- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነህ ወዳጄ?
- አለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንተ በቃ እኔ ካልደወልኩ አትደውልም?
- ምን ክቡር ሚኒስትር ያው ጊዜው ሒሳብ የምንዘጋበት ወቅት እኮ ነው?
- እሱማ የጠፋኸው ለምን እንደሆነ ይገባኛል?
- በጣም ቢዚ ነበርን፡፡
- ያው ካገኘኸው ቦነስ ጋብዘኝ እንዳልልህ ነው አይደል?
- ኧረ ሰሞኑን እንዲያውም አመም አድርጎኝ ነበር፡፡
- ውይ ምነው?
- ለሕክምና ወደ ውጭ ሄጄ ነበር፡፡
- ያው ዳጐስ ያለ አበል ይዘህ ነዋ የሄድከው?
- ኪኪኪ…
- እንደ እርስዎ መስሎዎት ነው አይደል?
- ማለት? አበል አልተሰጠኝም ለማለት ነው?
- ኧረ እኔ ራሴ ባጠራቀምኳት ገንዘብ ነው የምታከመው፡፡
- እሱን እንኳን ተወው፡፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- የውጭ ምንዛሪው በእጅህ አይደል እንዴ ያለው?
- ቢኖርስ ክቡር ሚኒስትር?
- ያው የቻልከውን ያህል ዘገን አድርገህ ነው የምትሄደው ብዬ ነዋ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ባንኩ እኮ የግሌ ሳይሆን የሕዝብ ነው፡፡
- ታዲያ መቼም ውጭ አገር በኢትዮጵያ ብር አትገበያይ?
- ክቡር ሚኒስትር እኔ ግን በራሴ ገንዘብ ነው የምታከመው፡፡
- እኔ እኮ ጉንፋን ሲያመኝ ለአበሏ ስል ዘልዬ ባንኮክ ነው የምሄደው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኛ ጋ ግን እንደዚያ የለም፡፡
- ለማንኛውም ዛሬ ለቁም ነገር ፈልጌህ ነው፡፡
- ምን ልታዘዝ ክቡር ሚኒስትር?
- አዲሱ የበጀት ዓመት ጀመራችሁ አይደል እንዴ?
- ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አዲሱን ዓመትም እየተቃረበ ነው፡፡
- እሱማ ትንሽ ይቀረዋል፡፡
- አይ ያው ዝግጅቱን ከዚሁ ነው የምትጀምሩት ብዬ ነው፡፡
- የምን ዝግጅት ክቡር ሚኒስትር?
- ይኼ የካላንደርና የአጀንዳ ኅትመቱን ነዋ፡፡
- እሱንማ ጨረታ አውጥተናል፡፡
- ጨረታ ምን ያደርጋል?
- እንዴት ማለት ክቡር ሚኒስትር?
- እኛው ነና ጉዳዩን መጨረስ ያለብን፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ባለፈው ነግሬህ ነበር እኮ?
- ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
- አዲስ ያቋቋምኩት ማተሚያ ቤት አለ ብዬ ነዋ፡፡
- ተወዳደሩ እንጂ ክቡር ሚኒስትር?
- እኔ እኮ በውድድር አላምንም፡፡
- ታዲያ በምንድነው የሚያምኑት?
- ልማታዊ አስተሳሰብ አለው ወይ በሚለው ነዋ፡፡
- ይቅርታ ያድርጉልኝና ክቡር ሚኒስትር፣ እኛ ደግሞ በውድድር ነው የምናምነው፡፡
- አንተ አይገባህም እንዴ?
- ጨረታውን ካልተወዳደሩ ምንም ልረዳዎት አልችልም፡፡
- እኔ እኮ ሁላችንም የምንጠቀምበትን መንገድ አስቤ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አጣብቂኝ ውስጥ እየከተቱኝ ነው፡፡
- የምን አጣብቂኝ ነው?
- ያው ባንኩ እኮ በቦርድ ነው የሚመራው፡፡
- ለሥራው አዲስ ነህ እንዴ? ከሌሎቹስ ጋር እንደዚህ አይደል እንዴ የምሠራው?
- እኔ የሌሎቹን አላውቅም፡፡
- አንተ ሐሳብ የሆነብህ ነገር ምንድነው?
- ሥራዬን እንዳያሳጡኝ ነዋ፡፡
- ስለእሱ አታስብ፡፡
- የልጆች አባት እንደሆንኩ ያውቃሉ?
- ከተባረርክም እኔ አስቀጥርሃለሁ፡፡
- የት?
- የእኛው ባንክ!
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ የመንግሥት የልማት ድርጀት ኃላፊ ጋ ይደውላሉ]
- ሰላም ወዳጄ፡፡
- እንዴት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ዛሬ እንዴት ደወሉልኝ እባክዎ?
- ለብርቱ ጉዳይ ፈልጌህ ነው፡፡
- ምነው ያቺን ሪፖርት ፈልገው ነው?
- የምን ሪፖርት ነው?
- ባለፈው ቦርድ ስብሰባ ላይ የቀረበውን ነዋ፡፡
- ስማ እኔና አንተ ከቦርድ ባለፈ ወዳጅነታችንን ማጠንከር አለብን፡፡
- ካሉማ ደስ ይለኛል፡፡
- አንተን ሳይህ ንቁ ነገር ስለሆንክ አንድ ፕሮጀክት አስቤልህ ነበር፡፡
- አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ያው ከፊታችን አዲስ ዓመት አለ፡፡
- ግን ገና ነው እኮ ክቡር ሚኒስትር?
- ቢሆንም አንድ ነገር አስቤ ነበር፡፡
- ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
- ያው ድርጅታችሁ ካላንደርና አጀንዳ ማሳተሙ አይቀርም ብዬ ነው፡፡
- እሱማ በመላው አገሪቷና በውጭ ባሉን ኤምባሲዎቻችን ነው የምናሰራጨው፡፡
- አየህ እዚህ ላይ ነው ጥሩ ሥራ የምንሠራው፡፡
- ምን ክቡር ሚኒስትር?
- ሥራውን ለእኔ ትሰጠኛለህ?
- የምን ሥራ ክቡር ሚኒስትር?
- የካላንደሩንና የአጀንዳውን ሥራ ነዋ፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር አካሄዱን እያወቁት?
- አካሄዱ ምን ችግር አለው?
- ማለቴ ስንትና ስንት የግዢ ሒደት አለዋ፡፡
- ምን በፊት ከነበረው ኃላፊ ጋር እንደዚህ አይደል እንዴ የምንሠራው?
- ቢሆንም ግን ትንሽ ያሠጋል፡፡
- እኔው አይደለሁ እንዴ የቦርድ ሰብሳቢ?
- እሱንማ አውቃለሁ፡፡
- ታዲያ ከሥራዬ እንዳልፈናቀል ብዬ ነዋ፡፡
- ብትፈናቀልስ?
- የልጆች አባት መሆኔን ረሱት እንዴ?
- ከዚህ የምታገኘው ኮሚሽን እኮ አንቀባሮ ነው የሚያኖርህ፡፡
- ስለዚህ ክቡር ሚኒስትር?
- ያዋጣሃል፡፡
- ምኑ?
- ሙስናው!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ኢንቨስተር ይደውልላቸዋል]
- ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ዛሬ ከየት ተገኘህ እባክህ?
- እኔ እኮ ዘመድ ጠያቂ ነኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እሱ እንኳን ጉዳይ ሲኖርህ ነው የምትደውለው፡፡
- በእውነት ዛሬ ሰላም ልልዎት ነው የደወልኩት፡፡
- ቁም ነገረኛ ወጥቶሃል ማለት ነው?
- በዚህ እንኳን አልታማም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሥራ እንዴት ነው ታዲያ?
- ያውቁት የለ የእኛን ሥራ፣ አንዱ ሲደክም ሌላው ይነሳል፡፡
- ጥሩ ነው ይልቁንስ እንኳን ደወልክ፡፡
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- እናንተ ካላንደርና አጀንዳ ታሳትማላችሁ አይደል?
- ኧረ ለእኛ ሥራ እኮ እንደዚህ ዓይነቱ ነገር ብዙም አይጠቅምም፡፡
- አየህ ቢዝነስህ የሚደክመው እኮ ለዚህ ነው፡፡
- እንዴት?
- ፕሮሞሽን ላይ እየሠራህ አይደለም?
- ያው የእኛ ሥራ እኮ ኤክስፖርት ማድረግና እዚህ አገር የምናስገባቸውን ዕቃዎች መጋዘን ተከራይቶ መሸጥ ነው፡፡
- ቢሆንም አየህ የምትሠራውን ሥራ ለመንግሥትም ሆነ ለሌሎች አካላት ማስተዋወቅ አለብህ፡፡
- ታዲያ ምን እየመከሩኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ካላንደርና አጀንዳ ማሳተም ግዴታ ነው፡፡
- ችግሩ ደግሞ የማውቀው ማተሚያ ቤትም የለም፡፡
- ስለእሱ አታስብ፡፡
- እንዴት?
- እኔ ያስመጣሁዋቸው የማተሚያ ማሽኖች አሉ፡፡
- እንደዚያ ከሆነማ ለእኔ ሥራ አቀለሉልኝ፡፡
- ስለዚህ ሥራውን ትሰጠኛለህ?
- አዎ ግን ከእርስዎም የምፈልገው ነገር አለ፡፡
- ምን?
- 10 ሺሕ ሔክታር መሬት!
[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ስልክ ደወሉላቸው]
- እሺ የእኛ አዋቂዎች፡፡
- ምን እያልሽ ነው?
- ምን እያደረጋችሁ እንደሆነ ታውቃላችሁ?
- ያው አገሪቷን በልማት ጎዳና እያስጓዝናት ነው፡፡
- እኔ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ?
- ጠይቂኝ፡፡
- ከልጅ ልጅ ቢለዩ፣ ዓመትም አይቆዩም ሲባል አልሰማህም?
- ሰምቻለሁ፡፡
- እኛ ታዲያ የእንጀራ ልጆች ነን?
- ማን ናችሁ እናንተ?
- እኛ ‹‹ሀ››ዎች፡፡
- ‹‹ሀ››ዎች ስትይ?
- እኛ ደረጃ ‹‹ሀ›› ግብር ከፋዮች፡፡
- ራስሽን ከጉሊትና ከጀበና ቡና ሻጭ እኩል ማየት ጀመርሽ?
- አየህ ግብር እኮ ለሁሉም ፍትሐዊ መሆን አለበት፡፡
- እሱማ ፍትሐዊ ነው፡፡
- ታዲያ ለምንድነው አንድ አገር ውስጥ ሁለት ዓይነት አሠራር የሚኖረው?
- አንቺ ሴትዮ ጤነኛ ነሽ?
- በጣም ጤነኛ ነኝ፡፡
- ምን እያልሽ ነው ታዲያ?
- በጣም ብዙ ሰዎችን እያስከፋችሁ ነው፡፡
- ማለት?
- የከተማው ሚሊየነር፣ ቢሊየነር እንዲሁም የከተማው ከፍተኛ ኢንቨስተር ተከፍቷል፡፡
- እንዴት ነው እናንተ ከጉሊት ቸርቻሪ ጋር አንድ የምትሆኑት?
- ምን አለበት?
- ሴትዮ ምን ይደረግ እያልሽ ነው?
- እኛ እንደ ጉሊት ቸርቻሪዎቹ ያመነውን እንክፈል፡፡
- ኪኪኪ…
- ምን ያስቅሃል?
- ሲባል አልሰማሽም እንዴ?
- ምን?
- ነጋዴን ያመነ…
- እ…
- ጉም የዘገነ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ለአንድ ኢንቨስተር ስልክ ደወሉ]
- ሄሎ ወዳጄ እንዴት ነህ?
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ዛሬ ከየት ተገኙ?
- ያው አንተ ስለማትደውል፣ እኔ ልደውል ብዬ ነው፡፡
- ሥራ ስለሚበዛብኝ እኮ ነው፡፡
- እስቲ ስለአንዳንድ ነገር እንወያይ ብዬ ነው፡፡
- ስለምን ክቡር ሚኒስትር?
- ያው እናንተ ትልልቅ ባለሀብቶች ስለሆናችሁ ካልረዳችሁን የት እንደርሳለን ብለህ ነው?
- የቻልነውን እያደረግን ነው እንግዲህ?
- አሁን ካሳዑዲ የሚመጡ ወገኖቻችንን እዚህ ለማቋቋም አስበናል፡፡
- ጥሩ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ግን የእናንተንም ዕርዳታ እንፈልጋለን፡፡
- እና ከሕዝብ ገንዘብ ሊሰበስቡ ነው?
- መጀመሪያማ ከባለሀብቱ ነው እንጂ፡፡
- እኛ ምን በወጣን?
- ምን እያልክ ነው?
- በቃ ሁሉም በዚህ መዋጮ በምትሉት ነገር ደስተኛ አይደለም፡፡
- ለምን?
- የሚወራውን አይሰሙም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ተወራ ደግሞ?
- ባለፈው ለቆሼ ተብሎ በገንዘብና በዓይነት ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ነው የተሰበሰበው፡፡
- ጥሩ ነዋ ታዲያ?
- ግን ተጎጂዎቹ በሚገባ እየተረዱ አለመሆኑን ሚዲያዎች እያናፈሱት ነው፡፡
- ወሬኞች በላቸው፣ አርፈው ሥራቸውን አይሠሩም?
- ይኼ አይደል እንዴ ሥራቸው?
- ማቃጠር?
- ማቃጠር ሳይሆን በተለያዩ አካላት የሚሠሩ ስህተቶችን ማጋለጥ፡፡
- እነሱ እባክህ ያልበላቸውን ነው የሚያኩት፡፡
- እሱ ብቻ አይደለም፡፡
- ሌላ ምን አለ?
- ይኸው በዚህ 40/60 እንኳን ስንቱ ሙሉ ክፍያ ከፍሎ ቤት ሲጠባበቅ ጥቂቶች ብቻ ነው ቤት ያገኙት፡፡
- መንግሥት እንግዲህ የቻለውን እያደረገ ነው፣ ከዚህ በላይ ምን ይደረግ?
- እኔማ ክቡር ሚኒስትር ለሳዑዲ ተመላሾች ብለው አፍዎን እንዳያበላሹ ብዬ ነው፡፡
- ማለት?
- የሚወራውማ መንግሥት በተለያዩ የመዋጮ ጉዳዮች ጨዋታ ጀምሯል እየተባለ ነው፡፡
- የምን ጨዋታ?
- እሟ ቀሊጦ!