Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየጣና ሐይቅ ሃምሳ ሺሕ ሔክታር ስፋት በእንቦጭ አረም ተሸፍኗል

የጣና ሐይቅ ሃምሳ ሺሕ ሔክታር ስፋት በእንቦጭ አረም ተሸፍኗል

ቀን:

በቅርብ ጊዜ ከተጋረጡ አደጋዎች መካከል አንዱ የሆነው የእንቦጭ አረም፣ በጣና ሐይቅ ላይ ከሃምሳ ሺሕ ሔክታር በላይ መሸፈኑ ታወቀ፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ ዳይሬክተርና የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ተመራማሪ የሆኑት ሳሙኤል ሳህሌ (ዶ/ር)፣ በአሁኑ ወቅት ይህ የእንቦጭ አረም ከ50 ሺሕ ሔክታር በላይ የሚሆነውን የጣና ሐይቅ እየጎዳ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እሳቸው የእንቦጨ አረም በሐይቁ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ምርምር እያደረጉ ነው፡፡

የጣና ሐይቅ በዚህ አረም አደጋ ላይ እንደሆነ የሚገልጹት ተመራማሪው፣ ይህንን ችግር ለመፍታት ባለፈው ወር ከጎንደር ዩኒቨርሲቲና ከደንና አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ውይይት  በጣና ሐይቅ ዙሪያ ያሉ የወረዳ አመራሮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተው የችግሩን አሳሳቢነት ለማስረዳት መሞከሩን ገልጸዋል፡፡

በእሳቸውና በሌሎች ምሁራን የተሠሩ ጥናቶች ቀርበው ውይይት መደረጉንም አስረድተዋል፡፡ እነዚህ  የምርምር ውጤቶችም ተዓማኒ እንደሆኑ ገልጸው፣ ጣና ሐይቅ በአሁኑ ወቅት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ያለ በመሆኑ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሊያስብበት እንደሚገባ ጠቁማዋል፡፡

ጣና ሐይቅ የገዳማት መገኛና የቱሪስቶች መስህብ ከመሆኑ በተጨማሪ ለአካባቢና ለአየር ጥበቃ የራሱን አስተዋጽኦ የሚያደርግ ስለሆነ ከአሁን መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሰሃራ በረሃ እየተስፋፋ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ሐይቁ ፈተና የተጋረጠበት ቢሆንም፣ በአረሙ ሳቢያ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ መውደቁን አስረድተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የውኃው መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

ተመራማሪው፣ ‹‹የጣና ሐይቅ ውኃ ቀነሰ ወይም ለመጥፋት መንገድ ላይ ሆነ ማለት ለአገሪቱ ትልቅ ኪሳራ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የእንቦጭ አረም ውኃው ውስጥ ያለውን አልሚ ምግብና ውኃውን በመጠቀም እንደሚያድግና ውኃውን ከሐይቁ እየወሰደና መሬቱን እያደረቀ እንደሚሄድ አስረድተዋል፡፡ በየጊዜው እየሄዱ ሁኔታውን እንደሚከታተሉ የሚናገሩት ተመራማሪው፣ አረሙ በየቀኑ ሊገለጽ በማይችል ሁኔታ እየሰፋ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ይህንን ችግር የተወሰኑ ወገኖች ብቻ በመረባረብ ሊፈቱት እንደማይችሉም ገልጸዋል፡፡

የሐረማያ ሐይቅ ሲደርቅ የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን እየሠሩ እዚያው እንደነበሩ የሚናገሩት ተመራማሪው፣ ጣናም የዚያ ዓይነት ዕጣ ፈንታ እንደተጋረጠበት ሥጋታቸውን ተናግረዋል፡፡

የሐረማያ ሐይቅ ሊደርቅ  የቻለው ወደ ውስጥ የሚገባው ደለል ክትትል ባለመደረጉ ምክንያት ምንጮች በደለሉ በመሞላታቸው እንደሆነ ገልጸው፣ ጣና ሐይቅም በዙሪያው ካሉ ከተሞች በሚወጣው ፍሳሽና በክረምት ወቅት ወደ ሐይቁ በሚገባው ደለል ሳቢያ ከዚህ በፊት ለአደጋዎች የተጋለጠ ቢሆንም፣ አሁን ደግሞ ሌላ አደጋ መከሰቱ የሐይቁን  ህልውና ጥያቄ ውስጥ እንዳስገባው ጠቁመዋል፡፡

አሁን ባለበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻልም መቆጣጠር እንደሚቻል ተመራማሪው አስረድተዋል፡፡ ይህ አደጋ ጣና ሐይቅ በሚያዋስናቸው አካባቢዎች በተለይም በሰሜን ጎንደር፣ ጎርጎራ፣ አቼራ፣ ደንቢያ፣ ደንቢትና ማክሰኝት በሚባሉት አካባቢዎች በከፍተኛ መጠን ተስፋፍቶ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ እንቦጭ አረም በአብዛኛው የሚከሰተውም በክረምት ደለል በሚመጣበት ወቅት እንደሆነ ገልጸው፣ ጉዳዩን አገራዊ አጀንዳ አድርጎ ዛሬ ነገ ሳይባል መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ከ10 እስከ 15 በመቶ ወይም ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የአካባቢው ሕዝብ ኑሮው የተመሠረተው በጣና ሐይቅ ላይ ነው፡፡ የባህር ዳር ከተማን ጨምሮ በምዕራብ ጎጃም፣ በደቡብና  ሰሜን ጎንደር ዞኖች የሚገኙ 54 ቀበሌ ገበሬ ማኅበራት መሠረታቸው ከጣና ሐይቅ ከሚገኝ የዓሳ ምርትና መስኖ እንደሆነ ይነገራል፡፡

በዓለም ትልቁ ወንዝ ዓባይ ጣና ሐይቅን አቋርጦ የሚሄድ ሲሆን፣ ወደ ሐይቁ ከሚገቡ ወንዞችና ጅረቶች መካከል ግልገል ዓባይ፣ ርብ፣ ጉማራ፣ እንፍለንዝና መገጭ ይገኙበታል፡፡ በጣና ሐይቅ ላይ ከ30 በላይ ደሴቶች ሲኖሩ፣ ደሴቶቹ በጥንታዊ ገዳማትና ታሪክ የታጨቁ ናቸው፡፡ ጣና ሐይቅ 90 ኪሎ ሜትር የጎን ስፋት፣ 385 ኪሎ ሜትር የጠርዝ ርዝመት አለው፡፡ ሐይቁ ከአራት እስከ 14 ሜትር ጥልቀት ሲኖረው፣ አማካይ ጥልቀቱ ስምንት ሜትር እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የአማራ ክልል የደንና የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ ኃላፊዎች በዚህ ጉዳይ ለማነጋገር   የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ የክልሉና የዞኑ ኃላፊዎችም በዚሁ ጉዳይ ላይ ስብሰባ ተቀምጠዋል ተብሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...