- መንግሥት ለረጅም ጊዜ ማበረታቻ እየሰጠ መቀጠሉን ሊያቆም እንደሚችል አሳሰበ
- የመግንሥትና የግሉ ዘርፍን ትብብር የሚገዛ ረቂቅ ሕግ ለምክር ቤት ቀርቧል
ፕሪሳይስ ኮንሰልት ኢንተርናሽናል የተባለው አማካሪ ኩባንያ በሚያዘጋጀው ዓመታዊው ፎረም ላይ የተገኙት የንግድ ኩባንያዎች ሥራ አስፈጻሚዎች፣ መንግሥት ሊያስተካክላቸው ይገባዋል ያሏቸውን ነጥቦች በማንሳት ለገንዝብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አቀረቡ፡፡
ባለፈው ሳምንት ለስድስተኛ ጊዜ በተካሄደውና ‹‹ዘ ስቴት ኦፍ ኢትዮጵያን ኢኮኖሚ›› በሚል ርዕስ በተሰናዳው የሥራ አስፈጻሚዎች ፎረም በተጋባዥነት የተገኙት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ፣ ከንግድ ማኅበረሰቡ አባላት ጋር ባደረጉት ቆይታ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል የናሽናል ኦይል ኩባንያ (ኖክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ጥላሁን ጥያቄዎቻቸውንና አስተያየታቸውን ካቀረቡት መካከል ቀዳሚው ነበሩ፡፡ አቶ ታደሰ፣ ‹‹እኔ ኪራይ ሰብሳቢ አይደለሁም፤›› በማለት ነበር ሐሳባቸውን መግለጽ የጀመሩት፡፡ መንግሥት ፖሊሲዎችን በሚቀርፅበትና በሚያረቅበት ወቅት የግል ዘርፉን ሐሳቦችና አመለካከቶች ለማካተት ሲሳነው ይታያል፣ ለውይይት የሚመጣውም ፖሊሲዎቹን ከቀረፀ በኋላ በመሆኑ ይህ ሊስተካከል ይገባዋል ያሉት አቶ ታደሰ፣ ‹‹መንግሥት ቀርቦ ያነጋግረን፣ በግንባር ያወያየን፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የንግዱን ማኅበረሰብ የሚመለከቱ ጉዳዮች በቀጥታ ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናትና ኃላፊዎች እንዲያውቀው ከማድረግ ይልቅ፣ በተዘዋዋሪ ወይም በሚዲያ በኩል እንዲያውቀው መደረጉ አግባብ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡ በተለይ ኩባንያቸው በተሰማራበት የነዳጅ ንግድና የሎጂስቲክስ አገልግሎት መስክ የድርሻውን ለማበርከት ቢጥርም ፈተና የሆኑበት በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ በመጥቀስ፣ መንግሥት የዘርፉን ተዋንያን ቀርቦ እንዲያነጋግራቸው ጠይቀዋል፡፡ በተለይ ዶ/ር አብርሃም ለግሉ ዘርፍ አባላት ጊዜ ሰጥተው ፊት ለፊት ለማነጋገርና ለማወያየት በመምጣታቸው መደሰታቸውን አቶ ታደሰ ገልጸው፣ ሌሎችም ባለሥልጣናት የዶ/ር አብርሃም ዓይነት ተነሳሽነት እንዲታይባቸው በመመኘት ሚኒስትሩን አሞግሰዋል፡፡
የትራንሽን ኩባንያ (የቀድሞው ቴክኖ ሞባይል ኩባንያን የተካ ድርጅት) ሸሪክ አቶ ሌቪ ግርማ በበኩላቸው፣ መንግሥት ለቆዳና ለጨርቃ ጨርቅ ዘርፎች የሰጠውን ትኩረት ለሞባይል ኢንዱስትሪው አለመስጠቱ ለምን እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡ ኩባንያቸው የ40 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ኤክስፖርት ቢያደርግም፣ ሌሎች አምራቾችም ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡት ምርት መጠን እየጨመረ ቢመጣም፣ ዘርፉ ለምን ተገቢውን ድጋፍና ዕውቅና እንደማይሰጠው ግራ እንዳጋባቸው ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት በሚያወጣቸው የግዥ ጨረታዎች ወቅት ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች ቅድሚያ የሚሰጥበት ሕግ ቢኖርም፣ በተግባር ግን ከጨረታ እንዲገለሉ እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ አቶ ሌቪ ይህ እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡
የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋልያ ቆዳ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ዓለማየሁ በበኩላቸው፣ መንግሥት ለዘርፉ ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም በፋይናንስ አቅርቦት ረገድ በተለይ ከረዥም ጊዜ ብድርና ከሥራ ማስኬጃ ገንዘብ አኳያ ፋብሪካዎች ከባድ ችግር እየገጠማቸው እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡ ትልቅ ነው በማለት ያቀረቡት ችግር ለረዥም ጊዜ ተብሎ የሚሰጠው ብድር ከአምስት ዓመት የማይልጥ መሆኑ ብቻም ሳይሆን፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ እንዲከፈል ታስቦ ለሚሰጠው ብድር የሚጠየቁት ወለድም ከፍተኛ ሊባል የሚችል መሆኑንና የሚጠየቁት የብድር ማስያዣ ለቆዳ ኢንዱስትሪው ተዋንያን ራስ ምታት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም መንግሥት እነዚህን ችግሮች እንዲፈታ ጥያቄ በማቅረብ በማበረታቻ ረገድም በሌሎች አገሮች ለላኪዎች የሚሰጡ የተለመዱ ማበረታቻዎችን በኢትዮጵያ እንዲተገበሩ ጠይቀዋል፡፡ ይኸውም ያመረቷቸውን የፋብሪካ ውጤቶች ወደ ውጭ በመላክ ከሚያመጡት የውጭ ምንዛሪ ገቢ አኳያ እየታየ ከ30 እስከ 35 በመቶ የሚሆነው በአገር ውስጥ የመገበያያ ገንዘብ ተለውጦ (ካሽ ባክ ኢንሴንቲቭስ) የሚመለስበት አሠራር በኢትዮጵያም እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡
ከዲጂታል ቴክሎጂ ትግበራና ከሠራተኛና አሠሪዎች አዋጅ አኳያ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የሚታዩ መጉላላቶች እንዲታዩ የሚሉትን ጨምሮ ሌሎችም ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ የፕሪሳይስ ኮንሰልት ኢንተርናሽናል መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሔኖክ አሰፋ ፎረሙን በመምራት እግረ መንገዳቸውን የአገሪቱ ወጪ ንግድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣቱን በማሳሰብ፣ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ለመቅረፍ ምን እያደረገ እንደሚገኝም ጠይቀዋል፡፡
ዶ/ር አብርሃም በሰጡት ምላሽ፣ የውጭ ምንዛሪ በብዛት እንዲመጣ ማድረግ የግሉ ዘርፍ ድርሻ እንደሆነና በብዛት ወደ ውጭ የመላክ ሥራም የመንግሥት ሳይሆን የንግድ ማኅበረሰቡ በመሆኑ፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ መሥራት የሚጠበቅበትም ይኼው አካል ነው ብለዋል፡፡ የመንግሥት ድርሻ የመሠረተ ልማት አውታሮችን የማቅረብ፣ ፖሊሲዎችን የማውጣትና የማገዝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንደሚፈልግ፣ ግልጽነት በተሞላበት አኳኋንም የንግዱን ማኅበረሰብ በማወያየት ችግራቸውን ለመረዳትና ለመቅረፍ ይሠራል ብለዋል፡፡
ይሁንና መንግሥት ከሚገባው በላይ ለረዥም ጊዜ የቆየ ማበረታቻ ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች ሲሰጥ መቆየቱንና ይህንንም የውጭ ሰዎች እንደሚገልጹላቸው የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ወደፊት እንዲህ ያለው ድጋፍ ሊኖር እንደማይችል በማሰብ ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚገባቸው ሥራ አስፈጻሚዎቹን አሳስበዋል፡፡ መንግሥት ኢኮኖሚውን ከሚገባው በላይ ከለላ በመስጠት ከውጭ ውድድር እንዳይገጥመው እየተከላከለ መቆየቱን በመጥቀስ፣ የውጭ ኩባንያዎች በፋይናንስ ኢንዱስትሪውና በሌላውም መስክ ሊገቡ የሚችሉበት ዕድል እንደሚኖርም አክለዋል፡፡
በሌላ በኩል በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል በአጋርነት ለመሥራት የሚያስችል ማዕቀፍ ለመፍጠር ረቂቅ ሕግ ተዘጋጅቶ ለተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡንም ዶ/ር አብርሃም አስረድተዋል፡፡ ሕጉ ያስፈለገው አጋርነቱን ለማምጣትና የግሉን ዘርፍ ለማደፋፈር፣ ብሎም ሥጋቶቹን ለመጋራት እንዲቻል ተብሎ በመሆኑ ከዚህ ቀደም በአጋርነት ለመሥራት ሲቀርቡ ለቆዩ ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ ረቂቅ ሕጉ በመጪው ዓመት እንደሚፀድቅ ታውቋል፡፡
ፕሪሳይስ ኮንሰልት ከአሥር ዓመት በፊት ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሱት በአቶ ሔኖክ አሰፋ የተመሠረተ ሲሆን፣ ላለፉት አምስት ዓመታትም የሥራ አስፈጻሚዎች ፎረም በማካሄድ በተለያዩ የንግዱ ዘርፍ ጉዳዮች ላይ የውይይት መድረክ በመፍጠር ሐሳቦች እንዲንሸራሸሩ ሲያመቻች ቆይቷል፡፡ የተመሠረተበትን አሥረኛ ዓመትም ከስድስተኛው ፎረም ጎን ለጎን ዘክሯል፡፡