በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የቀን ገቢ ግምቱ ይፋ ከሆነ በኋላ መመርያውን ተጠቅመው ቅሬታ ያቀረቡ ከ33 በመቶ በላይ የሚሆኑ ነጋዴዎች፣ ግብር መስተካከሉ ተገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የአዲስ አበባ ግብር አወሳሰንና አሰባሰብ ፕሮግራም ልማትና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ፈቃደ ማክሰኞ ሐምሌ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጠበት ወቅት እንደተናገሩት፣ በባለሥልጣኑ መመርያ መሠረት ቅሬታቸውን ያቀረቡ ነጋዴዎች ቅሬታቸው ታይቶና ተመርምሮ መፍትሔ እየተሰጠ ነው፡፡
ከሚያዝያ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል ሲካሄድ የቆየው የቀን ገቢ ግምት ተጠናቆ ይፋ ሲደረግ፣ ድብቅ ዓላማ ባላቸው ቡድኖች አማካይነት የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ሱቃቸውን እንዲዘጉና እንዲያምፁ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ድብቅ ዓላማ ባላቸው ቡድኖች አማካይነት የአዲስ አበባ ነጋዴዎች የንግድ ተቋማቸውን እንዲዘጉና እንዲያምፁ እየተደረገ መሆኑን አቶ ያሬድ ገልጸው፣ በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ አንዳንድ ሥፍራዎች የሚገኙ ነጋዴዎች የንግድ መደብሮቻቸው የመዝጋት አዝማሚያ ማሳየታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ባለሥልጣኑ የከተማዋን ነጋዴዎች ቅሬታ ተቀብሎ በተገቢው መንገድ እየፈታና ከነጋዴው ማኅበረሰብ ጋር ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ ድብቅ ዓላማ ባላቸው ቡድኖች አማካይነት ሱቆች እየተዘጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በአዲስ አበባ በተለይም መርካቶ አካባቢ የንግድ ተቋማትን የመዝጋት አዝማሚያ እየታየባቸው እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ የስፋት መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ እስካሁን እንዳልታወቀ ተናግረዋል፡፡
ብዙ ገንዘብ ወጥቶበትና ባለሙያ ተመድቦ ሲካሄድ የነበረው የቀን ገቢ ግምት ጥናት ከመሠረቱ ችግር ያልነበረበት መሆኑን አቶ ያሬድ ጠቅሰው፣ ‹‹ችግር የተፈጠረው መረጃው ይፋ ከሆነ በኋላ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ባለሥልጣኑ የቤት ሥራውን በተገቢው መንገድ ሲሠራ ቢቆይም፣ በከተማዋ ውስጥ ያሉ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት ነጋዴዎች ቅሬታ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ አትክልት ገብረ እግዚአብሔር በበኩላቸው፣ ‹‹ደረጃ ሐ ግብር ከፋይ የሚባሉት እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ብቻ ግብራቸውን መክፈል ስለሚጠበቅባቸው፣ ቅሬታቸውን እንዲያቀርቡ ቅድሚያ በሰጠነው መሠረት 99.2 በመቶ የሚሆኑ ቅሬታ አቅራቢዎች ቅሬታቸው ተፈቷል፤›› ብለዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋይ የሚባሉት ነጋዴዎች ሙሉ በሙሉ ግብራቸውን በወቅቱ ለመክፈል መስማማታቸውንም አክለዋል፡፡
ነጋዴዎቹ በዚህን ያክል መጠን ግብር ለመክፈል ከተስማሙ ለምን በአዲስ አበባ የተወሰኑ ቦታዎች የንግድ መደብሮች ተዘጉ? የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ነጋዴው ግብሩን በወቅቱ ለመክፈል ዝግጁ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ኃይሎች እያደረጉት ባለው ጥሪ እንዲህ ዓይነት ክስተት ሊመጣ ችሏል፤›› ብለዋል፡፡
የገቢ ግብር የሚመራበት መመርያ ቁጥር 123/2009 መዘጋጀቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ መመርያ መሠረት በአሁኑ ወቅት እየተሰበሰበ ያለው በዚህ ዓመት በተሰበሰበው መረጃ መሠረት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ቀጥታ ያልሆነ ታክስ የሚከፍሉት በ2003 ዓ.ም. በተቀመጠው መመርያ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ነጋዴዎች በ2003 ዓ.ም. የቀን ገቢ ግምት ካልነበራቸው ደግሞ በታሳቢ ይከፍሉ የነበረውን ይከፍላሉ፡፡ ይኼ ከሌላቸው ደግሞ ግብር ከፋዮች ወደ ታክስ አስተዳደሩ ሲቀርቡ የንግድ ትርፍ በአሁኑ ይሠራና ቀጥታ ያልሆነ ታክስን ግን ራሳቸው ባመኑት አሳውቀው እንዲከፍሉ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ በቀን ይኼን ያህል ነው የቀን ሽያጭ ተብሎ የታመነውን የመጨረሻ አድርገን እንይዛለን፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ባለሥልጣኑ የቀን ገቢ ግምት ሥራውን አከናውኖና ለሕዝቡ አሳውቆ ያጠናቀቀ በመሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት ከዚህ ሥራ እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
‹‹የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ እያለ የቀን ገቢ ግምት ሊሠራ የቻለው አንደኛ በቀጣይ መረጃውን የማያቀርቡ ከሆነ ለመጠቀም ሲሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ ነጋዴው አካባቢ ሥጋት ኖሮ ኦዲተሩ ይኼን መረጃ እጠቀማለሁ ብሎ ከጠየቀ ለመጠቀም ነው፣›› ብለዋል፡፡
እንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ሲያጋጥም የኑሮ ውድነት አያስከትልም ወይ? ይኼንን ችግር ለመፍታት ባለሥልጣኑ ምን ያስቀመጠው ጉዳይ አለ? የሚሉ ጥያቄዎች ከጋዜጠኞች የተጠየቁ ቢሆንም ኃላፊዎቹ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡