Tuesday, July 23, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፀረ ሙስና ኮሚሽንን ሊታደጉ ይገባል

በገደሙ ሁሉቃ

ሙስና ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋት ነው፡፡ ሙስና ጥቂቶች ተንደላቀው የሚኖሩበት ሲሆን፣ ብዙኃኑ ሕዝብ በድህነት እየማቀቀ እንዲኖር የሚያደርግ ነቀርሳ ነው፡፡ በአገራችን ሙስና የሚለው ቃል በግልጽ እየታወቀ የመጣው ከ1993 ዓ.ም. ወዲህ ቢሆንም ድርጊቱ ግን ለዘመናት የኖረ ነው፡፡ ነገር ግን ሙስና የሚለው ቃል በጣም የሚመች ባለመሆኑ ተቀባብቶና ተንቆለጳጵሶ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› የሚል ስያሜ ያገኘው ደግሞ በእኛው አገር ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ ነው፡፡ በእርግጥ ቤት፣ መሬትና ዕቃ የሚያከራይ ሰው ኪራይ ሰብሳቢ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ‹እኔ ቤት ስለማከራይ እኔም ኪራይ ሰብሳቢ እባላለሁ ወይ?› ያለውን አስታውሳለሁ፡፡ ቢሮ ውስጥ አንዳንድ ወጣት ሠራተኞችም ቤተሰቦቻቸው ቤት ስለሚያከራዩ ቃሉን እንፈራለን ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት በአሁኑ ወቅት በአገራችን እንደ ግዑዝ አካል ተደርጎ እየተወሰደ ያለ ትልቅ ቃል ነው፡፡ ግን ሙስና የሚለውን ቃል ላለመጥራት የታለመ መሆኑን ማንም የተረዳው አይመስለኝም፡፡

በመሠረቱ የኪራይ ሰብሳቢነት ትርጉም እሴት ሳይጨምር ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ወይም መፈለግ ሲሆን፣ የሙስና ትርጉም ደግሞ የመንግሥትን ሀብት ለራስ ጥቅም ማዋል ወይም ሌላ ሰው እንዲጠቀም ማድረግ ነው (የዓለም ባንክ ትርጉም ነው)፡፡ እሴት ሳይጨምር ጥቅም ማግኘት ወይም መፈለግ ማለት አንድ ሰው ወጪ ሳያወጣ ወይም ምንም ነገር ሳይጨምርበት ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ወይም መፈለግና ሙስና ለእኔ በጣም የተለያዩ ናቸው፡፡ በተለይም በፍላጎትና አቅርቦት መካከል ልዩነት ሲፈጠር አንዳንድ ጊዜ ተጨማሪ እሴት ሳይጨመር ተጨማሪ ገቢ ሊገኝ የሚችልበት አጋጣሚ ብዙ ስለሚሆን ሙሉ ለሙሉ ሙስና ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ አጋጣሚውን መጠቀም የሚለውን ትርጉም ስለሚሰጥ፡፡ ሌለው ተቀጽላ በመጨመር የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ወይም አመለካከት የሚባል ነገር አለ፡፡ ከላይ ከትርጉሙ አንፃር ሲታይ አንድ ሰው እሴት ሳይጨምር ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ሲፈልግ፣ ይህ ሰው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ያራምዳል ይባላል፡፡ አስተሳሰብ ወይም አመለካከት መያዝ ለእኔ ችግር አይመስለኝም፡፡ አስተሳሰብ መያዝ ሕገ መንግሥታዊ መብትም ነው፡፡ ሙስና ግን የተለየ ነው፡፡ ሙስና ጉቦ፣ ማጭበርበር፣ ማዳላት፣ መስረቅ የመሳሰሉት ትርጉም ያለው ስለሆነ፣ በተለይም በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ለሚሰጠው አገልግሎት የተሰጠውን ኃላፊነት በመጠቀም ከተገልጋይ ጉቦ መቀበል፣ የመንግሥት ሠነድ በማጭበርበር ገቢ ማግኘት፣ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ዘመዶችን መጥቀምና የመንግሥት ንብረት መስረቅ ሙስና ነው፡፡ እዚህ ላይ ሥራን አርፍዶ የሚመጣ ኃላፊና ሠራተኛም ሙስና ሠርቷል ማለት ይቻላል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት የሚለው ቃል ሙስና ለመሥራት ያሰበ ወይም የሠራ ሰው የዘየዱት ቃል ይመስለኛል፡፡ በአገራችን ሁለቱንም ቃላት በዝርዝር ለማስቀመጥ ሊሞክር እንጂ የጽሑፉ መነሻ ሌላ ነው፡፡ 

በአቶ መለስ ዜናዊ ሕይወት ዙሪያ በቅርቡ አንድ መጽሐፍ ገበያ ላይ ውሏል፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ከተጠቀሱት ርዕሶች ስለገንዘብ ስላላቸው አመለካከት ሳነብ የአሁኑን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አስታወስኩኝ፡፡ አቶ መለስ ዜናዊን የመሰለ ሰው ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ይፈጠራል ቢዬ አላስብም፡፡ ምናልባት በአንድ ትውልድ አንድ ሰው ከተገኘም በጣም ጥሩ ነው የሚል አስተሳሰብ አለኝ፡፡ አቶ መለስ ስለገንዘብ ምንም ዓይነት ዕውቀት የላቸውም፡፡ ገንዘብ በኪሳቸው አይዙም፡፡ ደመወዛቸውን ሰው ይቀበልላቸዋል፡፡ ውጭ ሲሄዱ ወደ መዝናኛ አይሄዱም፣ ገበያ ሄደው ዕቃ አይገዙም፡፡ የተሰጣቸውን ሽልማት ለዕርዳታ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ለሙስና ትግል ባላቸው አመለካከት በጣም ጽኑ አቋም ያላቸው ንፁህ ኢትዮጵያዊ ናቸው በሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩኝ፡፡ ሙስናን ይፀየፋሉ፡፡ ለሕዝባቸው በጣም ያስባሉ፣ ይጨነቃሉ፡፡ ለሕዝባቸው ዝናብ እንዲዘንብ ሁሌም ይመኛሉ፡፡ ሕዝባቸው በልቶ እንዲያድር ይመኛሉ፡፡ ለራሳቸው ግን አልኖሩም፡፡ ፈጠሪ ነፍሳቸውን በገነት ያኑረው፡፡ በምድር ባይደላቸውም ፈጠሪ ያስብላቸዋል፡፡ ሙስና  ስለሚያስከትለው ጉዳት በተለየ ገንቢ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ ‹መንግሥት በአንድ እጅ ነው ሙስናን የሚታገለው› ይላሉ፡፡ የፀረ ሙስና ትግሉ ተጠናክሮ እንዲሄድ በቂ አመራር ይሰጣሉ፡፡ ለዚህም የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎት ስላላቸው፣ ለምክር ቤት ሪፖርት ሲያቀርቡ አንድም ቀን ስለሙስና ጎጂነት ሳይናገሩ አላለፉም፡፡ መቼም መቼም ቢሆን እንዲህ ለአገሩ ዕድገት ከልቡ የሚሠራ ሰው በፍፁም አናገኝም ያልኩት ለዚህ ነው፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አቶ መለስን ተክተው ወደ ኃላፊነት ሲመጡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሥራ ኃላፊዎችን፣ የተወሰኑ ባለሀብቶችና ደላሎችን በሙስና ወንጀል እንዲከሰሱ ሲያደርጉ ብራቮ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ብለን ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ለፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርቡ ፀረ ሙስናን በተመለከተ ራሳቸው ትኩረት አድርገው እንደሚከታተሉ ለሕዝብ ቃል ገብተው ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ ባህር ዳርና መቐለ በተካሄደው የኢሕአዴግ ጉባዔዎች ላይ ስለሙስና ጎጂነት ትኩረት ሰጥተው አምርረው ይናገሩ ነበር፡፡ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ባካሄደው የጥናት ሪፖርት ይፋ ሲያደርግም፣ እንዲሁ በተወሰነ ደረጃ ስለሙስና አምርረው ሲናገሩ ነበር፡፡ በ2008 በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ ስለሙስና ሌላ ሐሳብ ይዘው ብቅ አሉ፡፡ ሙስናን ለማጥፋት በቅድሚያ የሥነ ምግባር ትምህርት በማስተማር የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል አሉ፡፡ እንዲሁም የተቋማት አሠራሮች ለሙስና ተጋላጭ እንዳይሆኑ የሙስና መከላከል ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ፡፡  በ2009 በጀት ዓመት ግን ስለሙስና ጎጂነና በሙስና ላይ ስለሚወሰድ ዕርምጃ ላይ የተናገሩት ደግሞ የተለየ ነው፡፡ ‹ሙስና እንደተሠራ ይወራል፡፡ ነገር ግን ማስረጃ ማግኘት አይቻልም፡፡ የሙስና ችግር በትልቁ ይወራና ማስረጃ ሲባል አይጥ የምታህል ነች› አሉ፡፡ ቀጥሎም የመንግሥት ኃላፊዎች ሀብታቸውን እንደሚያስመዘግቡና የተመዘገበው ሀብት ለሕዝብ ይፋ ሲሆን፣ ሕዝቡ የተመዘገበውን እያየ በልዩነት ሪፖርት ሲያቀርብ ዕርምጃ ይወሰዳል ብለው ቃል ገቡ፡፡ ሲተገበር ግን አላየንም፡፡ ሙስና ላይ ምርመራ ለማካሄድ እንደ አሜሪካ ዓይነት ኤፍቢአይ (FBI) አቋቁመናል አሉ፡፡ ግን ነው ወይ? አይደለም፡፡ በ2009 በጀት መጨረሻ ሪፖርት ላይ ስለሙስና በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የሙስና ወንጀሎች በኤፍቢአይ (FBI) እንዲመራመሩ ይደረጋል አሉ፡፡ ምን ያህል ውጤታማ እንደሚሆኑ ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ ነገር ግን በ2009 መጀመሪያ አካባቢ ሙስና በአገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን አንድ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁር አስረግጠው ሲናገሩ ሰምተው ይሆን ወይ ብዬ አስባለሁ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ራዕይ ለማሳካት ተግተው እንደሚሠሩ ቃል ገብተው ነበር፡፡ የሕዝብ ነቀርሳ የሆነውን ሙስናን በፅኑ መታገል የአቶ መለስ ዜናዊ ራዕይ ነበር፡፡ እሳቸው ሙስናን በጽኑ ለመታገል ያዋቀሩት የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንን ነው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም  ግን ከሥነ ምግባርና ከፀረ ሙስና ሥራዎች ውስጥ የሙስና ወንጀል ጥቆማ የመቀበል፣ የመመርመር፣ የመክሰስ፣ የማስቀጣትና የተመዘበረ ሀብት የማስመለስ ሥራዎችን ለፌዴራል ፖሊስና ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንዲሰጥ አደረጉ፡፡ ምክንያቱ ግን ለሕዝብ ግልጽ  አይደለም፡፡ ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተሰጠውን የዓቃቤ ሕግ ሥራ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም መስጠቱ ትክክል ነው ብሎ ያምናል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ በአገሪቱ ሰፊ አደረጃጀት ያለውና ከሕዝቡ ጋር ዕለት ተዕለት ቀጥታ ግንኙነት ያለው ተቋም ስለሆነ የሙስና ተጋላጭነቱ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በትራንስፓራንሲ ኢንተርናሽናል የባሮሜትር ጥናትና የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን የሚያደርጋቸው ጥናቶች ፖሊስ ለሙስና ተጋላጭነቱ ከፍተኛ መሆኑን በግልጽ ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም የፖሊስ አደረጃጀት በከፍተኛ ሁኔታ ለሙስና ተጋላጭ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ግን ባልታወቀ ምክንያት ደፍረው የሙስና ወንጀል ምርመራ ሥራን ለፌዴራል ፖሊስ ሰጡ፡፡ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ይህ ሥራ ሲያከናውን ከሕዝቡ የሚቀርበው የሙስና ወንጀል ጥቆማ እስከ 5,000 ድረስ ነበር፡፡ የፌደራል ፖሊስ ግን ይህን አላደረገም፡፡ ከውስጥ አዋቂ ምንጭ እንደተነገረኝ ከሆነ ከ1,000 ያልበለጠ የሙስና ወንጀል ጥቆማ መቀበሉን ሰምቻለሁ፡፡ ኮሚሽኑ በዓመት በሙስና ከተመዘበረ ሀብት እስከ ከሃምሳ ሚሊዮን ብር በላይ ያስመልስ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ፌዴራል ፖሊስ ግን ይህ ያህል ገንዘብ ማስመለሱን በሪፖርቱ ላይ አልገለጸም፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከነበረበትና ለ15 ዓመታት ሲጠቀምበት ከነበረበት ሕንፃ እንዲወጣ አድርገዋል፡፡ ኮሚሽኑም የሙስና ወንጀል ምርመራ ሥራ ሲወስድበት የማስተማርና የመከላከል ሥራ ለማከናወን ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግና ስትራቴጂና ሥልት በመቀየስ ወደ ሥራ በመግባት ላይ መሆኑን፣ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ለማየት ችያለሁ፡፡ ኮሚሽኑ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መነሻነት በፀረ ሙስና ትግል ላይ የኅብረተሰቡን ተሳትፎና ሚና የበለጠ ለማሳደግና ንቅናቄ ለመፍጠር እንዲያስችለው፣ ይህን የሚያስፈጽም የሰው ኃይል በማደራጀት የተለያዩ ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አውቃለሁ፡፡ ከ900 በላይ የሙያ ማኅበራትን በማደራጀት እንቅስቃሴ ያደርጋል፡፡ የእነዚህ ማኅበራት ሥራ አስፈጻሚዎች በየሦስት ወራት የአፈጻጸም ግምገማ የሚያካሄዱት እዚሁ ኮሚሽኑ ሕንፃ ውስጥ ነው፡፡ ኮሚሽኑ ከሙያ ማኅበራትና ከመንግሥት ተቋማት ለተውጣጡ አካላት የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ትምህርትና ሥልጠናዎችን የሚሰጠው በሕንፃው ውስጥ ነው፡፡ ለሠልጣኝ የምሳ መስተንግዶ የሚያደርገው በአነስተኛ ዋጋ በሠራተኞች መዝናኛ ክበብ ነው፡፡ ሕንፃውን ሲለቅ ግን እነዚህ ሥራዎች በኪራይ በሚያገኛቸው ሕንፃዎች ውስጥ የሚያከናውን ከሆነ ግን መንግሥት ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ ይሆናል፡፡

ሌላው የሠራተኞች ቢሮ እጥረት ነው፡፡ ኮሚሽኑ ከ300 በላይ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ የቤቶች ኮርፖሬሽን ግን ቢበዛ 140 ሠራተኞች የሚይዝ ስለሆነ ኮሚሽኑ ለ160 ሠራተኞች ሌላ ቢሮ መከራየት ይጠበቅበታል፡፡ ሠራተኞችን በሁለት በተለያዩ ቦታዎች ማስተዳደር ከመርህ አኳያ አይመከርም፡፡ ይህ እንግዲህ ኮሚሽኑ የሙስና ወንጀል ምራመራ ከተወሰደበት በኋላ የመጣ ዕዳ ስለሆነ አሁን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ኮሚሽኑን ሊታደጉት ይገባል፡፡ አባት የሌለው ተቋም እንዳይሆንና የአቶ መለስ ዜናዊን ራዕይ ለማሳካት ከልብ ከተነሱ የኮሚሽኑን ችግር ጆሮ ሰጥተው ማዳመጥ አለባቸው፡፡ ችግሩን መረዳትና ማቃለል ይኖርባቸዋል፡፡ የሕዝብ ተቋም ስለሆነ ማጠናከር አለባቸው፡፡

በአገሪቱ ባሉት ዘጠኙም ክልል መስተዳደሮች የሥነ ምግባርና  የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች እሉ፡፡ የእነዚህ የክልል ሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች አደረጃጀት የሙስና ወንጀል ምርመራና ዓቃቤ ሕግ ይዘው የተደራጁ ሲሆን፣ የፌዴራል የሙስና ወንጀል ሲቀነስበት የክልል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች የያዙትን አደረጃጀት እንዳሉ ይዘው ነው ያሉት፡፡ ከአገራዊ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ትግል ውጤታማነት አኳያ ሲታይና የክልሎች የሙስና ወንጀል ምርመራ ሥራ ውጤት ብቻ ሲገመገም፣ ኮሚሽኑ የፌዴራል ፖሊስና የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን በመጠየቅና በማሳመን ሪፖርት ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ዛሬ ያለው የመረጃ አያያዝ ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ ይህም የአገሪቱን የፀረ ሙስና ትግል ስትራቴጂና ሥልት የተለያየና ጉራማይሌ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አገሪቱ ወጥ የሆነ የፀረ ሙስና ትግል እንዲኖር ትኩረት መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡

መነሻዬ ላይ ወዳነሳሁት ሐሳብ ልመለስና ኅብረተሰቡ ዘንድ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት አንድ ዓይነት እየሆነ እየተወሰደ ነው፡፡ የመንግሥት ኃላፊዎችና ሚዲያዎች ኪራይ ሰብሳቢነት የነገሠበት የሚሉ አባባሎችን በተደጋጋሚ ስለሚያስተጋቡ፣ ኅብረተሰቡም ሙስና የሚለውን ኪራይ ሰብሳቢነት በሚል በመተካት እየተረዳ ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት ብቻውን ችግር አይደለም፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ የያዘ ሰው አስተሳሰቡን ወደ ተግባር ሲለውጥ ግን ችግር ይሆናል፡፡ ከዚህ አንፃር ሕዝቡ ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን ለይቶ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ ሁሉም ሰው የተለያየ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ሊኖረው ይችላል፡፡ የተፈጥሮ ሕግ ስለሆነ ተጨማሪ እሴት ሳይጨምር ጥቅም የማይፈልግ የሰው ልጅ አይኖርም፡፡ መጠኑ ይለያይ እንጂ ሁሉም ሰው የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ያራምዳል፡፡ ሙስና ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ሙስና በጥሬ ቃሉ ሌብነት ነው፡፡ ሙስና በአንድ ጉዳይ ላይ የመወሰን ኃላፊነት የተሰጠው ሰው ድርጊት ነው፡፡ የመንግሥት አገልግሎት በተለይም የአገልግሎቱ ፈላጊዎች ሲበዙበት፣ ወይም አገልግሎት ፈላጊው የሚጠበቅበትን ግዴታ ለማሟላት ሳይችል ሲቀር ክፍተቱን ለመሙላት ሲል፣ ወይም በተሰጠው ኃላፊነትን ተጠቅሞ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ተገልጋዮች ያለበትን ክፍተት በመጠቀም ሙስና ይሠራል፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ በመንግሥት ንብረትና ሰነድ ላይ ያለውን ቅርበት በመጠቀም ሙስና ይፈጽማል፡፡ ስለሆነም በኪራይ ሰብሳቢነትና በሙስና መካከል ያለው ብዥታ ለኅብረተሰቡ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ካልሆነም በኪራይ ሰብሳቢነት ጥላ ሥር ሆኖ ሙስና የሚለውን ስም ማጥፋት አይገባም፡፡ በጥቅሉ ሙስና ሌብነት ነው፡፡ መሸፋፈን አያስፈልግም፡፡

ስለዚህ መንግሥታዊ የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ ላይ መልካም አስተዳደር ለማስፈን ኪራይ ሰብሳቢነትን መታገል የሞት ሽረት ጉዳይ የተባለው ሙስና ላይ ብዥታን ስለፈጠረ፣ ሙስናን መታገል በሚል ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በኃላፊነት ዘመናቸው የአቶ መለስ ዜናዊን ራዕይ ዕውን ለማድረግ የገቡትን ቃል የሚያከብሩ ከሆነ፣ ሙስናን በፅኑ መታገል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሙስና በአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ልማት፣ ዕድገትና በሕዝቡ ኑሮ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በተለይ ሙስናን ፈጽመው ገቢ ያላቸው ሰዎች ገበያ ላይ የመግዛት አቅማቸው ከፍተኛ ስለሚሆን፣ ደሃው ሕዝብ ከእነሱ ጋር ተወዳደሮ ገበያ ውስጥ ግዥ መፈጸም ስለማይችል፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ይህንን ተረድተው በሕዝቡ ጎን ሊቆሙ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በተሟላ የአመራር ብቃትና ክህሎት እንዲመራ ማድረግና ኮሚሽኑ አሁን እደረሰበት ካለው እንግልት ማላቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ካልሆነ ግን የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ላለፉት 14 ዓመታት በተለይም አቶ መለስ በነበሩበት ዘመን ለሠራው ሥራ አሁን እየተቀጣ ነው ወደሚለው ድምዳሜ ይወስዳል፡፡

የኮሚሽኑ ሠራተኞች የታዘዙትን በማከናወናቸው ሞራላቸው ሊነካ አይገባም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መንግሥት ተቋሙን የማይፈልግ ከሆነ ደግሞ ለሕዝብ በግልጽ ይፋ በማድረግ መዝጋት አለበት፡፡ መንግሥት ይኼንን ያደርጋል የሚል እምነት ግን የለኝም፡፡ ለዚህ ያበቀኝ ግን አሁን እየተፈጸመ ያለው አዝማሚያ ለመዝጋት ነው እንዴ የሚያስብል ስለሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፀረ ሙስና ትግል ውጤትን በሚገባ ይረዳል፡፡ የተማረ ሕዝብ አለን፡፡ የሚጎዳውንና የሚጠቅመውን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በእርግጥ ኮሚሽኑ ራሱ የውስጥ ችግር ላይ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ይህ ደግሞ ማረም የሚቻል የውስጥ ችግር ነው፡፡ ተቋሙ የሕዝብ ስለሆነ መፍረስ ግን የለበትም፡፡ ኮሚሽኑ በሕዝቡ ዘንድ መልካም ስም (Goodwill) አለው፡፡ በሕዝብ አዕምሮ ውስጥ ከነሕንፃው ገብቷል፡፡ ምንም ባይሠራ እንኳን ቢያንስ ሙስና የሚፈጽሙትን ሰዎች ለፀረ ሙስና እናገራለሁ እየተባለ እንኳን ለማስፈራራት ይጠቅማል፡፡ ፖሊስ ለዘመናት ከሕዝብ ጋር አብሮ የኖረ ስለሆነ ሕዝብና ፖሊስ በጣም ይተዋወቃሉ፡፡ ፖሊስ በአደረጃጀቱ ብዙ ስለሆነ ሙስና ውስጥ የመግባት ነገር የተለመደና የኖረ ነው፡፡ የተሃድሶና የኪራይ ሰብሳቢነት መፈክር በፖሊስ ቤት የተፈለገውን ያህል ውጤት ሊያመጣ አይችልም፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ለወደፊት ታሪካቸው ተጨማሪ ግብዓት እንኳን ሲሉ ኮሚሽኑ ቢያጠናክሩና ቢታደጉ ይሻላል የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ ሕንፃውን ለኮሚሽኑ ይተውለት እላለሁ፡፡ የቤቶች ኮርፖሬሽንም  የመገንባት ‹ማንዴት› ስላለው የራሱን ሕንፃ መገንባት ይኖርበታል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ውሳኔዎ በጉጉት ይጠበቃል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles