Monday, February 26, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ነጠብጣቡን ማገናኘት . . . ዓባይ የዘመኑ እንቆቅልሽ በግጭት ወይስ በትብብር?

 በእስክንድር ከበደ

በአንድ ወቅት አንድ ዕውቅ ኢትዮጵያዊ ምሁር ለኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች በተዘጋጀ ዓውደ ጥናት ላይ የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹ንክኪ ካለ (Intensity of Contact) ግንኙነት አለ። ያለንክኪ ፍቅርም ሆነ ጥላቻ ሊኖር አይችልም› ብለው ነበር፡፡

ይህን የንክኪ ጽንሰ ሐሳብ ጸሐፊው ለዚህ ጽሑፍ እንደ መንደርደሪያነት የተጠቀመበት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ጎረቤተ ብዙ እንደ መሆኗ የንክኪዋ መጠንም ሆነ ፈርጅ እንደዚሁ የተበራከተ ነው። በእርግጥም ኢትዮጵያ የጎረቤትም ሆነ የጉርብትና ችግር የለባትም፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን አጎራባቾቿ በሙሉ በተለያዩ የፖለቲካ ርዕዮትና የፍልስፍና መንገድ የተቃኙ መሆናቸው ነው፡፡

ዓባይም አንድ የንክኪ ዘርፍ በመሆኑ ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር በሚኖራት ግንኙነት ላይ የራሷ አንድምታ ይኖረዋል፡፡ የወንዝ ንክኪ ከአየር ንክኪ ይልቅ በአንድ አገር ግንኙነት ላይ በበጎም ሆነ በክፉ ገጽታው የተሻለ ፋይዳ አለው፡፡ ንክኪው ከየብስ ንክኪ አንፃር ሲታይ ጠቀሜታውም ሆነ ጉዳቱ ብዙም አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ ከሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ ከጅቡቲ፣ ከኬንያና ከኤርትራ ጋር በየብስ ትዋሰናለች፡፡ ከእነዚህ አገሮች ጋር ያላት የንክኪ መጠን በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ቢሆን ጥቅሙ የሚያመረቃና ልማቱ ቋት የሚሞላ ሲሆን፣ ለጥፋት ከዋለም ጉዳቱ የከፋና የመጎርበጥ እንዲሁም የእያንዳንዱን አገር ህልውና የሚፈታተን እንደሚሆን ይታመናል፡፡

በሌላም በኩል ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ካላት ንክኪ አንፃር ሲሰላ ፋይዳው ከአማካይ በታች ቢሆንም ጉዳቱና ውስብስብነቱ ከሁሉም የላቀ ሆኖ ይታያል፡፡ በተለይም ወታደራዊ ኃይላቸው የፈረጠመ፣ ፖለቲካዊ ክንዳቸው የረዘመ፣ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው የደለበ አገሮች በሌሎች አገሮች ውስጥ ያላቸውን ጥቅም ለማስከበር አልፎ ተርፎም ተፅዕኖአቸውን ለማሳረፍና አመለካከታቸውን ለማስረፅ ከታላሚ (Target) አገሮች ጋር የየብስ ንክኪ ባላቸው አገሮች ሲጠቀሙ ይስተዋላሉ፡፡ እንዲሁም በተለያየ መንገድና ደረጃ በዲፕሎማሲያዊ ትግል ተግዳሮት የሚፈጥሩበት ሁኔታም ይስተዋላል፡፡

የግብፅን ሁኔታ የተመለከትን እንደሆነ፣ ከዚህ አመለካከት የፀዳች አይደለችም፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያየ መንገድ ንክኪ ባላቸው አገሮች በመጠቀም በኢትዮጵያ ውስጥ ያላትን ጥቅም ለማስከበር ደፋ ቀና ስትል ይታያል፡፡

በአንፃሩ ኢትዮጵያ ለመልካም ጉርብትና ከምንም በላይ ቅድሚያ በመስጠት የአጎራባች አገሮች ሰላምና ደኅንነት የተጠበቀ እንዲሆን፣ አልፎ ተርፎም ለአፍሪካ አንድነት ነፃነትና ብልፅግና ወሳኝ ሚና ለመጫወቷ ታሪክ ህያው ምስክር ነው፡፡ ለአብነት ያህልም የቀድሞው  የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት እንዲመሠረት ያደረገችው ግንባር ቀደም ተሳትፎ፣ ከአጎራባች አገሮች የሱዳንና የሶማሊያን የውስጥ ችግር ለመፍታት የተጫወተችው ሚና፣ በአኅጉር ደረጃ የኮንጎ፣ የላይቤሪያ፣ የሩዋንዳንና የቡሩንዲን የውስጥ ግጭት ለማስወገድ ያደረገችውን ጥረት ከእነዚህም በተጨማሪ ለዚምባቡዌና ለደቡብ አፍሪካ ነፃነት ያደረገችውን አስተዋጽኦ ማመልከት ይቻላል፡፡

 

ይሁን እንጂ ለዚህ በጎ የመልካም ጉርብትና እንቅስቃሴ በአጎራባቾቻችን በኩል አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ሲገባው፣ አንዳንድ ጎረቤቶቻችን ከግብፅ ጋር ድርና ማግ በመሆን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሲፈታተኑ ቆይተዋል፡፡ ጎረቤት አገሮች ይህን አሉታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ከብሔራዊ ጥቅማቸው አንፃር ብቻ ጠቃሚ ሆኖ ስላገኙት ሳይሆን፣ አንዳንዴም በስተጀርባው የውኃ ፖለቲካን ያዘለ የግብፅን ድብቅ አጀንዳ የማራመድ ዓላማን ለማሳካት የተደረገ እንቅስቃሴ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡

ኢትዮጵያና ግብፅ ከአንድ ወንዝ ውኃ የሚጠጡ፣ ረዥም ታሪክና የታሪክ ትስስር ያላቸው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች አባሎች ቢሆኑም፣ እንዳላቸው ትስስር ግንኙነታቻው በሚፈለገው መልክ ጠንካራ ነበር ማለት አያስደፍርም፡፡ ግብፅ ናይልን በተመለከተ ስታራምድ የቆየቻቸው ፖሊሲዎች በዓይነት የተለያዩ ቢመስሉም በይዘት አንድና አንድ ስትራቴጂ፣ ግባቸውም አንድና አንድ ነው፣ “ዓባይን ከምንጩ” የሚል ነው፡፡ 

 ታሪክ እንደሚያመለክተው የዓባይ ውኃ ጥያቄ የትናንትና ሳይሆን ዘመን ያስቆጠረ፣ እስከ ዛሬም ድረስ ዘለቄታዊ ዕልባት ያላገኘና ሥር የሰደደ ጥያቄ ነው፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ላይ ቀና አመላካከት የሌላቸው አንዳንድ የግብፅ ባለሥልጣናትና ምሁራን ኢትዮጵያ እስካለች ድረስ መሪዎቹ የመንፈስ እርጋታ፣ ሕዝቡም ሰላምና ዕፎይታ እንደማያገኝ ይዘክራሉ፡፡ ስለሆነም የግብፅ መንግሥት ፖለቲካዊ መረጋጋት፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ብልፅግናና የሕዝቡ ውሎ ማደር ዋስትና የሚኖረው ዓባይን ከምንጩ መቆጣጠር ሲቻል ነው የሚል ህልም አላቸው፡፡ ለዚሁ ግብ ስኬታማነት በኢትዮጵያ ላይ አፍራሽ አመለካከት ሲያራምዱ ይታያሉ፡፡

 

ዓባይን ከምንጩ የሚለው መርህ ግብፆች በራሳቸው የፈጠሩት ሳይሆን፣ ከእንግሊዝ ቅኝ ገዥዎች የተማሩት ነው፡፡ በተለይም በ18ኛው ክፍለ ዘመን እ.ኤ.አ. ከ1861 እስከ 1949 የኖረው ዕውቅ እንግሊዛዊ የፖለቲካ ጂኦግራፊ ምሁር ጆን ማኪንደር “The Heart Land” (The Land Foyer of Eurasia)” የሚባለውን አካባቢ መቆጣጠር ዓለምን መቆጣጠር ያስችላል የሚለው መርህ በግብፅ መሪዎች ዘንድ ሰርፆ በመግባቱ፣ የመምህራቸውን የማኪንደርን ፈለግ በመከተል “የራስጌ አገሮችን መቆጣጠር ዓለምን መቆጣጠር ያስችላል” በሚል እሳቤ የዓባይን ሸለቆ በተለይም ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ያላደረጉት ጥረት የለም፡፡

በቱርክ ሥልጣን የግብፅ አስተዳዳሪ ሆኖ የተሰየመው መሐመድ ዓሊ ፓሻ በግብፅ ያለውን የማምሉክ አስተዳደር ካስወገደ በኋላ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት በማቋቋም በርካታ ግድቦች፣ እርከኖችና ሰፋፊ የመስኖ ሥራዎች ከመጀመሩም ባሻገር ዘመናዊ የጦር ሠራዊት በማደራጀት ወደ ሱዳን፣ ኡጋንዳና ኢትዮጵያ ወሰን ያደረገው የመቆጣጠር እንቅስቃሴ፣ ከዲቪ እስማኤል ፓሻ የተባለው የመሐመድ ዓሊ ፓሻ የልጅ ልጅ ደግሞ የአያቱን ህልም ዕውን ለማድረግ በመጀመርያ ሶማሊያንና ሐረርን ለመቆጣጠር፣ በመቀጠል ደግሞ በ1875 ዓ.ም. በጉራዕ፣ በ1876 ዓ.ም. በጉንደት ያደረገው የጦርነት እንቅስቃሴ ለአብነት የሚጠቀሱ አንኳር የጠብ አጫሪነት ዕርምጃዎች ናችው፡፡

በአጠቃላይ በግብፅ ፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ ከመሐመድ ዓሊ ፓሻ እስከ ንጉሥ ፋሩቅ ድረስ በትረ መንግሥቱን የጨበጡ የግብፅ መሪዎች በሙሉ ታላቁ ህልማቸው ዓባይን ከምንጩ የመቆጣጠር ዕቅድ ስለነበር፣ በመጀመርያው የግብፅ ፖሊሲ ጎራ የሚካተቱ ናቸው፡፡

 

የጉራዕና የጉንደት የፀረ ወረራ አሻራ፣ የዓደዋው ፀረ ቅኝ አገዛዝ ድል ‘’ዓባይን ከምንጩ’’ የሚለውን የግብፅ ህልም ወደ እውንነት ሊለወጥ የማይችል መሆኑን ጠቋሚዎች ከመሆናቸውም በላይ ኢትዮጵያውያ፣ ለሉዓላዊነታቸውና ለነፃነታቸው ያላቸውን ፅኑ ዓላማ የሚያመላክቱ ናቸው። በመሆኑም የግብፅ ኢትዮጵያን የማጠቃለል ፖሊሲ ፋይዳ ትርጉም የለሽ እንቅስቃሴ እንደሆነ በማያሻማ ሁኔታ አሳይተዋል።

ስለሆነም የግብፅ መራሔ መንግሥታት ኢትዮጵያን የማጠቃለል ፖሊሲ ገቢራዊ ሊሆን እንደማይችል በመገንዘብ ስትራቴጂያዊ ዓላማው ያው ቢሆንም፣ በታክቲክ ደረጃ ለየት ያለ ፖሊሲ መከተል ግድ ሆነባቸው። በዚህም መሠረት ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎችን በማደራጀት፣ በመርዳትና በመንከባከብ አልፎ ተርፎም በቀጥታ በማስፈራራትና ወታደራዊ ኃይል በመገንባት ኢትዮጵያን የማዳከም እንቅስቃሴ ሲያራምዱ ቆይተዋል። ዛሬም ቢሆን ዓባይን ለጋራ ብልፅግና በጋራ ማልማት ሳይሆን ‹‹ዓባይ የለም ማለት ግብፅ የለችም›› (Out  Nilus Out Nihil) የሚለው ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ አለች ማለት የግብፅ ሕዝብ በልቶ አያድርም የሚል ሥር የሰደደ ውስጣዊ አመለካከት ስላላቸው፣ ኢትዮጵያን ለማሽመድመድ ወይም ለእነርሱ ጠቀሜታ እንድትንበረከክ ለማድረግ አዕምሮአቸው የሚላቸውን ሁሉ እየሠሩ ይገኛሉ።

እ.ኤ.አ. ከ1992 የግብፅ አብዮት ወዲህ ፕሬዚዳንት ጋማል አብዱልናስር ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር የቅርብ ግንኙነት ስለነበራቸው ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ዓይኑን ያፈጠጠ የከፋ እንቅስቃሴ ባታደርግም፣ ከ1956 ዓ.ም. የስዊዝ ካናል ጦርነት ወዲህ ‹‹የውኃ ደኅንነትን ማስጠበቅ›› በሚል ኢትዮጵያን በማግለል ያደረገችው የአስዋንን ግድብ የመገንባት እንቅስቃሴና የዓባይን ውኃ ከሱዳን ጋር ብቸኛ ተጠቃሚ ለመሆን ያደረጉት የ1956 ዓ.ም. የተናጠል ስምምነት ሲታይ፣ አገሮቹ በኢትዮጵያ ላይ ቀና አመለካከት ነበራቸው ለማለት አያስደፍርም።

ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት በትረ መንግሥቱን ከጨበጡ ወዲህ ደግሞ በህቡዕ የነበረውን ፀረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ በገሐድ በማውጣት የለየለት የጠብ አጫሪነት ፖሊሲ ማራመድ ጀመሩ። ከእነዚህም የጠብ አጫሪነት እንቅስቃሴዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

የግብፅ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ሌተና ጄኔራል ከማል ሐሰን ዓሊ ዲሴምበር 6 ቀን 1997 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ‹‹ግብፅ ሥልታዊ ጠቀሜታን    ለማስከበር ወደ ጦርነት ታመራለች››፣ እንዲሁም የግብፅ የመስኖ ሚኒስትር አብዱል አዚም አብዱል አታበሜይ እ.ኤ.አ. ሜይ 13 ቀን 1978 በሰጡት መግለጫ፣  ‹‹ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ እንድትጠቀም ግብፅ በፍፁም አትፈቅድም፤›› ሲሉ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት ደግሞ በሌላ ጊዜ ራሳቸው እ.ኤ.አ. ሜይ 30 ቀን 1978 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹ኢትዮጵያ በጣና ሐይቅ ላይ ግድብ ለመሥራት ብትሞክር ግብፅ ጦርነት ታውጃለች፤›› በማለት የተናገሩት ይገኙበታል።

ከዚህም ባሻገር የተለያዩ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎችን ከማደራጀትና ከማስታጠቅ በተጨማሪ፣ የጣና በለስ ፕሮጀክት ስኬታማ እንዳይሆን የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ለኢትዮጵያ የውኃ ልማት ብድር እንዳይሰጡ ግብፅ ያደረገችው ህቡዕ እንቅስቃሴ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።

ለዚህም የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምር ሙሳ እ.ኤ.አ. በየካቲት 1990 ከአንድ የአገር ውስጥ ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ‹‹ኢትዮጵያ መብታችንን እስካልነካች ድረስ ዕቅዶቿን ለማሰናከል ፍላጎት የለንም፤›› ማለታቸው ማስፈራሪያ አዘል መልዕክት ያለው መሆኑ ጥርጣሬ ያስነሳል፡፡ ‹‹መብታችንን እስካልነካች ድረስ›› የሚለው ሐረግ ግብፅ ከኢትዮጵያ በየዓመቱ የምታገኘው 84 ኪዩቢክ ሜትር ውኃና ከ100,000 ቶን በላይ ለም አፈር ቅንጣት ብትጎድል ወዮላት የሚል መልዕክት ያለው ይመስላል።

ግብፅ ኢትዮጵያንና ዓባይን ለመለያየት ወይም ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኙ የራስጌ አገሮችን ፍቅር ለማትረፍ ያላደረገችው ጥረት የለም። ከእነዚህም ከፍተኛ ጥረቶች አንዱ ‹ኡንዱጉ› የተባለውን ማኀበር መመሥረት ነበር። ‹ኡንዱጉ› የስዋህሊ ቃል ሲሆን፣ ትርጉሙም ወንድማማችነት፣ ጓደኝነት እንደ ማለት ነው። ግብፅ ይህንን ስትመሠርት መጠሪያው በስዋህሊ እንዲሆን ያደረገችው አስባበት እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም። ይኼ ማኀበር የተመሠረተው እ.ኤ.አ. በ1983 ሲሆን፣ የመጀመርያውን ጉባዔ በካርቱም ከጥቅምት 2 እስከ 4 ቀን 1983 ዓ.ም.፣ የሁለተኛውን በዛየር ኪንሻሳ ከመስከረም 3 እስከ 4 ቀን 1984 ዓ.ም.፣ ሦስተኛውን በካይሮ ከነሐሴ 7 እስከ 8 ቀን 1985 ዓ.ም.፣ አራተኛውና ሌሎች ቀጣይ ስብሰባዎችም ከዚያ በኋላ ተካሂደዋል፡፡  

እጅግ በጣም የሚያሳዝነውና የሚያስገርመው ነገር ቢኖር 86 በመቶ የዓባይ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ በማኀበሩ ውስጥ ያለመታቀፏ ነው። ግብፆች አንዳንዴ ሲያሰኛቸው ኢትዮጵያ በታዛቢነት እንድትገኝ አልያም የእነርሱ አርቲፊሻል ማኀበር ሰለባ እንድትሆን ሲወተውቱ መቆየታቸው አዲስ ነገር አይደለም። የዚህም ማኀበር ዋና ዓላማ  በቀጥታ ሲታይ ወንድማማችነትን ማጠናከር መስሎ ቢታይም፣ ድብቅ አጀንዳው ግን በዓባይ ላይ የሚደረጉ ማናቸውም የልማት እንቅስቃሴዎች ከግብፅ ዕይታ እንዳይወጡ መቆጣጠሪያ ዘዴ እንደሆነ ብዙም ጥናት የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም።

በኢትዮጵያ በኩል በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እስከ አምስተኛ ጉባዔ ድረስ አልፎ አልፎ ድምጿን ለማሰማት ከሞመከር ያለፈ እምብዛም የረባ እንቅስቃሴ ሲደረግ አልታየም። ከዚያ ወዲህ ግን ናይል 2002 ዓ.ም. በተባለውና በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1993 ዓ.ም. በተመሠረተው ጉባዔ ኢትዮጵያ መሳተፍ ከመጀመሯም በላይ፣ አምስተኛውንና ስምንተኛውን የናይል ጉባዔ በማስተናገድ ወደ መጫወቻ መድረኩ በቀጥታ የገባች ይመስላል።

የዓባይ ውኃን አጠቃቀም በተመለከተ ኢትዮጵያም ትሁን ሌሎች አዋሳኝ አገሮች ሁሉን የሚያካትት ወጥ ሕግ የላቸውም። ሆኖም በጋራ ለመጠቀም የሚያስችሉ ስምምነቶች አሏቸው። ከዚህ ውጪ የትኛው አገር ምን ያህል ውኃ መጠቀም እንደሚችል የሚያመለክት ነገር የለም።

በግብፅና በሱዳን የተደረገው እ.ኤ.አ የ1959 ስምምነት ሌሎችን የሚያካትት ሳይሆን ሙሉ በሙሉ የግብፅን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው። ይህ ውል በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን መብትና ግዴታ ከማመላከት ባሻገር የሚያመጣው ፋይዳ አይኖርም። ከዚህ ይልቅ የጋራ ሀብትን ግብፅ በማናለብኝነትና በብቸኝነት ለመጠቀም የምታደርገውን እንቅስቃሴ በጉልህ ያሳያሉ። በተለይም ግብፅ በዓባይ ዙሪያ (በኢትዮጵያ) ላይ የምታደርገው ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት አኳያ መታየት ስላለበት፣ ጉዳዩ በኢትዮጵያ በኩል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት በግብፅ ዓይን ሱዳን ቁልፍ ስትራቴጂ ከመሆኗም ባሻገር፣ ሱዳንን በክፉ የሚመለከት ኃይል ግብፅን አያስደስታትም፡፡ ስለሆነም ሱዳን በተቻለ መጠን ከግብፅ መዳፍ እንዳታፈተልክ የማያደርጉት እንቅስቃሴ የለም። ምንም እንኳን ግብፅ ሱዳን የሸሪዓ ሕግ በማወጇና ከሊቢያና ከኢራን ጋር የምታደርገው ድብቅ እንቅስቃሴ ባያስደስታቸውም፣ የሱዳንን መልካም ወዳጅነት ማጣት ግን አይፈልጉም።

ጠቅለል ባለ መልኩ የግብፅና የሱዳን ጥብቅ የፖለቲካ ግንኙነት ሲታይ እውነትም በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን መግባባት የሚያመላክት ሳይሆን፣ ግብፅ ከሱዳን በስተጀርባ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውን ጠቅላላ ሁኔታ ለመከታተል እንዲያመቻት የምታደርገው እንቅስቃሴ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ለዚህም ስኬታማነት የተለያዩ የግብፅ መሪዎች ከሱዳን ጋር በርካታ ስምምነቶች ያደረጉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል፣ እ.ኤ.አ. የ1959 የዓባይ ውኃ ክፍፍል ስምምነት፣ እ.ኤ.አ. የ1976 የመከላከያ ስምምነት፣ እ.ኤ.አ. የ1982 የውህደት ስምምነት፣ ግብፃውያንን ለመጥቀም የተደረገው የጆንግሊ ካናል ቁፋሮ ስምምነት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ዛሬ አል ኢትሃድ አልወጠኒ የተባለው ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ አንጃ በሱዳን ውስጥ የግብፅን ጥቅም የሚያስጠብቅ ግብፅ ዘመም ድርጅት ሲሆን፣ የሁለቱ አገሮች ስምምነት ሲጤን አብሮ ግምት የሚሰጠው ጉዳይ ነው።

ሶማሊያ የዓረባዊነት ስሜት ከሚታይባቸው የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች አንዷ ስትሆን፣ ግብፅም ይህንኑ መሠረት አድርጋ በሶማሊያ የምታደርገው እንቅስቃሴ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። በተለይም የሶማሊያ ችግር በኢትዮጵያ ሽምግልና እልባት እንዲያገኝ ግብፅ የሚጠበቅባትን ያህል ሚና አለመጫወቷ ሊጤን የሚገባው ጉዳይ መኖሩን ያመለክታል፡፡

ዓባይ 6,825 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው በዓለም ውስጥ በርዝመቱ የመጀመርያውን ደረጃ ይዞ የሚገኝ፣ አሥር አገሮችን የሚያዋስን፣ የወንዙ አመንጪና ባለቤት አገሮች የማይጠቀሙበት፣ በአንፃሩ ለወንዙ ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ የሌላቸው አገሮች ሙሉ በሙሉ በባለቤትነት የሚጠቀሙበት ትልቅ እንቆቅልሽ ያዘለ ወንዝ ነው።

እስከ ዛሬ ድረስ የተፋሰሱን አገሮች የሚያስተሳስርም ሆነ ወንዙን በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ስምምነት የለም። በአንዳንድ የተፋሰሱ አገሮች መካከል የተደረጉ ስምምነቶች ቢኖሩም፣ እነርሱም ሙሉ በሙሉ በግብፅ የፖለቲካ ጠበብት ለግብፅ ጥቅም ሲባል የተቃኙ በመሆናቸው በሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ተቀባይነት የላቸውም።

በተለይ በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ ዘመን ግብፅና ሱዳን የእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች  ስለነበሩ የእንግሊዝን ወቅታዊ ጥቅም ለማስከበር ሲባል ብቻ፣ በወቅቱ በዓባይ ላይ የተደረጉ ስምምነቶች ግብፆችን ከመጥቀሙ በተጨማሪ በወንዙ ላይ ለሚነሱ ውዝግቦች ሁሉ መነሻ ሆኗል።

ከዚህ በተጨማሪም እንግሊዞች በኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ስላልነበራቸው ኢትዮጵያን ለማዳከም ሲሉ በኢትዮጵያ ላይ የረዥም ጊዜ የቅኝ ግዛት ፍላጎትና ዕቅድ ያላትን ጣሊያንን የቅኝ ገዥ አጋር በማድረግ፣ በዓባይ ውኃ አጠቃቀም በተዋናይነት እንድትሠለፍ አድርገዋል።

ዛሬም ግብፅ የቅኝ ገዥዎችን ፈለግ በመከተል የዓባይን ወንዝ በብቸኝነት ለመጠቀም የማታደርገው ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የለም። ከእነዚህ ፈርጀ ብዙ እንቅስቃሴዎች አንዱ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች እንዳሉ እንዲተገበሩ ያላት ፍላጎት ነው።

  1. የ1902 የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ስምምነት

ይህ በዳግማዊ ምኒልክና በታላቋ ብሪታኒያ መካከል በአዲስ አበባ እ.ኤ.አ. ሜይ 15 ቀን 1902 የተፈረመው የመጀመርያው ዓባይ (ጥቁር) ነክ ስምምነት ነው። የዚህ ስምምነት አንቀጽ 3 በእንግሊዝኛው እንደሚከተለው ሰፍሯል፡፡

“The Emperor Menlik  engages not to construct or allow to be constructed any work across Blue Nile, Lake Tana or the Sobat which would arrest the flow of the water into the Nile except in agreement with the Government of Great Britain and the Sudan.”

የዚህ ስምምነት ፍሬ ነገር በጥልቀት ሲጤን አራት ጠቃሚ ነገሮችን የሚያመለክት ሆኖ ይታያል። አፄ ምኒልክ ከእንግሊዝ ጋር ያደረጉት ስምምነት ወንዙን በከፊልም ሆነ በተሟላ መልኩ እንዳይጠቀሙ የሚያግድ አይደለም። ምክንያቱም (Which Would Arrest) የሚለው ሐረግ ውኃውን ሙሉ በሙሉ እንዳይፈስ ከመገደብ ውጪ፣  ኢትዮጵያ ዓባይን ከመጠቀም የሚከለክላት ነገር የለም። “Except in Agreement with Great Britain” የሚለው ሐረግ ጊዜያዊነትን የሚያመለክት እንጂ ዘለቄታዊ አይደለም። ሌላው የስምምነቱ መንፈስ ከእንግሊዝና ከሱዳን መንግሥት ምክክር ውጪ ይላል እንጂ ስምምነቱ ግብፅን አይመለከትም። የከለከሉት ምኒልክን ስለሆነ ምኒልክ ሲያልፉ አብሮ የሚሞት ጉዳይ እንጂ ነባራዊነት የለውም።

  1. የ1906 ስምምነት

እ.ኤ.አ. ከ1906 ዓ.ም. ወዲህ ኢትዮጵያን የማያካትት ወይም ከኢትዮጵያ ዕውቀት ውጪ የተደረገው የናይል ውኃ ስምምነት የ1906 የሦስትዮሽ ስምምነት በመባል የሚታወቀው እንግሊዝ፣ ጣሊያንና ፈረንሣይ ለንደን ላይ እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 13 ቀን 1906 ያደረጉት ስምምነት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ስምምነት አውሮፓውያን ኢትዮጵያን ለመቀራመት ያደረጉት በመሆኑ፣ አፄ ምኒልክ ‹‹ስምምነቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፃረር ነው፤›› በማለት ውድቅ አድርገውታል።

3 . የ1925 የእንግሊዝና የጣሊያን ስምምነት (Exchange of Notes)

ዓባይን ከምንጩ ለመቆጣጠር ፍላጎት ያላት እንግሊዝ አሁንም በኢትዮጰያ በኩል ተቀባይነት እንደማታገኝ ስለገባት፣ ጥቅሟን ለማስከበር ስትል በጣሊያን በኩል የእጅ አዙር እንቅስቃሴ ቀጠለች። በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ. በ1925 ከጣሊያን ጋር ግብፅና ሱዳን በዓባይ ውኃ ጠቀሜታ ላይ ቅድሚያ እንዲኖራቸው ስምምነት ላይ ደረሱ። ከዚህ በተጨማሪም ጣሊያን በጥቁር ዓባይና በሶባት ላይ ምንም ዓይነት ሥራ ላለማከናወን ስምምነት አደረገች።

ይህ ስምምነት ሲደረግ በወቅቱ ኢትዮጵያ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል ስለነበረች፣ በዚያ በኩል በመልክዕተኛዋ አማካይነት በሉዓላዊነቷ ላይ የተቃጣ ስምምነት መሆኑን በማመልከት ከፍተኛ ተቃውሞዋን አሰማች። በዚህም ምክንያት ስምምነቱ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል።

4. የ1929 ስምምነት

ሌላው ስምምነት እ.ኤ.አ. ግንቦት 7 ቀን 1929 በግብፅና እንግሊዝ (ሱዳንን በመወከል) መካከል የተደረገው ስምምነት ሲሆን በዚህ ስምምነት መሠረት ግብፅ የውኃውን 48 ቢሊዮን ኪዩብክ ሜትር፣ ሱዳን ደግሞ አራት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ታገኛለች የሚለው ነው።

ይህ ስምምነት የፈጠረው አጋጣሚና አስደናቂ ነገር ቢኖር፣ ግብፅ በአንድ በኩል ሱዳን በውኃው የመጠቀም መበት እንዳላት ማወቋ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በውኃው የመጠቀም ቅድሚያ እንዳላት የሚያረጋግጥ የስምምነት ሐረግ ለመጨመር ያደረገችው ጥረት ነው።

ኢትዮጵያ የዚህን ስምምነት ዋጋም ሆነ የግብፅን ታሪካዊ መብት አልተቀበለችውም፣ ልትቀበለው የምትችለው ጉዳይም አይደለም። የመቀበል ግዴታም  (Binding Effect) የለባትም። ምክንያቱም ሁለቱ አገሮች የሚያደርጉት ስምምነት ሦስተኛውን ወገን/ካለእርሱ ስምምነት ማካተት አይገባውምና።

በሌላ በኩል ሱዳንም ብትሆን ነፃ ከወጣች ወዲህ ስምምነቱ በሱዳን ኪሳራ ግብፅን ለማበልፀግ ወይም የሁለቱን አገሮች ወዳጀነት ለማጠናከር የተደረገ እንቅስቃሴ ስትል ትተቸዋለች።

5. የ1959 ስምምነት

ይህ ስምምነት ሌሎች የዓባይ ተፋሰፍ አገሮችን በማግለል ግብፅና ሱዳን ብቸኛ ተጠቃሚ ለመሆን ያደረጉት ፍትሐዊ ያልሆነ ስምምነት ነው። በዚህ ስምምነት የታየው አዲስ ነገር ቢኖር ግብፅ የመጠቀም ቅድሚያ (Acquired Rights) የሚለውን አቋሟን በመለወጥ፣ የሱዳን ፍፁም የግዛት አንድነት (Absolute Territorial Integrity) በሚለው መርህ እስከ 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ እንድትጠቀም መፍቀዷ ነው።

ኢትዮጵያ በድርድሩም ሆነ በስምምነቱ ተቃውሞዋን ከማሰማቷ ባሻገር ስምምነቱን የማትቀበል መሆኗን አሳውቃለች። በሌላ በኩል የስምምነቱ መንፈስ ሲታይ በሁለቱ መካከል ያለውን መብትና ግዴታ ከማመላከት ባለፈ፣ ሌሎች አገሮችን ከግብፅና ከሱዳን ፈቃድ ውጪ የሚያካትት አይሆንም።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles