የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ በወንጀል መከላከል፣ በምርመራ፣ በሥነ ምግባር መኮንንነት፣ በሥርዓተ ፆታ ጥቃት መከላከልና ማስቆም ለአንድ ዓመት ያሠለጠናቸውን 1,179 ፖሊስ መኮንኖች መጋቢት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. አስመረቀ፡፡
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ጄኔራል ኮሚሽነር ኢተፋ ቶላ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፣ በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን የዕድገትና የልማት ቀጣይነት ለማረጋገጥ ሰላም ወሳኝ መሆኑንና ለዚህም የፖሊስ ኃላፊነት ቀዳሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከል የሚችል የፖሊስ ኃይል ለማፍራት ኮሚሽኑ የፖሊስ አባላትን በአቅም፣ በክህሎትና በአመለካከት ለመገንባት የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ኮሚሽነሩ አክለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዑመር ሁሴን እንደገለጹት፣ ኅብረተሰቡ ትክክለኛ ፍትሕ እንዲያገኝና በፖሊስ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታየውን የአቅም፣ የክህሎትና የአመለካከት ክፍተት ለመድፈን የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው፡፡
የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ፣ የፖሊስ ሠራዊት አባላት ሚና ከፍተኛ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
አቶ ዑመር እንዳሉት፣ የፖሊስን የአገልግሎት አሰጣጥ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር፣ ሳይንስን መሠረት ባደረገ መንገድ የአባላቱን አቅም ለመገንባት የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡
በዕውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር የተዋሀደ የፖሊስ ሠራዊት ለማፍራት የተጀመረው ሥልጠናና የአቅም ግንባታ ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ፕሬዚዳንቱ አክለዋል፡፡
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር አበበ ለገሰ በበኩላቸው፣ ሥልጠናውን ወስደው ወደ ተግባር የሚገቡ የፖሊስ ሠራዊት አባላት፣ ኅብረተሰቡ በፍትሕ ዘርፍ የሚያነሳውን ቅሬታ ለመፍታት ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ኮሌጁ በፖሊስ አገልግሎት ላይ የሚታየውን ክፍተት ለማጥበብና በሙያዊ ሥነ ምግባር የታነፀ የፖሊስ ኃይል በጥራትና በብዛት ለማፍራት፣ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በዲግሪ መርሐ ግብር ማሠልጠን እንደሚጀምር ጠቁመዋል፡፡
ሥልጠናው የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና በፖሊስ ሳይንስ መሠረት ለመሥራት፣ ዕውቀትና ክህሎት ያገኙበት መሆኑን ተመራቂዎቹ ተናግረዋል፡፡