Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየበዓል ፀጋ

የበዓል ፀጋ

ቀን:

ኢትዮጵያውያን ዓውደ ዓመታቸውን ወይም ድግሳቸውን ለማድመቅ በአለባበስ ማሸብረቅና የተለያዩ ምግችን ማዘጋጀት ወጋቸው ነው፡፡ አውደ ዓመትን ወይም ድግስን ደስ የሚል ድባብ ለማላበስም የቄጠማ ጉዝጓዞ የተለመደ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በተጠራንበት ግብዣ ቦታ መጀመርያ የሚቀበለን ይኼው ጉዝጓዝ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ጉዝጓዝ ቄጠማ እንዲሁ እንደቀድሞው ከጓሮ የሚታጨድ ወይም በርካሽ ዋጋ የሚገኝ አይደለም፡፡  ዋጋውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡

ክረምቱ አልፎ አዲስ ዓመት ሲገባ እንኳን ቤቱ መስኩም ቢሆን በሳርና በአደይ አበባ ያጌጣል፡፡ ሆኖም ለመብቀል እምብዛም ጥረት የማይጠይቀው ቄጠማ እንደልብ በሚበቅልበት ወቅት እንኳን ቅናሽ አይታይበትም፡፡

ወደ ሾላ ገበያ ከሚወስዱት መንገዶች አንዱ ከሆነው ለም ሆቴል ጀምሮ በግራና ቀኝ ያሉ የንግድ ቤቶች በአዲስ ዓመት ዘፈን በመታጀብ በር በራቸው ላይ ቄጠማ በመጎዝጎዝ የአዲሱን ዓመት በዓል ቀድመው አድምቀውታል፡፡

ከእነዚህ ሱቆች ልብስ፣ ጫማ፣ አልፎ አልፎ የቤት ዕቃ የሚገዙ ይታያሉ፡፡ ካፌዎች፣ የጀበና ቡና የሚሸጡ ሱቃቸውን በቄጠማ ጉዝጓዝ በማስዋብ ወደ ገበያው የሚመላለሱትን እንግዶች ተቀብለው ያስተናግዳሉ፡፡

በገበያው ከሚሸጡት በርካታ ነገሮች አንዱ የሆነው ቄጠማ በአዘቦትም ይሁን በበዓል ቀን የሚገኝበት ሾላ ቄጠማ ተራ ነው፡፡ ከገበያው በስተቀኝ በኩል ከኮብል ስቶን በተሠራው መንገድ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ይገኛል፡፡ ወ/ሮ ድባቤ (የአባታቸውን ስም መናገር ፈቃደኛ አይደሉም) ይባላሉ፡፡ ሳር በመነገድ ልጆች ወልደው እንዳሳደጉ ይናገራሉ፡፡ የቄጠማ ንግድ ምን እንደሚመስል ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ እንደ ሁሉም ንግድ ይኼውም እየተስፋፋ እንደመጣ በመግለጽ ገዢ በመኖሩ ግን እየሠሩ እንደሚያድሩ አብራርተዋል፡፡

ወ/ሮ ድባቤ ያሉበት አካባቢ ከጳጉሜን ጀምሮ የዓመት በዓልን ድባብ ይዟል፡፡ ሰዎች እንደየፍላጎታቸው አንድ ጭብጥ የምትሞላውንና ከአምስት ብር ጀምሮ የምትሸጠው ቄጠማ በርከት አድርገው በመግዛት ይሄዳሉ፡፡ እሳቸውም ከጀርባቸው የተቀመጠውንና በማዳበሪያ የተሞላ ሳር ጨበጥ ጨበጥ እያደረጉ በማሰር አንድ ዘለላ ከሴ በመጨመር ለገበያ ያዘጋጃሉ፡፡ አንድ ማዳበሪያ ቄጠማ በክረምት 400 ብር በበጋ ደግሞ እስከ 700 ብር ሊያወጣ እንደሚችል ወ/ሮ ድባቤ ይገልጻሉ፡፡ በክምር ያለውንም እንዲሁ በውድ እንደሚገዙት ተናግረው፣ ለደንበኞቻቸው በችርቻሮ በውድ ለማቅረብ እንደሚገደዱ ይገልጻሉ፡፡

 የቄጠማ ጉዝጓዝ በትልልቅ ሞሎች፣ በቡቲኮች መዘውተር ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ 22 አካባቢ ለሚገኘው ቡቲኩ ከወ/ሮ ድባቤ ቄጠማ ሲገዛ ያገኘሁት ዲኖሰፊ ተማም ለምን እንደሚገዛ ስጠይቀው፣ ‹‹ቤት ያሞቃል ሰዎች ሲገቡ ደስ ይላቸዋል፡፡ በዓል በዓል ይመስላቸዋል፤›› ብሏል፡፡ የዋጋው ነገር ግን ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ እንደመጣም ያስረዳል፡፡ ለቡቲኩ በሳምንት ለሦስትና አራት ቀን ቄጠማ የሚገዛ ሲሆን፣ ወጪውም ከአሥር ተነስቶ እስከ 50 ብር እንደደረሰ ይናገራል፡፡ በበጋና በበዓላት ወቅት ደግሞ በሳምንት እስከ መቶ ብር ሊደርስ እንደሚችል ገልጿል፡፡

የጉዝጓዝ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የከተማችን ባህላዊ የምግብ አዳራሾች ይገኙበታል፡፡ አቶ አለባቸው ታረቀኝ ይባላሉ፡፡ የጨጨሆ ባህላዊ ምግብ አዳራሽ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ድርጅታቸው በወር ምን ያህል ለቄጠማ እንደሚያወጣ ለቀረበላቸው ጥያቄ ገና አዲስ በመሆናቸው ማወቅ እንደማይችሉ፣ ይነስም ይብዛም ግን በቀን በቀን እየተገዛ እንደሚጎዘጎዝ ማስተዋላቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ አለባቸው ባደጉበት ገጠር ቄጠማ ለንግድ እንደማይውልና እንዲያውም ለጎረቤት በመስጠት ምርቃት የሚገኝበት እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ በከተማ ያዩት ነገር ግርምትን እንደፈጠረባቸው ተናግረው፣ ገና ለገና ለሰዎች ልዩ ስሜት ይሰጣል ተብሎ እንዲህ መሸጡም፣ መግዛቱም፣ አግባብ መስሎ እንደማይታያቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ጉዝጓዙ ልዩ ስሜት አለው፡፡ በተለይ ለውጭ አገር እንግዶች አግራሞትን ይፈጥራል፡፡ ለምን ዋጋው የተወደደ ይመስልዎታል? ብሎ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ በከተማ ውስጥ እንደ ልብ አለመገኘቱና በንግዱ አካባቢ አሁን አሁን ለበርካታ ሰዎች መተዳደሪያ እየሆነ መምጣቱ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ቀለሟ ታዬ በሰሚት አካባቢ የጀበና ቡና በመሸጥ ትተዳደራለች፡፡ አራት በአራት በሆነች ክፍል ውስጥ እንደ ምንጣፍ የሚመች ቄጠማ ተጎዝጉዟል፡፡ እንግዶች ስኒውን ከበው ቡናውን ፉት እያሉ ቁጭ ብለዋል፡፡ ከረከቦቱ ከፍ ባለ ወንበር ላይ ቀለሟ ሹርባዋን ተሠርታ የባህል ልብስ ለብሳ በዓል ቀን አስመስላዋለች፡፡

ለቄጠማ ልዩ ፍቅር እንዳላት ትናገራለች፡፡ ቀለሟ የጉዝጓዝ ፍቅር ያደረባት ከቤተሰቦቿ እንደሆነ በመግለጽ፣ ቄጠማ ውድ ቢሆንም፣ ‹‹በዓልን ከዚህ ውጪ ማሰብ ለእኔ ይከብደኛል፣ የበዓል ቀን ጠዋት ስነሳ በዓል መሆኑን የማውቀው ቄጠማ በመጎዝጎዝ ስጀምረው ነው፡፡ ከምግቡም ከመጠጡም በላይ ቤትን የሚያሞቀው ጉዝጓዙ ነው፤›› በማለት ታብራራለች፡፡ ቀለሟ የጀበና ቡና መሥራት ከጀመረች ጀምሮ በየቀኑ ቄጠማ የሚያቀርቡላት ሰዎች ያሉ ሲሆን፣ በቀን እስከ አሥር ብር ድረስ ወጪ ታደርጋለች፡፡ አቅራቢዎቿም ሴቶች ናቸው፡፡ በጀርባቸው ተሸክመው የሚያመጡትን ቄጠማ እንደሷ ላሉ ቤቶች በማቅረብ የዕለት ጉርሳቸውን ይዘው ይመለሳሉ፡፡ ሳሩን የሚያገኙት ሌሊት በመነሳት በወንዝና በከተማዋ ባሉ ኩሬዎች አካባቢ እንዲሁም ታጥረው ከተቀመጡ ግቢዎች በማጨድ ነው፡፡ ቀለሟም ለቤቷ ጉዝጓዝ ከሚያቀርቡላት ሴቶች ከሁለት ብር ተነስታ በየቀኑ 10 ብር እንደምታወጣ በመግለጽ ‹‹ወደፊት እንደ ስኳር እንዳያሰልፈን፤›› በማለት አስተያየቷን በቀልድ ደምድማለች፡፡

በሾላ ቄጠማ ተራ ውስጥ ቄጠማ ከአምስት ዓመት በላይ የሸጠችው አስቴር ማሞ በርካታ ደንበኞች አሏት፡፡ እኛም በተለያዩ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወንዶችን ጨምሮ አንዷን እስር በአምስት ብር ሲገዙና መጠኑ አነስተኛ በመሆኑ እስከ ከ30 ብር ድረስ ሲያወጡ አይተናል፡፡

የቄጠማ ጉዝጓዝ ከዕለት ወደ ዕለት ፈላጊው እየጨመረ በመምጣቱ ዋጋውም ከፍ ሊል እንደቻለ አስቴር ትገልጻለች፡፡ በተለይ የበጀና ቡና የሚሠሩ፣ ባህላዊ ቤቶች አሁን አሁን ደግሞ በቡቲኮች፣ በንግስ በዓሎች፣ አንድ አንድ ቦታ ይዘው የሚሄዱ ሰዎች የበዓል ፀጋ የሆነውን ቄጠማ በብዛት የሚጠቀሙ በመሆኑና በዛው ልክ የአቅርቦቱ ማነስና ቄጠማው የሚመጣው በከተማ ዳርቻ ካሉ ከተሞች በአይሱዙና በአህያ ተጭኖ በመሆኑ ዋጋው ተወዷል፡፡ በበጋ ወቅት ደግሞ የባሰ ይወደዳል፡፡

ሪፖርተርም ቄጠማ ይመጣባቸዋል በተባሉ ቦታዎች ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ እንደተመለከተው ትልቅ ንግድ እየሆነ መምጣቱንና መወደዱን ለመታዘብ ችሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...