በአዲሱ ዓመት ከፀብና ከጥላቻ የፀዳች ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር ማለት አለብን፡፡ ይህ የመልካም ምኞት መግለጫ አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ይሆን ዘንድ በብሩህ ተስፋ መነጋገር ይገባል፡፡ አዲሱ ዓመት ከአሮጌው ዓመት የዞረ ድምር ውስጥ የሚወጣበት፣ ብሩህ ተስፋ የሚፈነጥቅበት፣ ለጠብና ለግጭት መንስዔ የሚሆኑ አጓጉል ድርጊቶች የሚወገዱበት፣ ከኃይል ይልቅ በሰላማዊና በሠለጠነ መንገድ ችግሮች የሚፈቱበት፣ የሕዝብ ጥያቄዎች በአንክሮ ተደምጠው በፍጥነት ምላሽ የሚያገኙበት፣ ለዕልቂትና ለውድመት የሚዳርጉ ፉከራዎች ተገትተው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚረዱ ሰላማዊ መፍትሔዎች የሚመነጩበት፣ በማንነትና ዘር፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በአመለካከት፣ በአኗኗር ዘይቤና በመሳሰሉ ልዩነቶች ላይ የተመሠረቱ አውዳሚ ጥላቻዎች በኢትዮጵያዊነት ጠንካራ የአንድነት ስሜት የሚረቱበት፣ ወዘተ. እንዲሆን ሁሉም ወገኖች ቃል መግባት አለባቸው፡፡ ይህቺ የተከበረች ታላቅ አገርና ይህ የተከበረ ታላቅ ሕዝብ ከምንም በላይ የሚያስተሳስራቸው ትልቅ ፍቅር አለ፡፡ ይህንን ጥልቅና ዘመናት የተሻገረ፣ በመተሳሰብና በመከባበር ላይ የተመሠረተ የጋራ እሴት የሚንዱ አጓጉል ድርጊቶች ለዚህ ዘመን አይመጥኑም፡፡ ከምንም በላይ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ትልቅ መሠረት አለው፡፡ ይህ ነው የሚበልጠው፡፡
አዲሱ ዓመት መጀመር ያለበት በቅንነት ነው፡፡ ሸርና አሻጥር የክፉዎች ድርጊት ነው፡፡ በጥላቻ ውስጥ መዘፈቅና ደም በለበሰ ዓይን መተያየት ኋላቀርነት ነው፡፡ ልዩነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት መነጋገር ወይም መደራደር ሥልጣኔ ነው፡፡ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩዋትን ይህችን የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት አገር፣ በልማትና በዴሞክራሲ ታላቅ የማድረግ ኃላፊነት የእዚህ ትውልድ ነው፡፡ ዘመኑ እጅግ ከመሠልጠኑና በቴክኖሎጂ ከመገስገሱ አንፃር ወደ ቀድሞ ጠመንጃ ነካሽነት አስተሳሰብ ውስጥ መግባት ያስንቃል፡፡ አገር የጋራ እንደ መሆኗ መጠን በሁለንተናዊ ጉዳዮች በያገባኛል መንፈስ ለመሳተፍ፣ አንዱ ሰጪ ሌላው ተቀባይ መሆን የለበትም፡፡ በእኩልነትና በሰጥቶ መቀበል መርህ እየተነጋገሩ ልዩነትን አቻችሎ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመነጋገር የሚያስችለውን ጥርጊያ ማመቻቸት፣ የሁሉም ዜጎች መብትም ግዴታም መሆን አለበት፡፡ በተለይ ደግሞ ለአገራቸው ማንኛውንም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል የሚፈልጉና በሙሉ ፈቃደኝነት የሚቀርቡ ዜጎች መቼም ቢሆን ሊገለሉ አይገባም፡፡ አዲሱ ዓመት ሲጀመር መንግሥት ልብ ማለት የሚገባው የሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ እንዲያገኙ፣ አቅጣጫቸውን እየሳቱ አላስፈላጊ ችግሮች እንዳይፈጠሩና ከዚህ ቀደም ያጋጠሙ ፈተናዎች ገጽታቸውን ቀይረው እንዳይከሰቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሕዝብን ማዳመጥ ነው፡፡ ለሚነሱ ጥያቄዎች በሙሉ ምላሹ ምን መሆን እንዳለበት የሚያውቀው ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ የአርቆ አስተዋይነትና የማስተዋል ፀጋዎች ባለቤት ነውና፡፡
በኢትዮጵያ ምድር ካሁን በኋላ ደም መፍሰስ የለበትም፡፡ ዜጎች በሰበብ አስባቡ እስር ቤት መወርወር የለባቸውም፡፡ ሐሳባቸውን በመግለጻቸው ብቻ ለእንግልት ሊዳረጉ አይገባም፡፡ ለስደት የሚዳርጉ ብልሹ አሠራሮች መቆም አለባቸው፡፡ ዘራፊዎችና ሕገወጦች በሕግ ሊዳኙ ይገባል፡፡ ሕገወጥነት ከመወገዝ አልፎ በተግባር በቃ መባል ይኖርበታል፡፡ ሥልጣንን ያላግባብ መገልገልና ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማፈን መቆም አለበት፡፡ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያንን ክብር የሚያጎድፉ ድርጊቶች ይበቃቸዋል፡፡ በስመ ሥልጣን ፈላጊነት ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር የሚዶልቱ ኃይሎች አደብ ይግዙ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ሰላምና መረጋጋት ጠፍቶ ጦርነት እንዲቀሰቀስ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ኃይሎችም ከመወገዝ በተጨማሪ ይበቃል መባል አለባቸው፡፡ እናት አገር ኢትዮጵያ የተጣሉና የተኳረፉ ልጆቿ ወደ ጠረጴዛ ውይይት እንዲመጡና በዴሞክራሲያዊ መንገገድ እንዲደራደሩ ያገባናል የሚሉ ዜጎች በሙሉ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ችግሮቹን የሚፈታባቸው የእርቅና የሽምግልና ሥርዓቶች አሉ፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ከበሬታ ያገኙ የዕድሜ ባለፀጋዎችና ነገር አዋቂዎች የሚሳተፉባቸው ምሥጉን ሥርዓቶች ናቸው፡፡ ይህንን የመሰለ ፀጋና በረከት ባላት አገር ውስጥ ትልልቅ ሰዎች የጠፉ ይመስል፣ ለዓመታት በጥላቻና በቂም በቀል ውስጥ መኖር ያሳዝናል፡፡ በተለይ ይህ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከታቸው የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች በአዲሱ ዓመት በብርቱ ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ግትርነት፣ ጨለምተኝነት፣ ራስ ወዳድነት፣ አምባገነንነትና ክፋት የሞሉት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከያዘው ፅኑ ደዌ የሚገላገለው፣ የኢትዮጵያዊነትን የጋራ እሴቶች ሲያከብርና የዓመታት ስህተቱን ሲያርም ብቻ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገሪቱ ሥልጣን የመጨረሻው ሉዓላዊ ባለቤት ነው፡፡ ይህንን የተከበረ ሕዝብ ለማክበር የጋራ እሴቶቹን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የጋራ እሴቶቹ ዘር፣ እምነት፣ ባህል፣ ቋንቋን፣ አመለካከትና የመሳሰሉት ሳይገድባቸው በመፈቃቀርና በመከባበር ዘመናትን አሻግረውታል፡፡ በአንድ የአውሮፓ ኮሎኒያሊስት ኃይል ላይ ከተጎናፀፈው ታላቁ የዓደዋ የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት ድል በተጨማሪ፣ ለዘመናት ወረራ የቃጡበትን ሁሉ አሳፍሮ መመለስ አስችለውታል፡፡ ይህ የተከበረ ሕዝብ ልዩነቶች መኖራቸው እስኪዘነጋ ድረስ ተጋብቶና ተዋልዶ በፍቅር አብሮ ኖሯል፣ አሁንም እየኖረ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንና መስጊድ ጎን ለጎን የሚኖሩት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን አዲስ ዓመትን ጨምሮ በጋራ ከሚያከብሯቸው ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት በተጨማሪ ገበታቸው አንድ ላይ ነው፡፡ እነዚህን አስገራሚ የጋራ እሴቶች ተምሳሌት ማድረግ ሲገባው ተልከስክሶ የቀረው የፖለቲካ ኃይሎች እሰጥ አገባ፣ ካሁን በኋላ ከዚያ የስህተት አረንቋ ውስጥ መውጣት አለበት፡፡ ፖለቲካው በማኅበራዊ ሚዲያዎች ውስጥ በመሸጉ ከንቱዎች ወጀብ እየተገፋ በዘርና በሃይማኖት ወጣቱን ትውልድ እየበከለ ስለሆነ፣ ከዚህ በኋላ ለህልውናው ሲል መስመሩን ሊይዝ ይገባል፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ኃይልም ሆነ በተቃውሞ ጎራ የተሰባሰበው ኃይል ለዓመታት ከተዘፈቁበት ጥላቻ ውስጥ በመውጣት ለሕዝብ ፈቃድ ይገዙ፡፡ ዋናው ዳኛ እሱ ብቻ ነው፡፡
መንግሥት አገርን ከመጠበቅና ሕዝብን ከማስተዳደር ጎን ለጎን እስካሁን ያደረገውን ጉዞ ሲገመግም የሚረሳቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ዋናው የሕግ የበላይነት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ማለት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል እንደሆኑ በተግባር ማረጋገጥ ነው፡፡ ሕገወጦች በሕግ ተጠያቂ ሲሆኑ፣ ንፁኃን ደግሞ የሕግ ከለላ የማግኘት መብት አላቸው፡፡ የአገር ሀብት በመመዝበር ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የሚውሉ እንዳሉ ሁሉ፣ ያንኑ ድርጊት ፈጽመው ዝም የሚባሉ አሉ፡፡ ሕዝብ ለምን ይላል፡፡ ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡ በብልሹ አሠራር ሕዝብን የሚያሰቃዩ ከኃላፊነታቸው ተነስተው በሕግ መጠየቅ ሲገባቸው ለሌላ ሹመት ይታጫሉ፡፡ ለምን? በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብርና ደንታ ሳይኖራቸው የራሳቸውን ጥቅም የሚያጋብሱ፣ ብቃት ሳይኖራቸው ሹመት የሚደረብላቸው፣ ከሥነ ምግባሩም ሆነ ከሞራሉ ኢምንት ያልታደሉ፣ የዜጎችን መብትና ነፃነት የሚደፈጥጡ፣ በዚህች ታላቅ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ የማይፈልጉ፣ ፍትሕን የሚደረምሱ፣ ወዘተ. በየሥፍራው ሞልተዋል፡፡ እነዚህ ኃይሎች የሕግ የበላይነት ልጓም ካልተደረገላቸው አገር ያጠፋሉ፡፡ እነዚህን እስከ መቼ ታቅፎ መኖር ይቻላል? በሌላ በኩል በሕገ መንግሥቱ ሥልጣን ላይ መውጣት የሚቻለው በነፃ፣ ፍትሐዊና እውነተኛ ምርጫ መሆን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ እስካሁን በተካሄዱት ምርጫዎች ላይ አገራዊ ስምምነት የለም፡፡ በአዲሱ ዓመት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ብቻ መሥራት ይቻላል? ወይስ ችግር አለ? ችግር መኖር የለበትም፡፡ የሕግ የበላይነትን ማስከበር የሚቻለው የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ መንግሥት ማስከበር ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ሌላው ዕዳው ገብስ ነው፡፡
እናት አገር ኢትዮጵያ ከፍ ብላ አምራና ደምቃ የምትታየው ዴሞክራሲም እንደ ልማቱ ሲሳለጥ ብቻ ነው፡፡ ግማሽ ጎፈሬ ግማሽ ልጩ መሆን አይቻልም፡፡ ለዚህ ደግሞ መሠረቱ ካሁኑ መጣል አለበት፡፡ መንግሥት የተዘጋጋውን ምኅዳር ይክፈት፡፡ የነፃነት በሮች ወለል ብለው ይከፈቱ፡፡ የሲቪክና የዴሞክራሲ ተቋማት በነፃነት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ይደረጉ፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት ይንቀሳቀሱ፡፡ ዜጎች ሐሳባቸውን በነፃነት ይግለጹ፡፡ በነፃነት ይደራጁ፡፡ በፈለጉበት ሥፍራ በነፃነት ተንቀሳቅሰው ሥራቸውን ያከናውኑ፡፡ ይህ ዕውን መሆን ሲጀምር ሁሉም ወገኖች በኃላፊነት መንፈስ ግዴታቸውን ይወጣሉ፡፡ ከሕገወጥነት ይልቅ ሕጋዊነት፣ ከሥርዓት አልበኝነት ይልቅ ሥነ ሥርዓት፣ ከገጠመኝ ይልቅ መርህ፣ ከግዴለሽነት ይልቅ ኃላፊነት፣ ከስሜታዊነት ይልቅ ምክንያታዊነት፣ ከኢሞራላዊ ድርጊቶች ይልቅ ሥነ ምግባር፣ ወዘተ. የአገር ልማድና ባህል ይሆናሉ፡፡ ሞጋችና ጠያቂ ትውልድ በሰከነ መንገድ መብቱን እየጠየቀ ግዴታውን ይወጣል፡፡ ሌብነትና ዘረፋ በሕግ አደብ ይገዛሉ፡፡ አሉባልታና ሐሜት ከአሳፋሪው የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ በነው ይጠፋሉ፡፡ ዘርፈ ብዙ ጠቃሚ ሐሳቦች በነፃነት ለውይይትና ለክርክር ይቀርባሉ፡፡ በነፃነት ማሰብ የአገር ባህል ሲሆን፣ አስደማሚ የሆኑ ለዕድገት የሚበጁ ሐሳቦች ይፈልቃሉ፡፡ ሕዝብ ይበጀኛል ያለውን ይይዛል፡፡ የማይፈልገውን ይተዋል፡፡ አገር ሰላም ትሆናለች፡፡ ዴሞክራሲ በእርግጥም ሥርዓት ይሆናል፡፡ ዜጎች በፍትሐዊ መንገድ ከሀብት፣ ከትምህርት፣ ከሥልጣንና ከተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ይሳተፋሉ፡፡ የዜግነት ግዴታቸውን ይወጣሉ፡፡ ለዓለም ጥቁሮች ተምሳሌት የነበረችው ታላቋ ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ታላቅነቷ ትመለሳለች፡፡ ያኔ የከፍታዋ ዘመን ዕውን ይሆናል፡፡ ይህ ምኞት ይሳካ ዘንድ ግን አዲሱ ዓመት ከዘመናት ጎታች አስተሳሰቦች መላቀቅ አለበት፡፡ የከፍታው ዘመን ዕውን መሆን የሚችለው በኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴቶች ላይ ብቻ ነው!