- አዲሱ መመርያ ከፀደቀ የማዳበሪያ ግዥ በድርድር ይፈጸማል
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለመጪው ምርት ዘመን የሚያስፈልገውን የማዳበሪያ ግዥ በዚህ ወር እንደሚፈጽም ተገለጸ፡፡ ጨረታ ማውጣት ሳያስፈልገው ከዓለም አቀፍ አምራቾች ጋር ብቻ በመደራደር ግዥ ለመፈጸም በዝግጅት ላይ የሚገኘው አዲሱ የማዳበሪያ ግዥ ረቂቅ መመርያ መፅደቅ ይኖርበታል፡፡
ረቂቅ መመርያውን የማፅደቅም ሆነ የመሻር ሥልጣን ያለው የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ በሚቀጥሉት ሳምንታት መመርያውን ያፀድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሚኒስቴሩ ከዚህ በተጨማሪም ለ2010/2011 ምርት ዘመን የሚያስፈልገውን የማዳበሪያ ዓይነትና መጠን ከክልሎች ፍላጎት በመነሳት እያሰላ ሲሆን፣ መጠኑንም እንዲሁ በሚቀጥሉት ሳምንታት ለኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅርቦት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃን አወቀ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ በሐምሌ ወር መጨረሻ ወይም በነሐሴ ወር መጀመርያ የማዳበሪያ ግዥ ውስጥ ለመግባት አቅዷል፡፡
የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በዚህ ወር አዲሱን መመርያና ለቀጣዩ የምርት ዘመን የሚያስፈልገው ማዳበሪያ መጠን በቅርቡ እንደሚገልጽ የተናገሩት አቶ ብርሃን፣ ‹‹መመርያው ካልፀደቀ ግን እንደተለመደው የማዳበሪያ ግዥ በጨረታ ይፈጸማል፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በተቋቋመ በመጀመርያው ዓመት የተለያዩ የአሠራር ማሻሻያዎች በማድረግ ሁለት መሠረታዊ ውጤቶችን ማስመዝገቡ ተገልጿል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በማዳበሪያ ግዥ አሠራር ላይ የተወሰኑ ማስተካከያዎችን በማድረግ፣ 2.6 ቢሊዮን ብር (120 ሚሊዮን ዶላር) ማዳን መቻሉን መግለጹ ይታወሳል፡፡
የ2009/2010 ምርት ዘመን ማዳበሪያ በሐምሌ ወር መጀመርያ ተጠቃሎ መግባቱም ሌላ ስኬት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ባለፉት ዓመታት በተለይም በ2008 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ ወር ድረስ ማዳበሪያ ተጠቃሎ አልገባም ነበር፡፡
ኮርፖሬሽኑ በምርት ዘመኑ በዘጠኝ ቢሊዮን ብር ወጪ አሥር ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ከውጭ አገር ገዝቶ በማሠራጨት ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን አርሶ አደሮች የማዳበሪያ እጥረት እንዳጋጠማቸው ይናገራሉ፡፡ እንዲያውም አርሶ አደሮች ለመንግሥት ብዙኃን መገናኛ እንደገለጹት፣ የማዳበሪያ እጥረት ሲገጥማቸውና ያለውን ማዳበሪያ ገንዘብ ከፍለው ለመውሰድ ሲጠይቁ በብድር ካልሆነ እንደማይፈቀድላቸው አስረድተዋል፡፡
አቶ ብርሃን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ ከውጭ ያስገባውን ማዳበሪያ ለገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች፣ ዩኒየኖች ለመሠረታዊ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ማኅበራቱ ደግሞ ለአባላቶቻቸው ያከፋፍላሉ፡፡ ‹‹በዚህ ሒደት የሎጂስቲክስ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ክልሎች በቂ ማዳበሪያ ደርሷቸዋል፤›› በማለት አቶ ብርሃን ተናግረዋል፡፡
የማዳበሪያ ግዥ የገንዘብ አከፋፈልን በሚመለከት ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮዎች የሚሰጠው ምላሽ፣ በጥሬ ገንዘብ ግብይት ማካሄድ ማዳበሪያ ነጋዴ እጅ እንዲገባ ምክንያት ስለሚሆን ይህንን አሠራር ለመከላከል የብድር አሠራር የተሻለ አማራጭ ነው የሚል ነው፡፡
የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ ኢያሱ አብርሃ (ዶ/ር) እና ሌሎች የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ለማድረግ ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡