Sunday, February 5, 2023

‹‹አዋጁ የኦሮሚያን ክልል ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ ሌላ ፕላኔት ውስጥ እንዳለች ያደርጋታል ብሎ ማሰብ ስህተት ነው››

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር

ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ከተከሰቱ አገራዊ ቀውሶች መካከል፣ በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫና ከዚህ ጋር በተያያዘ የተቀሰቀሰው ግጭት አንዱ ነው፡፡

በ2008 ዓ.ም. በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞና ነውጥ ደግሞ ሌላው ሲሆን፣ በዚህ ችግር የተነሳ ከስድስት መቶ በላይ የሰው ሕይወትና በሚሊዮን የሚቆጠር የአገር ሀብት መውደሙ ይታወሳል፡፡

በ2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ለተቀሰቀሰው ግጭትና ሁከት ዋነኛ ምክንያት እንደሆኑ ከሚጠቀሱት ጉዳዮች መካከል አንደኛው ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችና ከአዲስ አበባ የጋራ ማስተር ፕላን ጋር የተያያዘው ነው፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ተፈጥሮ በነበረ ቅሬታና ከዚህ ጋር በተያያዙ ሌሎች ጉዳዮች ከፍተኛ ችግር ተፈጥሮ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

የአዲስ አበባን ከተማ ወደ ጎን ለማስፋት በተደረገው እንቅስቃሴ ከኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን፣ ማስተር ፕላኑ ብዙ ጥያቄዎችን አስነስቶ አልፏል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ዘንድ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲነሳ የነበረው ዋነኛው ጉዳይ ደግሞ ኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ ልታገኝ ስለሚገባት ልዩ ጥቅም እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የዛሬዋ አዲስ አበባ ከዛሬ አንድ መቶ ዓመት በፊት የኦሮሚያ አርሶ አደሮች ይኖሩባትና  ፊንፊኔ እያሉ ይጠሯት እንደነበር ይነገራል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1886 ወደ 1887 ዓ.ም. የዘመን መለወጫ ላይ የንጉሠ ነገሥቱ መቀመጫ እጅግ ቀዝቃዛና አየሩ ተስማሚ ካልሆነው የእንጦጦ ከፍታ ትንሽ ኪሎ ሜትር ወረድ ብሎ፣ ከባህር ጠለል በላይ 2,500 ሜትር ከፍታ ወዳለው ረባዳ ሥፍራ እንደተዛወረም ይነገራል፡፡ ዋና ከተማውን ወደዚህ ሥፍራ ለማዞር ሐሳብ ያመነጩትና ስሙንም አዲስ አበባ ብለው የሰየሙት የዳግማዊ ምኒልክ ባለቤት እቴጌ ጣይቱ እንደነበሩ ታሪክ ያስረዳል፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አዲስ አበባ ተብላ መጠራት እንደጀመረች የሚነገርላት የዛሬዋ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ኅብረት፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሌሎች ድርጅቶች መቀመጫ ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡

ከዳግማዊ ምኒልክ እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ከደርግ ዘመነ መንግሥት እስከ ኢሕአዴግ ድረስ በአጠቃላይ ለ130 ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ ዋና መዲና ሆና እያገለገለች የምትገኘው አዲስ አበባ፣ ከጥቅም ጋር በተያያዘ ብዙ ጥያቄዎች ሲነሱባት ቆይቷል፡፡ የደርግ መንግሥትን ገርስሶ ወደ ሥልጣን የመጣው የኢሕአዴግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ አራት ዓመት በኋላ በፀደቀው ሕገ መንግሥት፣ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ጥቅም ልታገኝ እንደሚገባት ደንግጓል፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ በግልጽ እንደሰፈረው አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የምትገኝ በመሆኗ፣ ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ማግኘት ይገባታል፡፡ ከዛሬ 22 ዓመታት በፊት የፀደቀው ሕገ መንግሥት ዝርዝሩ በሕግ እንደሚወሰንም አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት ባለፈው ሳምንት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀርቧል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ያሉ የኦሮሚያ ተወላጆች ከከተማዋ የሚገባንን ጥቅም አላገኘንም የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲያነሱ ተደምጧል፡፡ ከዛሬ 22 ዓመታት በፊት በተግባር ላይ የዋለው ሕገ መንግሥት ይኼንን ጥያቄ በሚመልስ ደረጃ የወጣ ቢሆንም፣ ምላሽ ሳይጠሰው ቆይቷል በማለት ምሬት ሲሰማ ነበር፡፡ በዚህና ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌሎች ጥያቄዎች አማካይነት በክልሉ ውስጥ ከዓመት በፊት በተቀሰቀሰው የሕዝብ ጥያቄ በርካታ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ንብረት ወድሟል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ልታገኝ ስለሚገባት ልዩ ጥቅም አዲስ ረቂቅ አዋጅ አፅድቋል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ይፋ ከሆነ ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ዋነኛ መነጋገሪያ ጉዳይ ቢሆንም፣ ጉዳዩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ወደፊት በየደረጃው የሕዝብ ውይይት ይደረግበታል ተብሏል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ቅዳሜ ሰኔ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ጋዜጣዊ መግለጫ በጽሕፈት ቤታቸው ሰጥተዋል፡፡ ዶ/ር ነገሪ ለአንድ ሰዓት ያህል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከሃምሳ ደቂቃ በላይ ሰሞኑን የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ልታገኝ ስለሚገባት ልዩ ጥቅም በተመለከተ ስለተደነገገው አዲስ ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ላይ፣ ‹‹ሕገ መንግሥታችን የህልውናችን መሠረትና በሰላምና በአንድነት ለመኖር ትልቁ እሴታችን ነው፤›› በማለት ንግግራቸውን የጀመሩ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ተፈቃቅደው በተወካዮቻቸው ወይም በቀጥታ በውይይት በመሳተፍ የደነገጉት ሕገ መንግሥት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ በዚህ ገዥ በሆነው ሕገ መንግሥታችን ውስጥ የኦሮሚያን ክልል በተመለከተ የተደነገገ አንቀጽ አለ፡፡ ይኼ ደግሞ ልዩ ጥቅም በማለት የተቀመጠ ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የኦሮሚያ ክልል ገዢ ፓርቲ ኦሕዴድና በክልሉ መንግሥት ቀደም ሲል ውይይት ተደርጎበት፣ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የኢሕአዴግ ምክር ቤትና የፌዴራል ተቋማት ኃላፊዎች፣ የሕግ ባለሙያዎችና ሌሎች አካላት ከተወያዩበት በኋላ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ነው ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሄድ የተደረገው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ ይኼንን ጉዳይ በመመርመር ወደሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ እንደመራው አስረድተዋል፡፡

ይኼ ጉዳይ ሕዝቡ ገና በተለያዩ ደረጃዎች የሚወያይበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ‹‹እውነታው ይኼ ሆኖ ሳለ ጉዳዮን በአግባቡ መረዳት የማይችሉ አካላት እንዳሉ እንረዳለን፤›› ሲሉ ከሕዝቡ ጋር ውይይት ሳይደረግ ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር ነገሪ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ስላለው ልዩ ጥቅም ከመነሳቱ በፊት ለዚህ መሠረት የሆነው ጉዳይ ምን እንደሆነ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ የዛሬዋ አዲስ አበባ ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት የኦሮሚያ አርሶ አደሮች የሚኖሩባት እንደነበረች ጠቅሰዋል፡፡ ከመቶ ዓመት በፊት የኦሮሞ አርሶ አደር ከቀዬውና ከመሬቱ የተፈናቀለበት ጊዜም እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ሥርዓቱ የዜጎችንና የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት የሚያስጠብቅ ስላልነበረ፣ በኦሮሚያ አርሶ አደር ላይ ብዙ ችግሮች ደርሰው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ባይሆንም ከተማዋ እንደ ተመሠረተች፣ ከዛሬ ሃያ ስድስት ዓመት በፊት የነበሩት ሥርዓቶች ሕዝባዊ ስላልነበሩ በዚህ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ የኦሮሞ ተወላጆችና አርሶ አደሮች ግፍ ሲደርስባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በፊትም ቢሆን ሥርዓቱ እንጂ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ችግር እንዳልነበረ የጠቆሙት ዶ/ር ነገሪ፣ አንዱ ብሔረሰብ ሌላውን የመጉዳት ዓላማ እንዳልነበረውም አክለው አስረድተዋል፡፡ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በራሳቸው ፈቃድ ተግባብተው የሚኖሩና አብረው የሚሠሩ፣ አገራቸውንም በጋራ ከውጭ ወራሪ ኃይል የጠበቁ፣ በርካታ የጋራ እሴቶች የነበሯቸውና አሁንም ያላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አሁን ደግሞ ያ መጥፎ ሥርዓት መቀረፉንና የአሁኑ ሥርዓት ሕዝባዊ መሆኑን ተናግረው፣ የአሁኑ መንግሥት ለፍትሐዊነትና ለሕዝብ አንድነት የቆመ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እንደተሳተፉበት የገለጹት ሕገ መንግሥት፣ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም በማግኘት መስተካከል እንዳለበት በሚገልጽ ሁኔታ መደንገጉን አስረድተዋል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ በተለይም ደግሞ በዚህ በአዲስ አበባ ይኖር የነበረው ለአዲስ አበባ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ከዚያም አልፎ ለአፍሪካና ለዓለም ሕዝብ የሰጠው ልዩ ስጦታ እንዳለ ያስታወሱት ዶ/ር ነገሪ፣ ‹‹ልዩ ስጦታ ስንል የበፊቱ ሥርዓት ያደረገው ግፍ እንዳለ ሆኖ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አንድ ላይ በመሆን ሕገ መንግሥት በሚያፀድቁበት ጊዜ፣ የኦሮሞ ሕዝብም በተወካዮቹ በኩል ድምፅ ሰጥቷል፤›› ብለው፣ ‹‹ከዚያን ጊዜ በፊት እንደነበረው በግፍ የፈለገውን ማድረግ ሳይሆን፣ በፈቃደኝነት የሰጠው ስጦታ እንዳለ ማስታወስም ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከዚያን በኋላ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ስለዚህ ልዩ ስጦታውን ማስታወስ ይገባል፤›› በማለት አክለዋል፡፡

ልዩ ስጦታ በልዩ ጥቅም ምላሽ ያገኛል ማለት ሳይሆን፣ አሁን እንደ ልዩ ጥቅም የቀረበው ጉዳይ የተዛባውን ታሪክ ለማስተካከልና ለወደፊት የምትገነባውን አገር የተሻለች ለማድረግ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ እርካታው የኢኮኖሚ እርካታ ወይም ደግሞ የታክስ መሰብሰብ እርካታ ሳይሆን፣ የህሊናና የሞራል እርካታ ነው ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል በሚነሳበት ጊዜ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቢሮዎች ውስጥ የሚሠሩት ሁሉ የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ናቸው ብሎ ማሰብ የተሳሳተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ  የሌላ ብሔር ተወላጆች በኦሮሚያ ውስጥ እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ጥቅም ካለ የእነዚህ ዜጎችም ጥቅም እንደሆነ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

‹‹አዲስ አበባ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ ብቻም ሳትሆን፣ የሁላችንም የጋራ መገለጫችን የሆነች በመሆኗ አዲስ አበባ የሁላችንም የፖለቲካ ማዕከልም ናት፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ የአፍሪካ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ማዕከል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ያሉባት ከተማ መሆኗን አብራርተዋል፡፡

‹‹ይኼንን እንደ ልዩ ስጦታ ከተረዳን በኋላ ልዩ ጥቅም የሚባለውን ደግሞ መገንዘብ እንደምንችል ግልጽ ነው፤›› ብለው፣ ‹‹አዋጁ የኦሮሚያን ክልል ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ ሌላ ፕላኔት ውስጥ እንዳለች ያደርጋታል ብሎ መገንዘብ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም ኦሮሚያ ከፊንፊኔ በምታገኘው ጥቅም አይደለም የምታድገው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ እንደየትኛውም ክልል በሕዝቦች ጥረት እንደምትለማ አክለዋል፡፡

‹‹ኢሕአዴግ ከአራቱ ክልሎች ውጪ ያሉትን ታዳጊ ክልሎች በማለት ልዩ ድጋፍ ያደርግላቸዋል፤›› ካሉ በኋላ፣ ይኼ ደግሞ አንድ ጠንካራ የጋራ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እንደሚረዳ፣ ስለዚህ ልዩ ጥቅም ሲነሳ አላስፈላጊ ትርጉም የሚሰጡ አካላት ስላሉ መታረም አለባቸው ብለዋል፡፡

ኦሮሚያን የተለየ ፕላኔት ለማድረግ ሳይሆን በታሪክ የተዛባውንና የሚገባውን ልዩ ጥቅም ለማስጠበቅ መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ዶ/ር ነገሪ ግልጽ መሆን አለበት በማለት አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡ ይኼ ልዩ ጥቅም ሁሉንም ያረካል ወይም ደግሞ ለኦሮሚያ ሕዝብ ካሳ ይከፍላል ተብሎ እንደማይታሰብም አብራርተዋል፡፡ ጥቅሙ የሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ አንድን ብሔር ከሌላ ብሔር ልዩ ለማድረግ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡ የተገለጹት ጥቅሞች ግለሰባዊ ሳይሆኑ ተቋማዊ እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ ለምሳሌ አንድ የኦሮሚያ ተወላጅ ኦሮሚያ ስለሆነ ብቻ አዲስ አበባ ውስጥ የተለየ ጥቅም ያገኛል ማለት አይደለም ብለዋል፡፡ ስለዚህ ይኼንን ልዩ ጥቅም በተዛባ መንገድ በመረዳትና ክፍተት በመፈለግ፣ በሕዝቦች መካከል መቃቃር እንዲፈጠርና የአብሮነት እሴታቸው እንዲሸረሸር ማድረግ ስህተት ነው ሲሉ ዶ/ር ነገሪ ጠቁመዋል፡፡

ይኼ አዋጅ ምንም እንኳ ከሃያ ሁለት ዓመታት በኋላ የመጣ ቢሆንም ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ መንግሥት ለሕዝቡ ትልቅ ክብር እንዳለውና ሕዝባዊ እንደሆነ ያሳየበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ዜጎቹን በእኩል ዓይን የሚያይና የሚያስተናግድ መንግሥት እንደሆነ ማሳያ ነው፤›› በማለት የመንግሥትን ሕዝባዊነትና ሁሉንም በእኩል ዓይን የሚያይ መሆን በመጥቀስ መንግሥትን አሞካሽተዋል፡፡

‹‹ይኼ አዋጅ አሁን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወደሚመለከተው አካል ሄዷል፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በየደረጃው ሕዝብ ይወያይበታል፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር ነገሪ በመግለጫቸው ካነሷቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ጉዳይ ይኼ ሲሆን፣ የመነሻ ሐሳባቸውን ካጠቃለሉ በኋላ ጋዜጠኞች በዚህና በሌሎች ተያያዥ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ እንዲያነሱ ዕድል ሰጥተዋል፡፡ የአብዛኛዎቹ ጋዜጠኞች ጥያቄም የነበረው ከዚህ አዋጅ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡

ዶ/ር ነገሪ መጀመርያ ከተነሱላቸው ጥያቄዎች አዋጁ ሕዝብ ሳይወያይበት ለምን ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ? ከዚህ በፊት ማስተር ፕላኑን በተመለከተ ሕዝቡ ሳይወያይበት ብዙ ኪሳራ በአገሪቱ አስከትሏልና አሁንም ያንን ዓይነት ቀውስ እንዳያስከትል ምን ተሠርቷል? የሚሉ ናቸው፡፡ ዶ/ር ነገሪ በምላሻቸው፣ ‹‹ሕዝብ ሳይወያይበት ወደ ምክር ቤት ሄዷል ለተባለው የዚህ አዋጅ መጨረሻው አይደለም፡፡ በየደረጃው ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከተወያዩበት በኋላ ነው የሚፀድቀው፡፡ ነገር ግን ይኼ ጉዳይ በመጀመርያ ደረጃ ሕዝብ ውክልና በሰጣቸው፣ በተለይም በክልሉ መሪ ፓርቲና በአዲስ አበባ አስተዳደር አመራሮች ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በየደረጃው ሌሎች የመንግሥት አካላትም ተወያይተውበታል፡፡ ሕዝብን በዜሮ ላይ ማወያየት አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው የተነሳላቸው ጥያቄ ከአዋጁ ይዘቱ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ አዋጁ የአዲስ አበባን ወሰን አላስቀመጠም፡፡ አሁንም ለአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ ክልል የመስፋፋት ዕድል የሚፈቅድ እንደሆነ ከብዙ አካላት ሲነሳ እንደሚሰማና በዚህ ላይ ምን የሚሉት ነገር እንዳለ የተጠየቁ ሲሆን፣ ‹‹የአዋጁ ይዘት የአዲስ አበባን ወሰን አይመለከትም፡፡ የወሰን ጉዳይ ራሱን የቻለ ነው፡፡ ከዚህ ከአዋጅ በተለየ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይኼንን ችግር ለመፍታት እየተሠራ ነው፡፡ ወሰኑን በተለመከተ ከሁለቱ ክልሎች የአመራር አካላት መረጃ ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ ይኼንን ለመፍታት የጋራ ምክር ቤት ይቋቋማል፡፡ አሁን የወሰን ማካለሉ ሥራ እየተከናወነ ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

 ‹‹አዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ እንድትስፋፋ ዕድል ይሰጣል ለተባለው ትክክለኛ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ግልጽ ነው፡፡ ሁሉም የምንሠራቸው ሥራዎች ከሕዝብ ሊደበቁ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም የሥልጣን ባለቤቱ ሕዝብ ነው፡፡ መንግሥት ራሱን በሌላ ደሴት አድርጎ ከሕዝብ ተለይቶ የሚሠራቸው የሉም፡፡ ዘላቂ ስለማይሆኑ፡፡ ስለዚህ ምንም ሚስጥር የለም፡፡ በተደጋጋሚ እንደተባለው ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያያዞ ብዙ ክርክሮችና ውይይቶች ነበሩ፡፡ የችግሩ መንስዔ ስለነበር አዲስ አበባ አሁን በያዘችው ማደግ ትችላለች፡፡ የምታድገው ደግሞ ወደ ኦሮሚያ በመስፋፋት ሳይሆን ወደ ላይ ነው፡፡ ይኼ ነው የተያዘው አቋም፡፡ ነገር ግን በየትኛውም ዓለም እንደሚደረገው ከባለመብቶች ጋር በመስማማት የሚደረግ ይኖራል፡፡ ምክያቱም ኢትዮጵያን የሚመራ መንግሥት ከኦሮሚያ የተለየ አይደለም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር ነገሪ ሌላ የተነሳላቸው ጥያቄ ከማኅበራዊ ጠቀሜታዎች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በአዋጁ ላይ ልዩ ጥቅም ተብለው የተደነገጉት ጤናና ትምህርት በመሆናቸው የሕዝቡን ተጠቃሚነትን የሚያሳዩ አይደሉም፡፡ ከዚያ ይልቅ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች በግልጽ የተቀመጡ ባለመሆናቸው አዋጁ ከይስሙላ ያለፈ ብዙም ምላሽ የሚሰጥ አይደለም የሚል ነገር ይነሳልና በዚህ ዙሪያ የሚሉት ነገር አለ የሚል ነው፡፡ ዶ/ር ነጋሪ በምላሻቸው፣ ‹‹ከዚህ ጋር በተያያዘ ይኼንን ጉዳይ የምናይበት አመለካከት መቃኘት አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ከአንዳንድ ወገኖች የሚነሳው ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ግብር ለመሰብሰብ ነው የሚባለው ጉዳይ ለሞራልም ጥሩ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ “የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄም አይመስለኝም፤” ብለዋል፡፡ ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከኢኮኖሚው ተለይተው እንደማይታዩና ገንዘብ ሳይወጣበት የሚገነባ ምንም ነገር የለም ብለዋል፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ ከምታገኘው ገቢ ለኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ለተባለው የምታወጣው ወጪ እንደሚኖርና በሕግ በተቀመጠው መሠረት የክልሉን ማንነት የሚያንፀባርቁ ነገሮች እንደሚገነቡ ጠቁመዋል፡፡

ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ጥቅም ማግኘት እንደሚገባት በሕገ መንግሥቱ ላይ ሰፍሯል፡፡ ይኼ ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ ከዋለ ደግሞ ከሃያ ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ለምንድነው በሕጉ ላይ የሠፈረው ጉዳይ እስከዛሬ ተግባራዊ ሊሆን ያልቻለው? ለብዙ የኦሮሞ ወጣቶች ሞት ምክንያት እስከሚሆንስ መጠበቁ ለምን አስፈለገ? አሁን አዋጁን ማውጣት ያስፈለገበት ምክንያትስ ምንድነው? አስገዳጅ ሁኔታዎችስ ምንድናቸው? ተብለው የቀረቡ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ዶ/ር ነገሪ፣ “ለምን ዘገየ ለተባለው ምናልባት ጥናት ተደርጎበት ምክንያቱን በሳይንሳዊ መንገድ መመለስ የሚሻል ይመስለኛል፤” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አሁን ግን የራሱ የሆኑ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ምክንያቶች ሊኖሩት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ ትርጉም ያለው ጉዳይ ግን ከሕዝቡ ውይይት ጋር ተያያዥ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡   

ሕዝቡ ውይይት በሚያደርግበት ጊዜ ስምምነት ላይ ባይደርስ ረቂቅ አዋጁ የሚሻርበት ዕድልስ አለው? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ፣ “ሕዝቡ ተስማማበትም አልተስማማበትም እንዴት ነው የሚደረገው ለሚለው ጥያቂ ይኼንን መተንበይ አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ተጨባጭ በሆኑ ነገሮች ላይ ብንነጋገር የተሻለ ይመስለኛል፤” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ሕዝቡ በሚወያይበት ጊዜ አቋሙ እንደሚከበርና የሕዝቡ ፍላጐት መሠረታዊ እንደሆነ ግን ሁላችንም መረዳት አለብን፤” ብለዋል፡፡

“አሁን አዋጁ እንዲወጣ ወቅታዊ ምክንያት አለ ወይ ለሚባለው የተለየ ወቅታዊ ጉዳይ ስላለ አይደለም፤” ብለዋል፡፡ “መንግሥት በተለያዩ ምክንያቶች ቅድሚያ ሰጥቷቸው የሚሠራቸው ሥራዎች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ባለፈው ዓመት ከነበረው አለመረጋጋት ጋር የሚያያዝ ነው ብለው የሚገምቱ አካላት ቢኖሩም፣ መንግሥት ግን በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተቀመጠውን መተግበር ግዴታው እንደሆነ ያውቃል፤” በማለት አዋጁን ለማውጣት ወቅታዊ አስገዳጅ ሁኔታ ሳይሆን የመንግሥት የአሠራር ሥርዓት መሆኑን በማስረዳት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ሕዝቡ አስገድዶት ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠትም ትልቅ ነገር ነው ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ማግኘት ስለሚገባት ልዩ ጥቅም ሰሞኑን ከወጣው ረቂቅ አዋጅ ጋር በተያያዘ የቀረበላቸው ሌላው ጥያቄ፣ አገር የጋራ ነው፡፡ ለአንዱ ልዩ ስጦታ የሚሆንበትና ለሌላው ደግሞ የማይሆንበት መንገድ ምንድነው? ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት የነበረውን ነገር ካነሳን በሌላውም አካባቢ ተመሳሳይ ጉዳይ ሊኖር ይችላልና ይኼንን እንደ ልዩ ስጦታ መቁጠሩ ግልጽ ቢደረግ” የሚል ነው፡፡ ዶ/ር ነገሪ በምላሻቸው እንዳስረዱት፣ ልዩ ጥቅምን በሚመለከት ሌላ አካባቢ ጥያቄ ካለ መግለጽ እንደሚቻልና እስካሁን ባለው ሁኔታ ግን እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ነገሪ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከጋዜጠኞች ብዙ ጥያቄዎች ቢቀርቡላቸውም፣ መጨረሻ አካባቢ የተነሳውና የብዙዎችም ጥያቄ የነበረው፣ አሁን ባለንበት ዘመን ክፍለ አኅጉራዊ ውህደት እየተፈጠረ ባለበት ወቅት፣ ለአንዱ ብሔር የተለየ ጥቅም መስጠቱ በአንድ አገር ላይ ኢትዮጵያዊነትን የበለጠ የሚያዳክምና የሚከፋፍል ነገር አይፈጥርም ወይ? ሌላ ጥርጣሬና መፈራራትንስ የሚፈጥር ጉዳይ አይሆንም ወይ? የሚል ጥያቄ ነው፡፡ ‹‹ይኼ አዋጅ ግለሰቦችን መሠረት ያደረገ አይደለም፡፡ ምናልባት የምናይበት መነፅር ችግር ከሌለበት በስተቀር፡፡ ይኼ ሁሉንም በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ዶ/ር ነገሪ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያውያንን ከሳዑዲ ዓረቢያ ለማስወጣት በሚደረገው ጥረት የሳዑዲ ዓረቢያን መንግሥት የአንድ ወር ተጨማሪ የምሕረት ጊዜ መጨመር በተመለከተ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ የዚህ ቀነ ገደብ መራዘም ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ እየተጫወተችው ያለው ሚና አንዱ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከ111 ሺሕ በላይ ዜጎች የጉዞ ሰነድ ወስደው ለመውጣት እየተጠባበቁ መሆናቸውን፣ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት የምሕረት ጊዜውን ማራዘሙን ተከትሎ ብዙ ኢትዮጵያዊያን የመዘናጋት ሁኔታ እየታየባቸው እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ከሳምንት በፊት በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተመላሾች ሲጨናነቅ የሰነበተ ቢሆንም፣ የጊዜውን መራዘም ምክንያት በማድረግ ብዙ ኢትዮጵያዊያን መዘናጋት እየታየባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሦስት ወራት ውስጥ ከ45 ሺሕ በላይ ብቻ ማመላለስ የቻለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሃያ ቀናት ውስጥ 111 ሺሕ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊንን እንዴት ወደ አገራቸው መመለስ ይችላል ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር ነገሪ፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ከአውሮፕላን በተጨማሪ ሌሎች የትራንስፖርት አማራጮችን ለመጠቀም በዝግጅት ላይ ነው ብለዋል፡፡    

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -