቃት የቻለ መሆኑን፣ 1200 የሚሆኑት የምርምር ስራዎቹም በሰብል ተለያይነት፣ በእንስሳት መኖ፣ በዕፅዋትና እንስሳት እርባታ፣ ተባይና በሽታዎችን መከላከል፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃና በመሳሰሉት ላይ መስራቱን የተመሰረተበትን 50ኛ አመት አምናሲያከብር ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡

ከ60 በላይ የተሻሻሉ የበቆሎ፣ ከ100 በላይ የተሻሻሉ የስንዴ፣ 36 የሚሆኑ የጤፍ፣ ከ50 በላይ የገብስና ከ44 የሚበልጡ የማሽላ ዝርያዎችን ለግብርናው ዘርፍ ማበርከቱን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ ይሁንና የምርምር ስራዎችን በተገቢው መጠን እንዲሰራ ለማስቻል ከወዲሁ ለችግሮቹ መፍትሄ መስጠት ግድ ይላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...