ሆ ብለን መጣን ሆ ብለን
ጌቶች አሉ ብለን
ሆ ብለን መጣን ሆ ብለን
እሜቴ አሉ ብለን
እውዬ (እኸ) እዋውዬ ካሽከር ተዋውዬ
ጌቶች አሉ ብዬ ገባሁ ሰተት ብዬ
አበባየሆሽ (ለምለም)
ባልንጀሮቼ (ለምለም) ቁሙ በተራ (ለምለም)
እንጨት ሰብሬ (ለምለም) ቤት እስክሰራ (ለምለም)
እንኳን ቤትና (ለምለም) የለኝም አጥር (ለምለም)
እደጅ አድራለሁ (ለምለም) ኮከብ ስቆጥር (ለምለም)
ኮከብ ቆጥሬ (ለምለም) ስገባ ቤቴ (ለምለም)
ትቆጣኛለች (ለምለም) የንጀራ እናቴ (ለምለም)
የንጀራ እናቴ (ለምለም) ሁለ’ልጅ አላት (ለምለም)
ለነሱ ፍትፍት (ለምለም) ለኔ ድርቆሽ (ለምለም)
ከሆዴ ገብቶ (ለምለም) ሲንኮሻኮሽ (ለምለም)
አበባማ አለ (ለምለም) በየውድሩ (ለምለም)
ባልንጀሮቼ (ለምለም) ወልደው ሲድሩ (ለምለም)
እኔ በሰው ልጅ (ለምለም) ማሞ እሹሩሩ (ለምለም)
አደይ የብር ሙዳይ ኮለል በይ
ከገዳይ ጋራ (ለምለም) ስጫወት ውዬ (ለምለም)
ራታችንን (ለምለም) ንፍሮ ቀቅዬ (ለምለም)
ድፎ ጋግሬ (ለምለም) ብላ ብለው (ለምለም)
ጉልቻ አንስቶ (ለምለም) ጎኔን አለው (ለምለም)
ከጎኔም ጎኔ (ለምለም) ኩላሊቴን (ለምለም)
እናቴን ጥሯት (ለምለም) መድሃኒቴን (ለምለም)
እሷን ካጣችሁ (ለምለም) መቀነቷን (ለምለም)
አሸተዋለሁ (ለምለም) እሷን እሷን (ለምለም)
አባቴን ጥሩ (ለምለም) መድሃኒቴን (ለምለም)
እሱን ካጣችሁ (ለምለም) ጋሻ ጦሩን (ለምለም)
አሸተዋለሁ (ለምለም) እሱን እሱን (ለምለም)
አደይ የብር ሙዳይ ኮለል በይ
እቴ አበባ ሽታ አበባዬ (አዬ እቴ አበባዬ)
እቴ አበባሽ ስትለኝ ከርማ (አዬ እቴ አበባዬ)
ጥላኝ ሄደች ባምሌ ጨለማ (አዬ እቴ አበባዬ)
እቴ አበባሽ እቴ እያለቺኝ (አዬ እቴ አበባዬ)
ጋሻ ጦሬን ወስዳ አሸጠቺኝ (አዬ እቴ አበባዬ)
እንኳን ጋሻ ይሸጣል በሬ (አዬ እቴ አበባዬ)
ከናጥንቱ ከነገበሬ (አዬ እቴ አበባዬ)
ሄሎ ሄሎ የገደል ሄሎ (አዬ እቴ አበባዬ)
ማን ወለደሽ እንዲህ መልምሎ (አዬ እቴ አበባዬ)
ወለደቺኝ መለመለቺኝ (አዬ እቴ አበባዬ)
ላፈንጉስ ዳርኩሽ አለቺኝ (አዬ እቴ አበባዬ)
ካፈንጉስ አምስት ወልጄ (አዬ እቴ አበባዬ)
አንዱ ዳኛ ያውም መልከኛ (አዬ እቴ አበባዬ)
አንዱ ቄስ ቆሞ ቀድስ (አዬ እቴ አበባዬ)
አንዱ ቂል ንፍሮ ቀቅል (አዬ እቴ አበባዬ)
አንዷ ሴት የሺመቤት (አዬ እቴ አበባዬ)
አንዱ ሞኝ ቂጣ ለማኝ (አዬ እቴ አበባዬ)
ይሸታል ዶሮ ዶሮ የማምዬ ጓሮ
ይሸታል ጠጅ ጠጅ የጌቶችም ደጅ
ሻሽዬ (እኸ) ሻሽ አበባ
ደሞም ሻሽ አበባ
እራስ ሥዩም ግቢ ይታያል ሲኒማ
የማነው ሲኒማ ያፀደ ተሰማ
ሻሽዬ (እኸ) ሻሽ አበባ
ደሞም ሻሽ አበባ
ትራሷም ባላበባ
ፍራሹም ባላበባ
እርግፍ እንደወለባ
የማምዬ ቤት (ለምለም) ካቡ ለካቡ (ለምለም)
እንኳን ውሻቸው (ለምለም) ይብላኝ እባቡ (ለምለም)
ከብረው ይቆዩን ከብረው
ባመት ወንድ ልጅ ወልደው
ሃምሳ ጥገቶች አስረው
ከብረው ይቆዩን ከብረው
ከብረው ይቆዩን በፋፋ
የወለዱት ልጅ ይፋፋ
ከብረው ይቆዩን በስንዴ
ወንድ ልጅ ወልደው ነጋዴ
ከብረው ይቆዩን ከብረው
(የሕዝብ ግጥም)
ምስል በሕይወት ከተማ
- ከአንድምታ ድረ ገጽ የተገኘ
ክረምት!
አሁን ባለንበት
ባለው ጊዜ ኹነት
ባለው ጊዜ ሒደት
የሚሰነብት
በልጉ ተመ‘ር መኸር
መኸሩ ተዘር ዘር
በዘረዘረበት
ክረምት ይወጣበት።
አሳቡ ሞልቶለት
ትልሙ ፈር ይዞለት
ዘሩ ሁሉ ሲያቆት
ፍሬ እምፍሬያት
ካናቱ በረከት
የሚቋደሱበት
አይቀር መቸም ያሸት
ቀኑ በያዘ ዕለት።
ዘሪው ዘር ለመዝራት
ተግቶ በዋለበት
ስጋቱ ወደ ምሽት
ምሽቱ ወደ ሌሊት
ሌቱ ወደ ውድቅት
ዘንበል እንዳለለት
በነፃነት ስሜት
ክረምት ይወጣበት።
- ኃይለ ልዑል ካሣ
(ነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም.)
***
በንብ ተወሮ ደቂቃዎችን በመቆየት የዓለም ሪከርድን የሰበረ
ሰዎች በዓለም ሪከርድ ለመስፈርና ዝናን ለማትረፍ የተለያዩ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡ በካናዳ ነዋሪ የሆነው ጁዋን ካርሎስም በዓለም ሪከርድ ለመስፈር ሲል በርካታ የንብ እንጀራ ፊቱ ላይ በመልበስ በንብ ተወሮ ታይቷል፡፡
ሲቢሲ እንዳሰፈረው፣ በኦንታሪዮ በሚገኝ የንብ ማነቢያ እርሻ ሠራተኛ የሆነው ካርሎስ፣ ከዚህ በፊት በዚህ ድርጊት ተይዞ የነበረውን ሪከርድ ለስምንት ተጨማሪ ደቂቃዎች በንብ ተወሮ በመቆየት አሻሽሎታል፡፡