በሔኖክ ያሬድና በብርሃኑ ፈቃደ
በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ጥናትና ምርምር መስክ ቁልፍ ከሆኑ ምሁራንና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች አንዱ፣ በኢኮኖሚክስና በማይክሮ ፋይናንስ ምርምርና ልማት ዘርፍም በላቀ ደረጃ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል ዶ/ር ወልዳይ አምሐ ይጠቀሳሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በቀድሞው የሐዋሳ ግብርና ኮሌጅ ለዓመታት በማስተማር ከፍተኛ ከበሬታንም አትርፈዋል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የምግብ ምርትና የምግብ እህል ንግድ (ሜዳክ) ፕሮጀክት ልዩ ፕሮግራሙን በኢትዮጵያ ሲዘረጋ፣ ለግብርና ሚኒስቴር አማካሪ ሆነውም ሠርተዋል፡፡
በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የብድርና ቁጠባ ሥርዓታቸውን ማሻሻል እንዲችሉ፣ በምክራቸው ዓይነተኛ ሚና መጫወታቸው ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ማኅበርን (አብቁተማ) ከ1990 ዓ.ም. ከመመሥረት ጀምሮ በሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተርነት እስከ ሕልፈታቸው ጊዜ ድረስ ሲመሩ የቆዩት ዶ/ር ወልዳይ፣ የኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የፋይናንስ አገልግሎት የሥልጠናና ምርምር ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆንም የሙያ ትሩፋታቸውን አቋድሰዋል፡፡
በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ዩኤስኤይአይዲ) በ1980ዎቹ መጨረሻ ከሚችጋን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ላዘጋጀው ፕሮጀክት ከፍተኛ ተመራማሪ ሆነውም ሠርተዋል፡፡
በአኅጉራዊው የአፍሪካ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ትስስር መሥራችነት ከመሳተፋቸውም ባሻገር፣ ለሦስት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበርንም በምክትል ፕሬዚዳንትነትና በፕሬዚዳንትነት ለአሥር ዓመታት መርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ አባልም ነበሩ፡፡ በአካዴሚው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ልማትና ዕቅድ የማስተርስ ዲግሪ፣ ከጀርመን የምዕራብ በርሊን ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ በእርሻ ኢኮኖሚክስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በ1987 ዓ.ም. ያገኙት ዶ/ር ወልዳይ፣ በዚያው ዓመት በሐዋሳ እርሻ ኮሌጅ ለማስተማር ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቸውን በአላማጣ ከተማ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወልድያ ከተማ ከተከታተሉ በኋላ፣ በ1968 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በ1972 ዓ.ም. በኢኮኖሚክስ ትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በመሥራት በተማሩት ሙያ ለማስተማር የሐዋሳ እርሻ ኮሌጅን ተቀላቅለዋል፡፡
በ1988 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ክፍል ትምህርት በረዳት ፕሮፌሰርነት በማስተማር ለዓመታት ዘልቀዋል፡፡ በሦስት አሠርታት ውስጥ በጥናትና ምርምር በግልና በቡድን በርካታ ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡
ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተባባሪ ፕሮፌሰርነት፣ ‹‹ባገኘው ጊዜ ሁሉ የሚያገለግል አጋዥ ምሁር›› በመሆን የማስተማርና የማማከር አገልግሎትን በማበርከት ላይ ነበሩ፡፡ በዕለት ተዕለት ሥራቸው ከሚያከናውኗቸው ምሁራዊ ተግባራት በተጨማሪም በሥራቸው ወቅት የሚያደርጓቸውን ጥናቶችና የምርምር ውጤቶችን በመፃፍና በማሳተም በአገር ውስጥና በውጭ አገር ጆርናሎች ከ15 ጽሑፎች በላይ ያሳተሙ ሲሆን፣ ከ50 በላይ አጫጭር መጣጥፍና አራት መጻሕፍት ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በትብብር ማሳተም የቻሉ ምሁር ስለመሆናቸው በተነበበው ሕይወት ታሪካቸው ተመልክቷል፡፡
ዜና ዕረፍታቸው ከመሰማቱ ሁለት ሳምንት አስቀድሞ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በተዘጋጀ መድረክ፣ ‹‹የፋይናንስ አቅርቦት ሁኔታ ተግዳሮትና ሒደት ለአነስተኛና መካከለኛ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት›› በሚል ርዕስ ያቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍም ተጠቃሽ ነው፡፡ በማኅበራዊ አገልግሎትም የኢትዮጵያ ግብርና ኢኮኖሚክስ ማኅበር አባል፣ የኢትዮጵያ የግብርና ኢኮኖሚ ጆርናል ተባባሪ አዘጋጅ (1997-1999) የማይክሮ ፋይናንስ ዴቬሎፕመንት ሪቪው ቡለቲን አዘጋጅ ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊና የኢኮኖሚክስ ክፍለ ትምህርት የድኅረ ምረቃ ፕሮግራም የውጭ ፈታኝም ሆነው አገልግለዋል፡፡
ዶ/ር ወልዳይ ጳጉሜን 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ከሐዋሳ ከተማ ወደ አዲስ አበባ በግል ተሽከርካሪያቸው በመጓዝ ላይ ሳሉ ከሻሸመኔ ወደ ሞጆ ይጓዝ ከነበረ ተሳቢ ኤሮትራክ ጋር በመጋጨታቸው ሳቢያ፣ በአደጋው እሳቸውን ጨምሮ የሌሎች ሁለት ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ ተሰምቷል። ከአደጋው በኋላ የከባድ መኪናው ሾፌር መሰወሩን፣ ፖሊስ ሹፌሩን ለማግኘት ክትትል እያደረገ እንደሚገኝና የአደጋው መንስዔም በመጣራት ላይ መሆኑን የምሥራቅ ሸዋ ዞን የሉሜ ወረዳ ፖሊስ መምርያ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ወልዳይ አምሐ ከአባታቸው ከአለቃ አምሐ ደስታና ከእናታቸው ከወ/ሮ ተመንዬን ተፈሪ የካቲት 5 ቀን 1949 ዓ.ም. በቀድሞው አጠራር በትግራይ ጠቅላይ ግዛት፣ በሐውዜን ወረዳ፣ በዓዲ በለስ ቀበሌ እንደተወለዱ የሕይወት ታሪካቸው ይገልጻል፡፡
ሥርዓተ ቀብራቸው በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቅዳሜ ጳጉሜን 4 ቀን 2009 ዓ.ም. የተፈጸመው ዶ/ር ወልዳይ አምሐ፣ ባለትዳርና የሦስት ወንዶች ልጆች አባት ነበሩ፡፡