Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  በሕግ አምላክፕሬዚዳንቱን ርዕሰ ብሔር ያደረጉ ጎዶሎ ሕግጋት

  ፕሬዚዳንቱን ርዕሰ ብሔር ያደረጉ ጎዶሎ ሕግጋት

  ቀን:

  በውብሸት ሙላት

  ርዕሰ ብሔር (Head of State) የአገር፣ የሕዝብ ወኪል ነው፡፡ በአንዳንድ አገሮች ርዕሰ ብሔሩ፣ ርዕሰ መስተዳድርም (Head of Government) ሊሆን ይችላል፡፡ በሌሎች አገሮች ደግሞ ርዕሰ ብሔሩና ርዕሰ መስተዳድሩ የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንድ በሚሆኑበት ጊዜ ርዕሰ ብሔሩ አገሪቱንም መንግሥትንም ይወክላል፡፡

  ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓትን ወይም ንጉሣዊ አስተዳደር በሚከተሉ አገሮች ፕሬዚዳንቱ/ንጉሡ ርዕሰ ብሔርም ርዕሰ መንግሥትም ነው፡፡ የፓርላማ ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች ደግሞ ርዕሰ ብሔሩና መስተዳድሩ የተለያዩ ናቸው፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ የሚሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ መንግሥትን ብቻ ይወክላል፤ ይመራል፡፡ አመጣጡም አብላጫ ድምጽ በማግኘት ወይም የጥምር መንግሥት በመመሥረት የተወሰኑ የሕዝቡ ክፍል የመረጠው ፓርቲ ወኪል በመሆን ነው፡፡

  •  

  የአሁኑ ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ መዋል ሲጀምር ግን ሁለቱ ተለያይተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ርዕሰ ብሔር ሲሆን ርዕሰ መስተዳድሩ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ በተግባር ላይ የዋለውን የፕሬዚዳንትነት አሠራር የሚመለከት ነው፡፡ ማጠንጠኛውም ፕሬዚዳንቱ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ስለሆነ ከአመራረጡ በመጀመር፣ ያሉትን ሥልጣንና ተግባር በመፈተሽ ብዙዎቹ ድንጋጌዎች በጅምር የቀሩ ስለሆነ እነሱን በማሳየት ፕሬዚዳንቱን እንደ ጽንሰ ሐሳቡ እውነተኛ ርዕሰ ብሔር የሚሆንበትን ብሎም የአገሪቱ የጅምላነቷ (የአንድነቷ) ተምሳሌትነቱ እንዲጨምር ያስችላል የሚለውን ሐሳብ መሰንዘራ ነው፡፡

  ርዕሰ ብሔሩ እንደ አንደኛ ዜጋ ይቆጠራል፡፡ የአገሪቱም የልዑላዊነቷ ተወካይ ነው፡፡ አገር ሲባል ሕዝቡ፣ ግዛቷ በአጠቃላይ (መሬቱም አየሩም)፣ መንግሥት እንዲሁም በሌሎች አገሮች ዘንድ እንደ አገር መቆጠሯ ተደማምረው ነው፡፡ ርዕሰ ብሔሩ የእነዚህ ሁሉ በአንድነት ወኪል ነው፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ (ጠቅላይ ሚኒስትሩ) ግን ከእነዚህ ከአራቱ የአገር አላባውያን የአንደኛው ወኪልም መሪም ነው፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያም ፕሬዚዳንቱ ‘ርዕሰ ብሔር’ ነው ሲባል የኢትዮጵያ ራስ ነው እንደማለት ነው፡፡

  ሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠው ‘ርዕሰ ብሔር’ የሚለው ሀረግ ላይ ያለው ብሔር ወኪልነቱ አንቀጽ 39 ላይ የተገለጸውን ትርጉም አይዝም፡፡ ብሔራዊ ባንክ፣ብሔራዊ መዝሙር፣ ብሔራዊ ቴአትር እንደሚባለው የሚያመለከተው አገሪቱን በጅምላነቷ ነው፡፡ ስለሆነም ‘ብሔር’ የሚለው የአማርኛውን ‘አገር’ የሚለውን ለመተካት ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን በታሪክ አገር ለመመሥረት አንድ ብሔር የመሆንን ትረካ የተከተለ ነው፡፡ እንግሊዝኛው “Head of State” ነው፡፡ ርዕሰ ብሔር ሲባል ‘ርዕሰ አገር’ ሲሆን፣ ‘ብሔር’ የሚለው ቃልም ከጥንትም ጀምሮ አገር ስለሆነ ‘ርዕሰ ብሔር’ ርዕሰ አገር ነው ማለት ይቻላል፡፡

  ሕገ መንግሥቱ ፕሬዚዳንቱ የአገሪቱ ራስ (ርዕሰ ብሔር) ነው ከማለት ውጭ ትርጓሜ አልሰጠም፡፡ በሌላ አዋጅም ላይ የተሰጠ ብያኔ የለም፡፡ ብያኔ ካልተሰጠው ትርጉሙን ማግኘት የሚቻለው ለፕሬዚዳንቱ ከተሰጠው ሥልጣንና ተግባር ስለሚሆን ይኼንኑ እንመለከታለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ርዕሰ ብሔሩ የሚሾምበትና የሚወርድበት ሁኔታ መመልከት ለርዕሰ ብሔሩ አገራዊ ወኪልነት የተሰጠውን ትኩረት ማየት ተገቢነት አለው፡፡

  የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 70 ፕሬዚዳንቱ የሚሰየምበትን ሁኔታ ይናገራል፡፡ ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ የሚሆንን ሰው የማቅረብ ሥልጣን የተሰጠው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ስንት ሰዎች በዕጩነት ሊቀርቡ እንደሚችሉ፣ ምን ዓይነት መስፈርት ማሟላት እንደሚገባቸው የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ከአንድ በላይ ዕጩ የሚቀርብም አይመስልም፡፡ የዚሁ አንቀጽ ቁጥር ሁለት ላይ እንደተገለጸው የቀረበው ዕጩ በሕዝብ ተወካዮችና በፌደሬሽን ምክር ቤቶች አባላት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ድጋፍ ከተቸረው ፕሬዚዳንት እንደሚሆን ይናገራል እንጂ፤ በቀረቡት ዕጩዎች ላይ ድምጽ እንደሚሰጥ አያመለክትም፡፡

  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንድ ተቋም ቢሆንም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊሳተፉበት ይችላሉ፡፡ የተለያዩ ፓርቲዎች በሚኖሩበት ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ የሚሆነውን ሰው የሚጠቆመው እንዴት እንደሆነ ሊገለጽ ይገባ ነበር፡፡ አብላጫ መቀመጫ ላገኘ ፓርቲም ስለመሰጠቱም ሕገ መንግሥቱ አያመለክትም፡፡ ነገሩ የበለጠ ውስብስብ የሚሆነው አንድ ፓርቲ ብቻውን መንግሥት መመሥረት ሳይችል ቀርቶ ጥምር መንግሥት በሚመሠረትበት ጊዜ ነው፡፡

  በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 70 ላይ የተገለጸው የአሰያየም ሁኔታ በኢትዮጵያ ታሪክ ‹‹ዘመነ መሳፍንት›› ተብሎ በሚታወቀው ወቅት የነበሩት ነገሥታት የሚሾሙበትን ሁኔታ ያስታውሰናል፡፡ ከታላቁ ራስ ዓሊ እስከ መጨረሻው ራስ፣ ትንሹ ራስ ዓሊ ድረስ ነገሥታቱን የሚሾሙት የየጁ ስርወ መንግሥት ራሶች ነበሩ፡፡ ራሶቹ የፈለጉትን ነገር ግን የንጉሥነት ዝርያ ያለውን፣ በሕዝቡ ዘንድ የተሻለ ተቀባይነት ያለውን፣ ለእነሱ ምቹ የሆነውን መርጠው ይሾሙ ነበር፡፡ ራሶቹ ርዕሰ መስተዳድርነቱን ሲቆጣጠሩ ርዕሰ መንግሥቱንም ይሾማሉ፤ ወይም ያነግሣሉ፡፡

  ልክ እንደዚያው ሁሉ አሁኑ ሕገ መንገሥትም ይሁን አሠራር መንግሥት ለመመሥረት በቂ መቀመጫ ያገኘው  ፓርቲ ርዕሰ ብሔሩን መርጦ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያጽድቃል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ያላለቀና ዝርዝር የሚፈልገው አንቀጽ ተጨማሪ ሕግ ስለሌለው የተለያዩ ፓርቲዎች በምክር ቤቱ መቀመጫ ሲኖራቸው፣ እንዲሁም ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ማግኘት ሳይቻል በሚቀርበት ጊዜ ሊፈጠር የሚችለውን ቀውስ አስቀድሞ ቅርጽ ማስያዝ ይገባል፡፡ ርዕሰ ብሔርን ያህልን የአገር ወኪልና ተምሳሌት በተሻለና ግልጽነት ባለው መንገድ የሚመረጥበትን መንገድ ማበጀትም ተገቢነት አለው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቢያንስ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ መመልከቱ አስተማሪነት አለው፡፡

  በእርግጥ ፓርላሜንታዊና ሪፐብሊካዊ የሆኑ አገሮች ፕሬዚዳንቱን የሚመርጡበት መንገድ ወጥነት ይጎድለዋል፡፡ እንደ አገራቸው ነባራዊ ሁኔታ የተቀረጸ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በቀጥታ በሕዝብ እንዲመረጥ በመፈለግ ብዙ አገሮች በተዘዋዋሪ መንገድ በፓርላማ የሚደረግን የፕሬዚዳንት ምርጫ እየተቃወሙት መጥተዋል፡፡  ጣሊያን፣ ፊላንድ፣ ሃንጋሪ፣ ጀርመን ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው፡፡

  ኦስትሪያ እያፈራረቀች በሁለቱም መንገድ ሞክራለች፡፡ በእስራኤል ፕሬዚዳንቱ በሕዝብ በቀጥታ ይመረጣል፡፡ ተወዳዳሪዎች ይኖራሉ፡፡ አሸናፊው ርዕሰ ብሔር ይሆናል፡፡ በሕንድ ሃምሳ ጠቋሚዎችና ሃምሳ ደጋፊዎች ያለው ሰው ለውድድር ሊቀርብ ይችላል፡፡ ከዚያም፣ የማዕከላዊው መንግሥት ሁለቱም ምክር ቤቶች እንዲሁም የክልሎቹ ምክር ቤቶች ድምፅ ይሰጣሉ፡፡ አብላጫ ድምጽ ያገኘው ፕሬዚዳንት ይሆናል፡፡

  በጀርመንም በቀጥታ በሕዝቡ ባይመረጥም ከክልሎች የሚወከሉ መራጮች፣ፓርቲዎች፣ የፓርላማ አባለት ወዘተ. ሊጠቁሙ ይችላሉ፡፡ የተጠቆመው ሰው ለመወዳደር ከተስማማ ሂደቱ ይቀጥላል፡፡ከዚያም ሁለቱ ምክር ቤቶችና ሌሎች ተጨማሪ ሰዎች በሚሰጡት ምሥጢራዊ ድምጽ ይመረጣል፡፡ ከእነዚህ አገሮች እና ከሌሎችም መረዳት እንደሚቻለው ፕሬዚዳንት የሚሆነው ሰው በምክር ቤቶች ብቻ አይመረጥም፡፡ በተጨማሪም እንዴት እንደሚጠቆምም ዝርዝር ሕግ አላቸው፡፡

  የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 70 ስለጥቆማው ብቻ ሳይሆን ፕሬዚዳንት የሚሆነውን ሰው መስፈርት አያስቀምጥም፡፡ ከኢትዮጵያ በስተቀር ይኼንን ጉዳይ ሳይገልጽ ያለፈ አገር ማግኘትም ይከብዳል፡፡ ለተለያዩ ምክር ቤቶች የሚወዳደሩትን ዕጩዎች ሳይቀር ቢያንስ የምርጫ ሕጉ ላይ ሲደነገግ ስለፕሬዚዳንቱ፣ ስለአገሪቱ ራስ ግን አልተገለጸም፡፡ በእስራኤል ማንኛውም እስራኤላዊ ዜግነት ያለውና እስራኤል ውስጥ የሚኖር ዕድሜው 35 የሆነ ዕጩ መሆን ይችላል፡፡ በጀርመን ዕድሜው 40 ሊሞላው ግድ ነው፡፡ ዜግነቱ ደግሞ ጀርመናዊ ሊሆን ግድ ነው፡፡ የህንድ ሕገ መንግሥት ደግሞ ከዕድሜና ከዜግነት መሥፈርቶች በተጨማሪ ለትርፍ የተቋቋመ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ የነበረ ሰው ለፕሬዚዳንትነት አይወዳደርም፡፡

  ለፕሬዚዳንትነት የሚጠቆመው ሰው የፖለቲካ አቋምና ወገንተኝነትንም በተመለከተ እንደሌሎቹ ጉዳዮች ሕገ መንግሥቱ በመለኪያነት ያስቀመጠው ነገር የለም፡፡ ከላይ ለማየት እንደተሞከረው ርዕሰ ብሔሩ የአገሪቱ የጅምላነቷ ተምሳሌት፣ የአንድነቷ ምልክትና ወኪል በመሆኑ ከፖለቲካ ፓርቲም ይሁን ከሌሎች ወገንተኛ ከሚያደርጉም ከሚያስመስሉም እንቅስቃሴዎች መራቅ አለበት፡፡

  የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት መተዳደሪያ አዋጅ ቁጥር 255/1994 ላይ ፕሬዚዳንቱ በአገሪቱ ከሚገኙ ፓርቲዎች ገለልተኛ መሆን እንዳለበት ይገልጻል፡፡ በፕሬዚዳንትነት ወቅትም ይሁን በኋላ ከፓርቲ ፖለቲካ መራቅን ይጠይቃል፡፡ በተለይ ከለቀቁ በኋላ ምንም ዓይነት ወገንተኛ እንዳይሆኑ የሚጠይቅ አዋጅ፣ ቀድሞም ወገንተኛ የነበረን ሰው ወደ ፕሬዚዳንትነት መንበር ማምጣት ይፈቅዳል ብሎ መከራከር ከሥነ አመክንዮም ይሁን  ከተምሳሌትነቱም ከዓለማውም አንጻር አሳማኝ አይሆንም፡፡ ነገር ግን ተግባሩ የዚህ ተገላቢጦሽ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡

  የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በተለያዩ ጽሑፎቻቸው እንደገለጹት ርዕሰ ብሔር በነበሩበት ወቅትም የፓርቲ ሥራ ይሠሩ ነበር፡፡ የድርጅትም አባል ነበሩ፡፡ አሁንም በፕሬዚዳንትነት የሚያገለግሉት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመም ቢሆኑ ቢያንስ እስከ ሹመታቸው ድረስ (አሁን ላይ ይልቀቁ ወይም አይልቀቁ ጸሐፊው መረጃ ባይኖረውም) የፓርቲ አባል እንደነበሩ የታወቀ ነው፡፡ ይህ አዋጅ የወጣው ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከፕሬዚዳንትነት መልቀቃቸውን ተከትሎ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

  ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ አጠቋቆምና የዕጩዎች መሥፈርት ካለማስቀመጥ ባለፈም ፕሬዚዳንቱ እንዴት ሊነሳ እንደሚችልና ሌላ ሰው እስኪሰየም ድረስ ማን ሊተካው እንደሚችል ሕገ መንግሥቱ ምንም ፍንጭ አይሰጥም፡፡ የተወሰኑ አገሮች ምክትል ፕሬዚዳንት አላቸው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሕንድ ናት፡፡ ፕሬዚዳንቱ በሞት፣ በራሱ ፈቃድ ወይም ሕገ ወጥ ነገር በመፈጸሙ ቢነሳ እስከሚቀጥለው ምርጫ ምክትሉ ይተካዋል፡፡ ጀርመን ደግሞ የክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች ለአንድ ዓመት ያህል በየተራ በምክትልነት ያገለግላሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ቢሞት ወይም ቢለቅ እስከሚቀጥለው ምርጫ በፕሬዚዳንትንት ያገለግላሉ፡፡

  እስራኤል ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥም አፈ ጉባዔው የፕሬዚዳንቱን ቦታ ደርቦ ይሠራል፡፡ በኢትዮጵያ ማን እንደሚተካው ሕገ መንግሥቱ ዝምታን መርጧል፡፡ ይሁን እንጂ አዋጅ ቁጥር 255/1994 ላይ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም በሁለቱ ምክር ቤቶች ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት እንደሚመረጥ ይጠቁማል፡፡ ከተሰበሰቡ ፕሬዚዳንቱን መሰየም ስለሚችሉ በምክር ቤቶቹ የጋራ ስብሰባ ተጠባባቂ የመምረጥ ምክንያቱ ግልጽ አይደለም፡፡

  በኢትዮጵያ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ያለመከሰስ መብት ይኑረው ወይንም አይኑረውም ሕገ መንግሥቱ መልስ አልሰጠም፡፡ የፕሬዚዳንትነቱን ዘመን ሳያጠናቅቅም ሊነሳ የሚችልበትን ሁኔታ አይገልጽም፡፡ በሌሎች አገሮች ርዕሰ መስተዳድር ያለመከሰስ መብቱ ተነስቶ ወይንም ደግሞ በፓርላማ ከሥልጣኑ ካልወረደ (Impeach ካልተደረገ) በስተቀር አይከሰስም፡፡ ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ ላይ ፕሬዚዳንቱ በሕጋዊ ውሳኔ ሊነሳ  እንደሚችል ይገልጻል፡፡ ሕጋዊ ውሳኔ ምን ማለት እንደሆነ፣ማን እንደሚወስን፣ እንዴት እንደሚወሰን ግን አዋጁም ላይ አልተገለጸም፡፡

  እስኪ ደግሞ የፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ተብለው የተቀመጡትን እንመልከት፡፡ እንደ ኢትዮጵያ፣ርዕሰ ብሔሩ እና ርዕሰ መስተዳድሩ በተለያዩ ሰዎች በሚመሩባቸው አገሮች ርዕሰ መስተዳድሩ በብዙ መልኩ ተምሳሌታዊ እንጂ ወሳኝ የሆኑ ሥልጣን እንደማይኖረው የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን፣ እነዚህ አገራዊ ተምሳሌት ያላቸው ሥልጣናት በራሳቸው የተለያዩ እንጂ አንድ ዓይነት አይደሉም፡፡

  በኢፌዴሪ በሕገ መንግሥት ላይ ለፕሬዚዳንቱ የተሰጡት ሥልጣኖችን (ምናልባትም ተግባርና ኃላፊነት የሚለው የበለጠ ይገልጻቸዋል) እንመለከት፡፡ በሕግ መሠረት የወንጀል ፍርደኞችን ይቅርታ ያደርጋል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች የወጡ ሕጎችን ያውጃል፡፡ በ15 ቀናት ካላወጀ ሕግ ሆኖ ይጸድቃል፡፡ የሁለቱን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ይከፍታል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡለትን አምባሳደሮችና ልዩ መልዕክተኞች ይሾማል፡፡ የሌሎች አገሮች አምባሳደሮችን ልዩ መልዕክተኞች የሹመት ደብዳቤ ይቀበላል፤ ያሰናብታል፡፡ በሕግ መሠረት ኒሻን፣ ሜዳይና ከፍተኛ የውትድርና ማዕረግ ይሰጣል፡፡ እነዚህን ተግባራት የመፈጸም ግዴታዎች አሉበት ማለት ነው፡፡ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸውን ወንጀለኞች ወደ ዕድሜ ልክ እሥራት የመቀየር ሥልጣን አለው፡፡ የመቀየርም ያለመቀየርም ሥልጣን አለው፡፡

  የጥምርነት የተመሠረተ መንግሥት ኖሮ በጊዜ ሒደት ጥምርነቱ ቢፈርስ ፕሬዚዳንቱ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አዲስ መንግሥት ይመሠርቱ ዘንድ በፓርላማው ውስጥ መቀመጫ ያለቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች ይጋብዛል፡፡ መመሥረት ካልቻሉ ምክር ቤቱ ይፈርስና በስድስት ወራት ውስጥ አዲስ ምርጫ ይደረጋል፡፡ የመፍረሱን ውሳኔ የሚሰጠው ግን በጠቅላይ ሚኒስተሩ ጥያቄ መሠረት ራሱ ፓርላማው ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ ከተቀመጡት በተጨማሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእረፍት ላይ በሚሆንበት ጊዜ ኦዲተር ጀነራሉ ተጠሪነቱ ለፕሬዚዳንቱ መሆኑ ነው፡፡

  ከላይ የተገለጹት ተግባራትን የሚፈጽም ሰው ነው በኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር ማለት፡፡ ከላይ ከተገለጹት ሌሎች በሕገ መንግሥቱ የተሰጡት የአገሪቱን አንድነት፣ሉዓላዊነት የሚያንጻባርቁም ሆኑ የሚወክሉ ሥልጣን አለው ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ እስኪ የሌሎች አገሮች ርዕሰ ብሔሮች ያላቸውን ሥልጣን እንመልከት፡፡

  የእስራኤል ፕሬዚዳነት  የጥምር መንግሥት ምሥረታ ሒደትን ይመራል፡፡ በእስራኤል አንድ ፓርቲ መንግሥት የመመሥረት ዕድሉ ጠባብ ስለሆነ የፓርቲ መሪዎችን በመጥራት መንግሥት እንዲመሠርቱ ይሠራል፡፡ ፕሬዚዳንቱን ከሚመለከቱ ሕጎች በስተቀር ሁሉም ላይ ይፈርማል፡፡ ዓለም አቀፍና የሁለትዮሽ ስምምነቶችንም ይፈርማል፡፡ የብሔራዊ ባንኩን ገዥና ኦዲተር ጀኔራሉን በፓርላማው አቅራቢነት ይሾማል፡፡ በርካታ ብሔራዊ ይዘት ያላቸውን ተቋማት ኃላፊዎች ይሾማል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ለወጉም ቢሆን ይሾማል፡፡ሚኒስትሮችን እንዲሾም 45 ቀናት ይሰጣል፡፡ ለወጉም ቢሆን ዳኞችን ይሾማል፤ በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ሁሉ ነገር ካቀ በኋላ፡፡ ይቅርታ እና ምሕረት፣የአምባሳደር ሹመትም ይሰጣልም፣ይቀበላልም፡፡ ፓርላማው ሲፈርስ የፕሬዚዳንቱን ስምምነት ማግኘት አለበት፡፡ የአገሪቱን ከፍተኛ ኒሻን ይሰጣል፡፡ የፓርላማ መክፈቻ ላይ (በዓመት ሁለት ጊዜ) ንግግር ያደርጋል፡፡ አገራዊ በዓላት ላይም ንግግር የሚያደርገው ፕሬዚዳንቱ ነው፡፡

  በጀርመን ደግሞ ፕሬዚዳንቱ አገሪቱን ይወክላል፡፡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ይፈርማል፡፡ አምባሳደሮችን ይሾማል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ያልሆኑ ሕጎችን አለመፈረም ይችላል፡፡ በበማናቸውም ሁኔታ በሕዝብ ዘንድም ሲቀርብ ጀርመንን እንደ አገር ሕልውናዋን፣ አንድነቷን፣ ጅምላነቷን ይወክላል፡፡ በፓርቲዎችም ሆነ በተለያዩ ቡድኖች መካከል ቅራኔ ወይንም አለመስማማት ሲጠፋ በሚዲያ አስተያየት መስጠት በሕግ ባይከለከልም አልተለመደም፡፡ ከፓርቲ ፓለቲካ በላይ ስለሆነ፡፡ የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሚኒስትሮች ምክር ቤት (የካቢኔ) ስብሳበ ላይ በመሳተፍ ለፕሬዚዳንቱ ሪፖርት ያቀርባል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ቻንስለሩንና ሚኒስትሮችን እየጠራ ይመካከራል፡፡ቻንስለሩም በአብላጫ መቀመጫ ያለው ፓርቲ በሌለበት ሁኔታ የተመረጠ በሚሆንበት ጊዜ ሚኒስትሮችም በቻንስለሩ የሚቀርብለትን ይሾማል፡፡ የመተማመኛ ድምፅ የተነፈገ ቻንስለርን ያባርራል፡፡ ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ፓርላማውንም ሊበትን ይችላል፡፡ ያውጃል፡፡ ዳኞችን ይሾማል፤ ያባርራል፡፡ ይቅርታና ይሰጣል፡፡ የክብር ሽልማት  ይሠጣል፡፡ በቻንስለር ከተፈረመ በኋላ ሕገ መንግሥቱ በሚያዘው መሠረት መውጣቱንና ሕግ መንግሥቱን አለመቃረኑን አረጋግጦ ይፈርማል፡፡ ካልሆነ ውድቅ ያደርጋል፡፡በፓርላማ ሲጸድቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ያጸድቃል፡፡

  በአውስትራሊያ በእንግሊዟ ንግሥት ፈቃድን በጠቅላይ ሚንስትሩ አቅራቢነት የሚሾመው አገረ ገዥ (Governor General) የጦር ኃይሎች ጠቅላይ  አዛዥ ነው፡፡ ሚኒስትሮችን፣ ዳኞችን፣ አምባሳደሮችን ይሾማል፡፡ ሜዳይ ይሰጣል፡፡ ሕጎች ላይ ይፈርማ፡፡ የተለያየ አስተዋጽኦ ያደረጉ ግለሰቦችን ያበረታታል፡፡ በጥምር መንግሥት ጊዜ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ይሰይማል፡፡ የመተማመኛ ድምፅ ያጣን ጠቅላይ ሚኒስትር ያባርራል፡፡ ሕገወጥ ድርጊት የፈጸመን ሚኒስቴር/ጠቅላይ ሚኒስቴርንም እንዲሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢጠይቅም ፓርላማው እንዲፈርስ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ ማድረግ  ይችላል፡፡ ከተቀበለው ደግሞ እንዲፈርስ በመወሰን እና ምርጫ እንዲደረግ የማዘዝ ሥልጣን አለው፡፡ ዕድሜያቸው 100 ዓመት የሞላን፣ በጋብቻ 50ኛ ዓመት የሞላቻውን ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› የሚል መልዕክት ይልካል፡፡ የሹመት (የማዕረግ) ዓይነቶችን ይወስናል፣ የባንዲራን ሕግ እንዲሁ፡፡

  በህንድ ደግሞ ከላይ ስለሌሎች አገር ከተገለጸው ጋር በብዙ መልኩ የተመሳሰለ ሆነ የጦር ኃይሎችም አዛዥ ነው፡፡ ሕጎች ላይ ይፈርማል፡፡ድጋሜ እንዲታዩ ሊመልስ ይችላል፡፡

  የጃፓን ንጉሣዊ ቢሆንም የሕዝቦች አንድነትና የአገሪቱ የውክልና ምልክት (ትዕምርት) ነው፡፡ አገራዊ ጉዳዮችን ከሚመለከታቸው ሚኒስትሮች (ካቢኔዎች) ጋር በመመካከር ይወስናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለወጉም ይሾማል፡፡ (ሹመቱን ያጸድቃል፣አለማጽደቅ አይችልም፡፡) በካቤኔ (በሚኒስትሮች ምክር ቤት) ሲቀርብለት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ፕሬዚዳንት ይሾማል፡፡ በምክር ቤትና በካቢኔ ሲጸድቁ በሕዝቡ ስም ሕጎችን  ያውጃል፡፡ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ፣አዋጅ፣የካቢኑ ደንቦች፣ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንም ጭምር፡፡ ፓርላማ ይበትናል፤ምርጫ እንዲካሄድ ያደርጋል፡፡

  ከላይ ከቀረቡት የአገሮች ተሞክሮ አንጻር በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ላይ የተገለጸውን ርዕሰ ብሔር ያህል እጅግ በጣም ያነሰ አገራዊ ተምሳሌትነት ተሰጠው፣ሥልጣንም የሌለው የለም፡፡ ሕግ በሚወጣበት ጊዜ ምንም ዓይነት የመመርመር ሥልጣን የለውም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ ቢሆን እንኳን ይፈርማል፤ ካልሆነም ሕግ ሆኖ ይወጣል፡፡ ፕሬዚዳንቱን የሚመለከቱ ሕጎችንም ጭምር ያውጃል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌው ስለፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት የወጣው አዋጅ ነው፡፡

  የአገሪቱ ራስ ፕሬዚዳንቱ ሆኖ ሳለ የትዳር አጋሩ ቀዳማዊት እመቤትነት ወይም ወንድም ቢሆን ምንም ዓይነት ሚና እንዲኖረው አልተደረገም፡፡ ተቀዳሚው ሰው ፕሬዚዳንቱ ከሆነ የትዳር አጋሩም በጋራ እንዲሁ እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ርዕሰ መስተዳድር የሆነ ሰው የትዳር አጋር ሳይሆን ‘ቀዳሚነት’ የሚሰጠው የአገሮችም ተሞክሮ ይሁን በአመክንዮም የፕሬዚዳንቱ ነው፡፡

  ፕሬዚዳንቱ የአገሪቱ ወኪል እስከሆነ ድረስ ከፖለቲካዊ ወገንተኝት መራቅ አለበት፡፡ መንግሥትም የአገሪቱ አንድ አካል እስከሆነ ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በፓርላማ ከተሾሙ በኋላ የርዕሰ መስተዳድሩን ቡራኬ ማግኘት  ይጠበቅባቸዋል፡፡ አገራዊ ተምሳሌትነት ያላቸውን (የአገር መከላከያ ሠራዊቱን አዛዥነት ጨምሮ) ወደ ፕሬዚዳንቱ ቢዞሩ ተገቢነት ነበረው፡፡ መንግሥት በመከላከያ ሚኒስትሩ ስለሚወከል፡፡ እነዚህ የተነሱት በምሳሌነት ነው፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ግን፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ ለፕሬዚዳንቱ የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ነው፡፡ የተሰጡትንም ተግባራት ለመወጣት የሚያሳችሉ ሕግጋትም ይጎድሉታል፡፡ ያሉትም ቢሆኑ ጅምር ናቸው፡፡ 

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...