Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ክራሞት

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ዘንድሮም በጤናማ ጉዞ ላይ እንደሚገኙ እየተገለጸ ነው፡፡ 2009 ዓ.ም. የነበረው አፈጻጸማቸውም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃም በሁሉም አፈጻጸም ዕድገት ማሳየታቸውን ይጠቅሳል፡፡ በመጀመርያው የዕድገትና ትራንፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የታየው የፋይናንስ ተቋናት ውጤታማነት፣ በሁለተኛውም የዕቅዱ ዘመን እየታየ መምጣቱ ተነግሯል፡፡ ሆኖም ዘርፉ በርካታ ችግሮች የሚገታዩበት በመሆኑ፣ የተሻለ እንቅስቃሴ ካልታየበት በቀር እስካሁን ካስመዘገበው ይበልጥ ውጤት ላያመጣ እንደሚችል ሥጋት የገባቸው ወገኖች አሉ፡፡ የውድድር ሜዳውን በሚገባ በማስተካከል የተወዳዳሪነት አቅም መፍጠር የሚያስችላቸው አሠራር መዘርጋት ግድ መሆኑንም የዘርፉ ተወናዮች ይናገራሉ፡፡

በተሸኘው በጀት ዓመት ጉልህ መነጋገሪያ ከነበሩ ፋይናንስ ቀመስ ጉዳዮች ውስጥ፣ የተቋማት ውህደት አይቀሬነቱ እየታየ መሆኑ አንዱ ነበር፡፡ ጠንካራ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ለመገንባት፣ አሁን ላይ ያሉት ተቋማት መዋሃዳቸው አይቀሬ እንደሚሆን ቁርጥ እንደሆነ የተሰማው በ2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥም ይህንኑ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ኢንዱስትሪው ከሚጠይቀው ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት አንፃር፣ ተቋማቱ ራሳቸውን ከሰርሳዎች ወይም ‹‹ሀከሮች›› ለመጠበቅ የሚችሉበት አሠራር እንዲዘረጉ ግፊት የተደረገበት ዓመትም ሆኖ አልፏል፡፡ በጋራም ሆነ በተናጠል ይህንን ሥርዓት እንዲዘረጉ ምክር የቀረበላቸው የፋይናንስ ተቋማቱ፣ በአዲሱ ዓመት ይህ ጉዳይ በይበልጥ ትኩረት እንደሚሰጠው እየተጠበቀ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው እንዲህ ያሉ ክስተቶች ታይተው፣ ሌሎችም ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን፣ ጥቂቶቹ እንዲህ በአጭሩ ቀርቧል፡፡

አዲስ የምርጫ ሥርዓት

2009 ዓ.ም. በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቋማት በአዲሱ የብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት በአዲስ የምርጫ መመርያ ለመተዳደር መንቀሳቀስ የጀመሩበት ወቅት ነበር፡፡

ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ የሚመሯቸውን ቦርድ አባላት ለመምረጥ የሚንቀሳቀሱት ተቋማቱ፣ አዲሱን መመርያ ተከትለው  የምርጫ ጊዜ ከመድረሱ ከወራት በፊት ለመጀመርያ ጊዜ በመገናኛ ብዙኃን ዕጩዎቻቸውን ያስተዋወቁበት ዓመት ሆኗል፡፡ የምርጫው ሒደት ኢንዱስትሪውን ሊመሩ የሚችሉ አዳዲስ የቦርድ አባላት የሚታዩበት እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም አነስተኛ ድርሻ ባላቸው ባለአክሲዮኖች የሚወክሉ ተመራጮች፣ በቦርድ አመራርነት እንዲሳተፉ መመሪያው ግዴታ መጣሉ ከሚጠቀሱለት አዳዲስ አሠራሮች ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር ብሔራዊ ባንክ፣ የባንኮች ፕሬዚዳንቶች የሚሾሙበትን መመርያ እያሻሻለ እንደሚገኝ ያስታወቀውም በተሰናበተው ዓመት ነበር፡፡ የባንኮች የቅርንጫፍ ሥርጭትን የሚመለከተውን መመርያ ለማስተካከል የሚያስችለውንም ዝግጅት እያካሄደ እንደሚገኝ ይፋ ያደረገውም በ2009 ዓ.ም. ነበር፡፡

በብሔራዊ ባንክ ከቀረቡት ረቂቅ መመርያዎች አንዱ፣ የባንክ ኃላፊዎችን የሹመት መሥፈርት ለማሻሻል የወጣው ይገኝበታል፡፡ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ተፅዕኖ ያላቸው ባለሙያዎችን ጨምሮ የቦርድ አመራሮች፣ ፕሬዚዳንቶች፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ የሥጋት (ሪስክ) ኦፊሰሮችን፣ የውስጥ ኦዲተሮችን፣ እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖችን ለመቆጣጠር የሚያስችል መመርያ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ተሻሽሎ በቀረበው በዚህ ረቂቅ መመሪያ ላይ የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎች ተወያይተውበታል፡፡ ረቂቁ ሦስት መሠረታዊ ማሻሻያዎችን አካቷል፡፡

አንደኛው ማሻሻያ የባንክ ፕሬዚዳንት ለመሆን በባንክ ሥራ መስክ በጠቅላላው የ12 ዓመታት የሥራ ልምድ ሲጠየቅ፣ ከዚህ ውስጥ ለአምስት ዓመታት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኖ ማገልገል እንደሚጠበቅ ረቂቅ መመርያ አስፍሯል፡፡ በቅድሞው መመርያ መሠረት ፕሬዚዳንት ለመሆን የሚጠይቀው በባንክ ሥራ አሥር ዓመት ያገለገለና አምስት ዓመት በዳይሬክተርነት መሥራት ነበር፡፡

ሌላኛው ማሻሻያ ምክትል ፕሬዚዳንትነትን የሚመለከት ነው፡፡ በዚህ ማሻሻያ መሠረት ምክትል ፕሬዚዳንት ለመሆን የአሥር ዓመታት የባንክ የሥራ ልምድና የአምስት ዓመታት የዳይሬክተርነት ልምድ መሆን የሚጠይቀው ነው፡፡ በግንቦት ወር የቀረበው ሌላኛው ረቂቅ ማሻሻያ፣ የቦርድ ዳይሬክተሮችን ስብጥር ይመለከታል፡፡ ቀድሞ በነበረው መመርያ መሠረት፣ አንድ የፋይናንስ ተቋም ካሉት የቦርድ አባላት ውስጥ 25 በመቶው የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቁ እንዲሆኑ ይጠይቅ ነበር፡፡ የተቀሩት 75 በመቶዎቹ ደግሞ የመጀመርያ ዲግሪ እንዲኖራቸው የሚጠቅስ መመሪያ ነበር፡፡ በተሻሻለው ረቂቅ መመርያ ግን ሁሉም የቦርድ አባላት የመጀመርያ ዲግሪ ሊኖራቸው እንደሚገባ ተደንግጓል፡፡ ይህ መመርያ በቅርቡ ፀድቆ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡

የሊዝ ፋይናንስ መመርያዎች

የካፒታል ዕቃዎች ግዥ ፋይናንስ ወይም የሊዝ ፋይናንስ ሥርዓት ተግባራዊ መሆን የጀመረውም በ2009 ዓ.ም. ነው፡፡ የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎትን ለመተግበር ያስችላሉ የተባሉ ሦስት መመሪያዎች የወጡትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ነበር፡፡ ከሦስቱ መመሪያዎቹ አንዱ ኩባንያዎች ሊኖራቸው የሚገባው ዝቅተኛ የማቋቋሚያ ካፒታል መጠንን ከየካፒታል ዕቃ ፋይናንስ አኳያ የወሰነበት ነው፡፡ ሁለተኛው መመሪያ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ተጠቃሚነት ላይ የተጣለውን ገደብ የሚያመለክት ሲሆን፣ ሦስተኛው ከካፒታል ዕቃ ፋይናንስ አኳያ የወጣው መመርያ ቢጣስ፣ ሊከተል የሚችለውን ቅጣትም የሚደነግግ ነው፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከሰኔ 2009 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሆኑ ካሳወቃቸው ሦስቱ መመርያዎች ውስጥ የካፒታል መጠንን የሚያመለክተውና የተጠቃሚነት ገደብን የወሰነበት መመርያዎች ላይ ማሻሻያ ያደረገ ሲሆን፣ ስለሚጣል ቅጣት የተመለከተው ድንጋጌ ግን አዲስ የወጣ መመርያ ነው፡፡ በተለይ የካፒታል መጠንን የተመለከተው ድንጋጌ መብት እስከ አንድ ቢሊዮን የሚደርስ የካፒታል ዕቃ ለመግዛት ፍላጎት ያላቸውን ኢንተርፕራይዞችን የሚያስተናግዱ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ አቅራቢ ኩባንያዎች የሚጠበቅባቸው ዝቅተኛ የተከፈለ ካፒታል 200 ሚሊዮን ብር መሆን እንዳለበት ያሳወቀበት ነው፡፡ እስከ 30 ሚሊዮን ብር የሚደርስ የካፒታል ዕቃ ለመግዛት ፍላጎት ያላቸውን ኢንተርፕራይዞች የሚያስተናርዱ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ኩባንያዎች፣ የተከፈለ የማቋቋሚያ ካፒታላቸው መጠን 400 ሚሊዮን ብር እንዲሆን ገዥው ባንክ ደንግጓል፡፡

መመርያው በክልሎች ወይም በከተማ አስተዳደሮች ድጋፍ የተቋቋሙ ኩባንያዎች ይህ የማቋቋሚያ ካፒታል መጠን እንደማይመለከታቸው አስቀምጧል፡፡ በአሁኑ ወቅት የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ሥራ ለመሥራት እስከ በጀት ዓመቱ መዝጊያ ድረስ ፈቃድ በመውሰድ ወደ ሥራ የገቡ አራት ኩባንያዎች እንደሆኑም ታውቋል፡፡

የዓረቦን ዋጋ መዋዥቅና ሥጋቶቹ

በመድን ድርጅቶች ዘንድ የዓረቦን ምጣኔ ወይም ለመድን ሽፋን እየተሰጠ የሚገኘው የመድን ሽፋን ዋጋ እየወረደ መምጣቱ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ከወቅታዊ ገበያ ጋር ሊጣጣሙ አልቻሉም የተባሉ የመድን ሽፋን ዓይነቶች ለኢንዱስትሪው ሥጋት መሆናቸው በይፋ የተነገረበትና ብሔራዊ ባንክም ይህንኑ የተመለከተበት ዓመት ሆኖ አልፏል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ብሔራዊ ባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መክረዋል፡፡ የዋጋ መዋዥቅ ሊያስከትል የሚችለውን ሥጋትና አደጋ ለመቀነስ የመድን ሰጪዎች ማኅበር ጥናት እያካሄደ እንደሚገኝ ከማስታወቁም በተጨማሪ የጥናት ውጤቱን በቅርቡ ለብሔራዊ ባንክ እንደሚያቀርብ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡ በጥናቱ ውጤት መሠረት ብሔራዊ ባንክ አንድ ውሳኔ እንደሚሰጥም ይጠበቃል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ዋጋ

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት መጨረሻ፣ ለአንድ ዶላር የሚከፈለው የምንዛሪ ዋጋ በአማካይ ወደ 23.244 ብር ከፍ ብሏል፡፡ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት የአንድ ዶላር አማካይ የምንዛሪ ዋጋ 21.00 እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ውስጥ የዶላር ምንዛሪ ዋጋ የጨመረው ወይም የብር የመግዛት አቅም የወረደው በሦስት ብር ገደማ እንደሆነ ያሳያል፡፡ እ.ኤ.አ. ጁላይ 8 ቀን 2014፣ በ19.703 የተመነዘረው ዶላር፣ በጁላይ 8 ቀን 2015 ወደ 20.724 ከፍ ሲል ዓምና ደግሞ ወደ 21.000 አሻቅቧል፡፡ በ2009 ዓ.ም. የውጭ ምንዛሪው የጥቁር ገበያ ዋጋ ከምንጊዜውም ይልቅ ከፍ ብሎ እንደነበር የሚጠቀስ ነው፡፡ አንድ ዶላር እስከ 30 ብር የተመነዘረበት ዓመት እንደነበር ተነግሯል፡፡ በጥቁር ገበያው አመካይ የነበረው የምንዛሪ ዋጋ ከ27 እስከ 28 ብር ነበር፡፡ ከዚሁ በተጓዳኝ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ እጥረታቸው ሳይቀረፍ ዓመቱን አጠናቀዋል፡፡ በመሆኑም፣ ከኢትዮጵየያ ንግድ ባንክ በተጨማሪ እንደ ቡና ባንክ፣ አዋሽ፣ ንብና ብርሃን ባንክ ያሉት ተቋማት የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸውን ለማሳደግ የሽልማት ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የውጭ መገበያያ ገንዘቦችን ለማሰባሰብ ሲጣጣሩ የታዩት፣ አንቆ የያዛቸውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ ነበር፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ለመቋቋም የተደረገው ጥረትና ውጤታማነቱ አጠያያቂ እንዳለ ሆኖ፣ እንደ ንግድ ባንክ ያሉት ግን የዓመቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከቀደሙት ዓመታት ይልቅ ባነሰ ውጤት አገባደዋል፡፡

የጠለፋ ዋስትና ሰጭ ኩባንያ

በፋይናንስ ዘርፉ ከሚጠቀሱ ዋነኛ ክንውኖች መካከል ሳይጠቀስ የማይታለፈው ኢትዮጵያን የጠለፋ ዋስትና ሰጭ ኩባንያ ባለቤት የሚያደርጋት ኩባንያ መቋቋሙ ነው፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከሚሰበስቡት ጠቅላላ የዓረቦን ገቢ ውስጥ እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን ለውጭ ጠለፋ ሰጪዎች የሚያውሉትን ክፍያ ለማስቀረት ታስቦ የተቋቋመው ኩባንያ፣ በይፋ ሥራ የጀመረው በጥቅምት 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡

በአንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ይህ ኩባንያ፣ ባንኮችንና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን በአባልነት የያዘ ነበር፡፡ የዚህ ተቋም መሥራች ዳይሬክተር ለመሆን የበቁት በኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሥራ አስፈጻሚነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ የወንድወሰን ኢተፋ ናቸው፡፡ አቶ የወንድወሰን የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚነታቸውን በመተው፣ ወደ አዲሱ ኩባንያ ሲያቀኑ፣ በምትካቸው አቶ ነፃነት ለሜሳ የመድን ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የተሰየሙበትም በ2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ የጠለፋ ዋስትና ሰጭ ኩባንያው፣ ለአገሪቱ የመድን ኩባንያዎች የጠለፋ ዋስትና ሽፋን አገልግሎቱን መስጠት ጀምሯል፡፡

አዳዲሶቹ የዋስትና ሽፋኖች

በተሸኘው ዓመት በኢንሹራስ ኢንዱስትሪው ውስጥ እንደ አዲስ የሚታዩ የመድን አገልግሎቶች ታይተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በአገሪቱ የመጀመርያ የተባለው የሕክምና ዋስትና በኢትዮ ላይፍና ጄኔራል ኢንሹራንስ ኩባንያ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትም የሕክምና ባለሙያዎን ጨምሮ ለሒሳብ ባለሙያዎች አዲስ የመድን ሽፋን ለመስጠት መዘጋጀቱን ያስታወቀውም በዚሁ በ2009 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን፣ እንደ የአውሮፕላን አምቡላንስ አገልግሎትን የመሳሰሉ አዳዲስ የመድን ሽፋኖች ለማቅረብ መዘጋጀቱንም አስታውቋል፡፡

በ17 የአገሪቱ መድን ሰጪ ኩባንያዎች የተመዘገበው የዓረቦን መጠን በ16.6 በመቶ ዕድገት በማሳየት በ2009 ዓ.ም. መዝጊያ ወቅት የሰበሰቡት የዓረቦን ገቢ 17.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይሁን እንጂ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ አጣብቂኝ ውስጥ ስለመግባቱ የሚያመለክቱ መረጃዎች የወጡትም በዚሁ ዓመት ነበር፡፡ ለኢንዱስትሪው ሥጋት ሆኖ የተቀመጠው ኩባንያዎቹ ለአንዳንድ ዘርፎች የሚሰጡት የመድን ሽፋን እና የሚያስከፍሉት ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት ይጠየቅ የነበረው ዋጋ ቀስ በቀስ መቀነሱ የኢንዱስትሪውን የወደፊት ጉዞ ያሰጋዋል ሲባል ቆይቷል፡፡ ይህም መስተካከል እንደሚኖርበት ተገልጿል፡፡

የውጭ ዜግነት ያላቸው ባለአክሲዮኖች

በአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ አነጋጋሪ ሆነው ከተሸኙ ዓበይት ክንውኖች አንዱ፣ በባንክና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ የያዙና የውጭ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ነው፡፡

በአገሪቱ ሕግ ኢትዮጵያውያን በባንክና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ መሳተፍ እንደማይችሉ ቢደነገግም፣ ተቋማቱ ግን የውጭ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን የአክሲዮን ባለቤት ሆነው መገኘታቸው በመረጋገጡ፣ ብሔራዊ ባንክ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ የጀመረበት ወቅት ነበር፡፡

በገዥው ባንክ ውሳኔ መሠረት፣ የፋይናንስ ተቋማቱ የውጭ ዜግነት ያላቸውን ባለአክሲዮኖች ተለይተው አክሲዮኖቻቸው እንዲሸጡ አዟል፡፡ ከዚህ ዕርምጃ በፊት ግን በርካታ ክርክሮች ቢደመጡም፣ የውጭ ዜግነት ባላቸው ባለአክሲዮኖች የተያዙ አክሲዮኖች እስከ 2009 መጨረሻ ያገኙት ትርፍ ተከፍሏቸው የአክሲዮን ድርሻቸው ግን እንዲሸጥ ተወስኗል፡፡ በመሆኑም ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ያወጡ አክሲዮኖች በግልጽ ጨረታ እንዲሸጡ ተደርጓል፡፡ በዚህ የአክሲዮን ሽያጭ አንድ አክሲዮን እስከ 20 ሺሕ ብር ሲሸጥ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የፕሮጀክት ፋይናንስ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለፕሮጀክት ፋይናንስ ብድር መስጠት ማቆሙንና ብድር የተፈቀደላቸው አካላትም፣ ሊሰጣቸው የነበረው ገንዘብ እንዲሰረዝ መደረጉ፣ በበጀት ዓመቱ አነጋጋሪ ሆነው ከታዩና አሁንም በእንጥልጥል ከሚገኙት መካከል የሚመደብ ጉዳይ ነው፡፡ ሚያዝያ 2009 ዓ.ም. ከንግድ ባንክ የወጣው ደብዳቤ ብዙዎችን አነጋግሮ ነበር፡፡ ለፕሮጀክት የሚሰጥ ብድር መቋረጡን የሚገልጸው ደብዳቤ፣ ያልተጠበቀ ዱብ ዕዳ ክስተት ሆኗል፡፡ ይህም ይባል እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ ንግድ ባንክ በዚህ መስክ በድር መስጠት እንደማይችል፣ ይልቁንም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለፕሮጀክት የሚውል ብድር አቅራቢ ሆኖ እንደሚጓዝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የንግድ ማኅበረሰቡን ባነጋገሩበት ወቅት አረጋግጠዋል፡፡

የባንኮች ዓርማ ለውጥ

      ሁለት የግል ባንኮች ከምሥረታቸው ጀምሮ ለዓመታት ሲገለገሉበት የቆዩትን  ዓርማዎች የቀየሩትም በተሸኘው የ2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ ‹‹አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ›› የሚለውን መጠሪያውን ወደ አዋሽ ባንክ በማሳጠር፣ ከ20 ዓመታት በላይ ሲገለገልበት የቆየውንም ዓርማ በአዲስ መተካቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ወጋገን ባንክም ሲጠቀምበት የቀደመውን ዓርማውን በማስቀረት ባንኩን በተሻለ መንገድ ይገልጽልኛል ብሎ ያመነበትን ዓርማ እንደቀየረ ይፋ ያደረገውም በ2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ ባንኮቹ በኢትዮጵያም ሆነ ወደ ፊት ከኢትዮጵያ ውጭ ለመንቀሳቀስ ያመቸናል በማለት ገላጭ ዓርማችን ነው በማለት በአዳዲስ ዓርማና መለያ መጠራትና መታወቅ ጀምረዋል፡፡

ቅበላና ሽኝት

      የፋይናንስ ተቋማትን የሚመሩና በኃላፊነት ቦታዎች ላይ የነበሩ ሰዎች የተተኩበት፣ ከኢንዱስትሪው መሪነታቸው የለቀቁበትም ዓመት ይኸው 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ጌታሁን ናና፣  የኢትዮጵያ ልማት ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙበት ክስተት አንዱ ነው፡፡ አቶ ጥሩነህ ኢተፋ አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሆነው ሥራ የጀመሩትም በ2009 ዓ.ም. ነው፡፡  

ከኢንዱስትሪው ከተሰናበቡት መካል ደግሞ የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረ፣ ከቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንትነት የለቀቁት አቶ እሸቱ ፋንታዬ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ወጋገንና ደቡብ ግሎባል ባንክም አዳዲስ ምክትል ፕሬዚዳንቶችን የተሰየሙበት ዓመት ነበር፡፡

ኢንዱስትሪውን በማገልገላቸው ለፋይናንስ ባለሙያዎች ዕውቅና መስጠት የተጀመረውም በ2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ በመሆኑም የመጀመርያውን ዕውቅና ያገኙት አቶ ጌታሁን ናና ሲሆኑ፣ ይህንንም ሽልማት ከብሔራዊ ባንክ ገዥው አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ተቀብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር በበኩሉ ከኢንዱስትሪው ለተሰናበቱ ፕሬዚዳንቶች ዕውቅና በመስጠት ጅምሩን ቀጥሏል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ብሔራዊ ባንክም በተጨማሪነት ለሦስት የዘርፉ ተዋናዮች ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ እንዲህ ያሉ ፕሮግራሞች የፋይናንስ ተቋማት ተቀራርበው እንዲመክሩ የሚጋዝ መልካም ተግባር እንደሆነም ገዥው ባንክም ሆነ የሚቆጣጠራቸው ባንኮች ያወደሱት ጅምር እንደሆነም ታይቷል፡፡

ትልቅ ካፒታል

አብዛኞቹ የአገሪቱ የግል ባንኮች ካፒታላቸውን ለማሳደግ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ በ2009 በጀት ዓመት ወቅት ከግል ባንኮች ውስጥ ከፍተኛ ካፒታል ለማስመዝገብ ውሳኔ ያሳለፉት የአቢሲኒያ ባንክ ባለአክሲዮን ናቸው፡፡ የባንኩ የተፈቀደ ካፒታል አራት ቢሊዮን እንዲሆን መወሰኑ ተዘግቧል፡፡

ኤቲኤሞች

በአሁኑ ወቅት ልማት ባንክ ሳይጨምር 17ቱም ባንኮች የኤሌክትሮኒክ የክፍያ ማሽን (የኤቲኤም) አገልግሎት ጀምረዋል፡፡ የኤቲኤም አገልግሎት ያልነበራቸው ባንኮች የኤቲኤም ባለቤት መሆን የቻሉት በ2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ በመሆኑም ሁሉም ባንኮች ባለኤቲኤም ለመሆን በቅተዋል፡፡ በአገሪቱ በሁሉም ባንኮች መጠቀም የሚያስችለው የክፍያ አገልግሎት የተጀመረውም በተሸኘው ዓመት ነበር፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ቪዛ ካርድ ዓይነት አገልግሎት የሚሰጠውና ‹‹ኢትዮ ፔይ›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው የካርድ ክፍያ ዘዴ ይፋ በ2009 ዓ.ም. ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል፡፡

ፋይናንስ ተቋማትን ከተመለከቱ ክስተቶች ውስጥ ንብ ባንክ በ680 ሚሊዮን ብር አንድ ሕንፃ መግዛቱ የሚጠቀስ ነው፡፡ የንብ ኢንሹራንስ ሕንፃ ግንባታ ግዥም አነጋገሪ ከሚባሉ ክስተቶች መካከል ይመደባል፡ ኦሮሚያ ኢንሹራንስና ቡና ባንክ የራሳቸውን ሕንፃ ለመገንባት መሠረት አስቀምጠዋል፡፡ ‹‹የፋይናንስ ዲስትሪክት›› እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፣ ዋና መሥሪያ ቤቶቻቸውን የሚያስገነቡት ሕብረት ባንክ፣ ንብና ዘመን ባንክ የግንባታ ሥራቸውን በማከናወን ላይ ከሚገኙት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ ናይል ኢንሹራንስም የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታውን ከግማሽ ምዕራፍ በላይ አጠናቋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ እንደሚሆን የሚጠበቀውን ባለ 42 ወለል ሕንፃ የሚያስገነባው ንግድ ባንክም፣ የግንባታውን ምዕራፍ ወደ 45 በመቶ አድርሷል፡፡ ወጋገን ባንክ በበኩሉ ዋና የመሥሪያ ቤቱን ሕንፃ አጠናቆ በአዲሱ ዓመት ወደዚሁ ሕንፃ በመግባጽ ሥራ እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡ ሕብረት ኢንሹራንስ በቃሊቲ የሚገኘውን ሕንፃ አጠናቆ ለማስመረቅ ተዘጋጅቷል፡፡

27 በመቶና ቦንድ ግዥ

የግል ባንኮች ከሚያበድሩት እያንዳንዱ የብድር መጠን ላይ 27 በመቶውን ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ መሠረት፣ ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ሦስት በመቶ ወለድ የሚታሰብበት ይህ ግዥ፣ አምስት ዓመት ስለሞላው የመጀመርያውን ዓመት ለቦንድ ግዥ ያዋሉትን ገንዘብ ከብሔራዊ ባንክ መውሰድ የጀመሩበት በ2009 ዓ.ም. ነው፡፡ ባንኮቹ ከሚያበድሩት ገንዘብ ውስጥ 27 በመቶውን ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ የሚያዘውን አሠራር ያሻሽል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የማሻሻል ሐሳብ እንደሌለ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የተናገሩበት ዓመት ነበር፡፡

የተበላሸ ብድር

የአገሪቱ ባንኮች የተበላሸ ብድር መጠን እየቀነሰ ቢመጣም መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ግን ከዚህ በተለየ ረድፍ ተሠልፏል፡፡ ምንም እንኳ ባንኩ የፖሊሲ ባንክ እንደመሆኑ መጠን፣ በመንግሥት ልዩ ዕይታ እንደሚሰጠው ቢታወቅም፣ ብሔራዊ ባንክ የተበላሸ የብድር መጠን ከአምስት መብለጥ የለበትም በማለት ለባንኮች ያስቀመጠውን መመርያ በማለፍ፣ የተበላሸ ብድር መጠኑ ወደ 25 በመቶ ማሻቀቡ የተሰማውም በዚሁ በ2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ የልማት ባንክ ዓመታዊ አፈጻጸም በዕቅዱ ልክ እንዳልነበረም ታይቷል፡፡

አስደንጋጩ ክስተት

      ስለፋይናንስ ተቋማት ሲነሳ ስማቸው አብሮ የሚጠቀሰው ታዋቂው ምሁር ወልዳይ አምሓ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ከሙያቸው ጎን ለጎን በኢትዮጵያ ፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ጉልህ ስምና ዝና የነበራቸው፣ በተለይ በማይክሮፋይናንስ ዘርፍ 35 ያህል ተቋማትን ያሰባሰበውን ማኅበር ከመጠንሰስ ጀምሮ በዋና ዳይሬክተርነት በመምራት ያደረጉት አስተዋጽኦ ይታወቃል፡፡ ከአኅጉር አልፈው ከዓለምአቀፍ ተቀባይነትን ያተረፉት የኢኮኖሚ ምሁሩ ወልዳይ (ዶ/ር) ከዚህ ዓለም በድንገተኛ አደጋ ከዚህ ዓለም የመለየታቸው መርዶ የተሰማበት አሳዛኝ ወቅት ሆኗል፡፡ ምሁሩ ሪፖርተር ጋዜጣን ጨምሮ በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘንድ እየቀረቡ የኢኮኖሚ ትንታኔዎችን በማቅረብ ትልቅ አስተዋጽኦ የነበራቸው ሰው ነበሩ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች