Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየልማታዊ መንግሥትና የብሔር ፌዴራሊዝም የማይታረቅ ቅራኔ እንደገና

የልማታዊ መንግሥትና የብሔር ፌዴራሊዝም የማይታረቅ ቅራኔ እንደገና

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

በቅርቡ በሪፖርተር ‹‹የልማታዊ መንግሥትና የብሔር ፌዴራሊዝም የማይታረቅ ቅራኔ›› በሚል ርዕስ ላወጣሁት ጽሑፍ አዋቂዎች ሐሳብ እንዲሰጡበት መጋበዜን አስታውሳለሁ፡፡ ለዚህ ግብዣዬ ይመስለኛል አንድ አገር ወዳድ ምሁር ‹‹ፌዴራላዊ ሥርዓትና ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት በኢትዮጵያ ያላቸው ተመጋጋቢነት›› በሚል ርዕስ ኮራ ያለ ጽሑፍ አውጥተዋል፣ አመሰግናቸዋለሁ፡፡

ጸሐፊው በልማታዊ መንግሥት ላይ ዴሞክራሲያዊ የሚለውን ቅጽልም ጨምረዋል፡፡ ይህን ጽንሰ ሐሳብ አቶ መለስ ዜናዊ ቬትናማዊ ፕሮፌሰር ኬኒቺ ኦህኖን ጠቅሰው፣ ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ ፓርቲ የብዙኃን ምርጫን በማሸነፍ በሥልጣን ለረዥም ጊዜ ቆይቶ የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲን ማስፈጸም እንደሚችል የጻፉትን ዓይቻለሁ፡፡ ኢሕአዴግና ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች እየተከራከሩበት ስለሆነ፣ ሁለቱም ፍልስፍናቸውን ለሕዝብ እንዲያብራሩ እተዋለሁ፡፡

ጸሐፊው በፌዴራሊዝም ሥርዓትም ሆነ በልማት ኢኮኖሚክስ ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው አንባቢ ሰው እንደሆኑ ገምቻለሁ፡፡ የሊቃውንትን አመለካከት በመጥቀስም ጽሑፋቸውን የጀርባ አጥንት ያለው አድርገውታል፡፡

ሆኖም ሰዎች በአመለካከታቸውና በግንዛቤያቸው ወይም ባገኙት መረጃ ልክ ሊለያዩ ስለሚችሉ፣ እሳቸው ካሉት ውስጥ አንዱን  ሐሳብ ብቻ መዝዤ ልሞግታቸው እሞክራለሁ፡፡

ጸሐፊው የኢኮኖሚ አስተሳሰብ ዕድገትን ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምረው በአውሮፓ በነበሩ የንጉሣዊ ሥርዓቶች መንግሥታት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ እየገቡ፣ በአገሮቻቸው በማቆጥቆጥ ላይ የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን በተለያዩ መንገዶች በመደገፍ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ ለማድረግ አሁን በዘመናችን የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ በምንለው በሚመስል አግባብ የተንቀሳቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡

ጸሐፊው የተናገሩት ትክክል ነው፡፡ እንዲያውም የ18ኛው ክፍለ ዘመን ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ዘመነ ንግድ (Mercantalism) ሲባል፣ የአሁኖቹ ልማታዊ መንግሥታትም ዳግማዊ ዘመነ ንግድ (Neo-Mercantalism) ተብለውም ይጠራሉ፡፡

ከተጨባጭ ሁኔታ የተነሳ አመለካከት ምን ጊዜም አሸናፊ ነው፡፡ ይህንን በኢኮኖሚክስ በርካታ ምሳሌዎችን ሰጥቼ እገልጻለሁ፡፡ አዳም ስሚዝ በነፃ ገበያ ሥርዓት የግል ገበያ ኢኮኖሚን (Microeconomics) የተነተነው፣ ከዘመነ ንግድ ችግሮች ተነስቶ ነው፡፡ የዘመነ ንግድ ችግር ነው ያለውም ብዙኃኑን አደህይቶ ጥቂት ነጋዴዎችን ብቻ አከበረ በማለት ነው፡፡

ሎርድ ኬንስ የግል ገበያ ድክመት ስላለበት የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ያስፈልገዋል ብሎ ብሔራዊ ኢኮኖሚን (Macroeconomics) የተነተነው፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አካባቢ አውሮፓውያን በገጠማቸው የኢኮኖሚ ቀውስ ተጨባጭ ሁኔታ ነው፡፡

በ1980ዎቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬጋን፣ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬት ታቸርና የጀርመን ቻንስለር ሔልሙት ኮል የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ያብቃ ያሉት በኢኮኖሚክስ ‹ስታግፍሌሽን› ተብሎ የሚታወቀው የሥራ አጥነትና የዋጋ ንረት በተመሳሳይ ጊዜ መከሰት፣ የብሔራዊ ኢኮኖሚው ፖሊሲን ውጤት አልባ ስላደረገው ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2008 በተከሰተው የገንዘብ ቀውስ ተጨባጭ ሁኔታ ምክንያት ምዕራባውያን እንደገና ወደ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተመለሱ፡፡

ታዳጊ አገሮችን በቀጥታ ወደ ገበያ ኢኮኖሚ የሚያስገባቸው ተጨባጭ ሁኔታዎች የሉም፣ ልማትን ማስቀደም አለባቸው የሚባለውም ከገበያዎች አለመጥራት (Market Imperfections) ተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳት ነው፡፡

ከቅርብ ወራት ጀምሮ በምዕራባውያን መንግሥታት ምርጫዎች የብሔርተኛ ተወዳዳሪዎች ማሸነፍ ደግሞ ምዕራባውያን ወደ ዳግማዊ ዘመነ ንግድ ዓይነት መንግሥትነት እየተቀየሩ መሆናቸውን እናያለን፡፡

በአውሮፓ ኢኮኖሚውን መምራት የተሳነውን የተከፋፈለ መሳፍንታዊና ባላባታዊ የፊውዳል አስተዳደር ሥርዓት ተክቶ ከ16ኛው እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን የቆየው የዘመነ ንግድ ኢኮኖሚ ያተኮረው፣ በውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ከገቢ ንግድ ይልቅ ወጪ ንግድን አስበልጦ አትራፊ በመሆን ወርቅ፣ ብርና የውጭ ምንዛሪ ሀብት ለአገር በማከማቸት በኃይልና በኢኮኖሚ ከሌሎች አገሮች በልጦ መገኘት ነበር፡፡

በውስጥ ፖሊሲውም የሕዝብ ቁጥር እንዲበዛ፣ ልጆችንም ጨምሮ ሠራተኞች በዝቅተኛ ደመወዝ ብዙ ሰዓት እንዲሠሩ፣ አገርን ከሚያከስረው የቅንጦት ፍጆታ ሸመታ እንዲታቀቡም ያደርግ ነበር፡፡ ከምርት ይልቅ ለንግድ ዋጋ በመስጠት የኬላ ቀረጥ ሕግን በማንሳት በአገር ውስጥ ሰዎች ያለእንቅፋት እንዲገበያዩ ያደርግም ነበር፡፡

በዘመነ ንግድ ኢኮኖሚ ፍልስፍና አውሮፓውያኑ አፍሪካና ላቲን አሜሪካን በቅኝ ግዛትነት ተቀራመቱ፡፡ ማዕድኖቻቸውን በዘበዙ፡፡ ጥሬ ዕቃ አቅራቢና የፋብሪካ ሸቀጥ ማራገፊያ አደረጓቸው፡፡

የቀድሞዎቹን የዘመነ ንግድ ሥርዓት መንግሥታትና የአሁኖቹን ዳግማዊ ዘመነ ንግድ መንግሥታት የሚለያቸው፣ የቀድሞዎቹ የተነጋገዱት የከበሩ ድንጋዮችን ወርቅና ብርን ሲሆን፣ የአሁኖቹ ያተኮሩት በፋብሪካ በተመረቱ ምርቶች ላይ ነው፡፡ እስያውያኑም ያደጉት የምዕራባውያንን ገበያ ሰብረው ለመግባት በመቻላቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት የቁም እንስሳት ሥጋን፣ የቅባት እህልን፣ ጥራጥሬን ከደሃው አፍ ነጥቃ የሦስት ቢሊዮን ዶላር ምርት ወደ ውጭ ስትልክ ከውጭ ያስገባችው ምርት እስከ 16 ቢሊዮን ዶላር ይደርስ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ለዕለት ጉርስ በዕርዳታ መልክ የምታገኘው ታክሎበት የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ተንቀሳቃሽ ሒሳብ  ጉድለት ስምንት ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስና ይኼም የሚሸፈነው በካፒታል ድጋፍና በብድር መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ለጸሐፊው በብሔራዊ ባንክ መረጃ ሰንጠረዥ አማካይነት ያለንበትን ሁኔታ ላሳያቸው፡፡

የጥሬ ገንዘብ አካል የባንክ ሀብቶች ንፅፅር

 

ዓመት

የውጭ ምንዛሪ ሀብት በቢሊዮን ብር

የአገር ውስጥ ብድር ሀብት በቢሊዮን ብር

የውጭ ምንዛሪ ሀብት ከአገር ውስጥ ብድር ሀብት ንፅፅር

2003

55.5

135.5

41 በመቶ

2004

39.8

189.1

21 በመቶ

2005

45.6

233.4

19.5 በመቶ

2006

56.1

299.7

18.7 በመቶ

2007

37.5

393.5

9.5 በመቶ

2008

21.5

490.2

4.4 በመቶ

የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት የጀርባ አጥንት ከሆኑት ሁለት የባንክ ሀብቶች መካከል የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጭ ድርሻ በ2003 ዓ.ም. ከነበረበት 41 በመቶ፣ በ2008 ዓ.ም. ወደ 4.4 በመቶ መቀነሱ አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው፡፡

ልማታዊ መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ ወደ የጨነገፈ መንግሥትነት (Failed State) ይቀየራል፡፡ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ሀብቷን አሟጣ ጨርሳ የዳግማዊ ግለ ነፃነት (Neo-Liberalism) መርህ በሆነው ግሎባላይዜሽን፣ የውጭ ኢንቨስተሮችን አድኑኝ እያለች ነው፡፡ ባለሥልጣናትም አገሪቱን ከውድቀት ለመታደግ ላይ ታች እያሉ ነው፡፡

በቅርቡ ኢትዮጵያን ጎብኝተው የተመለሱት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአገሪቱ መሪ የጻፉትን መጽሐፍ ጠቅሰው፣ ያገኛችሁትን ሁሉ አትገልብጡ በማለት ጠንካራ ምክር ሰጥተው ነው የተመለሱት፡፡ እኔንና እርስዎን የመሳሰሉ ሰዎች ውስጣችን ያለውን አውጥተን በመናገራችን መንግሥት ያገኘውን ሁሉ እገለብጣለሁ ብሎ ስህተት ውስጥ እንዳይገባ እንረዳዋለን፡፡ በተሳትፎዎ አከብርዎታለሁ፣ አመሰግንዎታለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]   ማግኘት

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...