በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር የሚገኘው ብሉ ናይል የፖሊፕሮፕሊንና ክራፍት ከረጢት ማምረቻ ኩባንያ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ99 ሚሊዮን ብር ሐራጅ የገዛውን ፓኬጂንግ ፋብሪካ፣ አራት ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ በማድረግ ሙሉ ዕድሳት አካሂዶ ሥራ አስጀመረ፡፡
ቅዳሜ ሐምሌ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ፋብሪካው በሚገኝበት በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት አዲሱ ፓኬጂንግ ፋብሪካ፣ ‹‹ብሉ ናይል የፖሊፕሮፕሊንና ክራፍት ከረጢት ማምረቻ ኩባንያ ቁርቁራ ቅርንጫፍ›› ተብሎ ተሰይሟል፡፡
በህንድ ባለሀብቶች የተገነባው ኢኖቫ ፓኬጂንግ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደረውን ብድር መመለስ ባለመቻሉ፣ ባንኩ ብድሩን ለማስመለስ ፋብሪካውን በሐራጅ ጨረታ ለብሉ ናይል ሸጦታል፡፡
ብሉ ናይል ለዚህ ፋብሪካ ተጨማሪ አራት ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ዕድሳቱን አጠናቆ፣ ቅዳሜ ሐምሌ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. አስመርቆ ሥራ አስጀምሯል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር አረጋ ይርዳው (ዶ/ር)፣ የቀድሞው ኢኖቫ ፓኬጂንግ በሽያጭ ወደ ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ከተዛወረ በኋላ የብሉ ናይል የፖሊፕሮፕሊንና ክራፍት ከረጢት ማምረቻ ኩባንያ ‹‹ቁርቁራ ቅርንጫፍ›› ተብሎ እንዲቀጥል መደረጉን፣ የቀድሞ ሠራተኞች የሥራ ዋስትናቸው ተረጋግጦ በሥራ ገበታቸው ላይ እንዲቀጥሉ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰሩ ጨምረው እንደገለጹት፣ ፋብሪካውን ሥራ ለማስጀመር በተካሄደው ጥገናና የማሻሻል ሥራ ሙሉ በሙሉ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ባለሙያዎች ተከናውኖ መጠናቀቁም አስደስቷቸዋል፡፡
‹‹በኮንትራት ሲያገለግሉ የነበሩ የፋብሪካው 72 ሠራተኞች ቋሚ ሠራተኞኛ እንዲሆኑ ተደርጓል፤›› ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡
በዕለቱ በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የቢሾፍቱ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጁላ ለማ፣ ሚድሮክ ቴክኖሎጁ ግሩፕ በቢሾፍቱ ከተማ ብዙ ኢንቨስተሮች ባልገቡበት ወቅት ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶችን የጀመረ የከተማው ባለውለታ ነው ብለዋል፡፡
‹‹በቀጣይም የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ጋር በይበልጥ ተባብሮ ይሠራል፤›› በማለት ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር 25 ኩባንያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ሰባት ኩባንያዎች በቢሾፍቱና አካባቢው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ ተሰማርተዋል፡፡
የብሉ ናይል የፖሊፕሮፕሊንና ክራፍት ከረጢት ማምረቻ ቁርቁራ ቅርንጫፍ፣ የማዳበሪያ ከረጢቶች፣ ብትን ጆንያዎችንና የዕቃ ማሸጊያ ፕላስቲኮችን ያመርታል፡፡