[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ የሚያውቁት ኢንቨስተር ደወለላቸው]
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነህ ወዳጄ?
- አለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በጣም ጠፍተሃል፡፡
- ያው የሥራውን ነገር ያውቁት የለ?
- በጣም ረዥም ጊዜ ሆነህ ከደወልክ ብዬ ነው?
- ገንዘቤን ራሱ ማኔጅ ማድረግ ጊዜ ይጠይቃላ፡፡
- ለነገሩ ዕድሜ ለእኛ በል፡፡
- ማለት ክቡር ሚኒትር?
- ሀብታም አደረግንሃ?
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- እኔ እኮ ሀብቴን እዚህ አይደለም ያፈራሁት፡፡
- እንዴት ማለት?
- ከውጭ ነዋ ይዤ የመጣሁት፡፡
- ይኸው እዚህ እየሠራህ አይደል እንዴ?
- እሱማ ለአገሬ አንድ ነገር ልሥራ ብዬ ነው፡፡
- ለመሆኑ ዛሬ እንዴት ደወልክ?
- ዛሬ ከጓደኞቼ ጋር ተገናኝቼ ሳወራ ነበር፡፡
- ስለእኔ ነው?
- ስለእርስዎ ሳይሆን ምናልባት እርስዎን ስለሚመለከትዎ ጉዳይ፡፡
- እኮ ስለምን?
- ስለ 40/60፡፡
- እና 40/60 ምን ሆነ?
- በአጠቃላይ የመንግሥት አቅጣጫ ሊገባኝ አልቻለም፡፡
- እንዴት ማለት?
- ያው እኔ በርካታ ሪል ስቴት ቢዝነስ ውስጥ ያሉ ጓደኞች አሉኝ፡፡
- እሺ፡፡
- በቃ መንግሥት የቤቶች ግንባታ ላይ መግባቱ በጣም አስገርሞናል፡፡
- ደግሞ ቤት ለምን ሠራችሁ ልትሉን ነው?
- ክቡር ሚኒስትር ቤት መገንባት እኮ የመንግሥት ሥራ አይደለም፡፡
- እና የማን ነው?
- የሪል ስቴቶች ነዋ፡፡
- እነሱማ መቼ ለደሃው ይገነባሉ?
- እናንተም ለባለሥልጣናት አይደል እንዴት የገነባችሁት?
- ምን?
- ይኸው ባለአራት መኝታ ቤቶቹ የ40/60 ቤቶች ለባለሥልጣናት ሊሰጥ ነው እየተባለ አይደል እንዴ?
- ታዲያ ምን አለበት?
- እሱማ ምንም የለበትም፡፡ ግን. . .
- ግን ምን?
- በሕዝብ ሀብት ለባለሥልጣናቱ መገንባት ተገቢ አይደለማ፡፡
- ምን አለበት?
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ባለሥልጣናቱ ከሕዝብ አይደለም እንዴት የወጡት?
- ኧረ ሌላ ሰው እንዳይሰማዎት?
- ቢሰማስ ምን ያመጣል?
- ለነገሩ እንደዚያ ብላችሁ አይደል እንዴ ቤቶቹን ልትወስዱ ያሰፈሰፋችሁት?
- ሰውዬ ልትሳደብ ነው እንዴ የደወልከው?
- እኔማ መንግሥት የመንግሥትን ሥራ ብቻ ለምን አይሠራም ለማለት ነው የደወልኩት፡፡
- የመንግሥት ሥራ ምንድን ነው?
- ከበላይ ሆኖ የቤቶቹን ግንባታ መቆጣጠር፣ ባንኮች ብድር እንዲለቁ ማመቻቸት እንጂ የቤት ችርቻሮ ውስጥ መግባት የለበትም ባይ ነኝ፡፡
- የምን ችርቻሮ ነው?
- ይኸው ባለአንድ፣ ባለሁለት፣ ባለሦስትና ባለአራት መኝታ ቤቶች እያላችሁ እየቸረቸራችሁ አይደል እንዴ?
- ሕዝቡ የሚፈልገውን ነገር ከማድረግ አንቆጠብም፡፡
- በዚህ ከቀጠላችሁ ግን መንግሥት ሌላ ነገርም ሲቸረችር እንዳይገኝ፡፡
- ሌላ ምን?
- ማስቲካ!
[የክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞው ወዳጅ ስልክ ደወለላቸው]
- ሰላም ወዳጄ፡፡
- ምን እየሆናችሁ ነው ግን?
- ምን ሆንን?
- ከዚህ በላይ ምን ትሆኑ?
- አልገባኝም፡፡
- ስለ40/60 ነው የማወራው፡፡
- ደረሰህ እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር ደረስዎት ወይ ልበል እንጂ?
- ማለት?
- የገነባችሁት ለእናንተው አይደል እንዴ?
- የምታወራው አልገባኝም?
- ይኸው ባለአራት መኝታ ቤቱን ልትወስዱት አይደል እንዴ?
- ምን አለበት?
- ትንሽ አታፍሩም ግን?
- ምን ያሳፍራል?
- ለነገሩ ማፈር ካቆማችሁ ሰነባበታችሁ፡፡
- ሰውዬ ስድቡን ተወዋ፡፡
- እኔ የሚገርመኝ በዚህ ሕዝብ ላይ መጫወታችሁ ነው፡፡
- እንዴት ነው የተጫወትንበት?
- ይኸው ስንቱ ከልጆቹ ጉሮሮ ነጥቆ እየቆጠበ ነው፡፡
- ታዲያ ቤቶቹ እኮ በመቆጠብ ነው የሚገኙት፡፡
- ይኸው እናንተ ሳትቆጥቡ ሊደርሳችሁ አይደል እንዴ?
- ማን ነው ሳይቆጥብ የሚደርሰው?
- ባለሥልጣናቱ ናችኋ፡፡
- ሰው ግን ምቀኛ ነው፡፡
- እንዴት?
- አሁን እኛ ሳንቆጥብ ቢደርሰን ምን አለበት?
- የሚያሳዝነው እኮ እሱ አይደለም፡፡
- ታዲያ ምኑ ነው የሚያሳዝነው?
- ስንቱ ባለሥልጣን የግል ቤቱን እያከራየ ከሕዝቡ ጋር መሻማቱ ነዋ፡፡
- አሁን ባለሥልጣናቱ የግል ቤት እንዳላቸው ማስረጃ አለህ?
- ይኼማ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
- እኔ ግን የምቀኛ ወሬ ነው ባይ ነኝ፡፡
- ሌላው የገረመኝ አንድ ነገር ነበር፡፡
- ምንድነው እሱ?
- ባለአራት መኝታ ቤት ገንብተናል የምትሉት ነገር ነዋ፡፡
- ባለአራት መኝታ ቤትም ገንብተናል እኮ፡፡
- ኧረ በሕግ አምላክ?
- ምነው?
- እንዴ እኔ እኮ በደንብ አስታውሳለሁ?
- ምኑን?
- አሁን አራተኛ መኝታ ቤት የምትሏት የልብስ ማጠቢያ ማሽን የሚተከልባትን ጠባብ ክፍል ነው፡፡
- ቢሆንስ?
- ሕዝብ አያውቅም ብላችሁ አትጫወቱበት ስልዎት?
- እ. . .
- ከጀመሪያው ባለሦስት መኝታ ቤቱ ተጨማሪ የልብስ ማጠቢያ ማሽን የሚተከልበት ጠባብ አራተኛ ክፍል ነበረው፡፡
- እ. . .
- በቃ ክቡር ሚኒስትር በመንግሥት አያምርም፡፡
- ምኑ?
- ማጭበርበሩ!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ የአገር ውስጥ ኢንቨስተር ደወለላቸው]
- ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ማን ልበል?
- ባለፈው ያገኙኝ ኢንቨስተር ነኝ፡፡
- ኧረ እኔ ብዙ ኢንቨስተር ነው የማገኘው?
- ባለፈው እዛ ትልቁ ሆቴል ተገናኝተን ነበር፡፡
- እሺ ምን ፈልገህ ነው?
- ችግር ገጥሞኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምን ችግር?
- ይኸው ከመንግሥት ቦታ ተረክቤ ፋብሪካ ለማቋቋም ግንባታ ጀምሬ ነበር፡፡
- በጣም ጥሩ፡፡
- እናም የፋብሪካውን 75 በመቶ ግንባታ ካጠናቀቅኩ በኋላ አቁም ተባልኩ፡፡
- ለምን ተብሎ?
- እኔም ግራ ነው የተጋባሁት፡፡
- ለመሆኑ መሬት ተረክበህ ግንባታውን በአፋጣኝ ጀምረሃል?
- ስነግርዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ምኑን?
- እንደተቀበልኩ ግንባታ ጀምሬ 75 በመቶውን አጠናቅቄያለሁ፡፡
- ጥያቄው እኮ 75 በመቶ የሆነው በማን ተለክቶ ነው?
- በማንም ቢለካ ብዙ ኢንቨስትመንት አውጥቼበታለሁ ስልዎት፡፡
- ታዲያ ምን ተፈጠረ?
- በቃ አቁም አሉኝ፡፡
- በሕጋዊ መንገድ ነው ቦታውን የተረከብከው?
- ሕጋዊ ካርታ ተሰጥቶኛል ስልዎት፡፡
- እና ችግሩ ምንድነው?
- በጣም የሚገርም እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ለመሆኑ ከቦታው ላይ ለተነሱ ካሳ ከፍለሃል?
- እሱንም ያደረኩበት ማስረጃ አለኝ፡፡
- ታዲያ እንዴት አቁም አሉህ?
- ግራ ነው እኮ የሚገባዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ተሻለ ታዲያ?
- መሬቴን ያስመልሱልኝ ክቡር ሚኒስትር?
- እኔ እኮ አይደለሁም የሰጠውህ?
- ማለቴ ቢያንስ መሬቱን እንዴት ማስመለስ እንደምችል ቢያማክሩኝ፡፡
- ምክሬን በነፃ መስጠት አልችልም፡፡
- ማለት?
- ምክሬ ያስከፍላል፡፡
- ሁላችሁም ነው እንዴ የተበላሻችሁት?
- ምን እያልክ ነው?
- መሬቱ እንዲመለስልኝ ስጠይቅ እነሱም ክፍያ ነው እኮ የጠየቁኝ፡፡
- እነማን?
- መሬቱን የሰጡኝ አካላት፡፡
- ታዲያ ምን ችግር አለው?
- ራሳቸው ነጥቀው ገንዘብ ሰጥቼ ላስመልስ?
- እኔ ክፋቱ አይታየኝም፡፡
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- አንድ ማሰብ ያለብህ ነገር አለ?
- ምን?
- እነሱስ ያለአንተ. . .
- እ. . .
- ማን አላቸው?
[አንድ የውጭ ኢንቨስተር ለክቡር ሚኒስትሩ ደወለላቸው]
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ልታዘዝ?
- ምን ዓይነት አገር ነው ያላችሁ?
- በዕድገት ላይ ያለች አገር ናታ፡፡
- ወይ ዕድገት?
- ምነው?
- በጣም እየተማረርኩ ነው፡፡
- በምኑ?
- በሁሉም ነገር፡፡
- አልገባኝም?
- ይኸው ያን ሁላ ገንዘብ አፍስሼ ፋብሪካ ባቆምም ውኃ በሳምንት አንዴ ነው የሚመጣው፡፡
- አየህ ውኃ አላቂ ሀብት ስለሆነ በቁጠባ ነው መጠቀም ያለብን፡፡
- እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- የምሬን ነው እንጂ፡፡
- መብራትም ቢሆን በፈረቃ ነው የሚደርሰኝ፡፡
- አንተ ሀብታም አይደለህ እንዴ?
- አዎ ነኝ፡፡
- ስለዚህ መብራት ቢጠፋብህ ጀነሬተር መግዛት ትችላለህ፡፡
- እሱማ ጀነሬተር አለኝ፡፡
- አየህ ለአንተ ቢጠፋብህ ችግር የለም፡፡
- በጣም ቀልደኛ ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ኧረ እኔ የእውነቴን ነው፡፡
- የዚህ አገር ጣጣ በዚህ መቼ ያበቃል?
- ሌላ ምን አለ?
- ይኸው ለፋብሪካ የሚሆን ጥሬ ዕቃ ከጉምሩክ ለማስለቀቅ መከራ ነው፡፡
- የምን መከራ ነው የምታወራው?
- ብቻ አገሪቷ የሰነፍ አገር ናት፡፡
- በል እዚህ ላይ ታቆማለህ፡፡
- እንዴት?
- ኢትዮጵያ እኮ የጥቁር ሕዝብ ተምሳሌት ናት፡፡
- አውቃለሁ፡፡
- የጣሊያን ወራሪ ኃይልን መክታ ያሸነፈች የጀግኖች መገኛ ናት፡፡
- ትክክል ነው፡፡
- ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት ቁልፍ ሚና የተጫወተች አገር ናት፡፡
- አልተሳሳቱም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ምንድነው የሰነፍ አገር ናት የምትለው?
- አንድ ነገር ግን ልንገርዎት?
- ምን?
- በታሪክ መኮፈስ. . .
- እ. . .
- ዳቦ አይሆንም!