Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ይድረስ ለሪፖርተርለከፍታ ዘመን የሚሆን የአስተሳሰብ ልዕልና ይኑረን

  ለከፍታ ዘመን የሚሆን የአስተሳሰብ ልዕልና ይኑረን

  ቀን:

  አዲሱ ነገር ባሮጌው ትናንት ውስጥ ነው፡፡ ዛሬ የተፀነሰውን ዘረኝነት ደካማ የሥራ ባህል ጭፍን አክራሪነት፣ በሥልጣን መባለግ በረብ የለሽ ልማድ መተብተብ፣ ከድንቁርና የማይተናነሰውን የስሜታዊነት ጽንስ ሳናመክን የነገን ብርሃን በተስፋ መጠበቅ ከምኞት ያለፈ ፋይዳ የለውም ፡፡

  ምሁራኖቻችን የጎጠኝነት ሰርጥ ውስጥ ሰጥመው እኛነታችንን አንሻፈው፣ አሊያም አንሸዋረው፣ አብሮነታችንን የኋሊት ከማንደርደር እስካልታቀቡ ድረስ፣ ቁርሾን እንደባልቴት እየተረኩ የአፍላ ልጆችን አስተሳሰብ በመመረዝ  ትውልድን ማክሸፍ፤ ቂምና በደል እያወረሱ ከጨለማ ባሻገር አሻግረን እያየን ብርሃንን ለማየት መጠበቅ ቅዠት ነው፡፡ ያውም የቁም ቅዠት፡፡

  ሐጎስ ገመቹና ደስታ በጎጥ መጎራበጣቸውን ትተው ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያችን እያሉ በአንድ ልብ ካልዘመሩ በቀር፣ የነገዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ከፍታ›› የለም፡፡ መሪዎቻችን እንደመሪ ካልቀደሙን፣ የሐሳብ ልዩነታችንን በሐሳብ ሙግት፣ ችግራችንን በውይይት፣ ክፍተቶቻችንን በንግግር መፍታት እስካልቻልን ድረስ፣ ነጌያችን አይበራም፡፡ ውይይት ባህሉ ባልሆነበት አገርና ሕዝብ ውስጥ እንደምንድን ነው ነገው ብሩህ የሚሆነው?

   ባለሀብቶቻችን እኛነትን አንቅረው ተፍተው በእኔነት ሰንኮፍ ውስጥ ተዘፍቀው፣ ትልማቸውን ያልተገባ ትርፍና ትርፍ ማጋበስ ብቻ አድርገው የሕዝብን ደም መምጠጥ እስካላቆሙ ድረስ ብርሃን አይጣም፡፡

  እኛ ከምንደግፈው የፖለቲካ ፓርቲ ውጪ መደገፍ ጭፍንነት ነው፤ እኛ ከምንከተለው ሃይማኖት ውጭ መከተል ኃጢዓት ነው ብሎ ማሰብ እስካልቆመ ድረስ፤ የሚነደፉት ፖሊሲዎች በእኛ ልኬት፣ በእኛ መጠን እስካልተሠሩ ድረስ መንግሥትን መደገፍ ካድሬነት፣ መቃወምም አሸባሪነት ተደርጎ የሚፈረጅበት የጅምላ አስተሳሰብ እስካለቆመ ድረስ ብርሃን አያበራልንም፡፡ ለምንጠላውም ሆነ ለምንደግፈው ነገር በስሜታዊነት መዋኘት እስካልቆመ ድረስ  ከፍታ ሱሚ ነው፡፡

  መሠረተ ልማቱን ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ለመዋል የይድረስ ለይድረስ ገንብቶ ማመስመረቁ፣  ባለሙያው አላግባብ በሚመዘብረው ጥቅማ ጥቅም ማነፍነፍ ላይ ተጠምዶ እየገነባ ሥራ በጀመረ ማግሥት የሚፈረካከስና ሬንጅ የጠማው አስፋልት መሥራት፣ በጥራት ጉድለት የዘመመ ኮንዶሚንየም በመገንባት ሠሪም አሠሪም በሰነፉበት አገር ውስጥ ብርሃን ብቻ ሳይሆን የብርሃን ጭላንጭል አይኖርም፡፡

  ለአገራችን  ያለን ፍቅር ሥጋ ለብሶ በመልካም አድራጎት ካልተገለጠ በቀር፣ በተሰማራንበት የሥራ መስክ ኃላፊነታችን እስካልተወጣን ድረስ ከገባንበት አዘቅት አንላቀቅም፡፡

  የትናንት ስተት ነገ እንዳይደገም የሚገስፀን፣ የሚያደራድረን የአገር ሽማግሌ እስክሌለን ድረስ፣ ከዘመን ዘመን፣ ከመንግሥት መንግሥት አንዱ የጀመረውን እኛ አፍርሰን እንደገና የመገንባት አባዜያችን እስካልተወን  ድረስ፣  ነገ  ከፍታ ሳይሆን ቁልቁለት ነው የሚጠብቀን፡፡

  በእናውቃለን ተወድረን፣ በይሉንታ ተሰድረን መቆለጳጰስና በትናንት አጉል ሙገሳና ይሉኝታ መታጠርን ካላቆምን፣ የሐሳብ ዕድገት ማምጣት የማይጨበጥ ህልም ነው፡፡ የሐሳብ ዕድገት የከፍታ ሁሉ መሠረት ነው፡፡ በአመክንዮ ላይ ተመርኩዘን፣ ሐሳብን በሐሳብ ካልተቸን፣ ተቺም ተተቺም ሳይሳቀቁ በሚያነሱት የሐሳብ ውጣውረድ ካልተነጋገሩ በቀር ብርሃን የሚባል ነገር የለም፡፡  

  ኪነ ጥበባችን የመንደር ነውርን እንደቁም ነገር ማስተጋባቱን በመተውና ከእርም በመራቅ፣ ጠንካራ የሥራ ባህል፣ ሠላም፣ አንድነትና ፍቅርን እስካላዜመልን ድረስ፤ የሃይማኖት አባቶች ስለ ፍቅር፣ ስለአንድነት፣ ስለወንድማማችነት፣ ስለታማኝነት በተግባር ኖረው እስካልሰበኩን  ድረስ፤ መጻሕፍት ላይ ቀረጥ እየጣሉ ዕውቀት እንዳይዛመት በማድረግ መጻሕፍት ቤቶች ወደ ሌላ የችርቻሮ ዘርፍ መገልበጣቸው  እስካልቆመ ድረስ የከፍታ ዘመን አይታሰብም፡፡

  ምንም እንኳን በጥንቱ ዘመን በዓለም ታሪክ ግንባር ቀደም መሆናችን ዛሬ ኋላ ቀር ከመሆን ባያድነንም፣ ለዛሬያችን እውነተኛ ለውጥ ከሻትን፣ ክፍተቶቻችን ላይ ካልሠራን፣ አዲስ ዓመት ማለት የቁጥር መቀያየር ካልሆነ በቀር የሚያመጣው አዲስ ለውጥና ኃይል አይኖርም፡፡ እንዲያውም ካልተለወጥን በድህነትና በስንፍና የኖርንበት ዘመን  በዘመን እየተተካ የኋላ ቀርነታችንን ጥልቀት የትየለሌ ከማድረግ ውጭ ሌላ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ሆኖ  መጭው  ግዜ  ብሩህ  ይሆንልን  ዘንድ  የሁልጊዜ ምኞቴ ነው !

  (አድሃኖም ምትኩ፣ ከአዲስ አበባ)  

  ***

  ብሌስ አግሪ ፉድስን የጠቀሱት ዘገባዎች ይታረሙ

  ድርጅታችን ብሌስ አግሪ ፉድስ ለቦራቶሪ ሰርቪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በISO 17025:2005 አክሬዲትድ ላብራቶሪ ሲሆን፣ ለተለያዩ የምግብ ዓይነቶች ዓለም አቀፍ ጥራቱን የጠበቀ የኬሚስትሪና የማይክሮባዮሎጂ ፍተሻ አገልግሎት የሚሰጥ የግል ተቋም ነው፡፡

  አገራችን ወደ አውሮፓ ኅብረት በምትልካቸው የተለያዩ የምግብና የግብርና ምርቶች ላይ ድርጅታችን ብሌስ አግሪ ፉድ ላቦራቶሪ ሰርቪስ ኅብረቱ የሚጠይቀውን የአፍላቶክሲን ደረጃ እያረጋገጥን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ሰርቲፊኬት በመስጠት የአገራችን ምርቶች በኅብረቱ ተቀባይነት እንዲያገኙ የበከሉላችንን ድጋፍ በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡

  ሆኖም የሪፖርተር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በነሐሴ 07 ቀን 2009 ዓ.ም. በቅፅ 22 ቁጥር 1804 በአማርኛው የቢዝነስና ኢኮኖሚ ዓምድ ሥር ‹‹የአውሮፓ ኅብረት ዝቅተኛ የአፍላቶክሲን ደረጃ ያሟሉ በርበሬ ላኪዎች ከገበያ ውጪ የመሆን ሥጋት ገብቷቸዋል››፤ እንዲሁም በእንግሊዝኛው ዕትም vol. XX| No. 1092 page 8 “Spice exporters fear losing EU markets›› በሚሉ ርዕሶች ለንባብ የበቁት ዘገባዎች የተዋቀሩበትና የቀረቡበት አግባብ ድርጅታችን እየሰጠ ካለው አገልግሎትና፣ የወጪ ንግዱን ከመደገፍ አንፃር እሴት የማይጨምር በአስፈጻሚ አካላት ተቀባይነት የሌለው ተደርጎ የቀረበ እንድምታ ያለው መሆኑን ተገንዝበናል፡፡

  በዘገባው ላይ የተጠቀሱት ላኪ ምርታቸውን ወደ ውጭ አገር ለመላክ ምርቴ የተቀባይ አገር የሚጠይቀውን ማስረጃ የሚሰጠኝ አካል አጣሁ ብሎ ላቀረቡት ቅሬታ፤

  1. ላኪው ድርጅት በገባው የኮንትራት ውል መሠረት ምርቱን ወደ ውጭ አገር ለመላክ ማሟላት ያለበትን ፎርማሊቲዎች ማሟላት አለማሟላቱ ሳይረጋገጥ፤
  2. የሚፈልገው ፈቃድ ምን እንደሆነ፤ ከየተኛው አስፈጻሚ ተቋም ሲሰጥ እንደነበረና ለምን ያንን ማግኘት እንዳልተቻለ ሳይረጋገጥ፤
  3. ቅሬታ ያቀረበው ድርጅት ምርቱን ወደሚልክበት አገር ሌሎች የአገራችን ላኪዎች ምንም ዓይነት ችግር ሳይገጥማቸው ምርቶቻቸውን እየላኩ በመገበያየት ላይ መሆናቸውን ሚዛናዊ በሆነ አቀራረብ መረጃ ሳይጠይቁ፤
  4. በዘገባው ላይ የተጠቀሰው ድርጅታችን ብሌስ አግሪ ፉድ ላቦራቶሪ ሰርቪስ በጉዳዩ ላይ ያለው አስተያየት ምን እንደሆነ መረጃ ሳትጠይቁ ድርጅታችን እየሰጠ ያለውን አገልግሎት በሚያሳንስና ገበያውን በሚጎዳ አኳኋን የቀረበው ዘገባ ትክክል አለመሆኑን እየገለጽን ብሌስ ከምግብ አምራች ድርጅቶችና ከሱፐር ማርኬቶች ጋር ለገበያ በሚቀርቡና ኅብረተሰቡ በሚመገባቸው ምርቶች ላይ አፍላቶክሲን እያስከተለ ያለውን የጤና ችግር አስመልክቶ የምርቶችን ጥራት የማረጋገጠ ሥራ ላይ እያከናወነ ባለው መጠነ ሰፊ የማርኬቲንግ ግንዛቤ የመፍጠር እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ ከማስገባት በሁለቱም ጋዜጣዎች ላይ የእርምት ማስተካከያ እንድታወጡ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

   (ሕሊና በለጠ ዋና ሥራአስኪያጅ፣ ብሌስ አግሪ ፉድ ላብራቶሪ ሰርቪስ)

  ከአዘጋጁ፡-

  በብሌስ አግሪ ፉድ ላቦራቶሪ ሰርቪስ በኩል የቀረበው ቅሬታ በመሠረቱ ከቀረቡት ዘገባዎች ውጭ ሆኖው የሚታዩ ናቸው፡፡ ድርጅቱ ስሙ የተጠቀሰው የላቦራቶሪ አገልግሎት በመስጠቱ ብቻ ነው፡፡ የግድ መጠየቅ ነበረብኝ የሚልበት አግባብ ከተስነጋዱት ዘገባዎች አኳያ ሲታይ ሚዛን አያነሳም፡፡ በዚያም ላይ ያቀረበው ቅሬታ ዘገባውን በራሱ በድርጅቱ ዕይታ በመተርጎምና ያልተገባ አቅጣጫ በመስጠት ያቀረበው ቅሬታ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በጉዳዩ ላይ ዳግም በቀረበ ዘገባ፣ የፌደራሉ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ኃላፊ ወደ አውሮፓ በሚላኩ አፍላቶክሲን ይዘት ያለባቸው ምርቶች ዙሪያ ሲደረግ የቆየውንና በቀደመው ዘገባም ችግር ገጥሞናል ያሉ ላኪዎች የተስተናገዱበትን አግባብ አቅርበን ሳለ፣ ብሌስ ላቦራቶሪ የራሱን፣ በይሆናል ላይ የተመረኮዘ ሐሳብና ተችት ከማቅረብ አልፎ ይታረሙልኝ ማለቱ ተቀባይነት ባይኖረውም፣ ሪፖርተር የማንንም ሐሳብ የማስተናገድ አቋም ያለው ነፃ የመገናኛ አውታር በመሆኑም ጭምር ይህንኑ የድርጅቱን ሐሳብ እንዲህ አስተናግዷል፡፡ 

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...