Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊልጓም ፈላጊ እግረኞች

ልጓም ፈላጊ እግረኞች

ቀን:

የሚነገራቸውን ከመተግበር ይልቅ ጥሰው መሄድ ይቀናቸዋል፡፡ ከመኪና እኩል እየተጋፉ ሲያሻቸውም አሽከርካሪዎችንና ደንብ አስከባሪዎችን እየተሳደቡ የሚያልፉም አሉ፡፡ ለእግረኛ ማቋረጫ የተዘጋጀውን መንገድ እንዲጠቀሙ አካባቢው ላይ የተሰማሩ በጎ ፈቃደኞች፣ ትራፊኮች፣ ፖሊሶችና ደንብ አስከባሪዎች ቢነግሯቸውም ጆሮ ደባ ልበስ ብለው ባልተፈቀደ መንገድ የሚሄዱ፣ ሥርዓት አስከባሪዎች ሲመጡባቸው ተሯሩጠው የሚያልፉም ይታያሉ፡፡ በሜክሲኮ፣ በፒያሳ፣ በአራት ኪሎና በሌሎችም ሕዝብ በብዛት በሚንቀሳቀስባቸው ሥፍራዎች የእግረኞች ከመኪና ጋር መዳፈር ፀሐይ የሞቀው ትዕይንት ከሆነም ከርሟል፡፡

የሰውና የመኪና ትራፊክ ፍሰት በእጅጉ ከሚበዛባቸው ሥፍራዎች አንዱ በሆነው መገናኛ የታዘብነውም አብዛኞቹ እግረኞች ለመንገድ አጠቃቀም ደንብ ተገዥ አለመሆናቸውን ነው፡፡ ሰዎች የመንገደኛ ማቋረጫ በሌለበት፣ መንገዶች በግንባታ ዕቃዎች በተዘጉበት ጊዜና መንገዱ ለእግረኛው አማራጭ በማይሰጥበት ጊዜ እግረኞች የመንገድ አጠቃቀም ሕግን የሚተላለፉበት ሁኔታ ቢኖርም፣ በመገናኛ ያስተዋልነው የእግረኛ ማቋረጫ መንገድ እያለ ከመኪና እየተሻሹ መጋፋትን፣ መኪና እየሄደ ዘሎ መግባትን፣ ደንብ አስከባሪዎች እያሉም የጎዳና ንግዱ ከእግረኛ መንገድ አልፎ መኪና መንገዱ መድረሱ ነው፡፡

በሥፍራው እግረኞችን በመንገደኛ ማቋረጫ ለማሻገር የተሰማሩ በጎ ፈቃደኛ ደንብ አስከባሪዎችም ከጠዋቱ 1 ሰዓት እስከ ረፋዱ 4 ሰዓት እንዲሁም ከሰዓት ከ10 ሰዓት እስከ 1 ሰዓት የሚቆዩበት ጊዜ ከመንገደኛ ጋር በጭቅጭቅ የተሞላ ነው፡፡ በየደቂቃው እግረኛውን እንዲህ አድርግ፣ አታድርግ እያሉ ከመናገር ባለፈም፣ እግረኛውን በእጅ  ገድቦ መያዝ፣ ቁም ከተባለበት የመንገድ አካፋይ ወጥቶ የእግረኛ ማቋረጫ (ዜብራ) መንገዱ ላይ የቆመውን ስቦ ማስወጣት፣ መኪና እያለፈ ዘሎ የሚገባውን ጎትቶ ማውጣት፣ በሐሳብ ሆኖ አስፋልት ላይ መሆኑን የረሳውን፣ እንዲሁም ሞባይሉን እያነጋገረ መኪና መንገድ መሀል የሚቆመውን ሃይ ማለትም የእነሱ ሥራ ነው፡፡ በታች ያሉትን የእግረኛ ማቋረጫ መንገዶች ትተው ለመኪና ብቻ በተፈቀደውና ከዳያስፖራ አደባባይ ተነስቶ ወደ ቦሌ በሚሄደው የላይኛው መንገድ ገብተው የሚዋዥቁም ቀላል አይደሉም፡፡ 

ያገኘናቸው ፖሊሶችም እግረኞች የሚባሉትን እንደማይሰሙ፣ ከእግረኛ ብዛት አንፃርም፣ በላይ የሚተላለፍ የእግረኛ መንገድ ቢሠራ ችግሩን ሊቀርፍ እንደሚቻል ነግረውናል፡፡ በሥፍራው ያነጋገርናቸው እግረኞችን ሲያሻግሩ ያገኘናቸው በጎ ፈቃደኛ አቶ ሃይረዲን አደም፣ ‹‹ለኛ ብለው ነው ሥርዓት የሚያሲይዙን፤›› የሚሉ ቢኖሩም፣ አብዛኛው ግን ቢነግሩት የማይሰማ ነው ይላሉ፡፡

በትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ሥር ሆነውና በማኅበር ተደራጅው የበጎ ፈቃደኛ ሥራ ከጀመሩ ስድስት ወራት ያስቆጠሩ ሲሆን፣ በአካባቢው በጠዋት ፈረቃ ከተሰማሩ 18 በጎ ፈቃደኞች ጋር ሆነው ይሠራሉ፡፡

‹‹በጎ አድራጊ አይበሳጭም አይናደድም እንጂ፣ ሥራው ዕድሜ የሚያሳጥር ነው፤›› ይላሉ፡፡ እንደ አቶ ሃይረዲን መመከሩ፣ ከመኪና መንገድ እግረኛውን ማስወጣቱና ፈር እንዲይዘ ማድረግ የዕለት ተዕለት ሥራቸው ቢሆንም፣ ምን አገባህ? ብሞት ብኖር አንተን ምን ይመለከትሃል? የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡ እግረኛው እንደ አጠቃላይ ሲታይም ደንቡን አክብሮ ከሚንቀሳቀሰው ይልቅ የሚያስቸግረውና ደንብ የሚጥሰው ይበዛል፡፡

‹‹ኅብረተሰቡ ግንዛቤ ስለሌለው ሳይሆን ልጓም ወይም ቅጣት ስለሚፈልግ ነው›› የሚሉት አቶ ሃይረዲን፣ ቢቀጣ ሥርዓት እየያዘ ሊሄድ እንደሚችል ያምናሉ፡፡ እሳቸው ሥራውን ከጀመሩ ስድስት ወራት ቢያስቆጥሩም ዓመት የቆዩም አሉ፡፡ እነዚህም በእግረኞች ላይ የሚያዩት ዳተኝነት ያለው ነው፡፡ ከዛሬ ነገ የሚሻሻል ሳይሆን እየባሰበት የሄደና ደንብ የሚጥስ እግረኛ ተበራክቷል፡፡ በመሆኑም አንድ ወር፣ 15  ቀናት ወይም አንድ ቀን ሠርቶ የሚቀር በጎ ፈቃደኛ አለ፡፡

ነሐሴ 5 እና 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በሥፍራው እንዳየነው፣ ዳተኝነቱ የሚጎላው በእግረኞች ላይ እንጂ በአሽከርካሪዎች ላይ አልነበረም፡፡ አሽከርካሪዎች የደንብ አስከባሪዎችንም ሆነ የትራፊኮችን ፊሽካ ወይም የእጅ ምልክት ዓይተው ሲቆሙ፣ ብዙዎች እግረኞች ግን ይህንን አይፈጽሙም፡፡ በመሆኑም ደንብ አስከባሪዎቹ ሁለት እጃቸውን ዘርግተው መገደብ፣ በድምፅ መናገር፣ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህም ሆኖ የመሻገሪያ መንገዱን ትተው በብረት ላይ በመዝለል የሚያቋርጡ፣ ለደንብ አስክባሪዎቹ ፊሽካ ጆሮ የማይሰጡ ጥቂት አይደሉም፡፡

‹‹መኪና አሽከርካሪዎች ቅጣት ስላለ ሕጉን ያከብራሉ፡፡ ለእግርኛ ባለመኖሩ የቱንም ያህል እውቀት ቢኖረው ደንብ ከመጣል አይመለስም፡፡ እኛንም እያስቸገረን ያለው ያውቃል የሚባለው የኅብረተሰብ ክፍል ነው እግረኛው እምቢ ካለ ቅጣቱ ተግባራዊ ቢሆን መልካም ነው›› ይላሉ አቶ ሃይረዲን፡፡

እግረኞችን ለመቅጣት የሚያችለው ደንብ ቁጥር 395/2009 የመንገድ ትራፊክ መቆጣጠሪያ በታኅሣሥ የጸደቀ ሲሆን፣ በ2010 ዓ.ም. መጀመሪያ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል የትራንስፖርት በለሥልጣን በሰኔ አጋማሽ ላይ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

መመሪያው የመንገድ ላይ ንግድ የሚፈጽሙ፣ ቁሳቁሶችን መንገድ ላይ የሚያስቀምጡና ለእግረኞች እንቅስቃሴ እንቅፋት የሆኑ አካላት ላይም ቅጣት የሚጥል ሲሆን፣ ተገቢ ጥንቃቄ ሳያርግ መንገድ ያቋረጠ፣ በግንብና ብረት የታጠሩ መንገዶችን የዘለለ እግረኛም ከ40 እስከ 80 ብር እንደሚቀጣ በመመሪያው ተቀምጧል፡፡ ደንብ ተላልፈው ቅጣት መክፈል የማይችሉ ደግሞ ተመጣጣኝ ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚደረግበት አግባብም ይኖራል፡፡

እግረኞች ለእግረኞች በተፈቀዱ ቦታዎች ብቻ እንዲያቋርጡና እንዲንቀሳቀሱ ለማስቸል ከጥቂት ዓመታት በፊት በደንብ ማስከበር እንቅስቃሴ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ ወራት ሳያስቆጥር ነበር ሥራው የተቋረጠው፡፡

በጥር 2009 ዓ.ም. የተጀመረው አገር አቀፍ የትራፊክ ንቅናቄ ግን እግረኞችም ግንዛቤውን አግኝተው በተለይ ለእግረኛ አመቺ በሆኑ ሥፍራዎች ደንብና ሕግ አክብረው አንዲንቀሳቀሱ የተለያዩ መድረኮችን እያዘጋጀ ይገኛል፡፡ የንቅናቄው አካል የሆነው ግንዛቤ ማስጨበጥ ሐምሌ 5 የተጀመረ ሲሆን እስከ ሐምሌ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. ይቆያል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ እንደገለጹት፣ እግረኞች በመንገዳቸው በግራ በኩል እንዲሄዱና በእግረኛ ማቋረጫ እንዲጠቀሙ ለሳምንት በሚቆይ ጊዜ የትራፊክ ፖሊሶች፣ የማኅበረሰብ ፖሊሶቸ፣ የወንጀል መከላከል አባሎች፣ በጎ ፈቃደኞች የተሳረፉበት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡

ግንዛቤው ከተገኘ በኋላ እግረኞችን የሚቀጣውን ደንብ ተፈፃሚ ለማድረግ መመሪያዎች ተዘጋጅተው ወደ ትግበራ በቅርብ ጊዜ የሚገባም ይሆናል፡፡ ከተማ ውስጥ ያለውን የመንገድ አጠቃቀም ቸልተኝነትና በዚሁ ሳቢያ የሚደርሰውን አደጋ ለመከላከልም የደንቡ ተፈፀሚ መሆን ወሳኝ ነው፡፡

በከተማዋ ግንባታ ባሉባቸው አካባቢዎች የእግረኛ መንገዶች ከጥቅም ውጭ መሆናቸው፣ የችግረኛ ማቋረጫ በማይታዩባቸውና እግረኛው ምርጫ በሚያጣበት ሁኔታ መኖሩን አስመልክቶም፣ ደንቡ ተፈፃሚ ሲሆን ይህን እንዴት ያየዋል ያልናቸው ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ፣ ‹‹ደንቡ በቀጥታ ትግበራ ላይ የሚውለው ለእግረኛ መንገድ የተሟላ አገልግሎት ባለበት ቦታ ላይ ነው፡፡ ብዘ ጊዜም  ጥሩ መሸጋገሪያ፣ የእግረኛ ማቋረጫ ባለበት ላይ እግረኞች ከደንብ ውጭ ይሆናሉ፡፡ ደንቡም የመንገድን ምቹነት ባገናዘበ መልኩ ተፈፃሚ ይሆናል›› ብለዋል፡፡

በትራንስፖርት ባለሥልጣን መረጃ መሠረት በ2008 ዓ.ም. ከ4,350 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን በትራፊክ አደጋ ያጡ ሲሆን፣ ከእነዚህ 43 በመቶ ያሉ እግረኞች ናቸው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...