ኢትዮጵያ የሕዝቧ ቁጥር 100 ሚሊዮን እንደደረሰ ቢነገርም የአገሪቱን ሁለንተናዊ ችግሮች ስር ነቀል በሆነ ሁኔታ ሊቀይር የሚችል ተመራማሪ ዜጋ በማፍራት በኩል ውስነነቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በአገሪቱ ከ30 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፣ ነጥሮ የወጣና አገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ሊያደርጋት የሚችል የተማረ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ግን ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም እየታዩ ካሉት ተስፋ ሰጭ ጭላንጭሎች መካከል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አማካይነት እየተሠራ ያለው ምርምር አንዱ ነው፡፡
ከተቋቋመ ከስድሳ ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ዩኒቨርሲቲው እስከዛሬ ድረስ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በተለያዩ የሙያ መስኮች አስመርቆ ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች 4,340 ወንድና 2,196 ሴት በድምሩ 6,536 ተማሪዎችን ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ባስመረቀበት ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ደሳለኝ መንገሻ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት በተከታታይ በተደረጉ ምርምሮች ከአፈርና ከሌሎች ግብዓቶች ነዳጅ ለማምረት የሚያስችል ምርምር በማካሄድ ከአዕምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የፈጠራ ባለቤትነት ሰርተፍኬት ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡
ከተመራቂ ተማሪዎች ከተሠሩ ዋና ዋና የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች መካከል አንዱ የተማሪ አቡሃይ ውብሸት ነው፡፡
ተመራቂው አቡሃይ ተወልዶ ያደገው ሰሜን ጎንደር ጃን አሞራ ሲሆን፣ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም እዚያው አጠናቋል፡፡ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በክረምት መርሐ ግብር በባዮሎጂ ትምህርት በመምህርነት ሙያ በዲፕሎማ ከተመረቀ በኋላ ተወልዶ ወዳደገበት ማኅበረሰብ በመሄድ የአስተማሪነት ሙያን ተቀላቅሏል፡፡
ጃን አሞራ ወረዳ በሚገኘው የገጠር ቀበሌ አስተማሪ ሆኖ ሲቀጠር ደስተኛ እንደነበር ያስረዳል፡፡ ሰውን የሚያክል ፍጡር መቅረጽ እጅግ የሚያስደስት ሙያ ሆኖ ቢያገኘውም በአካባቢው ያለው ሁኔታ ግን ደስታ ሊሰጠው አልቻለም ነበር፡፡ በአካባቢው መብራት ባለመኖሩ እሱን ጨምሮ የአካባቢው ማኅበረሰብ ችግር እንዴት ነው የሚፈታው እያለ በውስጡ ያወጣ ያወርድ እንደነበር ያስረዳል፡፡ ለዚህ ማኅበረሰብ የሚሆን ነዳጅ የሚያቀርብም አንድ ነጋዴ ብቻ ስለነበር ነጋዴው ነዳጅ ካላመጣ የአካባቢው ማኅበረሰብ በሙሉ በጨለማ ያድር እንደነበርም ይገልጻል፡፡ ነጋዴው ዕድል ቀንቶት ነዳጅ ካመጣ ደግሞ ዋጋውን ይቆልልና የአካባቢው ማኅበረሰብ ለመግዛት ይቸገር እንደነበር ያብራራል፡፡ ይህ ሁሉ ችግር በመጨረሻም መፍትሔ እንደወለደ ይናገራል፡፡ የሙያው አጋር የሆኑትን ሦስት ጓደኞቹን በመያዝ በአካባቢው ከሚገኝ ቆሻሻና የበሰበሰ ነገር ነዳጅ ማምረት እንዳለባቸው ያግባባቸዋል፡፡ ከእሱ ጋር አራት ሆነው የምርምር ሥራ ይጀምራሉ፡፡ በምርምር ሥራቸው ላይ ብዙም ውጤታማ ሊሆኑ ባለመቻላቸው ሦስቱ ጓደኞቹ ተስፋ በመቁረጥ ከምርምሩ ራሳቸውን ማግለላቸውን ያስታውሳል፡፡
አቡሃይ ለችግሮች እጅ ሳይሰጥ፣ ለፈተናዎች ሳይንበረከክ ምርምሩን እንደቀጠለ ያብራራል፡፡ አፈሩን ወደ ነዳጅ ለመቀየር ያደረገው ጥረት ተስፋ ሊሰጠው ስላልቻለ ወደሌላ ምርምር በመሻገር በአካባቢው በቀላሉ የሚገኝን በቆሎ ወደ ነዳጅ ለመቀየር አሁንም ሙከራውን ቀጠለ፡፡ የተለያዩ የፍተሻ መሣሪያዎችን በመሥራት በቆሎን ወደ ነዳጅ ለመቀየር ወጥቷል፣ ወርዷል፡፡ ይህ የምርምር ሥራ በቀላሉ ሊሳካ እንደማይችል ሲረዳ ለነገ ያቆይና ወደሌላ የምርምር ሥራ ይገባል፡፡
በቆሎን በመስመር የመዝራት ሒደት ቀላልና ጉልበት ቆጣቢ ለማድረግ በአንድ ፈረስና በአንድ ሰው፣ ወይም በሁለት በሬና በአንድ ሰው ብቻ በአንድ ጊዜ በቆሎና ማዳበሪያውን እየዘራ የሚሄድ የፈጠራ ሥራ እንደሠራ ይናገራል፡፡ ይህ የፈጠራ ሥራው ውጤታማ ሆኖ ለሽልማትና ለዛሬው ስኬቱ እንዳደረሰውም ይገልፃል፡፡ በዚህ ሥራውም በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማረያም ደሳለኝ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንንና በቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አያሌው ጎበዜ እጅ እንዲሸለም ያደረገው መሆኑን ያስረዳል፡፡
የተመራቂውን አቡሃይ የፈጠራ ሥራና መልካም ጅማሮ ያየው ጎንደር ዩኒቨርሲቲም ነፃ የትምህርት ዕድል ሰጥቶት የመጀመሪያ ዲግሪውን በኬሚስትሪ ትምህርት እንዲማር አድርጓል፡፡ ዘንድሮ ለመመረቅም በቅቷል፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲን ሲቀላቀል የፈጠራ ሥራውን መጀመሪያውኑ ጀምሮት የነበረውን ከብስባሽ ነገሮች ነዳጅ የማምረት ምርምሩን ቀጠለ፡፡ በዚህም የተነሳ የምርምር ሥራው ውጤታማ ይሆን ዘንድ የዩኒቨርሲቲውን ፕሮፌሰር ብርሃኑ አንዷለምን መድቦለት መሥራት እንደጀመረ ይገልጻል፡፡
ከተለያዩ ኦርጋኒክ ቁስ አካሎች ነዳጅ በምን ዘዴ ሊመረት እንደሚችል ይረዳል፡፡ ‹‹ከብስባሽ ነዳጅ ለማምረት ችለናል፡፡ ይህ ነዳጅ በተለያዩ ተሽከርካሪዎች ተፈትሾ ውጤታማ ሆኗል፤›› በማለት ያብራራል፡፡
አቡሃይ ከኦርጋኒክ ቁስ አካሎች ነዳጅ ብቻ ሳይሆን የመኪና ባትሪ መሙላት፣ ለሽንት ቤት የሚሆኑ የቆሻሻ ማፅጃ ኬሚካሎችንና የሞባይልና የላፕቶፕ ባትሪዎችን እንደገና በማደስ የፈጠራ ሥራ መሥራቱን ይናገራል፡፡
ነዳጁን ለማምረት በግብዓትነት የሚጠቀማቸውን ኦርጋኒክ ቁስ አካሎች የሚያገኘውም ከጃን አሞራ፣ ከበየዳ፣ ከጸለምት፣ ከአዳርቃይ፣ ከደብረ ታቦር፣ ከአፋር፣ ከመተማና ከጭልጋ አካባቢዎች እንደሆነ ያስረዳል፡፡
‹‹ይህ የተለያየ ብስባሽ የአፈር ዓይነት ከበሰበሰ በኋላ የተዘጋጁ ማሽኖች አሉን፡፡ አንዱ ማሽን ዲኮምፓዝ፣ ሁለተኛው ፈርመንት፣ ሦስተኛው ዲስትል ያደርጋል፣ አራተኛው ኩል አድርጎ ያወጣል›› በማለት የተለያዩ ቅሬተ አካል የሆነውን ብስባሽ እንዴት ወደ ነዳጅነት ሊቀየር እንደሚችል ለሪፖርተር አብራርቷል፡፡
‹‹ነዳጅ የሚሆነውን ኦርጋኒክ አካል ማግኘት የቻልኩት በ135 የአፈር ዓይነቶች ላይ ምርምር ካደረግኩ በኋላ ነው›› ይላል አቡሃይ፡፡ ‹‹135 የአፈር ዓይነቶች ላይ ምርምር አድርጌ 136ኛው የአፈር ዓይነት ማለትም ኦርጋኒክ ቁስ አካል ያለው ለማቀነባበሪያነት ወዳዘጋጀነው ማሽን ስናስገባው ነዳጅ መሆን ቻለ›› በማለት በምን ሁኔታ ነዳጁን ማምረት እንደቻለ ያብራራል፡፡
ይህ ነዳጅ መሆን የቻለው ብስባሽ አካል በተፈጥሮው መቀጣጠል የሚችል፣ ቅባት ያለው፣ ገበሬው ለእርሻ የማይጠቀምበት እንደሆነም አስረድቷል፡፡
አቡሃይ ይህንን ቅሬተ አካል ተጠቅሞ ነዳጅ በማምረትና የተመረተውን ነዳጅ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ባሉ ተሽከርካሪዎች ሙከራ ተደርጎበት ስኬታማ ቢሆንም፣ አሁንም የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ይዘረዝራል፡፡ ‹‹አሁን ያገኘነው ከእነዚህ አካላት እንዴትና በምን ሁኔታ ነዳጅ ማግኘት እንደሚቻል እንጂ ሌሎች የሚቀሩ ጥናቶች አሉ›› ብሏል፡፡ አቡሃይ ነዳጁን ከእነዚሀ አካላት ማምረት በመቻሉ ከአዕምሮዓዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የፈጠራ ባለቤትነት ሰርተፍኬት ማግኘቱንም ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡
ይህን የምርምር ሥራ በተመለከተ ሪፖርተር በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ ትምህርት አስተባባሪና ተመራማሪው ብርሃኑ አንዷለም (ፕሮፌሰር) አነጋግሯል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገለጻ፣ አቡሃይና እሳቸው ምርምር ላይ እየሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲያቸው ሰፋ ያሉ የምርምር ፕሮጀክቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ከዚያ ውስጥ የዕፁዋትና እንስሳት ቅሪት የሆኑትን ብስባሾች ወደ ነዳጅነት መቀየር መቻላቸውን አብራርተዋል፡፡
ብዙውን ጊዜ ከአፈር ጋር የተዋሐደ የከብት ፍግ፣ ከከተማ ቆሻሻ እንዲሁም ደግሞ የብዙ ዕፀዋት ብስባሽ፣ ራስ ዳሽን አካባቢ የሚገኙት አፈር የሚመስሉ ነገሮች በሙሉ ኦርጋኒክ ቁስ አካሎች ስለሆኑ ነዳጅ መሆን እንደሚችሉ አስተባባሪው አብራርተዋል፡፡ አፈር ኦርጋኒክ ይዘቱ ከአምስት በመቶ በታች ስለሆነ ነዳጅ ሊሆን እንደማይችልም አብራርተው ብስባሽ አካሎች ደግሞ 56 ከመቶ የሚሆነው ኦርጋኒክ ያላቸው በመሆኑ ወደ ነዳጅነት ሊቀየሩ እንደሚችሉ ተመራማሪው ግልጽ አድርገዋል፡፡
‹‹እንግዲህ የእኛ የምርምር ውጤት ያ ጥሬ ዕቃ ወደ ነዳጅነት የሚቀየርበትን ዘዴ ነው ያገኘነው›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ‹‹ያንን ዘዴ ልጁ መጀመሪያ ይዞት ከመጣው አሁን ቀይረን ወደ ላብራቶሪ ውስጥ አስገብተን ውጤት አሳይተናል፤›› ብለዋል፡፡
ተመራማሪው ባሁኑ ጊዜ ከላብራቶሪ ወደ ኢንዱስትሪ የሚሸጋገርበትን ዘዴ እያጠኑ መሆኑን ገልጸው፣ ምርት ላይ ለመድረስ ግን አሁንም ገና ብዙ መሠራትና መታወቅ ያለበት ነገረ እንዳለ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይህንን የምንሠራበት አንዳንድ የማምረቻ ዘዴ ሠርተን ከጨረስን በኋላ ‹‹ፓይለት ስተዲ›› የሚባል አለ፡፡ በኢንዱስትሪና በላብራቶሪ መካከል የሚሠራ፡፡ አሁን እሱን ለመሥራት እየተዘጋጀን ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡
ይህ ነዳጅ በተሽከርካሪዎች ላይ ተሞክሮ እንደሚሠራ የሚናገሩት ተመራማሪው፣ ‹‹በኢትዮጵያ ፔትሮሊየም ኢንተርፕራይዝ የኬሚካል አናሊስስ አሠርተን ከውጭ ከሚገባው ነዳጅ ጋር ተመሳሳይ ነው›› ብለዋል፡፡ ስታንዳርዱን ስናየው በነዳጅ ስታንዳርድ ውስጥ ነው ያለው በማለት ትክክለኛ ነዳጅ ማምረት መቻላቸውን አብራርተዋል፡፡
‹‹በጥቅሉ ነዳጅ እያልን እንጠራለን እንጂ ያለው ሦስት ዓይነት ነው፡፡ ለከባድ መኪና የሚሆነውና ዲዝል የሚባለው፣ በተለምዶ ቤንዚን እያልን የምንጠራው፣ ለአውሮፕላን የሚያገለግለው ጋዞሊን እና ኬሮሲን ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ በጥቅል ደግሞ ፔትሮሊየም ተብለው እንደሚጠሩ ገልጸዋል፡፡
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ከውጭ በማስመጣት አገሪቱን ለከፍተኛ ወጭ የሚዳርጋትን ነዳጅ በአገር ውስጥ ማምረት የሚቻልበት ዕድል ሰፊ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአጠቃላይ ፐሊመርስ የምንላቸው ነገሮች በተለይ ፕሮቲንና ካርቦሃይድሬት ያላቸው ቁሶች ከበሰበሱና ወደሌላ ነገር ከተቀየሩ የነዳጅ ጥሬ ዕቃዎች እነደሆኑ ግልጽ አድርገዋል፡፡ በየከተማው የሚገኘው ቆሻሻም ነዳጅ የማይሆንበት ነገር እንደሌለ አስረድተዋል፡፡