Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ሰሞኑን ጣና ሐይቅ እምቦጭ በሚሉት የአረም ነቀርሳ አደጋ ውስጥ መውደቁን አስመልከተው አያሌ ዘመቻዎች ሲካሄዱ፣ ነፍሴ ለሁለት ተከፍላብኝ ልጻፍ አልጻፍ ስል ከረምኩ፡፡

የጣናን ብዝኃ ሕይወት በተመለከተ ሠፊ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ መገናኛ ብዙኃኑም ሆኑ ከፍተኛ ተቋማቱ በሰፊው ያትታሉ፡፡ እኔም ይኼንኑ ጉዳይ በተመለከተ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ታዋቂ ምሁራን ባካሄዱት የጥናትና ምርምር ውይይት፣ እንዲሁም የጉብኝት መርሐ ግብር ላይ ተሳትፌ ነበርና ሁኔታው ግራ ገብ ቢሆንብኝ ሳመነታ እስካሁን ጉዳዩን ሳላነሳ ቆየሁ፡፡

የታዘብኩት ይህን ይመስላል፡፡ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከእምቦጭ አረም ጋር በተያያዘ ወደ 15 ሚሊዮን ብር ገደማ በጀት እንደነበረው፣ ሰፊ የምርምር ሥራዎችን እየሠራና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየታተረ እንደሆነ፣ ከአጋር አካላትም ሰፊ ድጋፍ እንዳለ ተነገረን፡፡ በተለይም፣ ‹‹አረሙን በኬሚካል ወይስ በማሽን በማንሳትና በመፍጨት ማስወገድ ይሻላል? የሚለው ላይ በጥንቃቄ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፤›› ተባለ ይገርማል፡፡ ይህ አረም እኮ በአሜሪካ እንደተንሠራፋና ጀልባ ላይ በሚገጠም ማሽን እየታፈሰ እየተፈጨ እንደሚወገድ ራሳቸው ይናገራሉ፡፡ አሜሪካኖቹ ያላገኙትን የኬሚካል መከላካያ እያጠናን ነው ሊሉን ፈልገው ይሆን?

ለማንኛውም አስገራሚው ነገር በጀልባ ላይ የሚገጠመው አረሙን የመሰብሰቢያና የመፍጫ መሣሪያ ከአምስት ሚሊዮን ብር በታች መገዛት እንደሚችል በባለሙያዎቹ ሲነገር መስማታችን ነበር፡፡ እናም አንዱ በውይይቱ ወቅት፣ “ይህን ካወቃችሁ ማሽኑን ከመግዛት ይልቅ ጥናትና ምርምር የምትሉት ጣናን የፈንድ (ዕርዳታ) ማሰባሰቢያ አድርጋችሁት እንጂ፣ መፍትሔው ጠፍቷቸሁ አይደለም፡፡ እባካችሁ በአገርና በሕዝብ ላይ አትቀልዱ፤›› የሚል አስተያየት ሰነዘረ፡፡ መልስ አልነበረም፡፡

ቀጥሎም ጎርጎራ አካባቢ ያሉ ገበሬዎችን የማናገር ዕድሉን አግኝቼ ነበር፡፡ አረሙን ከውኃው ላይ አንስተው ወደ መሬት ሲጥሉት ወዲያው እንደሚደርቅና በፊት በፊት ይህን ያደርጉ እንደነበር አጫወቱኝ፡፡ ‹‹አሁን አሁን ግን ደከመን፣ ዩኒቨርሲቲው ለዚህ የተመደበ ከፍተኛ በጀት እንዳለው እንሰማለን፣ እኛን ግን በነፃ ያደክሙናል፣ ችግሩ የጋራችን አይደለም እንዴ?›› ይላሉ፡፡

መጀመርያውንም እኮ ሕዝቡ ተፈጥሮን ለማከም ባዕድ አይደለም፡፡ ሕዝቡን ሲያርቁት አረሙ ይበልጥ ዋጣቸው እንጂ፡፡ እስከ መቼ ከሕዝብ በመነጠል ራስንም አገርንም ዳዋ ውስጥ ስንጥል እንኖራለን? ያሳዝናል፡፡ ሰሞኑንም ይኸው በዘመቻ ሕዝቡ መከራ እያየ ነው፣ አንዲት ማሽን ላለመግዛት፡፡

እናም እላለሁ፣ ‹‹ለማኝ ቁስሉን ያካል እንጂ አያክምም፤›› ለምን ቢሉ እንጀራው ነውና፡፡ ይልቅንስ በወቅቱ ከቀረቡትና በጣና ብዝኃ ሕይወት ላይ ዓብይ አደጋ ጋርጠዋል ተብለው በአንድ የዘርፉ ባለሙያ ከተነገሩን ጉዳዮች ውስጥ ጥቂቱን ላጫውታችሁ፡፡

1) ከጣና ቅርብ ርቀት ላይ ያለ የአበባ እርሻና በዚህ እርሻ ላይ ጥቅም ላይ የሚውለው ኬሚካል ሰውንም ሆነ አካባቢን አምካኝ መሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ ውስጥ ለውስጥ እየሰረገ ጣናንም ሆነ በአካባቢው ያሉትን ዕፅዋትና ነፍሳት አደጋ ውስጥ ከቷል፡፡

2) የዓባይና የጣና የውኃ ጋን የሆኑት ጮቄና ጉናን የመሳሰሉ አካባቢዎች በደን ምንጣሮና መሰል አውዳሚ ምክንያቶች የወደፊቱን የአካባቢውን ብዝኃ ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡

3) በባህር ዳር አካባቢ ካሉ አንዳንድ አይነኬ ሆቴሎች የሚለቀቁ የተበከሉ ፍሳሾች ጣናንና አካባቢውን አደጋ ላይ ጥለዋል፡፡

እናም እንላለን በወቅቱ አንዱ የጥናት አቅራቢ፣ ‹‹በብዝኃ ሕይወት ሚዛን ውስጥ አላስፈላጊው ፍጡር ሰው ብቻ ነው፤›› ያሉትን ወስደን ችግሮቹም መፍትሔዎቹም እኛው ስለሆንን፣ ለማይረባ የጥናትና ምርምር ዕርዳታ (ፈንድ) አገርን አንግደል፡፡ አገርን በማይለውጡና ማኅበረሰብን ተጠቃሚ በማያደርጉ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰቶች (ኢንቨስትመንት) ስም የአገርን ተስፋ አናምክን፡፡

ለእኛ ከእኛ ውጭ ማንም የለም!!

(በአካል ንጉሤ፣ በፌስቡክ ገጹ እንዳሰፈረው)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ምርቃት በመስቀል ክብረ በዓል

የመስቀል ክብረ በዓልን ከሚገልጹት ባህላዊ መገለጫዎች አንዱ ምርቃት ነው፡፡...

የማራቶን ባለክብረ ወሰኗ ከተዓምራዊ ጫማ ባሻገር ድሏ በታሪክ የሚዘከርላት አትሌት

በኢትዮጵያ በየዕለቱ የረሃብ፣ የመፈናቀል፣ የጦርነትና የኑሮ ግሽበት በተለያዩ የሚዲያ...

ግብፅ የያዘችው አቋም ድርድሩ የተመሠረተበትን መርህ ለመናድ ያለመ ነው ተባለ

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የውኃ አሞላልና የግድቡ ዓመታዊ...

በጦርነት የወደመውን የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ ለመጠገን ተቋራጮች ሊመረጡ ነው

ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰበት የባህር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል ምትክ...