Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲስ አበባ ፋብሪካዎች ለመገንባት ጥያቄ ላቀረቡ 189 ኢንቨስተሮች መሬት ተዘጋጀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ ከ200 በላይ የሚሆኑ ኢንቨስተሮች ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ለፋብሪካዎች ግንባታ መሬት እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም፣ በተለያዩ ምክንያቶች መስተናገድ ሳይችሉ ቆይተው በመጨረሻ ሰኞ ሰኔ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ለ189 ኢንቨስተሮች መሬት መዘጋጀቱ ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት፣ ኢንቨስተሮቹ በጠየቁት ልክ ባይሆንም ለ189 ኢንቨስተሮች መሬት ማዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ ሰኔ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው ስም ዝርዝር ስሙ ያልተካተተ፣ ወይም ያቀረበበት ቀን በትክክል አልተካተተም የሚል አልሚ በአሥር ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርግ አስታውቋል፡፡

የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ ኅዳር 24 ቀን 2004 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ፣ በአዲስ አበባ ከተማ መሬት ለአልሚዎች የሚቀርበው በጨረታ ብቻ እንዲሆን ደንግጓል፡፡ ነገር ግን የመሬት ጥያቄው ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ከሆነ አስተዳደሩ መሬት በምደባ ያቀርባል ይላል፡፡

እነዚህ የመሬት ጥያቄዎች ያቀረቡት ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ግንባታ  ቢሆንም፣ አስተዳደሩ በቂ ቦታ ማዘጋጀት ባለመቻሉና ጥያቄዎቹን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ማስተናገድ የተሻለ ነው የሚል ሐሳብ በማቅረቡ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት የአልሚዎቹ ጥያቄ መስተናገድ ሳይችል ቀርቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለእነዚህ የቆዩ ጥያቄዎች መልስ ከሰጠ በኋላ፣ በመቀጠል የሚመጡ የኢንዱስትሪ መሬት ጥያቄዎችን በኢንዱስትሪ ፓርኮች የማስተናገድ ዕቅድ ማውጣቱ ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይ ለኢንዱስትሪዎች ግንባታ መሬት ሲሰጥ የቆየበት የማስፋፊያ ቦታ በማለቅ ላይ በመሆኑ፣ የአልሚዎችን የተናጠል የመሬት ጥያቄ ማስተናገድ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡

በዚህ መሠረት ምናልባት ይህ የመሬት ጥያቄ መስተንግዶ የመጨረሻ ሊሆን፣ እንደሚችል፣ ከ189 ፕሮጀክቶች አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች የተስተናገዱት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ፋብሪካዎች በተለይ የምግብ፣ የብረታ ብረት፣ የፕላስቲክ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የቆዳ ውጤቶች፣ የአልሙኒየም ውጤቶች፣ የተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያና የመሳሰሉትን ያመርታሉ ተብሎ ታቅዷል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች