Saturday, April 1, 2023

በመንግሥት አሠራር ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ማሳደር የተሳነው ሚዲያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በተጠናቀቀው ዓመት መንግሥት በተወሰኑ በኃላፊነት ደረጃ በሚሠሩ የመንግሥት ሠራተኞችና የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ላይ የጀመረው የሙስና ምርመራን ጨምሮ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመንግሥት መዋቅርና አሠራር ላይ ጉልህ ክፍተት ስለመኖሩ በርካታ መረጃና ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡ የዋናው ኦዲተር የአቶ ገመቹ ዱቢሶ ሪፖርቶችና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎች በራሳቸው፣ በርካታ የአስፈጻሚው አካል ክፍተቶችንና የሕግ አግባብነት የሌላቸው ድርጊቶችን ለአደባባይ አብቅተዋል፡፡

በሌሎች አገሮች ሚዲያው እንኳን እንዲህ በይፋ የተገለጹ የተደራጁ የመንግሥት አካላት ሪፖርቶችን አግኝቶ፣ ማንነታቸው ያልተገለጸ ግለሰቦች ያደረሱትን ጥቆማ መሠረት አድርጎ የሚሠራው የምርመራ ዘገባ በአገሮቹ ሁለንተናዊ ሕይወት ላይና በመንግሥት አሠራር ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ሲፈጥር ማየት የተለመደ ነው፡፡

በአንፃሩ ሚዲያ በመንግሥት እንቅስቃሴዎች ላይ ነፃ የሆነ ዘገባ በማቅረብ፣ የተለያዩ ወሳኝ አጀንዳዎችን ለውይይት በማቅረብና የመንግሥትን ጥፋቶች በማጋለጥ በኢትዮጵያ ያደረገው አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል ባይሆንም፣ መሠረታዊ ለውጥ በማምጣት ረገድ ግን ስለተከናወነው ሥራ ማንሳት ግን አስቸጋሪ ነው:: በኢትዮጵያ ያለው ሚዲያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተንሰራፉ የመጡ መሠረታዊ የሀብት ዝርፊያዎችና የመብት ጥሰቶች ሳይስፋፉ በፍጥነት በማጋለጥ ረገድ ያለው ሪከርድ እጅግ በጣም ደካማ የሚባል ነው፡፡

በዚሁ ሐሳብ የሚስማሙት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፣ ‹‹የኮሙዩኒኬሽንና የሚዲያ ዘርፉ የሥርዓቱ አደጋ የሆኑትን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ሙስናን በምርመራ ጋዜጠኝነት ከማጋለጥ አኳያ ከፍተኛ ውስንነት አለበት፤›› ብለዋል፡፡    

ዶ/ር ነገሪ ይህን ያሉት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትና የፍትሕ አካላት ባለሙያዎች ማሠልጠኛ ማዕከል ከነሐሴ 28 እስከ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ በአዩ ኢንተርናሽናል ሆቴል ያዘጋጁትን የሦስት ቀናት ሥልጠና በመክፈቻ ንግግር ሲከፍቱ ነው፡፡ ሥልጠናው በፍትሕ አካላትና በሚዲያ ግንኙነት፣ በመረጃ ነፃነትና ተደራሽነት እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡

ሚኒስትሩ፣ ‹‹በሥልጠናው የኮሙዩኒኬሽንና የሚዲያ ዘርፉን ከመሠረቱ ለመለወጥ ታስቦ ለተጀመረው አገራዊ የሪፎርም ሥራ ግብዓት የሚሆኑ ዓበይት ነገሮች እንደሚገኙ ይጠበቃል፤›› ያሉ ሲሆን፣ ሚዲያው አገሪቱ ልታመጣ የምታስበው ለውጥ አካል ለመሆን ሕገ መንግሥቱንና የበታች ዝርዝር ሕጎችን በተገቢው መንገድ መረዳት እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡ ‹‹የኮሙዩኒኬሽንና የሚዲያ ዘርፉ ከውስጥ ድክመት፣ እንዲሁም ከውጭ በሚደርሱት የተለያዩ ጫናዎች የተነሳ የተለያዩ አመለካከቶች የሚንሸራሸሩበት የውይይትና የክርክር ዓውድ ለመሆን በቅቷል ለማለት አያስደፍርም፤›› ብለዋል፡፡

በሥልጠናው የመንግሥትና የግል ተቋማትን የወከሉ ተሳታፊዎች ሚዲያው በመንግሥት አሠራር ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ለማሳደር እንዳይችል ያደረጉት ውስጣዊና ውጫዊ የሚዲያው ተግዳሮቶች ላይ የተለያዩ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ እርግጥ ነው የአገሪቱ የመንግሥትና የግል የሚዲያ ተቋማት የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች ተመሳሳይነት ቢኖራቸውም መሠረታዊ ልዩነት አላቸው፡፡

በግሉ ሚዲያ ዘርፍ ስኬቶችንና ተግዳሮቶችን በተመለከተ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ነሐሴ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ባዘጋጀው ስብሰባ፣ ዘርፉን ወክለው የቀረቡ ተሳታፊዎች መንግሥት ለግል ሚዲያው የተመቸ በቂ ምኅዳር እንዳልፈጠረ ወቅሰዋል፡፡ ለአብነትም መንግሥት የግል ሚዲያውን አሁንም በአሉታዊ ጎን እንደ አፍራሽ እንደሚያይ፣ የመንግሥት ድርጅቶች ማስታወቂያ የሚሰጡበትና የሚከለክሉበት መሥፈርት ግልጽ እንዳልሆነ፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ኤክስፐርቶች በአስፈጻሚው አካል ተፅዕኖ ሥር ያሉ መሆናቸው፣ የአቅምና የሙያ ሥነ ምግባርን የማክበር ውስንነት፣ የግል የኅትመት ሚዲያ በተለይ አሁን አለ ብሎ ለመናገር እንደሚከብድ፣ አብዛኛዎቹ የብሮድካስት ሚዲያዎች ደግሞ በስፖርትና መዝናኛ ላይ እንደሚያተኩሩ አመልክተዋል፡፡

በአንፃሩ በዕለቱ ጥናት ያቀረቡት ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የመጡት አቶ ደሬሳ ተረፈና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህር ዶ/ር ተሻገር ሽፈራው ዘርፉ ያለውን ጥንካሬና ውስንነት አብራርተዋል፡፡ በዚህም ከውስንነት አንፃር አብዛኞቹ በአዲስ አበባና አካባቢው የተገደቡ መሆናቸውን፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን አስመልክቶ በሚቀርቡ አንዳንድ ፕሮግራሞች የሚመለከታቸው አካላትን እንደማያሳትፉ፣ በበቂ ጥናትና መረጃ ላይ የተመሠረተ የምርመራ ጋዜጠኝነት ፕሮግራሞችን አለማቅረብና የችግሮች መንስዔና መፍትሔን አለመጠቆም እጥረት እንዳለባቸው፣ የይዘት ባህሪ ወጥነት የሚጎድላቸው መሆኑ፣ ብዝኃነት ዓብይ ገጽታ በሆነበት ማኅበረሰብ ውስጥ በውስን ጉዳዮች ላይ ማተኮራቸው ተጠቃሾች መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ደሬሳ በአንዳንድ የንግድ ብሮድካስተሮች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በድፍረት በማቅረብ ረገድ መልካም ጅምር ጥረት መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ የግል ሚዲያው በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉበት ያመለከቱት አቶ ደሬሳ፣ በተለይ መረጃ ከማግኘት መብት ጋር በተያያዘ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማትና ኃላፊዎች መረጃ ሲጠየቁ አለመስጠት፣ የሚዲያ ውይይትና የክርክር መድረክ መሸሽ፣ ሚዲያውን በጥርጣሬ ዓይን ማየት፣ መረጃን አደራጅቶ አለመያዝ፣ ድረ ገጽ አለመኖር ትልቅ ችግር እንደፈጠረ አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥትና የልማት ድርጅቶች ማስታወቂያ ክፍፍል ፍትሐዊ አለመሆኑ፣ ከብሮድካስት ማሠራጫና ከስቱዲዮ መሣሪያዎች ግብዓቶች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቀረጥ መጠየቁና ለዘርፉ ልዩ ልዩ የማበረታቻ ሥርዓት አለመኖር፣ በኅትመት ሚዲያው የኅትመት ግብዓቶች ከፍተኛ ቀረጥ፣ ለዘርፉ ልዩ ልዩ የማበረታቻ ሥርዓት አለመኖር፣ የኅትመት ዋጋ መናር፣ የአከፋፋዮች ጫና፣ የአማተር አሳታሚዎች ድጋፍ ማጣት ከኅትመት እያስወጣቸው መሆኑ፣ በዘርፉ የሚታይ የማስፈጸም አቅም ውስንነት (በአመለካከትና በክህሎት) እና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን የሚሠራ ማዕከል አለመደራጀቱ ሌሎች ተግዳሮቶች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር ተሻገር የግል መገናኛ ብዙኃን ዓብይ ትኩረት የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የማይዘግቧቸውና ገበያው ግን የሚፈልጋቸው ጉዳዮች እንደሆኑም አስገንዝበዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሚያጓድሏቸው የዜና ይዘቶች ላይና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ቢዘግቧቸውም ተደራስያን በዘገባ አንፃርና አተረጓጎም ልዩነት ሊሳቡ በሚችሉባቸው አርዕስቶች ላይ በማተኮር እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡

የግል መገናኛ ብዙኃን በአብዛኛው በአገሪቱ ውስጥ አሉ የሚሏቸውን ከዴሞክራሲ፣ ከፍትሕ፣ ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ፣ ከሙስናና ከአስተዳደር በደሎች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ አተኩረው እንደሚሠሩም ዶ/ር ተሻገር ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም ዘገባዎቹ የተሟላ መረጃና የሁሉንም ባለጉዳዮች ሐሳብ ከማካተት አንፃር ጉልህ ችግሮች እንሚታዩባቸዋል ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡ የግሉ ሚዲያ የማኅበረሰቡን ፍላጎቶች የማያሟሉ፣ የተዛቡና የመረጃ ጉድለት የሚታይባቸውና የአስተያየት ጭነት የሚበዛባቸው ዘገባዎችን እንደሚያቀርብም አመልክተዋል፡፡

‹‹ከተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መረጃ ማግኘት ከባድ ፈተና በመሆኑ ብዙ የግል መገናኛ ብዙኃን በከፊል የበሰለ ወይም ያልተሟላ ዘገባ እንዲያቀርቡ አስገድዷቸዋል፡፡ በእርግጥ መረጃ በተቀላጠፈ ሁኔታ የማግኘት ችግር በግል መገናኛ ብዙኃን ላይ የበረታ ችግር ቢሆንም፣ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞችም የችግሩ ተጋሪዎች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር ተሻገርና አቶ ደሬሳ በአዳማው ሥልጠናም ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በሥልጠናው ላይ እነዚህ ምክንያቶች ሚዲያው በሚጠበቀው ደረጃ ውጤታማ እንዳይሆን በከፊል አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን አስገንዝበዋል፡፡ ዶ/ር ተሻገር በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ ጥናት አቅርበዋል፡፡ የምርመራ ጋዜጠኝነት በምርምር፣ ጠልቆ በመቆፈር፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሰዎች ጋር ቃለ መጠይቅ በማድረግና አቀናጅቶ በመጻፍ እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡ በአብዛኛው በሙስና፣ የሕዝብ ሀብትን በሕገወጥ መንገድ ጥቅም ላይ በማዋል፣ ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀም፣ በሕገወጥ እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የሚያተኩር መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ለእነዚህ ችግሮችና ወንጀሎች ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትና በእነሱ ዙርያ የተሰባሰቡ ግለሰቦች መረጃና ማስረጃ ለመደበቅና ለማጥፋት እንደሚሞክሩም ጠቁመዋል፡፡ ከፋ ካለም በምርመራ ዘገባው ላይ በተለያየ ደረጃ የሚሳተፉ ጋዜጠኞችን ደኅንነትና ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚጥሉም አመልክተዋል፡፡

የምርመራ ዘገባ ውስብስብ በመሆኑ ቢያንስ ረዘም ያለ ጊዜ፣ በርከት ያለ ሀብትና ወጪ፣ ዕውቀትና የረጅም ጊዜ የሥራ ልምድ ያለው የሰው ኃይል ቡድን እንደሚጠይቅም ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ለየት ያሉ ባህሪያትን ተቀብሎ መሥራት በኢትዮጵያ ላሉ ብዙ የሚዲያ ተቋማት አዳጋች እንደሆነና የምርመራ ጋዜጠኝነት በተወሰነ ደረጃ ቢሞከርም በአገሪቱ ብዙም የተለመደ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡ በተለይ ደካማ የኢኮኖሚ አቅም ላላቸው የግል የሚዲያ ተቋማት ይህ ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአገሪቱ ያለው የመረጃ ተደራሽነትና የተጠያቂነት ደካማ ባህል እንዲሁም የመንግሥት ቁርጠኝነት ማነስ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡

ተሳታፊዎች የምርመራ ጋዜጠኝነት የአገሪቱ ሚዲያ መደበኛ መገለጫ እንዳልሆነ ተስማምተዋል፡፡ ይሁንና ይህ ዕውን ያልሆነው ሚዲያው ውስጥ ባሉ ችግሮች ብቻ እንዳልሆነ ተከራክረዋል፡፡ የሀብትና የሰው ኃይል ችግር የሌለባቸው የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ውስጥ ተጀምረው የነበሩ የምርመራ ዘገባዎችን በመደበኛነት የሚያስተላልፉ እንደ ‹‹ዓይናችን›› ያሉ ፕሮግራሞች የተቋረጡት፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ግለሰቦች ተፅዕኖ መሆኑ ለዚህ ክርክር አንዱ ማሳያ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የሥራ አፈጻጸም የቆመለትን ዓላማ የማይወክል፣ የሕዝብ ድምፅ ከመሆን ይልቅ በባለሥልጣናት የሚታዘዝ መሆኑን በመግለጽ የሰላ ትችት እንደሰነዘረበትም ይታወሳል፡፡ ፓርላማው ይህን ትችት የሰነዘረው ሚያዝያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. የኮርፖሬሽኑን የሥራ ኃላፊዎችና የቦርድ አመራሮች ፓርላማ እንዲቀርቡ በጠራበት ወቅት ነው፡፡ የምክር ቤቱ አባላት ኮርፖሬሽኑ የሚያቀርባቸው ዘገባዎች የተመዘገቡ ውጤቶችን ብቻ የሚያጎሉና የኅብረተሰቡን ችግሮች የማይዳስሱ መሆናቸውን በማንሳትም ተችተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በወር 18 ሚሊዮን ብር የደመወዝ ወጪ ያለበት ተቋም መሆኑን የተናገሩት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሥዩም መኮንን፣ ይህንን ወጪ ለመሸፈን ተቋሙ ወደ ንግድ እያዘነበለ መሆኑን መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡ አቶ ሥዩም በወቅቱ የባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነት መኖሩን ሙሉ በሙሉ አምነዋል፡፡ ‹‹አንድ ለአንድ›› እና ‹‹አሳሽ›› በተሰኙ ፕሮግራሞች ባለሥልጣናትን ማፋጠጥ እንዲያቆም መጠየቁንም ተናግረዋል፡፡

በአንፃራዊነት ነፃነት ያላቸው የግል ሚዲያ ተቋማት ከፍተኛ የአቅምና የሀብት ውስንነት አለባቸው፡፡ በተለምዶ የመንግሥት ሚዲያ የሚባሉትና ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚሠሩት በሕጉ የሕዝብ ሚዲያ ተብለው የሚጠሩት ግን፣ የአቅምና የሀብት ውስንነት ባይኖርባቸውም የአስፈጻሚው አካል ጣልቃ ገብነት የሚጠበቅባቸውን ያህል እንዳይሠሩ እንቅፋት እንደፈጠረባቸው ተገልጿል፡፡    

በአዳማው ሥልጠና ጥናት አቅራቢዎቹና ተሳታፊዎቹ የሚዲያው ውስጣዊ ተግዳሮቶች እንደሆኑ ከለዩዋቸው ጉዳዮች መካከል ሚዲያው ከፍትሕ አካላት ጋር ያለው ግንኙነት በዕውቀት፣ በሙያ ሥነ ምግባርና በኃላፊነት የማይመራ መሆኑ አንዱ ነው፡፡ ዶ/ር ነገሪ በተለይ የፍትሕ አካላት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በሚፈለገው ደረጃ ተገንዝቦ መሥራት ላይ ክፍተቶች በሚዲያው በኩል እንደሚስተዋሉ አመልክተዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋዬ አስማማው በፍርድ ቤቶች እንቅስቃሴ ላይ ሚዲያው በርካታ አዎንታዊና ገንቢ ዘገባዎች ማቅረቡ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አልፎ አልፎ የዳኝነት ነፃነትና ገለልተኝነት መርህዎችን የማያከብሩ፣ በምርመራ፣ በክስ፣ በፍርድና በእርምት ሒደት ያሉ ሰዎች ያሏቸውን መብቶችና ክልከላዎች ያልተገነዘቡና የማያከብሩ የሚዲያ ሽፋኖች ለኅብረተሰቡ እንዲደርሱ በማድረግ በፍርድ ቤቶች ገጽታ ላይ ጉዳት እያስከተሉ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ተካ ገብረ ኪዳንና የፌዴራል የፍትሕ አካላት ማሠልጠኛ ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዓለም ገብረ መስቀል በበኩላቸው፣ ሚዲያው የፖሊስ፣ የዓቃቤ ሕግ፣ የፍርድ ቤትና የማረሚያ ቤትን ጨምሮ የፍትሕ አካላትን ሥልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ ከመረዳት አንፃር ጉልህ ጉድለቶች ስላሉበት ይህን ክፍተት እንዲሞላ የአቅም ግንባታ ሥራ ሊከናወን እንደሚገባ አስምረውበታል፡፡

አቶ ፀጋዬ በፍርድ ቤት የተያዙ ጉዳዮች እንዴት መዘገብ እንዳለባቸው የሚዘረዝር መመርያ አለመኖሩ ለዚህ ችግር አስተዋጽኦ እንዳበረከተም ጠቅሰዋል፡፡ ፍርድ ቤቶች የተሟላ መረጃ በወቅቱ ለሚዲያ እንደማይሰጡ ያስታወሱት አቶ ፀጋዬ፣ የሚዲያ ሰዎችም የፍትሕ አካላትን በተመለከተ የተሟላ ዕውቀት የሌላቸውና ሥነ ምግባር ያልተላበሱ እንደሆኑ ተችተዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር በመቀናጀት መመርያውን ለመቅረፅ ዕቅድ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝም አቶ ፀጋዬ አስታውቀዋል፡፡ በአንዳንድ ዘገባዎች የሚጣሱት የዳኝነት ነፃነትና ገለልተኝነት፣ እንዲሁም ንፁህ ሆኖ የመገመት መርህዎችን የተመለከቱ የሕግ ድንጋጌዎች አሁንም በሥራ ላይ ያሉ ቢሆንም፣ እነዚህ ድንጋጌዎች እርስ በርስ እንዲናበቡ አድርጎ በአንድ ሰነድ እንዲዘጋጁ ማድረግ ማስፈለጉን አቶ ፀጋዬ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ስለሚዲያና የፍትሕ አካላት ግንኙነት ሥልጠና የሰጡትና ለበርካታ ዓመታት በዳኝነት ከሠሩ በኋላ ከነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የለቀቁት አቶ ዓሊ መሐመድ፣ ሁለቱ ተቋማት በትብብር ቢሠሩ ፍትሕን በተሻለ መስፈን እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ሚዲያው በሕግ የተቀመጠውን አሠራር በመጣስ በርካታ ጥፋቶችን እንደሚፈጽም፣ በተለይ ፍርድ ቤቶች በታጋሽነት እያለፉ እንደቆዩ አመልክተዋል፡፡ ለዚህ ዓይነት ጥፋቶች ከተደነገጉ የወንጀል ቅጣቶች አንዱ የችሎት መድፈር ቢሆንም፣ ሚዲያውን በችሎት መድፈር መቅጣት ብዙም የተለመደ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

በወንጀል ሕግ አንቀጽ 449 ላይ የተደነገገው የችሎት መድፈር ወንጀል ሚዲያውን ያካትታል ወይስ አያካትም የሚለው ጥያቄ የሕግ ምሁራኑን ሲያወዛግብ ይስተዋላል፡፡ ቀደም ሲል ዳኛ የነበሩትን ጨምሮ በርካታ የሕግ ምሁራን ድንጋጌው በሚዲያ አማካይነት ስለሚፈጠር የችሎት መድፈር ጥሰት በግልጽ እንደማያካትት ይገልጻሉ፡፡

በጉዳዩ ላይ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ዓሊ፣ ድንጋጌው ክፍተት ቢኖርበትም በፍርድ ቤት አሠራር ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር ዘገባ የሚያሠራጭ ሚዲያ መቀጣት እንደሚኖርበት ተከራክራዋል፡፡ ‹‹ሕግ የመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው ለፍርድ ቤት ነው፡፡ የምሁራኑ ትርጉም ምናባዊ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሚዲያው የፍትሕ አካላትን በተመለከተ ሲዘግብ ምን መከተል እንዳለበት አዲስ ሕግ ማውጣት ባያስፈልግም፣ ዝርዝር የአሠራር ሥነ ሥርዓትና መርሕዎች የያዘ ማኑዋል ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አቶ ዓሊ በአፅንኦት ገልጸዋል፡፡ በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የሚዲያ ልማት ዳይሬክተር አቶ ታምራት ደጀኔ ግን በሥራ ላይ ያለው የሚዲያ ሕግ በጣም ጥሩ ስለሆነ፣ የሚወጣው መመርያ ወይም ማኑዋል አሳሪ ወይም አስገዳጅ እንዳይሆን ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ‹‹ሚዲያው ራሱን በራሱ በሚቆጣጠርባቸው እንደ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ባሉ ተቋማት ቢወጣ ምርጫዬ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች ሌላው ከሚዲያ ውጤታማነት ጋር በተያያዘ ያነሱት ችግር የመረጃ ተደራሽነትና ነፃነትን የተመለከተ ነው፡፡ በመረጃ ተደራሽነትና ነፃነት ላይ ሥልጠና የሰጡትና ከሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የመጡት አቶ ታደሰ ገዙ፣ የአስፈጻሚው የመንግሥት አካል የመረጃ አያያዝና አሰጣጥ ደካማ መሆንና ለተቋማቸው ወቅቱን የጠበቀ ሪፖርት አለማቅረብ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000 ተፈጻሚነትን እንደገደበው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሚዲያ ያለበት ችግር መንስዔ ከሕግ ዕጦት ሳይሆን ከፖለቲካውና ከመረጃ ልውውጥ ባህላችን ጋር የተቆራኘ ነው በማለት ክርክራቸውን የሚያቀርቡ ባለሙያዎችና አስተያየት ሰጪዎች በርካታ ናቸው:: በ1987 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 29 ቅድመ ምርመራ በማንኛውም መልኩ መከልከሉን፣ የሕዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት ዕድልና ሚዲያ በተቋምነቱ የአሠራር ነፃነትና የሕግ ጥበቃ እንዳለው መረጋገጡን ጨምሮ በርካታ መብቶችን በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡

በመርህ ደረጃ ሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡትን ነገሮች ለማብራራት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንቦች ሊወጡና እንደ ሁኔታው በተለያዩ መሥርያ ቤቶች ትዕዛዝና መመርያ ሊወጣ ቢችልም፣ ከሕገ መንግሥቱ በታች ያሉ ሕጎች በሕገ መንግሥቱ ያልተቀመጠ አዳዲስ ድንጋጌዎች ማምጣት አይቻልም::

የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000 የአዋጁ ትልቅ ስኬትም ሆነ ክፍተት በክፍል ሦስት ላይ የተቀመጠው መረጃ የማግኘት መብት ነው፡፡ ስኬቱ መረጃ የማግኘት መብትን ዘርዘር አድርጎ ከሥነ ሥርዓቱና ከማስረጃ ሒደቱ ጭምር ማቅረቡ ሲሆን፣ ድክመቱ ደግሞ መረጃ የማግኘት መብት ላይ የተቀመጡት ምክንያቶች እጅግ ብዙ መሆናቸው፣ እንዲሁም የቋንቋ አጠቃቀሙም አምታችና አሻሚ መሆኑ ለአስፈጻሚው አላግባብ እንዳይጠቅም መሠጋቱ ነው፡፡

ሕጉ ከማንኛውም መንግሥታዊ አካል ዜጎች መረጃን የመጠየቅ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብት እንዳላቸው፣ መረጃ ፈላጊዎቹ መረጃዎችን በተቻለ መጠን በፍጥነትና በዝቅተኛ ወጪ ሳይደክሙ የሚያገኙበት ሥርዓትና የአሠራር ሥነ ሥርዓት እንደሚመሠረት፣ እንዲሁም የሕዝብ ተሳትፎንና የሥልጣን ባለቤትነትን የማረጋገጥና እንዲሁም የአሠራር ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ውጤታማነት የሰፈነበት የመንግሥት አሠራርንና መልካም አስተዳደርን እንደሚያጠናክር ይገልጻል::

‹የማይገለጹ መረጃዎች› ብሎ የዘረዘራቸው በርካታ ክልከላዎች እንዳሉ ሆነው (ክልከላዎቹ ከኢፌዲሪ ሕገ መንግሥትና ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ጋር አብረው የማይሄዱና የመረጃ ነፃነትን መርህ ወደ ልዩ ሁኔታ የሚቀይሩ ናቸው በመባል የሚተቹ ናቸው)፣ በአንቀጽ 28 ላይ የመንግሥት አካላት የሚያዋቅሯቸው የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊዎች፣ በመረጃው መገለጽ ጥበቃ በተደረገላቸው ጥቅሞች ላይ የሚደርሰው ጉዳት በመረጃው መገለጽ ሊገኝ ከሚችለው የሕዝብ ጥቅም የሚበልጥ ካልሆነ በስተቀር፣ መረጃ ለማግኘት የቀረበ ጥያቄን ውድቅ ማድረግ እንደሌለባቸው ይደነግጋል:: በክልከላዎቹና በዚህ አንቀጽ መካከል ሚዛን ለመጠበቅ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችን ነፃና ገለልተኛ ውሳኔ ከግምት ውስጥ ማስገባት የግድ ይላል::

የመረጃ ነፃነት ሕጉ በርካታ ከዚህ በፊት ያልነበሩ አዳዲስ አሠራሮችን የሚያስተዋውቅ ቢሆንም፣ ሕጎቹ ተፈጻሚ የሚሆኑት በአዋጁ አንቀጽ 48(2) መሠረት አስፈላጊ የሆኑ ሁኔታዎችን ለማዘጋጀት ሲባል አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ከኀዳር 15 ቀን 2001 ዓ.ም. ከሁለት ዓመት በኋላ ሲሆን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ሊያራዝመው እንደሚችል ተደንግጎ ነበር፡፡ በመሠረቱ ኅዳር 15 ቀን 2003 ዓ.ም. አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ ከወጣ ሁለት ዓመት የሞላው ሲሆን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተጨማሪ አንድ ዓመት በማራዘሙ የተነሳ የአዋጁ ተፈጻሚነት የሚጀምረው ከኅዳር 15 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ነው::

ሕጉ ተፈጻሚ መሆን ከጀመረ አምስት ዓመታት ያለፈ ቢሆንም፣ የመንግሥት አሠራር በአዋጁ መሠረት እየተመራ እንዳልሆነ የሥልጠናው ተሳታፊዎች በምሬት ገልጸዋል፡፡ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ የሚቀርቡላቸው ሪፖርቶች በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመሠረቱ መሆናቸው በሥራቸው ላይ ጫና እንደፈጠረባቸው ለፓርላማው መናገራቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም በመረጃ ላይ ተመሥርተው ውሳኔ ለመስጠት መቸገራቸውን በአደባባይ መናገራቸው ችግሩ በተራ ዜጎች ላይ ያልተገደበና የሥርዓቱም ጭምር መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

በአዋጁ መሠረት መረጃ የማግኘት መብትን ተግባራዊ ለማድረግ መንግሥት የመረጃ አከፋፈል፣ የመረጃ አጠባበቅና የመረጃ አፈትላኪዎች ጥበቃ ሕጎችን እያረቀቀ መሆኑን መግለጽ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል:: እነዚህ ድንጋጌዎች የመረጃ ማግኘት መብትን አጠቃቀም በአሉታዊ ወይም በአዎንታዊ መልኩ እንዲያስተናግዱ፣ ከሕጎቹ ይልቅ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ቢያስፈልግም ሕጎቹ መውጣታቸው አስፈላጊ ነው::

የአዋጁ አንቀጽ 37 ለተለያዩ የመረጃ ዓይነቶች ተፈጻሚ ስለሚሆነው የክፍያ ተመን ሰንጠረዥ፣ ክፍያዎች ስለሚቀነሱበት ወይም መረጃ በነፃ ስለሚሰጥበት ዝርዝር ሁኔታ፣ ስለተከለከሉ መረጃዎች አጠባበቅና ምደባ ወይም ሚስጥርነታቸው ስለሚቀርበት ሁኔታ፣ እንዲሁም የመረጃ ነፃነት ሕጉ ድንጋጌዎችን አፈጻጸም ለማሟላት የሚያስፈልጉ ማንኛቸውንም ጉዳዮች የሚመለከቱ ደንቦችን የማውጣት ሥልጣን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተሰጥቷል፡፡ አዋጁ በተጨማሪም በአንቀጽ 38 ላይ የሚመለከታቸውን ወገኖች በማማከር ስሰነዶች አጠባበቅ፣ አስተዳደርና አወጋገድ የተግባር መመርያ የማውጣት፣ መመርያውን ከጊዜው ጋር ለማጣጣም በየጊዜው አስፈላጊ ማስተካከያዎችን የማድረግ ሥልጣን የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም እንደሆነም ይደነግጋል::

አቶ ታደሰ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት አስፈጻሚው የመንግሥት አካል በቅድሚያ ወቅቱን ጠብቆ ሪፖርት ማድረግና የተሻለ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት መዘርጋትን ጨምሮ፣ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

መንግሥት ከገዥው ፓርቲ በመጣ ባህልም ሆነ በሌላ ሁኔታ በግልጽነቱና በተጠያቂነቱ አይታወቅም፡፡ ይህ የመንግሥት ባለሥልጣናት ባህሪ ምንጭ የዜጎች ሚስጥራዊነት መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ በሌሎች አገሮች የአደባባይ መወያያ አጀንዳዎች በኢትዮጵያ እንደ ትልቅ ሚስጥር ይቆጠራሉ፡፡ ፊውዳሊዝምና ሶሻሊዝም ለዚህ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ቢያበረክቱም፣ የዜጎች የመረጃ ልውውጥ ባህል ባለፉት የኢሕአዴግ 26 ዓመታት የአስተዳደር ዘመን መሠረታዊ የሚባል ለውጥ አላመጣም፡፡

መንግሥት ብቻ ሳይሆን የሲቪል ማኅበራት፣ የሙያ ማኅበራት፣ የግል ድርጅቶች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና መሰል አካላት ከልሂቃኑና ከሌሎች ዜጎች ጋር ተዳምረው ሚዲያው ሊወጣ የሚገባውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ረገድ ድርሻቸውን አልተወጡም:: ሚዲያው በተለያዩ አካላት መካከል በተለይም በመንግሥትና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሐሳብ ልውውጥ እንዲደረግ ለመርዳት ያለውን የአስተባባሪነት ሚና የመንግሥትን የተለያዩ ሕጎች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ለሕዝብ በማድረስ ቅቡልነት ያለው መንግሥት ለመፍጠር የሚያደርገው እንቅስቃሴና ወደ ብጥብጥ የማያመራ ሐሳብ፣ አስተያየት፣ ዜናና ሐተታዊ ጽሑፍ እንዲያስተናግድ እነዚህ ተቋማት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ከጊዜ ወደጊዜ እየተመናመነ ይገኛል::

በቅርቡ፣ ‹‹የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በብዝኃነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ የእምነት፣ የባህል፣ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የአስተሳሰብና የፍላጎት ጉዳዮችን በጥንቃቄና በኃላፊነት መንፈስ በማስተናገድና የሕዝብን ጥቅም ማዕከል ባደረገ መልኩ መንቀሳቀስ ከሁሉም የሚዲያ አካላት የሚጠበቅ ተግባር ነው፤›› በማለትም ያስገነዘቡት ዶ/ር ነገሪ፣ ሚዲያው ካሉበት መሠረታዊ የአመለካከት፣ የሙያና የሥነ ምግባር ችግሮች ተላቆ በሰላም፣ በልማት፣ በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ግንባታ ውስጥ የደረጀ ሚና እንዲጫወት ለማስቻል ታቅዶ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሪፎርም ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

ይህ የሪፎርም ሥራ መሠረታዊ ለውጥ እንዲያመጣ የሚፈለግ ከሆነ፣ ሚዲያው መንግሥትን እየተከተለ የሚዘምር መሣሪያ ሳይሆን ነፃና ገለልተኛ በመሆን የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ የሚጠበቅበትን እንዲሠራና የተሻለ መንግሥትና የሕዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ተፅዕኖ መፍጠር እንድችል የሚያሳልጡ ዕርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ ይህም በሚዲያውና በፍትሕ አካላት መካከል የተሻለ ግንኙነት በመፍጠርና የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጁን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ መጀመር ይኖርበታል፡፡ ይህ በሌለበት የምርመራ ጋዜጠኝነትን ማሰብ እንደሚከብድ ብዙዎችን ያስማማል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -