Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከፌዴራል ወጪ ቁጠባ መመርያ በመነሳት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የራሱን እያዘጋጀ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፌዴራል መንግሥት በ2010 ዓ.ም. የተያዙ ዕቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ ለባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የተመደበው ገንዘብ በቁጠባ ጥቅም ላይ እንዲውል ባወጣው መመርያ መሠረት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የራሱን በጀት ለመቆጠብ የወጪ ቅነሳ መመርያ እያዘጋጀ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፎኢኖ ፎላ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ ለ2010 ዓ.ም. የያዘው በጀት ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ተግባራዊ እንዲሆን መመርያ እየተዘጋጀ ነው፡፡

‹‹የአስተዳደሩን ወጪ ለመቀነስ እየተዘጋጀ ያለው መመርያ በዚህ ሳምንት ይጠናቀቃል፤›› ሲሉ አቶ ፎኢኖ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ2010 በጀት ዓመት 35.8 ቢሊዮን ብር ያፀደቀ ሲሆን፣ ይህ በጀት ለካፒታልም ሆነ ለመደበኛ ፕሮግራሞች ወጪ በሚደረግበት ወቅት ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች እየተዘጋጀ ያለው መመርያ ይደነግጋል ተብሏል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ግንቦት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ተሰብስቦ የፌዴራል መንግሥት በጀት ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡

በዚህ መሠረት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የባለበጀት መሥሪያ ቤቶችን ወጪ ለመቀነስ ተግባራዊ መደረግ ያለባቸውን ጉዳዮች የሚያብራራ መመርያ አውጥቷል፡፡

በሐምሌ 2009 ዓ.ም. የወጣው መመርያ በካፒታልና በመደበኛ በጀት አወጣጥ ላይ መቅረት ያለባቸውን ወጪዎች ዘርዝሯል፡፡

መመርያውም በበጀት ላይ ከፀደቀው ፕሮጀክት ውጪ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ማካሄድ እንደማይቻልም ይገልጻል፡፡

በመደበኛ ወጪዎች ላይ መመርያው 19 ዓብይ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አስፍሯል፡፡ ከእነዚህ ውሳኔዎች መካከል የተሽከርካሪ ጥገና አንዱ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከትልልቅ የተሽከርካሪ አስመጪ ኩባንያዎች ጋር በቀጥታ ስምምነት ጥገና ሲደረግ ነበር፡፡ ከዚህ በኃላ ግን በጨረታ መከናወን አለበት፡፡ መስተንግዶን በሚመለከትም የሚካሄዱ ስብሰባዎች ሻይ፣ ቡናና ውኃ ከመሳሰሉት ወጪዎች በስተቀር ሌላ ግብዣ ማድረግ ተከልክሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከባለድርሻ አካላት ጋር ለሚካሄዱ ስብሰባዎችና ክብረ በዓላት ለተሳታፊዎች ቦርሳ፣ ቲሸርት፣ ባርኔጣ፣ ሻርፕና የተለያዩ የአገር ባህል ልብሶችን መግዛት ተከልክሏል፡፡

‹‹በተቻለ መጠን ስብሰባዎችን በየተቋማቱ መሰብሰቢያ አዳራሾች በማካሄድ ለሆቴሎች የሚወጣውን ወጪ ማስቀረት ያስፈልጋል፤›› ሲል መመርያው አስታውቋል፡፡

የውጭ አገር ጉዞን በተመለከተ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሲፈቅድ ብቻ የሚካሄድ መሆኑም ተገልጿል፡፡ መንግሥታዊ ተቋማት ከግል ኩባንያዎች አዲስ ቢሮ መከራየት አይችሉም፡፡ ተከራይተው ከፍተኛ ወጪ እየከፈሉ ያሉ መሥሪያ ቤቶችም ወጪያቸውን የሚቀንስበትን መንገድ በድጋሚ እንዲመለከቱ መመርያው አዟል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተመሥርቶ ከራሱ ነባራዊ ሁኔታዎች በመነሳት መመርያውን እያዘጋጀ መሆኑ ታውቋል፡፡

መረጃዎች እንደጠቆሙት ከእነዚህ ጉዳዮች በተጨማሪም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች የሚያካሂዷቸው ስብሰባዎች እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ እንዲካሄዱ መመርያው አስገዳጅ ድንጋጌ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች