Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልብሉይ ዜማዎች

ብሉይ ዜማዎች

ቀን:

ኢትዮጵያዊት ቆንጆና ጽጌሬዳ ከአንጋፋው ድምፃዊ ግርማ በየነ ተወዳጅ ዘፈኖች መካከል ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ወርቃማ የሙዚቃ ዘመን በሚባለው ወቅት ለሕዝብ ከደረሱ አያሌ ሙዚቃዎች ውስጥ ዛሬም እንደተወደዱ ከዘለቁት መካከልም ይጠቀሳል፡፡ በ1960ዎቹ፣ በ70ዎቹ እስከ 80ዎቹ እኩሌታ የተሠሩ ሙዚቃዎች ዘመኑን ካጣጣሙባቸው የዕድሜ ባለፀጋዎች በተጨማሪ በዛሬው ትውልድ ተደማጭ ሆነው ዘልቀዋል፡፡

እንደ ድምፃዊ ግርማ ከዕድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ እምብዛም በመድረክ የማይታዩ ድምፃውያን፣ ዐውደ ዓመትን በማስታከክ ወይም በሌላ ምክንያት ኮንሰርት ሲዘጋጅ ከሚናፍቃቸው ሕዝብ ጋር ይገናኛሉ፡፡ 2010ን ለመቀበል ከተዘጋጁ የሙዚቃ ድግሶች መካከል ግርማን ጨምሮ በርካታ አንጋፋና ወጣት ድምፃውያን በአንድ መድረክ የሚያቀነቅኑባቸው ይጠቀሳሉ፡፡

አንጋፋዎቹን ድምፃውያን መድረክ ላይ ለመመልከት እንቁጣጣሽን የመሰሉ በዓላትን ቢያስጠብቅም፣ አልፎ አልፎ የድሮና የዘንድሮም አድናቂዎቻቸው ሥራዎቻቸውን የሚታደሙበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የተካሄደው የአልበም ምርቃት ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ መርሐ ግብሩ ከሚጀምርበት ሰዓት አስቀድመው በቴአትር ቤቱ የተገኙ ብዙዎች ናቸው፡፡ አንጋፋ ሙዚቀኞች፣ በዕድሜ የገፉና ወጣት የግርማ አድናቂዎች ቴአትር ቤቱን ሞልተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ድምፃዊው መድረክ ላይ ወጥቶ ታዳሚውን እጅ ሲነሳ ሁሉም በአንድነት ከመቀመጫቸው ተነስተው አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሚስቴክስ ኦን ፐርፐዝ›› በሚል የግርማን የቀድሞ ሙዚቃዎች ያካተተው የኢትዮጲክስ ስብስብ አልበም 30ኛ ክፍል መውጣቱን ምክንያት ያደረገ መሰናዶ ነበር፡፡ ‹‹ጎልደን ይርስ ኦፍ ሞደርን ኢትዮጵያን ሚውዚክስ›› (የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ወርቃማ ዓመታት) በሚል ከወጣው የኢትዮጲክስ የመጀመርያ አልበም አንስቶ እስከ 2009 ዓ.ም. ድረስ የአንጋፋ ኢትዮጵያውያን ሙዚቃ ስብስቦች ታትመዋል፡፡

የጥላሁን ገሠሠ፣ መሐሙድ አህመድ፣ ዓለማየሁ እሸቴ፣ ሙላቱ አስታጥቄ፣ አስናቀች ወርቁ፣ እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩና ሌሎችም ሙዚቃዎችን ለአድማጭ ያበቃው የኢትዮጲክስ ስብስብ፣ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ዝናው የናኘ ነው፡፡ ስብስቦቹ በዋነኛነት በ60ዎቹ እና 70ዎቹ በአምሐ ሪከርድስ፣ ከይፋ ሪከርድስና ፊሊፕስ ኢትዮጵያ ሪከርድስ የታተሙ ነጠላ ዜማዎችና አልበሞች ናቸው፡፡ ለ30ኛ ዕትሙ የተመረጠው ግርማ ከአካሌ ውቤ ባንድ ዳግም የሠራቸው ሙዚቃዎች ናቸው፡፡

በ1960ዎቹና 70ዎቹ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ተስበው ሥራቸው በዚያው ዘመን ብቻ እንዲያተኩር የወደዱት የአካሌ ውቤ ባንድ አባላት፣ ግርማን መድረክ ላይ አጅበውታል፡፡ ግርማ በአድናቂዎቹ ተከቦ ቀደምት ሥራዎቹን ዳግም አቀንቅኗል፡፡ ‹‹ካንቺ ወዲህ ሴት አላምንም. . .›› ሲል ከተወዳጅ ሥራዎቹ አንዱን አስደምጧል፡፡

ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው ባለቤቱ እፀገነት ከሙዚቃዎቹ የአብዛኞቹ መነሻ በመሆን ትታወቃለች፡፡ በአልበም ምርቃቱ ዕለትም ድምፃዊው የፍቅር ዘመናቸውን እያስታወሰ አቀንቅኗል፡፡ በዘፈኖቹ መካከል የቀድሞውን ጊዜያቸውን የሚያስታውስ ልብ የሚነካ ንግግርም አድርጓል፡፡ ንግግሩ ስሜታቸውን የኮረኮራቸው ታዳሚዎች ያለቅሱም ነበር፡፡ ድምፃዊውን የሚያደንቁ የዕድሜ ባለፀጋዎችና በሃያዎቹ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች ተመሳሳይ ስሜት ተንፀባርቆባቸዋል፡፡

ድምፃዊው ወጣት ሳለ ያቀነቀናቸውን ሙዚቃዎች ወጣት ሆነው ካዳመጡ ታዳሚዎች ባሻገር የአሁኑ ትውልድም ዘፈኖቹን ይወዳቸዋል፡፡ ዛሬ ላይ ሆኖ ወደ ኋላ መለስ ብሎ የጥንት ሙዚቃዎችን ማድመጥ የብዙዎች ምርጫ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ ይህን የተገነዘቡ ወጣት ዘፋኞችም የቀድሞ ድምፃውያንን ሥራዎች በነጠላ ዜማ ከመሥራት አልበም እስከ መልቀቅ ደርሰዋል፡፡

ቆየት ያሉ ዘፈኖች በዛሬው ትውልድም መደመጣቸው መልካም ቢሆንም፣ ለቀደምቶቹ የሚሰጣቸው ትኩረት በዚህኛው ዘመን መዚቃዎች ላይ ጥያቄ ያጭራል፡፡ ወደ 1960ዎቹ የኢትዮጵያ ወርቃማ የሙዚቃ ዘመን ነው በሚለው የሚስማሙ፣ በየዘመኑ የሚሠሩ ሙዚቃዎች ትውልዳቸውን ገላጭ በመሆናቸው ማወዳደር ያስቸግራል የሚሉም አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡

እሌኒ ካሳ የ26 ዓመት ወጣት ስትሆን፣ ከ67 ዓመቱ አቶ ዓለሙ አዱኛ ጋር ተመሳሳይ ሙዚቃ ታዳምጣለች፡፡ ሁለቱም በየዘመናቸው ከተሠሩ ሙዚቃዎች ይልቅ ላለፈው ዘፈን ያላቸው ፍቅር ያመዝናል፡፡

‹‹የድሮ ዘፈኖች ማዳመጥ እመርጣለሁ፡፡ የ60ዎቹና 70ዎቹን ዘፈን ስሰማ ሰውነቴን ሐሴት ሲወረኝ ይሰማኛል፤›› ትላለች፡፡ እሌኒ፣ በሙዚቃ ይዘትም ይሁን አሠራር የቀድሞዎቹ ሚዛን እንደሚደፉ ታምናለች፡፡ ‹‹ቀድሞ የተሠሩ ሙዚቃዎች የተለየ ለዛ አላቸው፡፡ አንድ ሙዚቃ ለመሥራት የሚሳተፉት ልዩ ልዩ ችሎታ ያላቸው ሙዚቀኞች በመሆናቸው ሥራዎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆን አስችሏል፤›› ስትል ትገልጻለች፡፡

ወጣቷ ሙዚቃ አንዳች ትርጉም የሚሰጥ ሲሆን ያለ ዕድሜ ልዩነት እንደሚደመጥ ታምናለች፡፡ የቀድሞ ሙዚቃዎች የሚዳስሷቸው ርዕሰ ጉዳዮች ዘርፈ ብዙ በመሆናቸው እንደምትወዳቸው ትገልጻለች፡፡ ‹‹ሙዚቃ የስሜት ጉዳይ ነው፡፡ ለሁሉም ሰው ስሜት የሚሰጠው ሙዚቃ ይለያያል፡፡ ለኔ የቀድሞ ዘፈኖች ለሙያውና ለአድማጩ ክብር ተሰጥቶ በቅንነት የተሠሩ ስለሆኑ እመርጣቸዋለሁ፤›› ስትልም ታስረዳለች፡፡

የዓመታት የዕድሜ ልዩነትን የሰበሩ ሙዚቃዎች ለአቶ ዓለሙም ተመሳሳይ ስሜት ይሰጣሉ፡፡ ‹‹እያንዳንዱ ሙዚቃ የታዳጊነቴ፣ ወጣትነቴና ጎልማሳነቴን ዘመን ያስታውሰኛል፤›› ይላሉ፡፡ ከወጣቷ ጋር የሚስማሙት ቀደምቶቹ ሙዚቃዎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳይ ዳሳሽ እንደሆኑም ጭምር ነው፡፡ በደርግ ዘመን የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለምን እንዲያቀነቅኑ ግዴታ የተጣለባቸው ድምፃውያን የይዘት ጫና እያለባቸው እንኳን ለአድማጭ ጆሮ የሚጥሙ ሙዚቃዎች ይሠሩ እንደነበር ያትታሉ፡፡

‹‹ወጣቶች ድምፃውያን ወደ ኋላ የሚመለሱት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በእርግጥ የዚህ ዘመን ትውልድም የራሱን አሻራ አሳርፎ ማለፍ ስላለበት ጥሩ መሥራት ይጠበቅበታል፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ አንድ ሐሳብ በተለያየ መንገድ ቢገለጽና ሙዚቃ ሲሠራ ዘመን መሻገርን ታሳቢ በማድረግ ቢሆን ሲሉም ይመኛሉ፡፡

ለ32 ዓመቱ ሀብታሙ ስለሺ የሁለቱ አስተያየት ሰጪዎች ሐሳብ አይዋጥለትም፡፡ ‹‹ሁሉም ዘመን የየራሱ ቀለም አለው፡፡ በይዘትና በቅርፅም የተለያዩ ናቸው፤›› ይላል፡፡ የዚህ ዘመን ሙዚቃ አድናቂው ሀብታሙ፣ የተለያየ ዘዬ ያላቸውን ሙዚቃዎች በማዋሃድ የሚሠሩ የዘመኑ ሙዚቃዎች ድንበር ተሻጋሪ እንደሆኑም ያምናል፡፡

‹‹ከቀድሞ ሙዚቃዎች መካከል የተወደዱ እንዳሉ ሁሉ አድማጭ ያላገኙም አሉ፡፡ በዚህ ዘመንም ተወዳጅነት ያተረፉ ሥራዎችና እዚህ ግባ የማይባሉም አሉ፤›› ሲል ያስረዳል፡፡ ሙዚቃ ዘመን ይገድበዋል ብሎ አያምንም፡፡ ቀደምት ሙዚቃዎችን ማድመጥና ዳግመኛ መሥራትም ችግር ይፈጥራል ብሎ አያስብም፡፡ ሆኖም አድማጮች ዘመኑ ላፈራቸው ድምፃውያን ዕድል ቢሰጡ መልካም ነው ይላል፡፡ አማተር ዘፋኞች የድሮ ሙዚቃ በመሥራት ውስጥ የራሳቸውን ቦታ ማግኘት እንደሚገባቸው ያምናል፡፡

ጊታሪስት፣ የሙዚቃ ፕሮዲውሰርና መምህር ግሩም መዝሙር በበኩሉ ቀደም ባለው ጊዜ የሚሠራው ሙዚቃ ተቋማዊ ከመሆኑ በተቃራኒው ዛሬ ላይ የሙዚቃ ሥራ የግል ጥረት መሆኑን ያስረዳል፡፡ ድምፃውያን ሙዚቃቸውን ሠርቶ ገበያ ላይ የማዋል ኃላፊነት የራሳቸው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ፣ የሚሠሩ ሙዚቃዎች መመዘኛ የግል መለኪያ መሥፈርቶቻቸው ናቸው፡፡ የቀድሞውና የአሁኑ ሙዚቀኞች በዘመንና በቴክኖሎጂ ውጤቶች መለያየትም፣ የሚያስደምጡት ሙዚቃ መካከል ልዩነት አለ ይላል፡፡

ግሩም እንደሚለው፣ ቀድሞ የሚሠሩ ሙዚቃዎች ለዚህ ዘመን አድማጭ በሚሆን ሥልት እስከተሠሩ ድረስ ዳግም ቢከለሱ ጉዳት የለውም፡፡ ‹‹ሙዚቃ ዳግም መሥራት በመላ ዓለም ያለው አካሄድ ነው፡፡ ሆኖም ሙዚቀኛው በቀድሞ ሥራ የሚጨምረው ነገር ከሌለ ማበላሸት ይሆናል፤›› ይላል፡፡ የቀድሞውን ሙዚቃ ዘዬ ዘመኑ ባመጣው ሥልት መከለስ የአሁኑን አድማጭ ወደ ድሮ መውሰድ መሆኑም ያክላል፡፡

ሙዚቃ ዳግም እንደሚሠራው አዳዲስ ዘፈኖችም ለአድማጭ ይቀርባሉ፡፡ በአንድ ዘመን ያሉ ሙዚቀኞች ወደ ሌሎች ማማተራቸውም እንግዳ አይደለም፡፡ በሙዚቀኛው አስተያየት፣ የቀድሞ ድምፃውያንን ለማስመሰል ሲሞከር ግን ችግር ይሆናል፡፡ ‹‹ሁሉም ሥራዎች በአንድነት መጨፍለቅ አይቻልም፡፡ ለዚህ ዘመን አድማጭ ሲቀርቡ ሙያዊ ሒደታቸውን ከተከተሉ ይወደዳሉ፡፡ ለማስመል ከመሞከር የራስ ቀለም መፍጠር ይመረጣል፤›› ሲል ያስረዳል፡፡

በሚውዚክ ኢን አፍሪካ ዌብ ሳይት ‹‹ፓፑላር ሚውዚክ ኢን ኢትዮጵያ›› በሚል የተጻፈ ሀተታ፣ ዘመነኛ የኢትየጵያ ሙዚቃ እንደ ሬጌ፣ ሶልና ሂፕ ሃፕ ያሉ ሥልቶችን በማከል እያደገ መምጣቱን አስነብቧል፡፡ ጃኖ ባንድ፣ አብነት አጎናፍር፣ አቢ ላቀውና ሚካኤል በላይነህን እንደ ማሳያ በሚጠቅሰው ጽሑፍ፣ አዲሱ ትውልድ ሙዚቃውን ወደ ዓለም አቀፍ አድማጭ ለማስረጽ ድክ ድክ እያለ መሆኑን ተመልክቷል፡፡

ከዚህ ጽሑፍ በተለየ ዘ ኢንዲፔንደት ‹‹ዘ ጎልደን ኤጅ ኦፍ ኢትዮጵያን ሚውዚክ›› በሚል ርዕስ ያስነበበው ሐተታ፣ አንባቢን ወደ ኋላ የሚመልስ ነው፡፡ ክብር ዘበኛ፣ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያና ሌሎችም የኢትዮጵያን ሙዚቃ ወደ ላቀ ደረጃ አድርሰዋል ያላቸውን ያወድሳል፡፡ ጽሑፉ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው የባንድ ሙዚቃ ለገነነበት ዘመን ነው፡፡ በሮሃ ባንድ፣ ራስ ባንድ፣ ቬነስ ባንድ፣ ዋቢ ሸበሌ ባንድና ዳህላክ ባንድ የተሠሩ ሙዚቃዎች አንድ ማሳያ ይጠቀሳሉ፡፡

በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የተሠራው የስሜነህ በትረዮሐንስ የጥናት ጽሑፍ፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ አዝማሪዎች ከነበራቸው ሚና አንስቶ ይዳስሳል፡፡ በየዘመኑ ከነበረው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዐውድ አንፃር የአገሪቱ ሙዚቃዎች በተቃኙበት ጽሑፍ፣ የኪነት ቡድኖችና ቴአትር ቤቶች ጉልህ ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ በየክፍለ ሀገሩ የነበሩ ኪነቶች የሚሠሯቸው ሙዚቃዎችና በቴአትር ቤቶች በተለይም በዓላትን ምክንያት በማድረግ ለሕዝብ የሚቀርቡ ሥራዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡

ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ኮሎኔል ለማ ደምሰው ዘፈኖች ልጃቸው ሚካኤል ለማ ዳግም ሠርቶ ‹‹ደስ ብላኛለች›› የሚል አልበም ማሳተሙ ይታወሳል፡፡ የሙሉቀን መለሰን ዘፈኖች ዳግም የሠራው ድምፃዊ ብዙአየሁ ደምሴም ይጠቀሳል፡፡ እንደ ሐመልማል አባተና ንዋይ ደበበ በጥምረት የተሠሩ ዘፈኖችን ዳግም ተሠርተው ማድመጥ እየተለመደ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ እየተዘወተረ የመጣው ከሁለት የተለያዩ የድሮ ዘፈኖች በመቀንጨብ አንድ ሙዚቃ መሥራትና ሪሚክስ ማድረግ ነው፡፡

አንዳንዶቹ ድምፃውያን በሕዝብ የሚወደዱ የድሮ ዘፈኖችን ዳግም በማቀንቀን ዝና ለማትረፍ ይጣጣራሉ፡፡ ይህ የኮፒ ራይት ጥያቄ ያስነሳባቸው አጋጣሚዎችም ጥቂት አይደሉም፡፡ በብዙዎች የሚነሳው ጥያቄ የአሁኑ ትውልድ የቀድሞ ሥራዎችን በሚወደው መጠን ቀጣዩ ትውልድ የዚህን ዘመን ሥራዎች ያወድሱ ይሆን? የሚለው ነው፡፡ የሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዚዳንቱ ኪቦርዲስትና አቀናባሪ ዳዊት ይፍሩ፣ ሙዚቀኞች የኮፒ ራይት መብታቸው ተጠብቆ የሚገባቸውን ክፍያ ሲያገኙ የሙዚቃ ገበያ ውድድር ስለሚለወጥ የተሻለ ሙዚቃ መሥራት እንደሚቻል ያምናሉ፡፡

ግጥምና ዜማ ደራሲ፣ ድምፃዊና አቀናባሪ መብታቸው ሲከበር ለፈጠራ ሥራ ስለሚነሱ የሚሰጧቸው ሙዚቃዎችም ደረጃቸውን የጠበቁ እንደሚሆኑ ያስረዳሉ፡፡ በሮሐ ባንድ የነበራቸውን ወቅት በማስታወስ ቀድሞ ሙዚቃ የሚሠራበትን ሁኔታ ያትታሉ፡፡ ግጥምና ዜማ ከተሠራ በኋላ ይገባል በሚሉት ዘዬ መግቢያ፣ መሸጋገሪያና መደምደሚያ ያበጁለታል፡፡ የባንዱ ስድስት አባላት የተለያየ ኃላፊነት ስላላቸው፣ ሁሉም ባለሙያ የየድርሻውን ተወጥቶ በስተመጨረሻ የሙሉ ባንድ ጥምረታቸው ውጤት ከሕዝብ ዘንድ ይደርሳል፡፡ ሒደቱ ከአንድ ወር እስከ ሁለትና ከዚም በላይ ሊወስድ ይችላል፡፡

‹‹ወቅታዊ ይዘት የሌለው ሙዚቃ ተደማጭነት ስለማይኖረው የሕዝቡን ፍላጎት የተመረኮዘ ሙዚቃ ይሠራል፤›› ይላሉ፡፡ ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃውን የሚያሳድግ ሥራ ሲሠራ፣ የሚገኘውን ገቢ ብቻ ታሳቢ በማድረግ እንዳልሆነም ያክላሉ፡፡ በዚህ ዘመን የሚሠሩ ሙዚቃዎች ገበያ ተኮር በመሆናቸው የይድረስ ይድረስ ስለሚሆኑ ዘመን ተሻጋሪነታቸው ላይ ጥያቄም ያነሳሉ፡፡

በሙዚቀኛው አስተያየት፣ የቀድሞ ሙዚቃዎችን ቀነጣጥቦ ዳግም ከመሥራት ወጥ ሥራዎች ሊተኮርባቸው ይገባል፡፡ ዘመነኛ ቴክኖሎጂ ለሙዚቃው የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ቢኖርም ጎጆ ጎጂ እያመዘነ መሆኑንም ያስረዳል፡፡ የዘመኑ ውጤት በሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሙዚቃውን መማሳደግ ሲቻል፣ በአንድ ኪቦርድና ኮምፒውተር ሙዚቃ መሥራት በቂ ነው ብሎ መውሰድ እንደማያሻ ይገልጻሉ፡፡

‹‹ለሥራው ተጨንቆ የሚሠራውን ባለሙያ ውጤት በጣጥሶ በሶፍትዌር እንደ አዲስ ማቅረብ የባለሙያውን ቅስም ይሰብራል፡፡ ቴክኖሎጂ ያመጣቸው የተሻሉ አማራጮችን በቀና መጠቀም ግን ይቻላል፤›› ይላሉ፡፡ ዛሬ ዛሬ የሚሠሩ ሙዚቃዎችን ከቀደምቶቹ ያነሱ ጥበባዊ ዋጋ ያላቸው ናቸው ብሎ መደምደም እንደማይቻል ሙዚቀኛው ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ በቁጥር ቢያንሱም አሁንም ግሩም ሙዚቃዎች እንደሚሠሩ ያምናሉ፡፡

የየዘመኑ አንፀባራቂ ከዋክብት የሆኑ ሙዚቀኞች ለአገሪቱ ሙዚቃ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ መኖሩ አይካድም፡፡ ሙዚቃ ለማኅበረሰቡ ልብ የቀረበ ጥበባዊ ውጤት እንደመሆኑ፣ ሕዝቡ ከሚቀርቡለት ሥራዎች መካከል ትርጉም የሚሰጠውን ይመርጣል፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጡ ኮንሰርቶችና ፌስቲቫሎች ለወቅቱ ድምፃውያን ዕድል የሚሰጡ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ከሌላ አገር ተወላጆች ጋር የሚጣመሩባቸው መድረኮችም መበራከታቸው ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ነው፡፡

ቀደምቱ ሥራዎች ወጣትና አዛውንቱ መካከል ድልድይ እንደፈጠሩት ዛሬ የሚሠሩ ሙዚቃዎች የነገ ዕጣ ፈንታ ተመሳሳይ ይሆን? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ፣ በየዘመኑ በሚፈጠሩ ዕድሎች ተጠቅሞ የሙዚቃን ተደራሽነት ማስፋት ያለው ጠቀሜታ ቀላል አይደለም፡፡ ሙዚቀኛው ዳዊት፣ ‹‹100 ሚሊዮን ሕዝብ አለ፡፡ ድምፃዊውም በዝቷል፡፡ ካለው ሰፊ ገበያ አንፃር የተሻለ ሥራ የሚሠሩት ነጥረው የሚወጡት የፈጠራ ሥራ ሲከበር ነው፤›› ይላሉ፡፡

እንደ ግርማ በየነ ያሉ አንጋፋ ድምፃውያንን የሚያደንቁ አድማጮች፣ ከቀደምቱ ጎን ለጎን በዚህ ዘመን ሊያዳምጧቸው የሚጓጉላቸው ሙያተኞች እንደሚሹ እሙን ነው፡፡ የሚሠራው ሙዚቃ ደረጃውን ጠብቆ እስከቀረበ ድረስ ጆሮ ገብ የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ሙያውና አድማጩም ተከብሮ የተሠሩ ወጥ የዚህ ዘመን ሥራዎች ሲወደዱም ታይቷል፡፡ የድሮ መዚቃዎች የዕድሜ ክልልን ሰብረው ሕዝቡን እንዳዋሃዱ ሁሉ የወጣት ድምፃውያን ሥራዎችም የዛሬና የድሮ አድማጮች ሲያስማሙም ተስተውሏል፡፡ ጥያቄው የሚሆነው ሰንቶቹ የዚህ ዘመን ሙዚቃዎች ይህንን ክብር ይቆናጠጣሉ? የሚለው ነው፡፡

ረ2/12/09cial et  ss 4

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...