Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልከቻይና ጓዳ

ከቻይና ጓዳ

ቀን:

ለሰስ ያለውና መንፈስን የሚያረጋጋው የቻይና ክላሲካል ሙዚቃ ከቻይና ጋር ያስተዋወቀኝ ከዓመታት በፊት ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች መካከል ከመሰንቆና ክራር ጋር በመጠኑ የሚቀራረብ ቅርፅ ያላቸው የቻይና ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች የሚፈጥሩት ድምፅ ማራኪ ነው፡፡ ቻይናውያን ለዘመናት የተገለገሉባቸው ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች በተቀረው ዓለምም እየታወቁ ሲሆን፣ በተለይም ባህላዊ ክላሲካል ሙዚቃቸው የበርካቶችን ትኩረት አግኝቷል፡፡ ሙዚቃ የተለያየ ቋንቋ በሚናገሩ ሕዝቦች መካከል ትስስር የሚፈጥር ድልድይ ነውና በመሣሪያ ብቻ ከተቀነባበሩ የቻይና ባህላዊ ሙዚቃዎች በተጨማሪ ሌሎችም ዘፈኖቻቸው ይደመጣሉ፡፡

ኪነ ጥበብና ባህል ነክ ክንዋኔዎችን እንደሚዘግብ ጋዜጠኛ ከቻይና ሙዚቃ ባለፈ ሌሎችም የባህል መገለጫዎቻቸውን ለመገንዘብ ጥረት አደርግ ነበር፡፡ በሰባተኛው መቶ ክፍል ዘመን ገደማ የቻይናን ደኅንነት ለመጠበቅ የተገነባው ታላቁ የቻይና ግንብ ከተቀሩት የአገሪቱ ታሪካዊ ሥፍራዎች በበለጠ ስለሚማርከኝ ስለግንቡ የሚያትቱ ጽሑፎችን አንብቤያለሁ፡፡

‹‹ዘ አርት ኦፍ ዋር›› በተሰኘው ጽሑፍ የሚታወቀው ቻይናዊው ጄኔራልና ፈላስፋ ሰን ዙ ሌላው ስለቻይና የተገነዘብኩበት ድልድይ ነው፡፡ ከጥንታዊ የቻይና ፍልስፍና በተጨማሪ ዘመናትን ያስቆጠሩ እምነቶችና ሥርዓቶችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ፒንይን ወይም ስፕሪንግ ፌስቲቫል በመባል የሚታወቀው የቻይናውያን አዲስ ዓመት በድምቀት የሚከናወን ሲሆን፣ ልታደማቸው ከምፈልጋቸው ባህላዊ ፌስቲቫሎች ዝርዝር ውስጥ ይገኛል፡፡ በፎቶግራፍና በቪዲዮ ያየኋቸው በአንበሳና በድራገን አምሳያ በተሠሩ አልባሳት የታጀቡ ባህላዊ ዳንሶችን በዕውን የመቃኘት ዕድል እንደሚኖረኝ ተስፋም አለኝ፡፡

ጥንታዊው ማርሻል  አርትስ ጎልቶ የሚታይባቸው የቻይና ፊልሞች ስለአገሪቱ ማኅበረሰብ ለማወቅ ያግዛሉ፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ከተሞች ቁጥራቸው እየተበራከተ የመጣው የማርሻል አርትስ ማሠልጠኛ ተቋሞች ብዙዎቻችንን ከእንቅስቃሴው ጋር አቀራርበዋል፡፡ በዋኛነት በግንባታውና በሌሎችም ዘርፎች የተሰማሩ ቻይናውያንን መመልከት ከተለመደም ሰነባብቷል፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን ለንግድ ወደ ቻይና ከማቅናታቸውና ቻይናውያን ኢትዮጵያ ውስጥ ከመበራከታቸው ጋር በተያያዘ የባህል ልውውጡም እየጎለበተ ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የቻይና ሬስቶራንቶች ቁጥር እየጨመረ የመጣውም ለዚሁ ነው፡፡

የሪፖርተር ጋዜጣ ቢሮ አካባቢ በሚገኙ የቻይና ሬስቶራንቶች አልፎ አልፎ ከሚመገቡ መካከል አንዷ ነኝ፡፡ ሲዝሊንግ ቺክንና ኑድልስ በብዙ ኢትዮጵያውያን የሚዘወተሩ ምግቦች ሲሆኑ፣ ሌሎችም የቻይና ባህላዊ ምግቦች ዕውቅና እያተረፉ ነው፡፡ በእርግጥ በሃይማኖትና በባህል ልዩነት ምክንያት የቻይናን ባህላዊ ምግቦች የማይመገቡ ጥቂት አይደሉም፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ ቻይና ከቻይናም ወደ ኢትዮጵያ የሚጓጓዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ የማንዳሪን ቋንቋ አስፈላጊነት ስላጎላው ቋንቋውን በግልና በተቋም የሚያስተምሩ ተበራክተዋል፡፡ አብዛኞቹ ተማሪዎች ደግሞ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ ቋንቋው ከመግባበያነቱ ባሻገር የፊደላቱ አጣጣል ጥበብ የተላበሰ ነው፡፡ ማንዳሪን ካራክተሮች የበለጠ ለማወቅ ጉጉት ያደረብኝ ‹‹ዳሉ ቻይንኛን በቀላሉ›› የተሰኘ የማንዳሪን መማሪያ መጽሐፍ በአማርኛ ለጻፈችው ሊና ጌታቸው ቃለ መጠይቅ ካደረግኩ በኋላ ነበር፡፡ በቻይናና በአፍሪካ መሀከል ያሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ ጉዳዮችን ያማከሉ ጽሑፎች የምታዘጋጀው ሊና፣ ኢትዮጵያውያን ከቻይናውያን ጋር እንዲግባቡ ለማስቻል ያሰናዳችውን መጽሐፍ ስትገልጽ፣ ቻይናውያን በትንሹም ቢሆን ቋንቋቸውን ለመቻል ጥረት በሚያደርግ ሰው እንደሚደሰቱ ነግራኝ ነበር፡፡

እኔም ቋንቋውን እንድማር መጽሐፉን ሰጠችኝ፡፡ ቋንቋውን በጥልቀት ለማወቅ ጊዜ ቢወስድም ሰላምታ አሰጣጥና ሌሎችም ቀላል የዘወትር መግባቢያ ቃላትን በአጭር ጊዜ ተረዳሁ፡፡ በቻይና መንግሥት ሪሰርች ኤንድ ትሬኒንግ ኢንስቲትዩት የ21 ቀን ሥልጠና ጥሪ ሲደርሰኝ በቅድሚያ ሻንጣዬ ውስጥ የከተትኩትም ይህን መጽሐፍ ነበር፡፡ ሴሚናር ፎር ኦምኒሚዲያ ሪፖርተርስ ኦፍ ዴቨሎፒንግ ካንትሪስ በሚል ቤጂንግ፣ ቻይና የተዘጋጀውን ሥልጠና ለመውሰድ የቪዛ ማመልከቻ ቅጽ፣ የሕክምና ማስረጃና ሌሎችም ሰነዶች በሦስት ቀናት አሰናድቼ ሰኔ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ላይ ወደ ቻይና ጉዞ ተጀመረ፡፡

የአሥር ሰዓቱን በረራ ያገባደድኩት የኦታም ፑልቶን ‹‹የሲሳዬ ልጆች›› የተሰኘ መጽሐፍ በማንበብ ነበር፡፡ በቻይናና በአፍሪካ ጥንታዊ ፍልስፍናዎች የተሳበው ደራሲው፣ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና ማንዳሪን ቋንቋዎች ጽሑፎችን ያሰናዳል፡፡ የአማርኛ ርዕሱ በማንዳሪንም የተተረጎመውን መጽሐፍ ወደ ቻይና እየተጓዙ ማንበብ ተምሳሌታዊ እንደሆነ በማመን ጉዞዬን አጣጣምኩበት፡፡ በንባቤ መካከል ስለቻይና ያለኝ መረጃና በዕውን አገሪቱን ስጎበኝ የሚገጥመኝ ነገር ምን ያህል ይጣጣሙ ይሆን? ስል ራሴን እየጠየቅኩ ነበር፡፡

ቤጂንግ ካፒታል ኢንተርናሽናል ኤርፖርትስ ስደርስ ከናይጄሪያ፣ ማላዊ፣ ዚምባቡዌና ኬንያ የተውጣጡ ጋዜጦች አገኘሁ፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አብረን ብንጓዝም ወደ ተመሳሳይ ሴሚናር እያቀናን መሆኑን አላወቅንም ነበር፡፡ በቻይናው የሥልጠና ማዕከል የምትሠራ ወጣት ተቀበለችንና ወደ ምናርፍበት ሆቴል የሚወስደን መኪና እስከሚመጣ ጥቂት የማንዳሪን ቃላትን ታስተምረን ጀመር፡፡ ቃላቱን እየተለማመድን ስለየአገራችን መገናኛ ብዙኃን እየተወያየን ነበር፡፡ ሥልጠናው ዘመን አመጣሽ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ሚዲያን በማዘመን ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ከ23 አገሮች የተውጣጡ 65 ተሳታፊዎች ተካተውበታል፡፡

በአውሮፕላን ማረፊያው የነበረን ቆይታ የአፍሪካን ሚዲያ ከሌሎች ተሳታፊ አገሮች ጋር ያነፃፀርንበት ነበር፡፡ ባለንበት የመረጃ ዘመን (ኢንፎርሜሸን ኤጅ ወይም ዲጂታል ኤጅ በመባል የሚጠራው) በአንድ አካባቢው ያለ ክንውን በሰከንዶች በርካታ ማይሎችን አቆራርጦ በመላው ዓለም ይዳረሳል፡፡ በዚህ ፈጣን የመረጃ ልውውጥ በአህጉረ አፍሪካ ያሉ ሚዲያዎች ድርሻቸው ምንድነው? የሚለው የብዙዎቻችን ጥያቄ ነበር፡፡

አፍሪካ ታዳጊ አህጉር እንደመሆኗ በየአገራችን ያለው የኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ብዙም ባለመጎልበቱ ኒው ሚዲያ በጅማሮ ደረጃ እንደሚገኝ ተስማማን፡፡ ሆኖም ከአፍሪካ አገሮች መካከል በዲጂታል ሚዲያ የተሻሉት የትኞቹ ናቸው? የሚለው አከራክሮናል፡፡ ሁላችንም በየአገራችን ያለውን ሚዲያ ምን ያህል እንደዘመነ እየገለጽን መፎካከር ጀመርን፡፡ ሆኖም ውስን የኢንተርኔት ዝርጋታና የሚቆራረጥ የኤሌክትሪክ ኃይል የየአገራችንን ሚዲያ እየተፈታተኑት መሆኑ ወደተቀራረበ ሐሳብ ያመጣን ይመስላል፡፡

የምንጠብቀው መኪና እስከሚመጣ ዶላር ወደ አርኤምቢ (ዩዋን) ቀየርኩ፡፡ አንድ አርኤምቢ በአራት ብር ስለሚመነዘር፣ ብሩን ወደ ዶላር ከዚያም ወደ አርኤምቢ እየለወጥሉ አሰላሁ፡፡ መኪናችን ሲደርስ ሾፌሩ በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት መዘግየቱን እየገለጹልን ሻንጣዎቻችንን ጫንና ወደ ሆቴሉ አቀናን፡፡ በኢትዮጵያና በቻይና መከካል የአምስት ሰዓት ልዩነት ስላለ ቤጂንግ የደረስነው አመሻሽ ላይ ነበር፡፡ ወቅቱ በጋ በመሆኑ ከፍተኛ ወበቅ ነበር፡፡ የደረስነው ምሽት ላይ ቢሆንም፣ የበጋው ቀን ዘለግ ስለሚል ብርሃን ነበር፡፡

ሆሊደይ ኢን በአውሮፕላን ማረፊያው አቅራቢያ የሚገኝ ሆቴል ነው፡፡ ለአምስት ቀናት በሆቴሉ እንደምንቆይ አዘጋጆቹ ገለጹልንና የየክፍላችንን ቁልፍ አስረከቡን፡፡ ስማችንና የመጣንበትን አገር የሚገልጽ ባጅ ተሰጥቶን ጠዋት የምንነሳበት ሰዓት ተነገረን፡፡ ወደ ክፍሌ ከመሄዴ በፊት ከሆቴሉ የዋይፋይ ኮድ ተቀብዬ ኢንተርኔት ለመጠቀም ስሞክር የምፈልጋቸውን ድረ ገጾች ለማግኘት እንደማልችል የሚገልጽ መልዕክት በስልኬ ስክሪን ተነበበ፡፡ የሆቴሉ እንግዳ መቀበያ ክፍል ሠራተኞች ብዙም እንግሊዝኛ ስለማይችሉ ችግሩን ላስረዳቸው አልቻልኩም፡፡

ከናይጄሪያ ከመጡት ሦስት ጋዜጠኞች አንዱ ቻይና የጉግል ድረ ገጽን እንደማትጠቀምና ከጉግል ጋር የተያያዙ ድረ ገጾችን ማግኝት እንደማይቻል ገለጸልኝ፡፡ ቻይና ውስጥ በዋነኛነት አገልግሎት የሚሰጠው ባይዱ ሲሆን፣ ያሁንም መጠቀም ይቻላል፡፡ ስለአሠራሩ ሙሉ መረጃ ባይኖረኝም ስለ አሊባባና ዊቻት አውቅ ስለነበር የተቀረውን ዓለም ትቼ ወደ ቻይናው የኢንተርኔት ዓለም ገባሁ፡፡ ቻይና ከሌላው ዓለም በተለየ ታላቁን ጉግል ቸል  ብላ በራሷ መንገድ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ እንደ ፌስቡክና ትዊተር ያሉ የማኅበረሰብ ድረ ገጾችን ለምኔ ብላ ቻይናን ያማከሉ እንደ ዊቻት ያሉ ድረ ገጾችን ትጠቀማለች፡፡ እንደ ቴንሴንት ያሉ የቻይና ቴክኖሎጂያዊ ተቋሞች በአገሪቱ ገናና ሲሆኑ፣ በቻይናውያን ጥቅም ላይ የሚውሉ ነገሮች በቻይና የተሠሩና ቻይናን ያማከሉ መሆን አለባቸው የሚል አቋም የያዙ ይመስላል፡፡

ከ1.4 ቢሊዮን በላይ የሕዝብ ቁጥር ከዓለም ቀዳሚ በሆነችው ቻይና የሚጠበቅብኝን የ21 ቀናት ቆይታ አሐዱ ያልኩት በሴሚናሩ መክፈቻ ነበር፡፡ ከሆቴሉ በቅርብ ርቀት የሚገኘው የሪሰርች ኤንድ ትሬኒንግ ኢንስቲትዩት ቅጥር ግቢ ውስጥ የማዕከሉ አመራሮች አቀባበል አደረጉልን፡፡ ከ65 ተሳታፊዎች መካከል አብዛኞቹ በየአገራቸው ባህላዊ አልባሳት ተውበው ነበር፡፡ በቻይና ቆይታችን የቻይናውን ግዙፍ ሚዲያ ሲሲቲቪን ጨምሮ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ ጋዜጠኞችና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሥልጠና እንደሚሰጡን ተገለጸልን፡፡ አምስት ቀናት በቤጂንግ ቆይተን ቀጣዩን አምስት ቀናት ከቻይና ግዛቶች በአንዷ ኒንሻ እንደምናሳልፍና በተቀሩት ቀናት ወደ ቤጂንግ እንደምንመለስ አሳወቁን፡፡ ከመግቢያ ንግግሩ በኋላ ተሳታፊዎች የቡድን ፎቶግራፍ ይነሱ ጀመር፡፡ ከየአገሩ ከመጡ ተሳታፊዎች ጋር ለመተዋወቅና ስለኢትዮጵያ ያላቸውን አስተያየት ለማድመጥ የቻልኩትም በዚህ ወቅት ነበር፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከል በቅድሚያ የተዋወቅኩት ከበሀማስ ከመጣ ጋዜጠኛ ጋር ነበር፡፡ ‹‹በቅርቡ አዲስ አበባ ነበርኩ፤›› ብሎ ነበር ንግግር የጀመርነው፡፡ አባቱ አፍሪካን እየተዘዋወሩ ሳለ ኢትዮጵያ ሲደርሱ አገሪቷን በጣም ስለወደዷት ለመቅረት ወሰኑ፡፡ ከበሀማስ ወደ ኢትዮጵያ ኑሯቸውን አዙረው ኢትዮጵያዊት አግብተው ልጅ ወልደው እየኖሩ ነው፡፡ ጋዜጠኛው አባቱ እንደ አገሩ የሚቆጥሯትን ኢትዮጵያን ሲጎበኝ ሐሴት ተሰምቶት እንደነበረ ነግሮኛል፡፡ በአዲስ አበባ ቆይታው ካስገረሙት ነገሮች መካከል የብሔራዊ ፈተና በተካሄደበት ወቅት ፈተናው እንዳይሰረቅ በሚል ኢንተርኔት መቋረጡን ነበር፡፡ ከወራት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለስና ላሊበላን ጨምሮ በርካታ ታሪካዊ ቦታዎችን እንደሚጎበኝም ነግሮኛል፡፡

ከፊሊፒንስ የመጣው ሌላው ተሳታፊ ወንድሙ አዳማ ዩኒቨርሲቲ መምህር እንደሆነና ወንድሙ ስለኢትዮጵያ ከሚነግረው ባለፈ ኢትዮጵያዊ አግኝቶ ስለአገሪቷ አውርቶ እንደማያውቅ ገለጸልኝ፡፡ ስለአገሪቱ ታሪክ በመጠኑ ገልጬለት ኢትዮጵያን ቢጎበኝ የበለጠ እንደሚደሰት ነገርኩት፡፡ ከሞሪሽየስ፣ ኮሎምቢያ፣ ካምቦዲያ፣ ዩክሬይን፣ ሞንጎልያ፣ ጋያናና ሌሎችም አገሮች ከመጡ ተሳታፊዎች ጋርም ጥሩ ቆይታ ነበረን፡፡ ከተሳታፊዎቹ መካከል ጠንካራ ትስስር የተፈጠረው ከጃማይካውየን ጋር ነበር፡፡ ስድስት ጃማይካውያን የሴሚናሩ ተካፋይ የነበሩ ሲሆን፣ ስለኢትዮጵያ ታሪክና ነባራዊ ሁኔታ ጥሩ መረጃ አላቸው፡፡

‹‹ኢትዮጵያና ጃማይካ ጠንካራ ታሪካዊ ትስስር አላቸው፤›› ሲሉ ስለሁለቱ አገሮች ግንኙነት ገልጸውልኛል፡፡ በተለይም ስለ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ስለጥቁር ሕዝቦች ትግል፣ ስለራስታፈራይና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ዘለግ ላለ ጊዜ አወሳን፡፡ ከመካከላቸው ኢትዮጵያን ጎብኝቶ የሚያውቅ አልነበረም፡፡ እኔም ጃማይካ የመሄድ ዕድል አልገጠመኝም፡፡ ሆኖም አንዳችን ሌላችንን ወደየአገራችን ለመጋበዝ ቃል ተገባብተን ተለያየን፡፡

ቀጣዮቹ ቀናት ከተለያዩ የቻይና ሚዲያዎች የተውጣጡ ጋዜጠኞች ሥልጠና የሰጡበት ነበር፡፡ ከቻይና ግሎባል ቴሌቪዥን ኔትወርክ (ሲጂቲቪ)፣ ከቻይና ሬዲዮ ኢንተርናሽናል (ሲአርአይ)፣ ከፒፕልስ ደይሊና ከቻይና ናሽናል ሬዲዮ (ሲኤንአር) የተውጣጡ ጋዜጠኞች በሚዲያ ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ከተሞክሯቸው አካፍለዋል፡፡ ዛሬ ዛሬ ብዙዎች ስልካቸውን ከእጃቸው አይነጥሉም፡፡ መረጃ ለማግኘትም በርካታ አማራጮች አሏቸው፡፡ በቻይና ቆይታዬ አጠገባቸው ካለ ሰው ጋር ሲነጋገሩ ያየኋቸው ሰዎች እምብዛም አይደሉም፡፡ ሰብዌይ ውስጥ፣ ሬስቶራንት ውስጥና መንገድ ላይም ሁሉም ሰው ስልኩ ላይ ብቻ ያነጣጥራል፡፡ በዙሪያቸው ስላለው ሰውና ክንውንም ግድ ያላቸው አይመስልም፡፡

ይህ ከቴክኖሎጂ ጋር ያለው ጠንካራ ቁርኝት መገናኛ ብዙኃን መረጃን ለማሰራጨት የሚመርጡትን መንገድም ቀይሯል፡፡ አብዛኞቹ የቻይና ሚዲያዎች በዲጂታል መንገድ መረጃ ማሰራጨትን ስለሚመርጡ እንደ ጋዜጣና መጽሔት ያሉ ሚዲያዎች ህልውና ጥያቄ ውስጥ ነው፡፡ ይህ የቻይና እውነታ ብቻ ሳይሆን ቀስ በቀስ የሌሎች አገሮችም መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

ከአሠልጣኞቻችን መካከል ግዋን ጁዋን የተባለችው ጋዜጠኛ፣ 93.5 በመቶ ቻይናውያን ዜና የሚያነቡት በስልካቸው መሆኑን ገልጻለች፡፡ መገናኛ ብዙኃን መረጃቸውን የሚያሰራጩበት መንገድ በዘመነ ቁጥር ተከታታዮቻቸውና ገቢያቸውም እየጨመረ መምጣቱን በጥናት አስደግፋም ተናግራለች፡፡ ጋዜጠኞች መረጃ ከሚሰበስቡበት ወቅት ጀምሮ ለሕዝብ ሲያደርሱም ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ነው፡፡ ዘመን አመጣሹ ኒው ሚዲያ ቀስ በቀስ ባህላዊውን (ትራዲሽናል ሚዲያ) እየተካ መሆኑም ግልጽ ነው፡፡ በዚህ የለውጥ ሒደት ውስጥ በየአገራችን ያለው ሚዲያ ስላለበት ሁኔታ ጽሑፍ አሰናድተን እንድናቀርብ ተጠይቀን ነበር፡፡

በአገራችን ኦንላይን መረጃ በማቅረብ ረገድ ጅማሮዎች ቢኖሩም ከሌሎች አገሮች አንፃር ብዙ ርቀት አልተራመድንም፡፡ ዘመን አመጣሹን ዘዬ ከመከተል በፊት የመሠረተ ልማት ዝርጋታው መቅደም እንዳለበት እሙን ነው፡፡ መረጃን በዘመናዊ መንገድ ለማቅረብ የሚደረጉ ጥረቶች በመሠረተ ልማት ዝርጋታ መጓተት መፈተናቸው የሚዲያዎቹን ተደራሽነት ውስን ያደርገዋል፡፡ ምንም እንኳ ሕዝቡ በፍጥነት መረጃ የሚሰጡትን ሚደያዎች ቢመርጥም፣ ሚዲያዎቹ በሚፈለገው ፍጥንት መራመድ ካልቻሉ ትርጉም አይኖረውም፡፡

ሊዚ ዩንግ የተባለው አሠልጣኝ ትራዲሽናል ሚዲያዎች ራሳቸውን ሲያዘምኑ ገቢያቸውም እንደሚጨምር ተናግሯል፡፡ አንድ ሁነት በተፈጠረ በሰከንዶች ውስጥ ለሕዝብ ማድረስና ሕዝቡ ዜናውን ከማንበብ፣ ከማድመጥና ከመመልከት ባለፈ አስተያየት በመስጠትና በሌላም መንገድ እንዲሳተፍ ማድረግ እንደሚያሻም ያክላል፡፡ በተለይም የወጣት ሚዲያ ተከታታዮችን ትኩረት ለመሳብ እንደ ቨርቹዋል ሪያሊቲ ያሉ ቴክኖሎጂዎች እንደሚያስፈልጉ ጠቁሟል፡፡ በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ ያስረዳንን ቨርቹዋል ሪያሊቲ በዕውን ተመልክተንም ነበር፡፡ ኒንሻ ውስጥ የጎበኘነው ሙዘየም ከአራት አቅጣጫ በሚታዩ ስክሪኖች ቪዲዮ የሚታይበት የቨርቹዋል ሪያሊቲ ክፍል አለው፡፡ በክፍሉ ከሚገኝ ከፍ ያለ ቦታ ሆነን ወደ ታች ስንመለከት በቪዲዮ ውስጥ በሚገኘው ቦታ በዕውን ያለን ይመስል ነበር፡፡ በዕውን ካለንበት ቦታ በተቃራኒው በቪዲዮው መቼት ውስጥ እየተንቀሳቀስን የሚያስመስለውን ክፍል የመሰለ ቴክኖሎጂ በአገራችን ለመተግበር ምን ያህል ጊዜ ይወስድብን ይሆን? ስል ራሴን እየጠየቅኩ ነበር፡፡

የቻይና ናሽናል ሬዲዮ (ሲኤንአር) ጋዜጠኛ ዋንግ ሊያንግ ጋዜጠኞች መረጃ ከሚያደርሱት ሕዝብ ጋር የበለጠ እንዲቀራረቡ ኒው ሚዲያ ዕድል ይፈጥራል ሲል ይገልጻል፡፡ ቻይና ውስጥ ‹‹ስማርት ኮምዩኒቲ›› በሚል ሙሉ በሙሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የተመረኮዘ ሕይወት ያላቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ በቤታቸው ያሉ ቁሳቁሶች ባጠቃላይ ማለት ይቻላል ዲጂታል ናቸው፡፡ እንደ ማሳያ የጎበኘነው ቤት ምግብ ለማብሰል፣ መብራት ለማብራትና ለማጥፋት፣ መጋረጃ ለመክፈትና ሌሎችም እንቅስቃሴዎች በሪሞት ኮንትሮል የሚቆጣጠሩበት ነው፡፡ ቆሻሻ መጣያው ሳይቀር ዲጂታል ነው፡፡

ዘመኑ የደረሰበትን ሳላደንቅ ባላልፍም፣ ይህ ሁሉ የቴክኖሎጂ ውጤት የሰው ለሰው ግንኙነታችንን አያላላውምን ስል መጠየቄ አልቀረም፡፡ ማኅበራዊ ትስስሩ ጠንካራ በሆነበት አገር ለሚኖር የሳሳው የሰው ለሰው ትስስር እንግዳ ይሆንበታል፡፡

ቻይና ውስጥ የሚገኙ የሚዲያ ተቋሞችን በጎበኘንበት ወቅት ቴክኖሎጂን የተገበሩበትን መንገድ አስቃኝተውናል፡፡ በቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ የተመልካቾችን ብዛትን ምላሻቸውን የሚቆጣጠሩበት ክፍል አለ፡፡ በትልልቅ ዲጂታል ካርታዎች ከየጣቢያው የሚተላለፉ መርሐ ግብሮችና የተመልካቾች ምላሽ ይታያል፡፡ ከአገሪቱ ውጪ ያሉ ታዳሚዎች ቁጥርና የሚያዘወትሩት መርሐ ግብር ዝርዝርም በስክሪኑ ይታያል፡፡ ፒፕልስ ዴይሊ ጋዜጣ እ.ኤ.አ. ከ1948 ጀምሮ ለንባብ ያበቃቸው ጋዜጣዎች በዲጂታል አርካይቪንግ ይገኛሉ፡፡ ጋዜጣው የወጣበትን ቀን፣ ወርና ዓመተ ምሕረት በስክሪኑ በመጻፍ የሚፈለገው ጋዜጣ በሰከንዶች ይገኛል፡፡

በአገሪቱ ያሉ የቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያዎች እንዲሁም ጋዜጦች የመንግሥት ????a ypoal

ሲሆኑ፣ የግል ሚዲያ የለም፡፡ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሰብስክራይበር ያላቸው ሚዲያዎች በመንግሥት ቁጥጥር ስር መሆናቸው እንዲሁም አገሪቱ የዓለም ሕዝብ ከሚጠቀምባቸው የማኅበረሰብ ድረ ገጾች መገለሏ በነፃ የመረጃ ፍሰት ላይ ተፅዕኖ አያደርግምን? የሚለው የብዙዎቻችን ጥያቄ ነበር፡፡ ያሰለጠኑን ጋዜጠኞችና ሚዲያዎቻቸውን ያስጎበኙን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ቻይናውያን እንደ ዊቡ እና ዊቻች ያሉ ድረ ገጾችን መጠቀም እንደሚመርጡ ገልጸውልናል፡፡ ቻይና ውስጥና በሌሎች አገሮች ያሉ ክንውኖችንም መረጃ የማድረስ ሚናን ሚዲያዎቹ እየተጫወቱ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በሥልጠናው ከሚዲያ በተጨማሪ የቻይና ታሪክ፣ ባህል፣ የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም፣ ማርሻል አርትስና ሌሎችም ጉዳዮች ተዳሰዋል፡፡ ወደ 70 ሚሊዮን የሚጠጋው ሕዝቧ በድህነት የሚኖረው ቻይና የናጠጡ ሀብታሞች መኖሪያም ናት፡፡ ቤጂንግ ውስጥ ስዘዋወር ላምበርጊኒና ፌራሪ መኪናዎቻቸውን በፍጥነት የሚያሽከረክሩ ባለፀጋዎችና በየጎዳናቸውና በስብዌይ ዳርቻ የሚለምኑ የኔቢጤዎችን ተቃርኖ አስተውያለሁ፡፡ በከፍተኛ ሀብትና በድህነት መካከል ያለው ተቃርኖ የበለጠ የሚስተዋለው ከዋና ከተማዋ ቤጂንግ ወጥተው ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሲጓዙ ነው፡፡

ከቤጂንግ አንድ ሰዓት በአውሮፕላን ተጉዘን የጎበኘነው ኒንሻ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ነዋሪዎቹ እንደ ቤጂንግ ሰዎች ግላዊ ሳይሆኑ ከሰዎች ጋር ለመግባባት ጥረት የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በእርግጥ እንግሊዝኛ የሚናገር ሰው ስለሌለ በጉግል ትራንዝሌት ስጠቀም ነበር፡፡ መናገር የምፈልገውን በእንግሊዝኛ ጽፌ የማንደሪን ትርጓሜውን ከስልኬ አስነብባለሁ፡፡ በአፕልኬሽኑና በሰውነት እንቅስቃሴ በመታገዝም ለመግባባት ስሞክር ነበር፡፡

????a ypoal

በአየር ሁኔታ ረገድ ኒንሻ ከቤጂንግ የተሻለ ነው፡፡ ከኢንደስትሪ መስፋፋት ጋር በተያያዘ የተበከለ አየር በሚሳብበት ቤጂንግ ብዙዎቹ ነዋሪዎች ፊታቸውን በጭንብል ሸፍነው ይጓጓዛሉ፡፡ ሙቀቱ ከመጠን በላይ በመሆኑ ወንዶች ከወገባቸው በላይ እርቃናቸውን ሲሆኑ ሴቶች ቁምጣና አጫጭር ካናቴ ያዘወትራሉ፡፡ ቻይና የአየር ብክለትን ለመከላከል በየጥቂት ሜትሮች ልዩነት የዛፍ መትከል ዘመቻ ብታራምድም፣ ኢንዱስትሪዎቻቸው ካደረሱት ጉዳት ለማገገም ረዥም ጊዜ የሚወስድ ይመስላል፡፡

ብዙዎች ለመጓጓዣነት የሚመርጡት ሳይክል ሲሆን፣ አውቶቡስና ሰብዌይም በአነስተኛ ገንዘብ ለተጠቃሚዎች ቀርበዋል፡፡ የሥልጠናው አዘጋጆች ከሚዲያ ተቋሞች በተጨማሪ ታላቁ የቻይና ግንብ፣ ፎርቢድን ሲቲ፣ ቴምፕል ኦፍ ሔቨንና ሌሎችም ታሪካዊ ቦታዎችን አስጎብኝተውናል፡፡ የአበባ ፓርኮችና የፊልም ስቱዲዮዎችን የመቃኘት ዕድልም ነበረን፡፡ በተጓጓዝንባቸው ቦታዎች በአጠቃላይ የገጠሙን ቻይናውያን ጥቁር ሰዎች ሲመለከቱ ይደናገራሉ፡፡ አብረውን ፎቶ ለመነሳት የሚጠይቁና በአንክሮ የሚመለከቱን ነበሩ፡፡ ቆዳዬንና ፀጉሬን ለመንካት የሞከሩ የነበሩ ሲሆን፣ ሰዎችን በዚህ መንገድ መመልከት ተገቢ ባለመሆኑ ድርጊታቸው አናድዶኝ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ የሥልጠናው ተሳታፊዎች ግን ሕዝቡ ከቻይና ውጪ ስላለው ዓለም መረጃ የሌለው በመሆኑ ጥቁሮችን በአንክሮ የሚመለከቱት ግራ በመጋባት እንጂ በንቀት አይደለም ሲሉ ሞግተውኛል፡፡

ወደ ቻይና ከማቅናቴ በፊት በሩቅ የነበረኝ ምልከታ በዕውን በቦታው ሆኜ ሳነጻጽረው፣ በሙዚቃና ሥነ ጥበብ ረገድ የጠበቅኩትን አግኝቻለሁ፡፡ ለጥንታዊ ፍልስፍና፣ ታሪክ፣ ባህልና እምነታቸው የሚሰጡት ግምት ትልቅ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡ በየሄድኩበት ቦታ የአማልክቶቻቸውን ምስል ማየት ማስረጃ ይሆናል፡፡

ብዙዎቹ ቻይናውያን አሠልጣኞቻችንን ጨምሮ እንግሊዘኛ ቢችሉም በማንዳሪን መነጋገር ይመርጣሉ፡፡ አሠልጣኞቻችን በማንዳሪን ሲያስተምሩን ጎን ለጎን የእንግሊዝኛ አስተርጓሚ ነበር፡፡ ለጥቂት ቀናትም ቢሆን በቻይና ለመቆየት ቋንቋውን ማወቅ የግድ መሆኑን ታዝቤያለሁ፡፡

ቻይናውያን ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገሮች እንደመዘዋወራቸው ዓለም አቀፋዊ ናቸው ለማለት አልደፍርም፡፡ ሁሉም ነገር ከቻይና አንጻር፣ በቻይና ተሠርቶ፣ ለቻይናውያን የሚቀርብ ነው፡፡ ልብሱ፣ ምግቡ፣ መጠጡ፣ ሚዲያው፣ መገልገያ ቁሳቁሱና ሁሉም ነገር የቻይና ነው፡፡ የራሳቸው ለሆኑ ነገሮች የሚሰጡት ቦታ የዕድገታቸው ምስጢር ይሆን? ወይንስ ከዓለም ገለል ብለው መኖራቸው ተፅዕኖ አሳድሮባቸዋል? የሚለውን ጥያቄ አንባቢ እንደየምልከታው ሊመልሰው ይችላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...