– መድን ድርጅት በበኩሉ ከውል ውጭ ጥያቄ እንደቀረበበት በመግለጽ ከባንኩ ጋር ውይይት ላይ ነኝ ብሏል
– በዓመት ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ለሞርጌጅ ዋስትና ይከፈላል ተብሏል
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሠራተኞቹ ማበረታቻ ይሆን ዘንድ በረጅም ጊዜ የሚከፈል የቤት መግዣ ብድር ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በዚህ አግባብ ተጠቃሚ የነበሩ ከ3,000 በላይ ሠራተኞች ለብድሩ ዋስትና ይሆን ዘንድ የገቡትን የመድን ዋስትና ግን ከስድስት ወራት በፊት መነሳቱን፣ ለሠራተኞቹ የተሰጠው ብድርም ሳይከፈል ይቀራል የሚል ሥጋት እንደሌለ በማስታወቅ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋስትናውን እንዲያነሳ ጠይቆ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የንግድ ባንክ ሠራተኞች ለሪፖርተር በገለጹት መሠረት፣ ባንኩ ለሠራተኞች የቤት መግዣ የሰጣቸውን ብድር በገቡት ስምምነት መሠረት በወቅቱ መክፈል ቢሳናቸው፣ ይህንን ኪሳራ ለመሸፈን የሚያስችል መድን ገብቶላቸው በዚያ መሠረት ለኢትዮጵያ መድን ድርጅት ክፍያ ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡
ይሁንና ባንኩ ‹‹ሞርጌጅ ፔይመንት ፕሮቴክሽን ኢንሹራንስ›› ወይም በአጭሩ ሞርጌጅ ኢንሹራንስ እየተባለ የሚጠራውን ይህንን ዋስትና ከመንፈቅ ወዲህ ማንሳቱን፣ ለዋስትናው መነሳት ምክንያቱም ለሠራተኞቹ የቤት ግዥ ክፍያ የተገባው ዋስትና ሥጋቱ ዝቅተኛ መሆኑን በማሰብ እንደሆነ ከሠራተኞቹ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በዚህ መሠረት ባንኩ ዋስትና አያስፈልገውም ቢልም፣ ‹‹መድን ድርጅት ግን እምቢተኛነቱን በማሳየት ጥያቄያቸውን ለማስተናገድ ፈቃደኛነቱን እንዳላሳየ፤›› ገልጸዋል፡፡
ሠራተኞቹ እንደሚገልጹት፣ የሞርጌጅ ኢንሹራንሱ የብድር ጥያቄያቸው በባንኩ እንደተስተናገደ፣ ቀድሞውኑ ሙሉ በሙሉ ይከፈላል፡፡ በመሆኑም ንግድ ባንክ ዋስትና አያስፈልገውም በማለቱ እስካሁን የተከፈለው በታሳቢነት ተቀናሽ ተደርጎ ለወደፊቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ይጠበቅ የነበረው ቀሪ ገንዘብ እንዲመለስላቸው ጥያቄ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ በሠራተኞቹ መረጃ መሠረት ከ3,000 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች በዓመት የሚከፈለው የሞርጌጅ ዋስትና ቢያንስ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚደርስ ይገመታል፡፡
ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነፃነት ለማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጥያቄ እየተነሳበት የሚገኘው የሞርጌጅ ኢንሹራንስ ዘርፍ፣ ተበዳሪው የተበደረውን ገንዘብ ሳይከፍል በሞት ቢለይ ለብድሩ ማካካሻ በቀረው የዕዳ መጠን ላይ መድን ድርጅት ካሳ ለመክፈል ተዋውሏል፡፡ የሞርጌጅ ኢንሹራንስ በሁለት አበይት ምክንያቶች ይቋረጣል ያሉት አቶ ነፃነት፣ አንደኛው ምክንያት ተበዳሪው ብድሩን አጠናቆ ሲከፍል በሁለተኛ ደረጃም ተበዳሪው ሲሞት የተገባው የመድን ውል እንደሚቋረጥ ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ቅደመ ሁኔታዎች ከባንኩ ጋር በተደረጉ የውል ስምምነቶች በግልጽ መቀመጣቸውን በመግለጽ፣ ሠራተኞቹ በባንኩ ክፍያ የተፈጸመበትን የሞርጌጅ ኢንሹራንስ የመድን ገንዘብ ለምን ማስመለስ እንዳልቻለ እንዲጠይቁ መክረዋል፡፡ ባንኩና መድን ድርጅት በተዋዋሉት መሠረት ከላይ በአቶ ነፃነት ከተጠቀሱት ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ ቢሟላ መድን ድርጅት ለዋስትና የተከፈለውን ገንዘብ ለመመለስ ፈቃደኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹ገንዘቡ እንዲመለስላችሁ የምትፈልጉ ከሆነ እያንዳንዱ ተበዳሪ ዕዳውን ከፍሏል ብላችሁ ጻፉልን ብንላቸውም ይህንን ማድረግ ተጠያቂነት ያመጣብናል፤›› በማለታቸው ገንዘቡን ከዋስትና ስምምነቱ ውጪ ለመመለስ የሚችልበት ዕድል በባንኩ ሊፈጠርለት እንዳልቻለ አቶ ነፃነት አስረድተዋል፡፡ ባንኩ የሕዝብ ገንዘብ የሚያስተዳድር ተቋም በመሆኑ ጭምር ውሉን መሰረዝ እንደማይችል የጠቀሱት አቶ ነፃነት፣ መድን ድርጅት ብቻ ሁለት ቢሊዮን ብር በባንኩ የተቀመጠ ገንዘብ ያለው በመሆኑ በተዘዋዋሪ ይህንን ገንዘብ ስለሚያበድር ጥንቃቄ የተሞላበት አካሔድ መከተል እንደሚገባውም ያሳስባሉ፡፡
ንግድ ባንክ ለሠራተኞች በሰጠው የሞርጌጅ ብድር መሠረት አንድ ተበዳሪ ዕዳውን ሳይከፍል ቢሞት፣ አማራጩ ንብረቱ ሳይነካ ዕዳውን ይሰርዝለታል ማለት ነው፡፡ ይህ አሠራር የሕዝብን ገንዘብ አበድሮ መልሶ የሚቀበልበት ዕድል ሳይኖረው እንደመሠረዝ የሚቆጠር በመሆኑ፣ ከዚህ ይልቅ ግን የሞርጌጅ ኢንሹራንስ ክፍያው በዝቷል ከተባለም ሌሎች አማራጮች መከተል እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡
ምንም እንኳ ከአሁን በኋላ የሞርጌጅ ኢንሹራንስ እንደማይገባ ባንኩ ቢያስታውቅም፣ እስካሁን የነበረውን መሰረዝ እንደማይችል፣ ይህም በሁለቱ መካከል በተገባው አስገዳጅ ውል መሠረት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ሠራተኞቹ ለሞርጌጅ ኢንሹራንስ የተከፈለባቸው ገንዘብ እንዲመለስላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ በሚመለከት አማራጮችን ለማየት የሚያስችሉ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውና ወደፊትም ተጨማሪ ውይይቶች እንደሚካሔዱ አቶ ነፃነት ገልጸዋል፡፡
ንግድ ባንክ የመድን ድርጅትን ምልከታ ያላካተተ ጥናት በማድረግ በየዓመቱ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ የሞርጌጅ ወጭ እያወጣ እንደሚገኝ በመገንዘቡ ይህንን የመድን አገልግሎት ለማቋረጥ እንደተነሳ ይነገራል፡፡ በየዓመቱ በሞት የሚለየው ሰው የሚያስወጣው ወጪ ከአምስት እስከ አሥር ሚሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ እንደሆነም በጥናት መረዳቱን አቶ ነፃነት ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ግን ለሞርጌጅ ኢንሹራንስ የሚከፈለው አረቦን ለአንድ ጊዜ ተከፍሎ ከ20 ዓመታት በላይ የሚቆይ እንደሆነ፣ መድን ድርጅትም በዚህ ጊዜ ውስጥ ለሚከሰቱ ሥጋቶች ዋስትና በመስጠት የሚሠራበት አካሔድ ወደፊት የሚኖሩ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ሲታከሉበት፣ በአሁኑ ወቅት የሚከፈለው የዋስትና ገንዘብ እንደሚገመተው የተጋነነ አይደለም ይላሉ፡፡ ባንኩ መድን ድርጅትን ቢያማክር ኖሮ ሌሎች የመድን አማራጮችንም መጠቀም ይቻል እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ግን ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ የሞርጌጅ ኢንሹራንስ ውሉን ማቋረጡን የሚገልጽ ደብዳቤ ለመድን ድርጅት መጻፉን አቶ ነፃነት አስታውሰዋል፡፡
የንግድ ባንክን አቋም በዚህ ዘገባ ለማካተት ሙከራ ቢደረግም ሊሳካ አልቻለም፡፡ የሞርጌጅ ኢንሹራንስ ውሉ እንዲቋረጥ ዋናው ምክንያት የሆነው የኮንስትራሽንና ቢዝነስ ባንክን ከመጠቅለሉ ጋር እንደሚገናኝ ይነገራል፡፡ የቀድሞው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ሠራተኞች እንዲህ ያለው የቤት ግዥ ብድር ክፍያ የተመለከተ ዋስትና ከንግድ ባንክ ጋር ከመቀላቀላቸው በፊት ገብተው ስለማያውቁ፣ ዋስትናውን እንደማይቀበሉት በማስታወቃቸው ባንኩ አሠራሩን ወጥ ለማድረግ በማሰብም ጭምር የመድን ሽፋኑን እንዳቋረጠ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ንግድ ባንክ የሞርጌጅ ኢንሹራንሱን ያነሳው አንድም ለሠራተኞቹ እንደ ጥቅማጠቅም እንዲታይለት ለማድረግ በማሰብ፣ በሌላ ጎኑ ደግሞ ከኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ የተረከባቸው ከ3,000 በላይ ሠራተኞች ከዚህ ቀደም በነበሩበት ባንክ የዚህ ዓይነት የመድን ሽፋን እንዲገቡ የማይገደዱ በመሆናቸው፣ አንድ ወጥ አሠራር ለመዘርጋት በማሰብ ዋስትናው እንዲቀር እንዳደረገም ይነገራል፡፡
መድን ድርጅት ለባንኩ ካቀረባቸው አማራጮች መካከል ነባሩን የሞርጌጅ ኢንሹራንስ ሙሉ ለሙሉ ከሚቀር፣ ሠራተኞቹ ጥቂት በመሆናቸው በድርድር የሚከፈለው የአረቦን መጠን ቅናሽ እንዲደረግበት ቢጠይቅ ሊስተካከል የሚችልባቸው አማራጮች እንደነበሩ አቶ ነፃነት አስታውሰዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለሠራተኞቹ ወደ ሕይወት መድን መቀየር የሚችልበት አሠራር እንዲፈጠር ማድረግ የሚቻልበት አማራጭ በመስጠቱ፣ ባንኩ በመድን ድርጅት የቀረቡለትን አማራጮች በመመልከት ለውይይት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ አቶ ነፃነት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡