Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የአዲስ አበባ በጀት ቀመር ‹‹ከወጪ መደብ›› ወደ ፕሮግራም በጀት ሊሸጋገር ነው

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የአዲስ አበባ በጀት 40.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል

  ከንቲባ ድሪባ ኩማ የ2009 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2010 በጀት ዓመት ዋና ዋና ዕቅድ ሪፖርት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ሐምሌ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት፣ የከተማ አስተዳደሩ መሥሪያ ቤቶች የበጀት አመዳደብ ‹‹ከወጪ መደብ›› አሠራር ወደ ‹‹ፕሮግራም በጀት›› አሠራር እንደሚሸጋገር ገለጹ፡፡

  ይኼንን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳዳር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በካቢኔ መፅደቁን፣ ምክር ቤቱም እንዲያፀድቀው መቅረቡን ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

  ‹‹ይህ የፋይናንስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በምክር ቤት ፀድቆ ተግባራዊ መደረግ ሲጀምር፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የውስጥ አደረጃጀት የበለጠ ውስጣዊ ነፃነት እንዲጎናፀፍና መሥሪያ ቤቶቹ ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት እንዲችሉ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፤›› በማለት ከንቲባ ድሪባ በሪፖርታቸው አስታውቀዋል፡፡

  የወጪ መደብ የበጀት አመዳደብ ሥርዓት ላለፉት አሥርት ዓመታት ሲተገበር የቆየ ሲሆን፣ በዋናነት የበጀት ዝውውር በሚያስፈልግበት ወቅት ረዥም ሒደት የሚከተልና የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮንና የከንቲባውን ይሁንታ የሚፈልግ ነው፡፡ ይኼ አሠራር ለፕሮጀክቶች መጓተት እንደ ዓብይ ምክንያት ተደርጎ ሲቀርብ የቆየ በመሆኑ፣ በአዲሱ አሠራር ችግሩ ይቀረፋል ተብሏል፡፡

  አዲሱ አሠራር አንድ ባለበጀት መሥሪያ ቤት ሊያካሄድ ያቀዳቸውን ፕሮጀክቶች መሠረት ያደረገ በጀት በጥቅሉ እንዲመደብ የሚያደርግ ሲሆን፣ የበጀት ዝውውር ካስፈለገም የሚፈቅድ አሠራር ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥትም ይኼንን አሠራር ከአምስት ዓመታት በፊት ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ይኼ አሠራር ከንቲባ ድሪባ ኩማ እንደገለጹት፣ ለኃላፊዎች ነፃነት የሚሰጥ ነው፡፡

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር በ2009 በጀት ዓመት 33.4 ቢሊዮን ብር ለካፒታልና ለመደበኛ ወጪዎች ማፅደቁ ይታወሳል፡፡ ባለፉት 11 ወራት 31.5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 26.5 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን፣ ይኼም 85 በመቶ የዕቅድ አፈጻጸም እንዳለው ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

  ከወጪ አንፃር ባለፉት 11 ወራት 22.4 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገ መሆኑንና ከዚህ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው ለካፒታል ፕሮጀክቶች እንደሆነ ተገልጿል፡፡

  ለ2010 በጀት ዓመት የሚያስፈልገውን 40.5 ቢሊዮን ብር በጀት ምክር ቤቱ አፅድቋል፡፡ ይህም በጀት በፕሮግራም በጀት አመዳዳብ ሥሌት የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡

  ከንቲባ ድሪባ ከበጀት በተጨማሪም በንግድ አሠራር፣ በመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮችና በውኃ አቀርቦት ላይ የአስተዳደሩን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ከንቲባው እንዳሉት ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል ሁለት መሠረታዊ ሥልቶች ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ የመጀመርያው በዘርፉ መዋቅር፣ በንግዱ ማኅበረሰብና በሸማቾች ማኅበራት የሚከናወን መደበኛ ተግባር ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከፀረ ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ ግብረ ኃይል ጋር በጋራ የተሠራ ሥራ ነው፡፡

  በዚህ መሠረት በበጀት ዓመቱ በ242,500 የንግድ መደብሮች ላይ መደበኛ ቁጥጥር ለማድረግ ታቅዶ በ189,328 መደብሮች ላይ ቁጥጥር ተደርጓል ብለዋል፡፡

  ‹‹በዚህ ቁጥጥር በሕገወጦች ላይ ሕጋዊና አስተዳዳራዊ ማስተካከያዎች የተወሰዱ ሲሆን፣ 13 ሺሕ መደብሮች የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 8,597 መደብሮች ታሽገው እንዲቆዩ፣ 158 መደብሮች ንግድ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ተደርጓል፤›› በማለት ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰነድ አልባ ባለይዞታዎችን ጉዳይ በ2009 ዓ.ም. ለማጠናቀቅና ባለጉዳዮችን ሲያስተናግድ የቆየውን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የማፍረስ ዕቅድ ይዞ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ሥራው መጠናቀቅ ባለመቻሉ ለቀጣዩ በጀት ዓመት ተሸጋግሯል፡፡

  በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ1988 ዓ.ም. በፊት ጥያቄ የቀረበላቸው 4,553 ሰነድ አልባ ባለይዞታዎች ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ በተደረገው ሥራ፣ 4,175 ለሚሆኑ ባለይዞታዎች ጥያቄ ተመልሷል፡፡ 378 የሚሆኑት ደግሞ ጥያቄያቸው ለቀጣዩ በጀት ዓመት ተሸጋግሯል፡፡

  ከ1988 ዓ.ም. እስከ 1997 ዓ.ም. አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድ የተያዙ 11,029 ይዞታዎች ጥያቄያቸው ተስተናግዷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 9,430 ባለይዞታዎች የተዘጋጀላቸውን ካርታ ተረክበዋል፡፡ ቀሪዎቹ 1,599 ባለይዞታዎች እስካሁን መጥተው ካርታቸውን አልተረከቡም፡፡ በዚህ ሒደት በአጠቃላይ 37 ሺሕ ባለይዞታዎች ካርታ ተሰጥቷቸዋል፡፡

  በመልሶ ማልማት ፕሮግራም 186 ሔክታር መሬት ላይ ያረፉ 2,228 ቤቶች ለማፍረስ ታቅዶ 1,980 ቤቶች የፈረሱ መሆናቸውን፣ በዚህም 102 ሔክታር መሬት ሙሉ ለሙሉ ከሰው ንክኪ ነፃ መሆኑን ከንቲባ ድሪባ ገልጸዋል፡፡

  በንፁህ ውኃ አቅርቦት በኩል በተለይ ከፍተኛ የሆነ የውኃ ችግር የሚታይባቸው ኪስ ቦታዎች ላይ የሚታየውን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት፣ በተመረጡ አካባቢዎች 17 ጉድጓዶችን ለመቆፈር ታቅዶ የ13 ጉድጓዶች ቁፋሮ ተጠናቋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም ከንቲባ ድሪባ ባቀረቡት ሪፖርት በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች የሚያነሱትን የውኃ እጥረት ችግር ለመቅረፍ፣ በተለይም ለከተማው የመጠጥ ውኃ መገኛ የሆኑ አካባቢዎችን የንፁህ መጠጥ ውኃ አገልግሎት ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር የአሥር ጉድጓዶች ቁፍሮ ይካሄዳል ብለዋል፡፡

  ‹‹ቁፍሮ የሚካሄደው በሰበታ፣ በቡራዩ፣ በለገጣፎ፣ በሱሉልታ፣ በገላንና በአቃቂ ገጠራማ አካባቢዎች ነው፡፡ ለሚቆፈሩት ጉድጓዶች ሳይት መረጣ የኦሮሚያ ውኃ ሥራዎች ድርጅት እያካሄደ ነው፤›› በማለት ከንቲባ ድሪባ አስረድተዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች