Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየፓርላማው የዓመቱ አፈጻጸም በራሱ ሕግ ሲለካ

የፓርላማው የዓመቱ አፈጻጸም በራሱ ሕግ ሲለካ

ቀን:

በውብሸት ሙላት

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመስከረም ወር የመጨረሻው ሰኞ የጀመረውን የዚህን ዓመት መደበኛ ተግባሩን አጠናቅቆ አባላቱም ዕረፍት ላይ ናቸው፡፡ እንደባለፈው ዓመት ለአስቸኳይ ጉዳይ ካልተጠሩ በስተቀር ዕረፍታቸው እስከ መጪው የመስከረም ወር የመጨረሻው ሰኞ ድረስ ይቀጥላል፡፡ ምናልባት ለአራት ወራት ተራዝሞ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሁንም የሚራዘም ከሆነ ከሁለት ሳምንት በኋላ መመለሳቸው አይቀሬ ይሆናል፡፡

በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ በተለይም የሥልጣን ክፍፍል ባለበት አገር፣ ራሱን የቻለ ሕግ አውጪ አካል መኖር ግድ ነው፡፡ ምንም እንኳን ስሙ ሕግ አውጪ ቢሆንም፣ ሥልጣኑ ግን ሕግ በማውጣት ብቻ የተገደበ አይሆንም፡፡ ያወጣቸውን ሕጎች በአግባቡ መፈጸማቸውን ወይንም አለመፈጸማቸውን የመከተታልና የመቆጣጠር ተጨማሪ ሥልጣን ይኖረዋል፡፡

ይኼ ጽሑፍ፣ እነዚህን ኃላፊነቶች እንዲወጣ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ የተጣለበት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ  ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ዓመት ያከናወናቸውን የሕግ ማውጣትና የአስፈጻሚው አካል ላይ ያደረገው ክትትልና ቁጥጥር ጠቅለል አድርጎ ይገመግማል፡፡

የፓርላሜንታዊ አሠራርን በሚከተሉ አገሮች እንደሚደረገው ሁሉ በኢትዮጵያም ቢሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ ጥቅል መርሆችን ሥራ ላይ ለማዋል የሚረዱ ሕጎችን ያጸድቃል፡፡ ፖሊሲዎችን ያወጣል፡፡ በጀት ያጸድቃል፡፡ የሕግ አስፈጻሚውም  ምክር ቤቱ ባወጣቸው ሕግጋትና ፖሊሲዎች መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ ስለሚጠበቅ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ እነዚህም በትክክል ስለመፈጸማቸው ክትትል ማድረግ ዓበይት ተግባራቱ ናቸው፡፡

በዚህ ረገድ ዘንድሮ ስድሳ ስምንት አዋጆችን አጽድቋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በሕግ አወጣጥ ረገድ ያከናወናቸውን ተግባራት በቅድሚያ እንቃኛለን፡፡

የፌዴሬሽንም ይሁን ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዓመታዊ ሥራቸውን የሚጀምሩት በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የመክፈቻ ንግግር ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱም በንግግራቸው ከሚያካትቷቸው ነጥቦች ውስጥ አንዱ ፓርላማው (የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) በዓመቱ ውስጥ መውጣት ስላለባቸው ሕጎች ነው፡፡

እንደ ወትሮው ሁሉ፣ ፕሬዚዳንቱ፣ በዚህ ዓመትም መውጣት ካለባቸው አዋጆች ውስጥ ሁለቱን ይፋ አድርገው ነበር፡፡ አንደኛው የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ የሚኖረውን ልዩ ጥቅም የሚመለከት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የምርጫ ሥርዓቱን የሚቀይረው ሕግ ነው፡፡ የመጀመርያውን በተመለከተ ምክር ቤቱ ለዕረፍት ሊዘጋ ሰሞን ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቅ አዋጅ ቀርቦለት ወደ ቋሚ ኮሚቴዎች መመራቱ አገር ያወቀው ጉዳይ ነው፡፡

ስለ ሁለተኛው ግን እስካሁን የተሰማ ነገር የለም፡፡ በ2010 ዓ.ም. የወረዳና የቀበሌ ምርጫ መኖሩ ቢታወቅም ሕጉን ግን ለማሻሻል ስለመጀመሩ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ይኼ ሕግ፣ የምርጫ ሥርዓቱን ከአንደኛ አላፊ፣ የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት ወደ ቅይጥ ወይንም ተመጣጣኝ ውክልና የሚቀይረው ከሆነ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ስለሚጠይቅ አወጣጡ እንደሌሎቹ ሕጎች ቀላል አይሆንም፡፡ ለማንኛውም ፓርላማው የምርጫ ሕጉን ማውጣት ሳይጀምር ዓመቱ ተጠናቋል፡፡

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት አንድ መሠረታዊ ጥያቄ አለ፡፡ ይኸውም የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የምክር ቤቶቹ የመክፈቻ ንግግርን ፓርላማው ካጸደቀው በኋላ ተፈጻሚ ባይሆን የሚኖረው ውጤት ምንድን ነው? በሌላ አገላለጽ፣ የፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ የተገለጹ ጉዳዮች ተፈጻሚነታቸውን በተመለከተ ምን  የሕግ ማዕቀፍ አለ? የሚለው ነው፡፡

ለነገሩ በቀድሞዎቹ ፕሬዚዳንቶች ንግግር ላይ ተካትተው ነገር ግን ሕግ ያልወጣላቸው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ለአብነት በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ዘመን “ዓለም አቀፍ የግለሰብ ሕግ” እና “የአስተዳደር ሕግ” እንደሚወጣ ቢናገሩም ሕጎቹ እስካሁን አልወጡም፡፡ ባለፈው ዓመት የተናገሩት ሳይፈጸም በሚቀጥለው የመክፈቻ ንግግር ላይ በድጋሜ ስለሌላ ሕግ መውጣት መናገራቸውን ይቀጥላሉ፡፡

ፕሬዚዳንቶቹም፣ ይኼንን ለመከታተል የሚችሉበትን የሕግ ማዕቀፍ የሚያወጣላቸው ይኼው ምክር ቤት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና ምክር ቤቱ ራሱ ላይ ግዴታ የሚጥል የቁጥጥርና ክትትል ሕግ እስካሁን አላወጣም፡፡ ምክር ቤቱ ባይፈልግ እንኳን ፕሬዚዳንቶቹም ረቂቅ ሕግ ማቅረብ ይገባቸው ነበር፡፡

ሌላው ከሕግ ማውጣት ጋር የሚያያዘው ችግር ፓርላማው አዋጅ ሲያወጣ አዋጁን ለማስፈጻም የሚረዱ ዝርዝር ሕጎችን በደንብ ወይንም በመመርያ እንዲወጡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አለበለዚያም ለሌሎች ተቋማት ከሚሰጠው ውክልና ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምክር ቤቱ በሚያወጣቸው ሕጎች ላይ “ደንብ” ወይም “መመርያ” እንዲወጣ ከተገለጸ የሚመለከታቸው ተቋማት በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ማውጣት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀጽ 60 ንዑስ ቁጥር 6 ይደነግጋል፡፡

ይሁን እንጂ፣ ደንብና መመርያ እንደሚወጣላቸው የተገለጹ አዋጆች ቢኖሩም እንዳንዶቹ እንኳንስ በሦስት ወራት ይቅርና በሦስት ዓመትም ያልወጣላቸው አሉ፡፡ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁን በምሳሌነት ብንወስድ ከጸደቀ አሥራ ሦስት ዓመታት ቢሆኑትም፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የቤት ሠራተኞችንና በሃይማኖት ድርጅቶች ስለሚሠሩ ሠራተኞች ሁኔታ ደንብ እንደሚያወጣ ቢገለጽም እስካሁን አልወጣም፡፡

ባለፈው ዓመት የወጡትን የገቢ ግብርና የግብር አስተዳደር አዎጆቹን ብንመለከትም፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያው ደንብ ማውጣት ያለበት በሦስት ወራት ቢሆንም፣ አዋጆቹ ከወጡ ከአሥራ አንድ ወራት በኋላ ነው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ረቂቅ ደንቡን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የላከው፡፡ ሌሎች በርካታ መውጣት ያለባቸው መመርያዎችም እንዳሉ በእነዚህ በአዋጆች ላይ ቢገለጽም ያልወጡት ግን በርካታ ናቸው፡፡ ሕጉ፣ በሦስት ወራት መውጣት እንዳለባቸው መደንገጉን ግን ያው ደንግጓል፡፡

ፓርላማውም ውክልና የሰጣቸውን ተቋማት እንደውክልናቸው መፈጸማቸውን በመከታተል ቢያስፈጽም ኖሮ እነዚህ ሕጎች ይወጡ ነበር፡፡

ከላይ ከተገለጹት በተጨማሪ የደንቦችንና የመመርያዎችን ሕጋዊነት ቁጥጥር የሚደረግበት ሥርዓት አለማበጀት ደግሞ ሌላው ሳንካ ነው፡፡ ከመርሕ አንፃር መውጣት አለመውጣታቸውን እንዲሁም ከአዋጆቹ ጋር የማይጋጩ መሆናቸውን መከታተልና የማረጋገጫ ሥርዓት መኖር ነበረበት፡፡ ይኼንን ለማድረግ ደግሞ አደረጃጀትን ማስተካከል፣ አቅምንም ማጎልበት ይገባ ነበር፤ ደንቦችና መመርያዎች ከአዋጆች ጋር እያገናዘቡ ለመመርመር ይረዳ ዘንድ ማለት ነው፡፡

የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መመርያዎችን ያወጣሉ፡፡ እነዚህ መመርያዎች ደግሞ ሕግ ስለመሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ ይሁን እንጂ፣ መመርያዎቹ በነጋሪት ጋዜጣ አይወጡም፡፡ በሌላ መንገድም አይታተሙም፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ይኼንን ሁኔታ አይጠይቁም፤ አይከታተሉም፡፡ ማንኛውም መመርያ በአግባቡ ተሰራጭቶ ለሕዝብ መድረስ እንዳለበትና ይኼንንም መመርያውን ያወጣው ተቋም የበላይ ኃላፊ ስርጭቱን የመከታተል ግዴታ እንዳለበት ከላይ የተጠቀሰው ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀጽ 60(7) ላይ ተገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ምክር ቤቱ ራሱ አግባብ ባለው አካል የወጡ ሕጎች በትክክል እየተሰራጩ መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት የዚሁ ደንብ አንቀጽ 62 ይደነግጋል፡፡

ነገር ግን፣ አንዳንድ ተቋማት መመርያ ማውጣት ወይንም አለማውጣታቸው የሚታወቅበት ሥርዓት የለም፡፡ እንደ አዋጅና ደንብም በነጋሪት ጋዜጣ አይታተሙም፡፡ በድረ ገጻቸው ላይም የማያስቀምጡ ብዙ ናቸው፡፡ መመርያ የሚያወጡ ነገር ግን ድረ ገጽ የሌላቸው በርካታ ተቋማት መኖራቸው የታወቀ ቢሆንም፣ አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ደግሞ ያወጡትን መመርያ ኮፒው ለማድረግ እንኳን የማይፈቅዱ መኖራቸውም ገሃድ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ቢሆንም በእንግሊዝኛ ብቻ የወጡ መመርያዎችም አሉ፡፡ እነዚህን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቻ የወጡ  መመርያዎችንም የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ እንደሆኑ ወስኗል፡፡

ፓርላማውም ሆነ ሕግ እንዲያወጡ ውክልና የሰጣቸው ተቋማት የሚያወጡትን ሕግ በተመለከተ በተቻለ መጠን ኅብረተሰቡን ማሳተፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ተሳትፎ በራሱ መብት ቢሆንም ከዚህ በተጨማሪም ሕዝብ የራሱን ጉዳይ ራሱ መወሰኑን ለማረጋገጥ ምቹ ሕግና ፖሊሲ ማውጣት፣ እነዚህም ሲወጡ ሕዝቡን የማሳተፍና ለውሳኔ የሚሆን ሐሳብ የማበርከት መብትንም ያካትታል፡፡ ይሁንና፣ በርካታ ሕጎች ሲወጡ ቢያንስ ሕጉ በቀጥታ ተፅዕኖ የሚያሳርፍባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን ቀድሞ አለማማከርና አለማወያየት የተለመደ ነው፡፡

ተሳትፎ፣ ዜጎች በመንግሥታዊ ጉዳዮች ማለትም የፖለቲካ ሥልጣን በመያዝ፣ ሕግና ፖሊሲዎችን በማውጣት ረገድ፣ በሕዝባዊ ውይይትና ክርክር በጽሑፍም ይሁን በቃል፣ በራሳቸውም ወይንም በወኪላቸው በኩል መሳተፍን ይመለከታል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም እነዚህን ሁኔታዎች የሚያሳልጥ የሕግ ማዕቀፍ ማውጣትና ሌሎች ስልቶችን የማመቻቸት ግዴታ አለበት፡፡ ይሁን እንጂ፣ ምክር ቤቱ በዋናነት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተዘጋጅቶና ጸድቆ ለሚቀርቡት አዋጆች በውይይት በተመደበው ጊዜ በአካል በመገኘት ወይንም በፖስታ አስተያየት መስጠት እንደሚቻል ሁልጊዜ ማስታወቂያ ይተላለፋል፡፡ ነገር ግን፣ ውጤታማ ተሳትፎ ለማድረግ አስቀድሞ ረቂቅ አዋጁን ማግኘት በራሱ አዳጋች ነው፡፡ ምክር ቤቱ በድረ ገጹ ረቂቅ ሕጎች አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር አያስቀምጥም፡፡ ረቂቅ የበጀት አዋጁ ብቻ ከሰሞኑ በዚህ ፋይል ላይ ተቀምጧል፡፡ በመሆኑም፣ የሕግ አወጣጡ ሒደት ላይ በተገቢው ሁኔታ ሕዝብን ለማሳተፍ የተመቻቸ ሥርዓት አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ብዙም ፍላጎት ያለ አይመስልም፡፡ ይኼ ችግር፣ ደንብና መመርያ የማውጣት ሥልጣን የተሰጣቸው ላይ ሲሆን ደግሞ እጅግ የከፋ ነው፡፡

እንግዲህ ምክር ቤቱ ሕግ በማውጣት ረገድ ካሉበት እንከኖች ውስጥ የተወሰኑትን ብቻ ናቸው  ከላይ የተገለጹት፡፡ የወጡትን ሕግ ጥራትና ለአገሪቱና ለሕዝቧ ሁለንተናዊ ዕድገት ከሚኖራቸውን ፋይዳ አንፃር፣ ከሕገ መንግሥታዊነታቸው አኳያ ወዘተ በመፈተሽ የምክር ቤቱን ውጤታማነት መገምገምም ይቻላል፡፡

እንግዲህ ምክር ቤቱ በሕግ አወጣጥ ረገድ ስላለው አፈጻጸም፣ በዚሁ ዓመት የፌዴራሉ መንግሥት የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም ይፋ ያደረገው ሪፖርትም ካላይ ከቀረበው ሐሳብ ጋር የተስማማ ነው፡፡ ምክር ቤቱ  ላወጣቸው ሕግች ማስፈጸሚያነት የሚውሉ ደንብና መመርያ መውጣት አለመውጣቱን እንደማይከታተል ገልጿል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ፣ ምክር ቤቱ በዚህ ዓመት የነበረውን የሕግ ማውጣት ተግባሩ ከበፊቱ የተሻለና ውጤታማ እንደነበር አፈ ጉባዔው መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ የሕግ አውጪው ክትትልና ቁጥጥር የሚመነጨው ያወጣቸው ሕጎች፣ ያጸደቃቸው ፖሊሲዎች በትክክል ሥራ ላይ መዋላቸውን ለማረጋገጥ ካለበት ኃላፊነት ነው፡፡ በሹመት ጊዜም ይሁንታውን የሚሰጣቸውና ቃለ መሐላ የሚያስገባቸው ባለሥልጣናት ግዴታቸውን ስለመወጣታቸው በቅርበት ለማረጋገጥ ነው፡፡

 

ሕግ አውጪው ባስቀመጠው የአሠራር ሥርዓት ያልሠራን ሚኒስትር ወይም ሹመኛ፣ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሆነ በዚሁ በኩል ዕርምጃ እንዲወሰድበት የማድረግ ሥልጣን እንዳለው ከላይ የተገለጸው ደንብ ይገልጻል፡፡ በዚህ ረገድ፣ ዕርምጃ የተወሰደበት ባለሥልጣን ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም፡፡

በዚህ ዓመት የነበረውን የክትትልና የቁጥጥር ሥራን በተመለከተ አፈ ጉባዔው ሪፖርት የሚያሳው እየተሻሻለ መምጣቱንና ውጤታማ እንደነበሩ ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ግን፣ ከወራት በፊት የወጣው የመንግሥት ጥናት ደግሞ ምክር ቤቱ በሕገ መንግሥቱና ራሱ ባወጣው ደንብ የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ እንዳልሆነ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ የአስፈጻሚው አካልን ዴሞክራሲያዊ ከማድረግ አንፃር የምክር ቤቱ አሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ላይ እንደተቀመጠው የክትትልና ቁጥጥር ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡ የመጀመርያው አስፈጻሚው አካል የሚያከናውናቸው ሥራዎች ሕግንና ሥርዓትን ተከትለው እየተፈጸሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ፣ አስቀድሞ ምክር ቤቱ ሥርዓት ማበጀት አለበት ማለት ነው፡፡

ሁለተኛው የክትትልና የቁጥጥር ዓላማ ደግሞ፣ ፈጣን፣ ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋና ዘላቂ ልማት መኖሩን ማረጋገጥ ነው፡፡ መርሑ ይኼ ቢሆንም ቅሉ፣ በርካታ የልማት ተቋማት በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸው ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የመንግሥት ገንዘብ እየባከነ መሆኑን ለፓርላማው ለራሱ በተለያዩ ጊዜያት ሪፖርቶች መቅረባቸው ይታወቃል፡፡ ይባስ ብሎም፣ ምርት ሳይጀመሩ አገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ወለድ በመክፈል ላይ መሆኗን ፓርላማውም ጭምር ያውቃል፡፡

 ሦስተኛው ደግሞ፣ ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን እንዲሰፍን ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ዓመትም ይሁን ባለፈውም፣ አስፈጻሚው ራሱ ያመነው የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩ ነው፡፡ እንደመፍትሔም፣ አስፈጻሚው ራሱ “በጥልቀት መታደስ” የሚል አሠራር ሲያመጣ ሕግ አውጪው የዘረጋው ሥርዓት ግን የለም፡፡

ፓርላማው መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ሲባል ማቋቋም ያለበት ካለበት ተቋማት ውስጥ የእንባ ጠባቂና  የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ተቋማት ሰብዓዊ መብትን ከማስፋፋትና ከማስጠበቅ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማረምና ለማስተካከል ሲባል የተቋቋሙ ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ባለፈው ዓመት የተነሳውን ችግር ከመቅረፍ አኳያ እምብዛም የጎላ ድርሻ ነበራቸው ማለት ባይቻልም፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በተወሰነ መልኩ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተፈጸሙትን መንግሥታዊ ችግሮች ማጣራቱ እርግጥ ነው፡፡ የእንባ ጠባቂው ተቋም ግን በቅርቡ ያቀረበው ሪፖርት ጥልቅ ተሃድሶ ስለማጣው ከፍተኛ ለውጥ ሳይሆን እዚህ ግባ የሚባል የመልካም አስተዳደር ለውጥ አለመኖሩን ነው፡፡ ከሁለቱ ተቋማት በተጨማሪም፣ ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ የሆነው የፌዴራሉ ኦዲተር ጀኔራል የበርካታ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በርካታ መሥሪያ ቤቶች የሒሳብ አያያዝና የግዢ ዝርክርክነት ለፓርላማው ሪፖርት ቢያቀርብም፣ እዚህ ግባ የሚባል ዕርምጃዎች መወሰዳቸው ግን አልተሰማም፡፡

አራተኛው የክትትልና ቁጥጥር ዓላማ፣ የቡድንና የዜጎች መብትን ማስከበር ሲሆን፣ በደንቡ ላይ የተገለጸው የመጨረሻው ዓላማ ደግሞ በመንግሥት አካላት መካከል የተቀናጀ አሠራር ማስፈን ማስቻል ነው፡፡

ከላይ የተገለጹትን ዓላማዎች ለማሳካት ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚውን ሊቆጣጠር የሚችልባቸው የተለያዩ ሥልቶች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ የመጀመርያው ፓርቲያዊ ቁጥጥር ሲሆን፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ባሉበት ፓርላማ የገዥው ፓርቲ የሚፈጽማቸውን አስተዳደራዊ እንከኖችና ሕግን ያለማስፈጸም አድራጎቶችን የሚያጋልጡበትንና ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚደረግበት አካሔድ ነው፡፡

ከፓርቲያዊ ቁጥጥር ውጭ ደግሞ በቋሚና ልዩ ኮሚቴዎች አማካይነት የሚደረጉ ቁጥጥሮችም መኖራቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ ዓመት ከወትሮው በተሻለ ሁኔታ በርካታ ቋሚ ኮሚቴዎች የሚመለከታቸውን መሥሪያ ቤቶችን የመስክ ጉብኝት በማድረግና ተጠርተውም ሪፖርት በማስቀረብ ክትትል ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህ ባለፈም፣ ምክር ቤቱ በርካታ ተቋማት ያለባቸውን ችግር እንዲያስተካክሉ ስፍር ቁጥር የሌለው ማሳሰቢያ መስጠቱ ይታወቃል፡፡ የምክር ቤቱን ድረ ገጽ የጎበኘ ሰው ከሚያገኛቸው ዜናዎች ውስጥ በርካታዎቹ ለተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተሰጡ ማሳሰቢያዎችን ነው፡፡

ሌላው የቁጥጥር ሥልት ሹመኞችን ጠርቶ በመጠየቅና ሪፖርት እንዲያቀርቡ በማድረግ ነው፡፡ ሚኒስትሮቹ፣ በምክር ቤቱ በመቅረብ ሪፖርት ሲያደርጉ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ የምክር ቤቱ አሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብም ለዚህ ሥርዓት ዘርግቷል፡፡  በመሆኑም፣ ማንኛውም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ኃላፊ በዓመት ቢያንስ አንድ ጊዜ ሪፖርት የማቅርብ ግዴታ አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በኮሚቴዎች ጥሪ ሪፖርት ሊቀርብ ይችላል፡፡

የፓርላማ አባላትም ሪፖርት አቅራቢዎቹን መጠየቅ እንደሚችሉ በደንቡ ላይ የተቀመጠ አሠራር ነው፡፡ ነገር ግን አባላት ማቅረብ ያለባቸውን ጥያቄ አስቀድመው ማሳወቅ አለባቸው፡፡ ጥያቄዎቹ ግን የማመን ወይም የመካድ ዓይነት ይዘት ሊኖራቸው አይገባም፡፡ አንድ ኃላፊ ሪፖርት ሲያቀርብም አባላቱ በመርሕ ደረጃ መጠየቅ የሚችሉት አንድ ጥያቄ ብቻ ነው፡፡ የአጠያየቅ ሥርዓትን የሚመለከቱ እንዲህ ዓይነት በርካታ ገደቦች አሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ባለሥልጣናቱ የሚፈጸሟቸውን የሕግ ጥሰቶች ማውጣት የሚያስችል የአጠያየቅ ሥርዓት ፓርላማው አለው ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡

የቁጥጥርና ክትትል ዓላማውና  ሥልቱ ምንም ይሁን ምን የፓርላሜንታሪያዊ ሥርዓት በራሱ ደግሞ የዳበረ ዴሞክራሲ እስከሌለ ድረስ መዋቅራዊ ችግር ያለው መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የተወሰኑ የአስፈጻሚው አካል የፓርላማ አባላት ስለሚሆኑና እነዚህ ደግሞ ከፍተኛ የፓርቲ ባለሥልጣናት የሆኑት በሁለቱም ቦታዎች ስለሚገኙ የቁጥጥሩ ሒደቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትሉ የገዥው ፓርቲ ሊቀመንበርና ምክትል ከሆኑና እንደ ኢሕአዴግ በጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚመራ ከሆነ በፓርቲው መዋቅር  የበታች እርከን ላይ የሚገኙ አባላት፣ ምንም እንኳን የፓርላማ አባል ቢሆኑም ቅሉ፣ አለቆቻቸውን በሕጉ መሠረት ብቻ ይቆጣጠራሉ ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም ሕግ አውጪው አስፈጻሚውን እንዴት ሥራውን ማከናውን እንዳለበት የሚያሳይ የአስተዳዳር ሥነ ሥርዓት ሕግ ማውጣትና መተግበር ነበረበት፡፡ ይኼ ሕግ አስፈጻሚው በሕግ የተሰጧቸውን የመወሰን ሥልጣን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ለማሳየት ይረዳል፡፡  በተጨማሪ፣ አስተዳደር ሕግ መኖር፣ ሰብዓዊ ክብርን ለማስጠበቅ ይረዳል፡፡ የዜጎችን ተሳትፎ ያሳድጋል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ያረጋግጣል፡፡ መንግሥታዊ ተቀባይነትን እንዲሻሻልም ያደርጋል፡፡ መብቶችንና ጥቅሞችን ማስከበሪያና እንዳይጣሱ ለመከላከል ያግዛል፡፡ ፓርላማው ግን ይኼንን ሕግ ባለማውጣት ለአስፈጻሚው የአፈጻጸም ችግር አስተዋፅኦ አድረጓል፡፡ ይኼ ሁሉ እንዳለ እየታወቀ፣ አፈ ጉባዔው ያቀረቡት የምክር ቤቱ የአፈጻጸም ሪፖርት ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...