ኢትዮጵያ በዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት) አማካይነት በዓለም ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው ዘጠኝ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች መካከል አንዱ የስሜን ብሔራዊ ፓርክ ነው፡፡
በዩኔስኮ ከሠላሳ ዘጠኝ ዓመታት በፊት ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጋር የተመዘገበው ፓርኩ በዓለም ቅርስነት መዝገብ ሰፍሮ መቆየት የቻለው ለ18 ዓመታት ብቻ ነበር፡፡
በፓርኩ ክልል ውስጥ ሰዎች ሰፍረው መንደር መመሥረታቸው፣ ልቅ እርሻና ለግጦሽ ከብቶች መሰማራት፣ ፓርኩን ሰንጥቆ የሚያልፍ መንገድ መኖርና የፓርኩ ወሰን ክልል እየጠበበ መምጣቱን ተከትሎ ዩኔስኮ ከሁለት አሠርታት በፊት በአደጋ ቀይ መዝገብ ውስጥ አስገብቶታል፡፡ የዩኔስኮ ገምጋሚ ቡድን በ1987 ዓ.ም. ፓርኩ ያለበትን ሁኔታ አጠቃላይ ሪፖርት የቀረበለት የዩኔስኮ 20ኛው መደበኛ ጉባኤ ፓርኩ በአደጋ መዝገብ ውስጥ እንዲገባ በ1988 ዓ.ም. መወሰኑ ይታወሳል፡፡
በብሔራዊ ፓርኩ ላይ የተደቀነውን ፈተና ለመፍታት መንግሥትና የአማራ ክልል ባደረጉት ጥረት ፓርኩ ከአደጋ መዝገብ ውስጥ እንዲወጣ መደረጉ ተገልጿል፡፡ ከኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን (ኢዱልጥባ) የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ መንግሥት በፓርኩ ውስጥ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከፓርኩ ለማስወጣት የ158 ሚሊዮን ብር ካሳ ክፍያ ሲፈጽም የአማራ ክልልም ለተነሺዎች ምትክ ቦታ በማዘጋጀት የከተማ ቦታ በመስጠትና ተነሺዎች ንብረታቸውን እንዲያጓጉዙ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ በመደገፍ ሥራው ስኬታማ እንዲሆን ማድረጉን የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን ዘውዴ ገልጸዋል፡፡
በዓለም ቅርሶች ቀይ (የአደጋ) መዝገብ ዝርዝር ውስጥ የገባውን የስሜን ብሔራዊ ፓርክ ወቅታዊ ገጽታ ለመመልከት የተገኘው የዩኔስኮ ልዑክ በሚያዝያ ወር ባደረገው ግምገማ መነሻ ሪፖርቱን በማቅረቡ ሰኔ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በፖላንድዋ ክራኮው ከተማ በተካሄደው የዓለም ቅርስ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ከመከረበት በኋላ ፓርኩ መሻሻል በማሳየቱ ከዩኔስኮ የአደጋ መዝገብ እንዲወጣ ወስኗል፡፡
ለውሳኔው ያበቃውም በፓርኩ ሰፍረው የነበሩ 412 አባወራዎች በመውጣታቸው፣ ፓርኩን አቋርጦ የሚያልፈውን መንገድ በመዝጋት ሌላ አማራጭ መንገድ መሠራቱ፣ እንደ ዋልያና ጭላዳ ዝንጀሮ ያሉ ብርቅዬ እንስሳት ጠብቆ በማቆየት የተሠራው ሥራና የእንስሳቱ ቁጥር መጨመር ዓይነተኛ መሆኑን ኮሚቴው ገልጿል።
እንደ አቶ ዘሪሁን አገላለጽ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ፓርኩን ለመታደግ የ10 ዓመት ዕቅድ በማዘጋጀት እንቅስቃሴ ተደርጓል። 140 ደርሶ የነበረውን የዋልያና ቀይ ቀበሮ ቁጥርም 800 ማድረስ መቻሉንና የቱሪስት ማቆያዎችም መሠራታቸውን ከቀይ መዝገቡ ለመውጣት አስተዋጽዖ ማድረጉን ሳይገልጹ አላለፉም።
በቀጣይም ከዚህ ቀደም የገባበት የአደጋ መዝገብ ውስጥ እንዳይገባ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ እንክብካቤ ለፓርኩ ይደረግለታልም ብለዋል።
አጠቃላይ የቆዳ ስፋቱ 412 ኪሎ ስኩዬር ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የስሜን ብሔራዊ ፓርክ፣ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ አይቤክስ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ቀይ ቀበሮና የምኒልክ ድኩላን ጨምሮ የበርካታ የዱር እንስሳት መገኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዓይነተ ብዙ ዕፀዋትና አስደናቂ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ በጋራ የያዘ ስፍራ ነው፡፡
በሰሜን ጎንደር ዞን የበየዳ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የተገኘውን መረጃ ጠቅሶ በኩር ጋዜጣ እንደዘገበው፣ ከበየዳ ወረዳ 17 ቀበሌዎች ውስጥ 15ቱ የስሜን ብሔራዊ ፓርክ አዋሳኝ ናቸው፡፡ በፓርኩ ዙሪያ የሚገኙት ተራሮች ራስ ደጀን (4543 ሜትር ከባሕር ወለል በላይ)፣ ግልገል ደጀን (4510 ሜትር)፣ አናሎ (4473 ሜትር)፣ ወይኖ በር (4465 ሜትር)፣ አቡነ ያሬድ (4453 ሜትር)፣ ጠፋው ለዘር (4409 ሜትር)፣ የመሳሰሉ ከፍተኛ ተራሮች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከስሜን ብሔራዊ ፓርክ በተጨማሪ በዩኔስኮ በተለያዩ ዓመታት ያስመዘገበቻቸው ባህላዊ ቅርሶች፡- የአክሱም፣ ፋሲል ግንብ፣ ሐረር ጁገል፣ ኮንሶ መልክዓ ምድር፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና የጢያ ትክል ድንጋዮች መሆናቸው ይታወቃል፡፡
በተያያዘ ዜና የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ኮሚቴ እንደ ስሜን ብሔራዊ ፓርክ ሁሉ ለ14 ዓመታት በአደጋ መዝገብ ውስጥ ገብቶ የነበረው የአይቮሪኮስት ኮሜ ብሔራዊ ፓርክ ተነስቶለታል፡፡
በሌላ በኩልም እስከ ሐምሌ 5 ቀን የሚዘልቀው የኮሚቴው 41ኛ ስብሰባ ለዓለም ቅርስነት በዕጩነት በቀረቡ ባህላዊ ቦታዎች ላይ ውሳኔ የሚሰጡ ሲሆን ከእነሱም አንዷ ሆና የቀረበችው የኤርትራዋ መዲና አስመራ ናት፡፡ ዩኔስኮ በድረ ገጹ እንዳመለከተው፣ ከተማዋ የታጨችው ‹‹አስመራ፡ የአፍሪካ የዘመናዊ ሥልጣኔ አሻራ ከተማ›› በሚል ነው፡፡