Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹በባህረ ሰላጤው አካባቢ ያለው ችግር ካልተፈታ የአፍሪካ ቀንድን ሊያቃውስ ይችላል››

‹‹በባህረ ሰላጤው አካባቢ ያለው ችግር ካልተፈታ የአፍሪካ ቀንድን ሊያቃውስ ይችላል››

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

በባህረ ሰላጤው የዓረብ አገሮች መካከል ያለው ውዝግብ በፍጥነት ካልተፈታ፣ ለኢትዮጵያ ሥጋት እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓርብ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2010 በጀትን ለማፅደቅ በተገኙበት ወቅት፣ በባህረ ሰላጤው አካባቢ ያለው ቀውስ በኢትዮጵያ ላይ ስለሚኖረው አንድምታ ተጠይቀዋል፡፡

‹‹ይህ ጉዳይ በሰከነ ሁኔታ መፈታት አለበት የሚል አቋም በእኛ በኩል ይዘናል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ‹‹በውስጣቸው ያለው አለመግባባት በፍጥነት ካልተፈታ የአፍሪካ ቀንድን በዋነኝነትም ኢትዮጵያን ሊያቃውስ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አቋም ብቻ ሳይሆን የያዘችው ግፊትም እያደረገች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በአፍሪካ ኅብረት እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በኩል ጭምር ግፊት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዋናው ጉዳይ የቀይ ባህር መስመር አንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የንግድ ዕቃ የሚመላለስበት በመሆኑና የኢትዮጵያም ወጪና ገቢ ዕቃ በዚሁ መስመር የሚተላለፍ ስለሆነ፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስባት ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌላ በኩል ያነሱት የአገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ መቀዛቀዝ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ችግር እንዲጎላ ካደረጉት ጉዳዮች መካከል የአበባ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ መንግሥት ያደረገው ጥረት ክልሎች መሬት ባለማቅረባቸው መገታቱን ጠቁመዋል፡፡

አሁንም ቢሆን የመሬት ማነቆው እንዳልተፈታ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአማራጭ መፍትሔነት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታዎች ውስጥ የሚገኙ መሬቶችን መጠቀም መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በዚህ የመፍትሔ አቅጣጫ ሦስት ሺሕ ሔክታር መሬት መገኘቱንና ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ለአበባ ኢንቨስትመንት ጥቅም ላይ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት በኩል ሌላው ፈተና የሆነው ችግር የኃይል አቅርቦት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሁለት ሺሕ ሜጋ ዋት ኃይል ማቅረብ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡

አገሪቱ አሁን ካላት 4,600 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ግማሹን የሚወስድ በመሆኑ፣ ተጨማሪ ኃይል በፍጥነት መቅረብ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማው የተገኙት በ2010 ዓ.ም. በጀት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ ጥያቄዎች ከረቂቅ በጀቱ ጋር የሚገናኙ አልነበሩም፡፡ ለ2010 ዓ.ም. የቀረበው 320.8 ቢሊዮን ብር በጀት በፓርላማው ፀድቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...