Monday, March 27, 2023

የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሒደትና ማብቂያው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ለአንድ አገር ዕድገት ቁልፍ ተደርገው  ከሚወሰዱት ጉዳዮች መካከል አንዱ የዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት ነው፡፡ በአንድ አገር የዴሞክራሲ ደረጃው ከፍ ባለ ቁጥር በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ከፍተኛ የሆነ ቅርርብና ቁርኝት በመፍጠር፣ የአገርን ሁለንተናዊ ዕድገት ማምጣት ይቻላል፡፡ መንግሥት ጠንካራ የሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ሲገነባ በሕዝቦች መካከል ብሔራዊ አንድነት ከመፍጠር ባሻገር፣ አገሪቱን ከሌሎች አገሮች የተሻለችና ከፍ ያለች በማድረግ በኩል የሚኖረው ሚና ጉልህ ነው፡፡

የዴሞክራሲ ሥርዓት በጎለበተበት አገር ዕድገቱም አብሮ እየጎለበተ እንደሚሄድ የአውሮፓና የአሜሪካ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ሰዎች መሠረታዊ መብቶቻቸው ሲከበሩላቸው ሙሉ በሙሉ ጊዜያቸውንና አዕምሮአቸውን በሥራ የሚያሳልፉ ይሆናሉ፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ራስን በኢኮኖሚ የተሻለ በማድረግ አገርንም የሚያለማ ዜጋ መፍጠር እንደሚቻል ብዙዎችን ያስማማል፡፡

በአፍሪካ አገሮች ውስጥ መሪዎች ከተወሰኑት በስተቀር የሰው ልጆችን መሠረታዊ መብቶች ባለማክበራቸው የተነሳ ዜጎች መብቶቻቸውን ለማስከበር ደፋ ቀና ሲሉ ይታያሉ፡፡ መብቶቻቸው የተከበሩላቸው ባለመሆናቸውም ጊዜያቸውን በሥራ ከማሳለፍ ይልቅ መሠረታዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር ከላይ ታች ሲሉ ይታያሉ፡፡ ገፋ ሲል በሰላማዊ ሠልፍና በተለያዩ መንገዶች ጥያቄዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ ስደትን መዳረሻቸው ያደርጋሉ፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ባልሰፈነባቸው የአፍሪካ አገሮች እየሆነ ያለውም ይህ ነው፡፡

መንግሥታት ለይስሙላ በሕገ መንግሥት ላይ ዴሞክራሲ እንዲጎለብትና የሰው ልጅ መሠረታዊ መብቶች እንዲከበሩ ሕግ ቢያወጡም፣ ተግባራዊ ስለማያደርጉት ከሕዝብ ጋር ሆድና ጀርባ ሲሆኑ ይታያል፡፡ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ኢማኑኤል ሲግማ (ፕሮፌሰር) ‹‹መንግሥት ዴሞክራሲን በአገሩ ካልገነባ ሕዝቡ ጀርባውን ይሰጠዋል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የመንግሥቱም ጊዜ ያጥራል፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚም ይመነምናል፤›› በማለት ለአንድ አገር ዕድገት የዴሞክራሲ መጎልበት ያለውን ፋይዳ ያስረዳሉ፡፡

ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዋነኛ ተዋናይ እንደሆኑ ከሚጠቁሰት መካከል አስፈጻሚው አካል፣ ሚዲያ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማኅበራት ሚና ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ካሉት ሦስቱ የመንግሥት አካላት ማለትም ሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚው መካከል ሕግ አስፈጻሚው አካል ከፍተኛ የሆነ የቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን በትክክል ከተቆጣጠረና ሕግና ሕገ መንግሥቱን ብቻ መሠረት አድርጎ ሕዝብን ካገለገለ፣ አገር በሁለንተናዊ ዕድገቷ ከአንድ ምዕራፍ ወደ ሌላ የዕድገት ምዕራፍ መሸጋገሯ የማይቀር ይሆናል፡፡

የዴሞክራሲ ሥርዓት ከተዘረጋ ሚዲያው ኅብረተሰቡን መሠረት ያደረገ ሥራ በማከናወን በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል ይታመናል፡፡ በበለፀጉ አገሮች ሚዲያ እንደ አራተኛ መንግሥት የሚቆጠረው ለዴሞከራሲ ሥርዓት ያለው አቅም ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ የሚዲያ ሚና እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም፣ እንደ አፍሪካ ባሉ አገሮች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ሆኖ የሕዝቡን ፍላጎት ሳይሆን የገዥውን ፓርቲ ራዕይና ዓላማ የሚያራምድ በመሆኑ፣ ብዙ እንደማይራመድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ሕዝብና መንግሥት በሐሳብ ሳይገናኙ ይቀራሉ፡፡

ለዴሞክራሲ ግንባታ ሌላው ማራመጃ መሣሪያ ተደርገው ከሚቆጠሩ ባለድርሻ አካላት መካከል ሲቪል ማኅበራት ይካተታሉ፡፡ ሲቪል ማኅበራት ዜጎች በመደራጀት ዴሞከራሲያዊ መብቶቻቸውን እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ የሚያስችሉ መሣሪያዎች እንደሆኑ ይነገራል፡፡

ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ቁልፍ ሚና አላቸው ተብለው የሚጠሩት እነዚህ አካላት ተግባራቸውን በትክክል ሲወጡ ብቻ ውጤታማ ሥራ ሊከናወን እንደሚችል ምሁራን ይናገራሉ፡፡ በዚህ መሠረት ሰኔ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ‹‹የኛ ጉዳይ›› በሚል ርዕስ ለሚተላለፈው የቴሌቪዥን ፕሮግራም፣ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በውይይቱ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የአስፈጻሚ አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተገኝተው ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡ መምህራን ለውይይቱ መነሻ የሚሆን ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

የመነሻ ጽሑፍ ካቀረቡት መካከል አንዱ ደመቀ አቺሳ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የአስፈጻሚው አካልና የፖለቲካ  ፓርቲዎች ሚና ምንድነው? ለዴሞክራሲ ሥርዓት እሴቶች ምንድናቸው? በዴሞክራሲ ግንባታ ሒደት ላይ የነዚህ ባለድርሻ አካላት ተግዳሮቶች ምንድናቸው? ወዘተ. የሚሉትን አብራርተዋል፡፡ ደመቀ (ዶ/ር) እነዚህ ባለድርሻ አካላት ለዴሞክራሲ ግንባታ ያላቸውን አስተዋጽኦ ሲያብራሩ፣ ተሳታፊዎች በጥሞና ያዳመጡ ቢሆንም፣ ወደ ጥያቄና መልስ በተሄደበት ወቅት ግን ከታዳሚው በጣም ብዙ ቅሬታዎችና አስተያየቶች ይሰሙ ነበር፡፡

‹‹ከኃይለ ሥላሴ ጀምሮ ሕግ አስፈጻሚዎች ለብዙ ዘመናት ከሕገ መንግሥቱ ውጪ የሆነ ሥልጣን ነበራቸው፡፡ ንጉሡ ተጠያቂነት አልነበራቸውም፡፡ በደርግ ዘመነ መንግሥትም ሕገ መንግሥት ለይስሙላ ቢኖርም አስፈጻሚው አካል ተጠያቂ አልነበረም፤›› በማለት የኢሕአዴግን መንግሥት የአስፈጻሚ አካላት ተጠያቂነት ከድሮው ሥርዓት ጋር እያነፃፀሩ አቅርበዋል፡፡ ጥናት አቅራቢው ይህንን ቢሉም፣ ቅንጅትን የወከሉ አንድ ተሳታፊ፣ ‹‹እኔ ራሴን አሁን ካለው የኬንያና የአሜሪካ ዜጋ ጋር ነው የማወዳደረው እንጂ፣ በደርግ ዘመን ወይም ከዚያ በፊት ከነበረው ሥርዓት ጋር አላወዳድርም፤›› በማለት ኢሕአዴግ ራሱን ካለፉት ሥርዓቶች ጋር እያወዳደረና ራሱን እያሞካሸ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ከሚያጣ፣ ችግሩን በተለይም በአስፈጻሚው አካል ዘንድ እየታየ የመጣውን ሥር የሰደደ ችግር መፍታት እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡

ቪኮድ ሲቪል ማኅበርን የወከሉት አቶ ታደለ ደርሰህ በበኩላቸው፣ የዴሞክራሲ ውበቱ ልዩነትን ማስተናገድ ቢሆንም ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ 26 ዓመታት ሙሉ አንድ ወጣት ከዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ይዞ የሚወጣበት በመሆኑ፣ ኢሕአዴግ በደርግና በኃይለ ሥላሴ መፅናናት እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡ የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን በበኩላቸው፣ በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ መንግሥታት የሚወቀሱት ከወደቁ በኋላ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ጥናት አቅራቢው በመነሻ ጽሑፋቸው ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቁጥር መብዛትና ግልጽ ዓላማ ያላቸው ባለመሆኑ፣ በአገሪቱ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ እንዳይፈጠር እንቅፋት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ የሰማያዊ ፓርቲ የወቅቱ ፕሬዚዳንት አቶ የሸዋስ አሰፋ በጽሑፍ አቅራቢው ላይ ከፍተኛ የሆነ የተቃውሞ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ አቶ የሺዋስ፣ ‹‹ያለንን ዓላማ የምናስተላልፍለት ሚዲያ እስካላገኘን ድረስ ዓላማችንን በምን እናሳውቅ?››  የሚል ጥያቄ አዘል አስተያየት አቅርበዋል፡፡ ኢቢሲን ጨምሮ ሁሉም ሚዲያዎች የአንድ ፓርቲ ሐሳብ ብቻ መፍሰሻዎች እንደሆኑ በቅሬታ አቅርበዋል፡፡ የራዕይ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ በበኩላቸው፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቁጥር ለምን ጨመረ ለሚለው አስተያየት፣ ‹‹ይሂዱና ሕገ መንግሥቱን ይጠይቁት፤›› በማለት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቁጥር መጨመር ሕጉ የሚፈቅደውና ቁጥራቸው የበዛ ቢሆንም፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ደመቀ (ዶ/ር) በመነሻ ጽሑፋቸው ላይ ኢሕአዴግ ብቻ ግልጽ ፖሊሲ እንዳለው አብራርተዋል፡፡ አቶ የሺዋስ፣ ‹‹ኢሕአዴግ ብቻ ነው ግልጽ ፖሊሲ ያለው ብለው ባቀረቡት ሐሳብ በጣም ነው የተገረምኩት፡፡  ምክንያቱም መደገፍ ይቻላል፡፡ አባል ከሆኑ ሊገባዎት ይችላል፡፡ ነገር ግን የሰማያዊን ፓርቲ ሳያነቡ የለም ብለው ደምድመው መናገርዎ ስህተት ነው፤›› በማለት ተቃውመዋል፡፡

አቶ ታደለ በበኩላቸው፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ወደ 17 የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ ተብሏል፡፡ በየትኛው ሰዓትና ሚዲያ ነው አጀንዳቸውን አቅርበው ሕዝብ እንዲመርጣቸውና ግልጽ ፖሊሲያቸውን እንዲያሳውቁ የሚያደርጉት?›› በማለት የጥናት አቅራቢውን ሐሳብ ተቃውመዋል፡፡ አቶ ተሻለ በበኩላቸው፣ ‹‹ይቅርታ ይደረግልኝና ምነው አንድ ቀን እኛ ወንበር ላይ ተቀምጠው ቢያዩት? ወይም በአንድ ምርጫ ገብተው እንቅስቃሴውን ቢያዩ? እንደ ኢትዮጵያዊ ይህንን ስናገር ልቤ ይቆስላል፡፡ ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም ከአንድ ኢትዮጵያዊ ያውም ከአንጋፋው ዩኒቨርሲቲ የወጣ ምሁር እንደ ውጭ ዜጋ ይህን መሰል አስተያየት በተቃዋሚዎች ላይ መስጠት ተገቢ አይመስለኝም፤›› ብለዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ፣ ኢሕአዴግ ይዞት ከተነሳው ራዕይ አንፃር በአሁኑ ወቅት ግልጽ የሆነ ፖሊሲ እንዳለው አስረድተው፣ በአሁኑ ወቅት እየተፈጠረ ባለው የአውራ ፓርቲ ሥርዓት ተቃዋሚዎች ተጎጂ እንዳይሆኑ ፖሊሲያቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ ሊዘጋጅ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የቅንጅት ተወካይ ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እጅና እግር ታስሮ ባለበትና በነፃነት የጻፈና የተናገረ እስር ቤት በሚገባበት ወቅት፣ በምን ሁኔታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፖሊሲያቸውን ማስተዋወቅ እንዳለባቸው ጥያቄ አዘል አስተያየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የአውራ ፓርቲ ሥርዓት እየመጣ መሆኑ ተገልጿል፡፡ አቶ የሺዋስ የአውራ ፓርቲ ሥርዓት እየመጣ መሆኑን ጠቅሰው፣ እያንዳንዱ ፓርቲ ደንብና ሥርዓት ቢኖረውም ጽሑፍ አቅራቢው ጠቅልለው መናገራቸውን ኮንነዋል፡፡ በዚህም የወገንተኝነት ነገር እንደሚታይባቸው ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች በአብዛኛው ትኩረት ያደረጉት በተያዘው አጀንዳ ላይ ሳይሆን፣ በአገሪቱ ላይ በሚታዩ ሌሎች ተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮች ነበር፡፡

ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የባለድርሻ አካላት ሚና ምንድነው የሚለው የመወያያ ርዕስ ሆኖ ቢቀርብም፣ ብዙ ሐሳቦች ከዚህ አጀንዳ ውስጥ ሲንሸራሸሩ ነበር፡፡ የቅንጅት ተወካይ፣ ‹‹አሁን የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት ምን ያህል ዓመታት ያስፈልገናል?  ዛሬ ላይ ብንጀምር ምን ያህል ዓመት ይፈጅብናል?  ምክንያቱም ኢሕአዴግ 26 ዓመት ሙሉ ዴሞክራሲ ሒደት ነው እያለን ነው፡፡ ስለዚህ ሒደት ሆኖ የሚኖረው እስከ መቼ ነው?›› የሚል ጠንከር ያለ ጥያቄያቸውን በወቅቱ ለነበሩ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች አቅርበዋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ጊዜ የመጻፍ ነፃነት ተከብሯል ይባላል፡፡ ስለጻፉ አይደለም እንዴ ጋዜጠኞች እስር ቤት የሚገቡት? በአሁኑ ጊዜስ የሕዝቡን ብሶት የሚናገሩ ምን ያህል ሚዲያዎች አሉ? ባለሥልጣናት በምን ሁኔታ እዚህ ቦታ ላይ እንደወጡ ብናውቅም ባናውቅም በማስፈጸም ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች ይጠየቃሉ ወይ?›› የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡

አቶ አባዱላ በበኩላቸው፣ የዴሞክራሲ ግንባታ በ24 ሰዓት ሊፈጸም እንደማይችል ግልጽ አድርገዋል፡፡ ‹‹ይህ ቢሆን ኖሮ ከ1984 ዓ.ም. ማግሥት ጀምሮ ተግባራዊ ባደረግነው ነበር፤›› ብለዋል፡፡ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ያልተፈጠረባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም፣ በማማረር የተለወጠ አገር እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

መድረኩን ይመራ የነበረው ጋዜጠኛ የሚሰጡ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ከአጀንዳው እንዳይወጡ በተደጋጋሚ ጊዜ አስተያየት ቢናገርም፣ ተሳታፊዎች ግን ከመናገር አልተቆጠቡም ነበር፡፡ የቅንጅት ተወካይ ይህን አስተያየት ከሰጡ በኋላ አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ዓባይ ስብሃት አካሄዱ መስተካከል እንዳለበት ጣልቃ በመግባት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ‹‹አጀንዳው ለዴሞክራሲ ግንባታ የባለድርሻ አካላት ሚና ምን መሆን አለበት የሚል እንጂ ስለኢሕአደግ፣ ቅንጅትና ሰማያዊ ፓርቲ ምን አገባን? በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ደግሞ ፕሮግራም ያዙልንና በሌላ ቀን እንወያያለን፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ከመሠረቱ ወደ ጭቃ እየገባን ነው፤›› በማለት አካሄዱ እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡

በዚህ የውይይት መድረክ ብዙ ተሳታፊዎች አስተያየት ለመስጠት ዕድል እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ባለማግኘታቸው፣ መድረኩን ጥለው ሲወጡ ተስተውሏል፡፡

በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚዲያውና የሲቪል ማኅበራት ሚና ምን መሆን አለበት የሚለውን የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር መሰለ መንግሥተአብ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ሚዲያ አገር መገንባትና ዴሞክራሲን የማስፈን አቅም ቢኖረውም የማፍረስ አቅም እንዳለውም አብራርተዋል፡፡ በብዙዎች ዘንድ አራተኛ መንግሥት እየተባለ እንደሚጠራም አስረድተዋል፡፡ ሚዲያ ሁሉንም ዓይነት መስተጋብሮች የሚያራምድ ከመሆኑ አንፃር ፋይዳው የጎላ እንደሆነ በመግቢያ ጽሑፋቸው ላይ አብራርተዋል፡፡

ሚዲያ ያለው ፋይዳ ጉልህ እንደሆነና ከዚህ እስከዚህ ተብሎ ሊለካ እንደማይችል የተናገሩት አንድ ስማቸውን ያልጠቀሱ አስተያየት ሰጪ፣ ሚዲያው በገዥው ፓርቲ ሥር ተጠርንፎ የተያዘ በመሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆኑ ሌሎች ማኅበራት ለሕዝቡ የሚጠቅሙ የዴሞክራሲ እሴቶችንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ማስተላለፍ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡

ጥናት አቅራቢው ሲቪል ማኅበራት ለዴሞክራሲ ግንባታ የራሳቸው ዋጋ ቢኖራቸውም፣ ባልተገባ መንገድ ሲተገበሩ እንደሚታዩም ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ እነዚህ ችግሮች አስፈጻሚው አካል በተገቢው መንገድ ለሕዝብ አገልጋይ ካለመሆኑ የመነጩ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ኢሕአዴግም በአሠራሬ ላይ ክፍተት ስላለ ቆም ብዬ በመፈተሽ ችግሬን ለማስተካከል እየሞከርኩ ነው ሲል የተደመጠ ሲሆን፣ በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ እያለፈ መሆኑንም ይናገራል፡፡ ይህ እንዳለ ቢሆንም አቶ ተሻለ ከረቂቅ እስከ ደቂቅ፣ ከመሬት እስከ ጠፈር ያሉት ጉዳዮች በሙሉ በኢሕአዴግ ቁጥጥር ሥር እንደሆኑ ያብራራሉ፡፡ ‹‹ሁሉም ነገር እኔም ጭምር በእነሱ ቁጥጥር ሥር ነኝ፤›› በማለት የኢሕአዴግን የበላይነትና ሁሉንም የእኔ ባይነት አባዜ ተቃውመዋል፡፡ ዓላማው በሥልጣን መቆየት እንጂ ይህንን ሥልጣን ሕዝባዊ አድርጌ ከወገኖቼ ጋር በዴሞከራሲ መንገድ እንዴት ልቀጥል? የሚል እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ አቶ ካሳ በበኩላቸው፣ ችግሮችን ወደ ውጭ ከመግፋት ይልቅ ወደ ውስጥ በማየት እያንዳንዱ ሰው አስተዋጽኦውን ማበርከት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ሁሉንም ነገር እኔ ብቻ ልቆጣጠር የሚል ቅዠት የለበትም፤›› በማለት ሚኒስትሩ ገልጸው፣ አሁን ባለው ሁኔታ እንከን የሌለበት አስፈጻሚ አካል በአገሪቱ ተገንብቷል ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

አቶ ካሳ በአሁኑ ወቅት ኢሕአዴግም እየሠራ ያለው አንድ ጊዜ ከወደቀ በኋላ ሌላ ኃይል መጥቶ ትክክል አይደለም ብሎ እንዲተቸው ሳይሆን፣ ያልሠራኋቸው ሥራዎች አሉ እያለ እየተመለከተ የሚሠራ መንግሥት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በመድረኩ ላይ መንግሥት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ የተገለጸ ሲሆን፣ አቶ ታደለ አጥር በማጠር በአገሪቱ ላይ ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል በመግለጽ፣ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የተወሰነ ኪሎ ሜትር ተሂዶ የአበባ እቅፍ ሊሰጣቸው እንደሚገባ መንግሥትን አሳስበዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችና አመራሮች የተገኙ ሲሆን፣ ከነዚህ መካከል ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳና ምክትላቸው ወ/ሮ ሽታየ ምናለ፣ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዛዲግ አብርሃና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡

ደመቀ (ዶ/ር) ባቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ ብዙ የተቃውሞ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣ በማጠቃለያ ንግግራቸው፣ ‹‹እኔ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ብሆን ኖሮ እንደዚህ ዓይነት አስተያየት የሰጡትን ግለሰቦች ወደ እስር ቤት እወረውራቸው ነበር፤›› በማለታቸው፣ ብዙዎች በመደናገጥ ከአንድ አንጋፋ ዩኒቨርሲቲ ከሚያስተምር ምሁር የማይጠበቅ እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

በመድረኩ ላይ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሊረጋገጥ የሚችለው በሒደት እንደሆነ ቢገለጽም ሒደት ነው፣ ሒደት ነው እየተባለ 26 ዓመታት ሙሉ ለውጥ የታየ ባለመሆኑ መንግሥት እንዲያስብበት አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡ ለሕዝብ የዴሞክራሲ ሥርዓት በመገንባት ላይ ነን እየተባለ ሁሌ የማታለያ ቃላትና የመደለያ ጥቅማ ጥቅም ከመስጠት ይልቅ፣ ቁርጠኛ ሆኖ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ዛሬ ነገ ሳይባል መግባት ተገቢ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ራሳቸውን ፈትሸውና የሕዝብ አገልጋይነት ስሜት ተላብሰው ዕርዳታ እየለመኑ ሕዝቡን ከማስተዳደር አባዜ ወጥተው፣ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት መሥራት እንዳለባቸው በርካቶች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ነፃ መድረክ በማዘጋጀትና የፖለቲካ ምኅዳሩን በማስፋት ያላቸውን ፖሊሲና ስትራቴጂ ለሕዝቡ ማሳወቅ እንዳለባቸው፣ እነሱም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ የሚል አስተያየትም ተሰንዝሯል፡፡

በአገሪቱ ያሉ ሚዲያዎች በተለይም የመንግሥት ሚዲያዎች ባለቤትነት በመንግሥት ቢሆኑም ነፃ፣ ግልጽና ሕዝብን መሠረት አድርገው እንዲሠሩም ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ሲቪል ማኅበራትም እንዲደራጁና ለዴሞክራሲ ግንባታ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መንግሥት ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -