Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

  የሳምንቱ ገጠመኝ

  ቀን:

  በአንድ ቀን ውስጥ አንድ ሰው ስንት ዓይነት ነገሮች ያጋጥሙታል? እኔ ግን በአንድ ቀን ውስጥ ከሦስት ጉዳዮች ጋር ተገጣጥሜያለሁ፡፡ ሁሉም ጉዳዮች እኔን በቀጥታ ባይመለከቱኝም፣ በቅርብ የማውቃቸው ሰዎችን ያጋጠሙ በመሆናቸው ችላ ብዬ ማለፍ አልፈለግኩም፡፡ ለማንኛውም ለጥንቃቄ ይረዳን ዘንድ ለአንባቢያን እንዲህ በየተራ አቅርቤያቸዋለሁ፡፡

  የመጀመሪያው ባለ ገጠመኝ የሥራ ባልደረባዬ ናት፡፡ ከጓደኛዋ ጋር ለምሣ ተቀጣጥረው ስለነበር እሷ ቀድማ ትደርሳለች፡፡ የሬስቶራንቱ ደንበኞች በርካታ ስለሆኑ፣ ሦስት ወንበሮች ያሉት ጠረጴዛ ትመርጥና የሚበሉትን በማዘዝ በመድረስ ላይ ያለችዋን ጓደኛዋን ስትጠባበቅ ዓይኗ አንድ ነገር ላይ ያርፋል፡፡ ሦስት ሴቶች ጨዋታቸው ደርቶ ምሣቸውን ሲመገቡ አንድ ባዶ መቀመጫ ላይ ቦርሳዎቻቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ሴቶቹ ምግባቸውና ወሬያቸው ላይ ስላተኮሩ፣ አጠገባቸው ሌላ ጠረጴዛ ከበው የተቀመጡ ሁለት ወጣት ሴቶች በያዙት ጋዜጣ እጃቸውን ሸፍነው የሴቶቹን ቦርሳዎች ሲቦጠብጡ ጓደኛዬ በሰያፍ ታያለች፡፡

  ዓይኗን በመጠራጠር ተንጠራርታ እንደገና ስታይ ሦስቱም ቦርሳዎች አፋቸው ተከፍቶ በፈጣን እጆች ሞባይሎች፣ የገንዘብ መያዣ ቦርሳዎችና ሌሎች ጠቃሚ ነገሮች እየተመዘበሩ ፌስታል ውስጥ ይከተታሉ፡፡ በዚህ መሀል የጓደኛዬ ጓደኛ ትደርሳለች፡፡ እነዚያ ሁለት ሌቦች ቀስ እያሉ ቦርሳዎቹን ዘጋግተው ከጨረሱ በኋላ ፌስታላቸው ውስጥ የጠቀጠቁትን የሴቶቹን ንብረትና ገንዘብ ይዘው ከመሰወራቸው በፊት፣ ለጓደኛዋ ነግራት ተንደርድረው ሄደው ሴቶቹን አንቀው ይይዛሉ፡፡ ጂም አዘውታሪ የሆነችው የሥራ ባልደረባዬ ጠንከር ያለች በመሆኗ ሌቦቹን አንቃ ስትይዝ ጓደኛዋ ፌስታሉን በቁጥጥር ሥር ታውላለች፡፡ የተዘረፉት ሴቶች ጉዳዩ ተነግሯቸው እየተርበተበቱ ቦርሳዎቻቸውን ሲፈትሹ ኦና መቅረታቸውን ያያሉ፡፡ ፌስታሉ ውስጥ የተጠቀጠቀው ንብረትና ገንዘብ ጠረጴዛ ላይ ሲዘረገፍ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ጉድ ይላሉ፡፡ ፖሊስ እስኪመጣ ድረስም ሌቦቹን የሬስቶራንቱ ጥበቃዎች ይረከቧቸዋል፡፡ ሊዘረፉ የነበሩት ሴቶች ለሥራ ባልደረባዬና ለጓደኛዋ ምሥጋና ሲያዥጎደጉዱና ምሣ ካልጋበዝን ብለው ሲያስቸግሩ፣ የሥራ ባልደረባዬን የገረማት ሁለት በ40ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ግን፣ ‹‹ድንቄም! ሀብታም ለተሰረቀ የሌላው አጎብጓቢ መሆን ነው የሚገርመው . . . ›› እያሉ ሲሳለቁ በጣም እንዳሳዘናት ነገረችኝ፡፡ ሌብነትን ማበረታታት ምን የሚሉት በሽታ ይሆን?

  ሁለተኛው አጋጣሚ የተፈጠረበት ጎረቤቴ ነው፡፡ ጎረቤቴ ታክሲ ቢጠብቅ ቢጠብቅ ማግኘት ባለመቻሉ የሞላ የከተማ አውቶቡስ ውስጥ ይገባል፡፡ በተሳፋሪዎች ከአፍ እስከ ገደፉ የሞላው አውቶቡስ ውስጥ ኪስ አውላቂዎችም ተሰማርተው ኖሮ ከመቅጽበት የኪስ ቦርሳው ተመንትፏል፡፡ ቦርሳው ውስጥ ደግሞ ሦስት ሺሕ ብር አለ፡፡ ለቲኬት ቆሯጩዋ መሰረቁን አስታውቆ በር እንዳትከፍት ይነግራታል፡፡ ቲኬት ቆሯጩዋ ለሾፌሩ አስታውቃ ጉዞው ሲገታ አንድ ልጅ እግር ጎረቤቴን በዓይኑ ጠቀስ ያደርገዋል፡፡ ጎረቤቴ መልሶ በምልክት ሲጠይቀው ልጁ ወንበሩ ሥር ይጠቁመዋል፡፡ ዓይኑን ወደዚያ ሲያዞር አስቤዛ የተሞላበት ፕላስቲክ ዘንቢል ያያል፡፡ ጎረቤቴ ዝቅ ብሎ ገለጥ ገለጥ ሲያደርግ ቦርሳውን ተወሽቆ ያገኘዋል፡፡ ቦርሳውን ከፍቶ ገንዘቡን ከቆጠረ በኋላ ለሾፌሩ መገኘቱ ተነግሮት ጉዞው ይቀጥላል፡፡

  ጎረቤቴ መውረጃው ደርሶ ልጅ እግሩን በምልክት አመስግኖ ሲወርድ ሌሎች ሦስት ሰዎችም አብረውት ይወርዳሉ፡፡ አንደኛው ያለምንም ኃፍረት፣ ‹‹ኪስህ ውስጥ ገብቶ ሲሰርቅህ አይቼ ነበር፡፡ ነገር ግን ፈርቼ ዝም አልኩ . . .›› እያለ ሲያወራ የተቀሩት ሁለቱም ማየታቸውን አረጋገጡለት፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ሌቦቹ ብዛት ስለነበራቸው ፈርተው ነው፡፡ አንድ አውቶቡስ ሙሉ ተሳፋሪ እፍኝ የማይሞሉ ሌቦችን ፈርቶ ሲዘረፍ ይውላል፡፡ ያ ታዳጊ ባይኖር ኖሮ ያንን ገንዘብ ከዘንቢል ውስጥ ማን ጠርጥሮ ያወጣ ነበር? ሌቦቹ የሰረቁት ገንዘብ በአጋጣሚ ቢገኝ ኖሮ የዘንቢሉ ባለቤት የሆኑት አቅመ ደካማ ሴት ሌባ ሊባሉ ነበር? ‹‹አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ›› የሚባለው እንዲህ ዓይነቱ ሲያጋጥም ነው፡፡

  ሦስተኛው ገጠመኝ የሚመለከተው ዘመዴን ነው፡፡ ይህ ዘመዴ ሕመምተኛ እህቱን ሊያሳክም ሆስፒታል ይሄዳል፡፡ በስንት መከራ ወረፋ ደርሶት ሐኪሙ ዘንድ ይዟት ገብቶ ምርመራ ይደረግላታል፡፡ የላቦራቶሪ ምርመራ ታዞላት አስፈላጊውን ሁሉ አከናውና መልሱን ይዘው ሐኪሙ ዘንድ ይቀርባሉ፡፡ ሐኪሙ በምርመራ ውጤቱ መሠረት ለታካሚዋ የተለያዩ መድኃኒቶች ያዛል፡፡ እህቱን በድጋፍ ይዞ ወዲያ ወዲህ ያለበት የደከመው ዘመዴ፣ ሆስፒታሉ ውስጥ የሚገኝ ፋርማሲ ሄዶ ለመግዛት ቢፈልግ አልተቻለውም፡፡ ወይ እሱ እሷን ደግፎ መቀመጥ አለበት፡፡ አሊያም ሌላ ሰው ደግፎለት እሱ መድኃኒቱን መግዛት አለበት፡፡ ግራ ገብቶት እያለ አንዲት ወጣት ቀረብ ብላ፣ ‹‹ምን ልርዳህ?›› ትለዋለች፡፡ ችግሩን ይነግራታል፡፡

  ወጣቷ በፍፁም ትህትና መድኃኒቱን እንደምትገዛለት ትነግረዋለች፡፡ የሐኪሙን ማዘዣ ሲሰጣት፣ ‹‹መጀመሪያ ዋጋውን ጠይቄ ልምጣና ትሰጠኛለህ፤›› ብላ በፍጥነት ወደ ፋርማሲ ትሄዳለች፡፡ አሥር ደቂቃዎች ካለፉ በኋላ ትመጣና በአጠቃላይ 1,400 ብር እንደሚያስፈልግ ትነግረዋለች፡፡ ብዛት ያለው መርፌ፣ የተለያዩ እንክብሎችና ፈሳሽ መድኃኒቶች በመታዘዛቸው ሳያቅማማ ገንዘቡን ይሰጣታል፡፡ ቢጠብቅ ቢጠብቅ ወጣቷ የውኃ ሽታ ሆነች፡፡ ካሁን ካሁን ትመጣለች እያለ ከአንድ ሰዓት በላይ ቢጠብቅ እሷ የለችም፡፡ አንዲት የፅዳት ሠራተኛ እህቱን እንዲጠብቁለት ለምኖ ፋርማሲ ሲሄድ በሩ ዝግ ነው፡፡ አሁን በትክክል ገባው፡፡ ያቺ ትህትና የተላበሰች ውብ ወጣት ሕይወት አድን የሆነውን የመድኃኒት መግዣ ገንዘብ ይዛ ጠፍታለች፡፡ ሰብዓዊነት በአረመኔነት ተተክቶ ሲያገኘው እንደዚያን ቀን አዝኖ እንደማያውቅ ነገረኝ፡፡

  (አህመድ ሸሪፍ፣ ከጎተራ)

   

   

   

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...