የዓለም ሙዚቃ ቀን በዓለም ለ35ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለአምስተኛ ጊዜ ተከብሯል። የዘንድሮው በዓል በባሕር ዳር ከተማ ሐምሌ 1 እና 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ሲከበር የሙሉዓለም የባህል ማዕከል የሙዚቃ ጓድ ትርዒቶቹን አቅርቧል። በውይይት መድረኩ ላይ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ባሕር ዳርን የበለጠ ለማስተዋወቅ እንደሚረዱ ያመለከቱት የባሕር ዳር ከተማ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ በሰላም ይመኑ፣ ‹‹ቤተ ተውኔት ለመሥራት ጥያቄ ላቀረቡ አካላት ፈቃድ በመስጠት የከተማው ሕዝብ በኪነ ጥበብ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ አመቻችተናል፤›› በማለት አስረድተዋል። በአልባብ ቴአትርና የሙዚቃ ፕሮሞሽን አማካይነት የዓለም ሙዚቃ ቀን ማክበር የተጀመረው በ2004 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሲሆን፣ ሁለተኛውን ሐዋሳ፣ ሦስተኛውን በድጋሚ አዲስ አበባ፣ አራተኛውን የመቐለ ከተማ ማዘጋጀታቸው ታውቋል።