Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኬይ ግሩፕ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ሁለተኛ ውል ምዕራፍ ለመገንባት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ግንባታው ከፈቀደለት የህንዱ ኩባንያ ይነጠቃል

የህንድና የአሜሪካ ኩባንያዎች በሽርክና ያቋቋሙት ኬይ ግሩፕ ባለፈው ሐሙስ ሰኔ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጻፈው ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያንና የህንድን የረዥም ጊዜ ወዳጅነት ለማስጠበቅ ለበርካታ ዓመታት ሲጓተት ለቆየው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ መፍትሔ ይዞ መቅረቡን ገለጸ፡፡ ኩባንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ለኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን መመርያ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡

ኩባንያው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፈው ደብዳቤ ለስኳር ፕሮጀክት የሚሆኑ ኦሪጅናል ቴክኖሎጂ ያለው አምራች ኩባንያ መሆኑን ገልጾ፣ ሙሉ ፋብሪካ መገንባት የሚያስችል አቅምና የቴክኒክ ብቃት እንዳለው አስረድቷል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ የስኳርና የኢታኖል ፋብሪካ የማቋቋምና የስኳር ተረፈ ምርት በመጠቀም ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል የማምረት ፍላጎት አለን፤›› ሲል ኩባንያው ገልጾ፣ ከሦስተኛ ወገን (ከህንድ ኤግዚም ባንክ) ለፕሮጀክቶች የሚሆን ፋይናንስ እንደሚያመጣም አስታውቋል፡፡

‹‹በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የግንባታ ሒደት ላይ ግንዛቤ አለን፡፡ ፋብሪካውን  በመገንባት በኢትዮጵያና በህንድ መካከል ያለው የጋራ ጥቅምና ወዳጅነት የማስጠበቅ ፍላጎት አለን፤›› ሲል የኩባንያው ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ማብራርያ ሰጥቶ፣ ‹‹ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ጋር ድርድር ለማድረግ ይፈቀድልኝ፣›› በማለት ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ኬይ ግሩፕ ይኼንን ጥልቅ ፍላጎት የገለጸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ብቻ አይደለም፡፡ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትርና ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር በጻፈው ደብዳቤም ይኼንኑ ሐሳብ ገልጿል፡፡

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በ1998 ዓ.ም. ሥራው ለህንዱ ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አላየንስ በይፋ ተሰጥቶ ግንባታው ቢጀመርም፣ በተለያዩ ምክንያቶች በታሰበው መንገድ መሄድ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ፋብሪካው በሁለት ምዕራፎች የተከፈለ ፕሮጀክት ነው፡፡ የመጀመርያው ምዕራፍ 13 ሺሕ ኩንታል፣ ሁለተኛው ምዕራፍም 13 ሺሕ ኩንታል፣ በድምሩ 26 ሺሕ ኩንታል ስኳር በቀን የማምረት አቅም እንዲኖረው ታስቦ የተጀመረ ነው፡፡

ነገር ግን የመጀመርያው ምዕራፍ ፕሮጀክት በ1998 ዓ.ም. ተጀምሮ በጥቅምት 2007 ዓ.ም. ቢጠናቀቅም፣ የቴክኒክ ችግር ስላጋጠመው፣ ከዚሁ ጋርም ፕሮጀክቱ ረዥም ጊዜ የወሰደ በመሆኑ ባለፈው ዓመት ባጋጠመው ድርቅ አገዳው ለከብቶች መኖ እንዲውል ተደርጓል፡፡

የስኳር ኮርፖሬሽን ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጋሻው አይችሉም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት ተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክት የመጀመርያው ምዕራፍ 98 በመቶ ደርሷል፡፡ ፋብሪካው በሙከራ ስኳር ማምረት የሚችልበት ደረጃ ላይ ቢደርስም፣ ነገር ግን የሸንኮራ አገዳ በተለያዩ ምክንያቶች በመጥፋቱ በድጋሚ ማልማት አስፈልጓል ብለዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ልማቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ በመሆኑ በመስከረም 2010 ዓ.ም. ወደ ምርት ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ርብርብ እየተደረገ ያለውም ለዚሁ ለመጀመርያው ምዕራፍ ነው፤›› በማለት አቶ ጋሻው ገልጸው፣ ‹‹ሁለተኛው ምዕራፍ የማስፋፊያ ፕሮጀክት 20 በመቶ ላይ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የመጀመርያውን ምዕራፍ ለማጠናቀቅ ዘጠኝ ዓመታት በመውሰዱ ምክንያት፣ ሁለተኛውን ምዕራፍ ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አላይንስ ራሱ ይቀጥለዋል ወይ? የሚለው ጉዳይ የመንግሥትን ውሳኔ ገና አላገኘም፡፡

በዚህ ሒደት ሌላው ግዙፍ የህንድ ኩባንያ ቦቬት ኢንጂነሪንግ ሊትድ፣ ከአሜሪካው ሚስ ጄኤን ቦቬትና አሶሴት ጋር በሽርክና ኬይ ግሩፕ የተሰኘ ኩባንያ በማቋቋም፣ በተንዳሆ ላይ ልዩ ፍላጎት በማሳደር ለመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የድርድር ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ኬይ ግሩፕን ያቋቁሙት ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የስኳር ፕሮጀክት የሌላቸው ቢሆንም፣ በአፍሪካ በሱዳንና በቶጎ የስኳር ፕሮጀክቶች እንዳላቸው ታውቋል፡፡

የሱዳን ፕሮጀክት ማግኘት የቻሉትም የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ እየገነባ ከሚገኘው ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አላየንስ ተነጥቆ ተሰጥቷቸው መሆኑ ታውቋል፡፡ የሱዳን መንግሥት የስኳር ኩባንያ  ማሽኩር ሹገር ካምፓኒ ሊትድ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሙዋሚያ ባዳዊ፣ እ.ኤ.አ. ጥር 15 ቀን 2017 ለኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ የጻፉት ዳብዳቤ የነበራቸው የግንባታ ውል መቋረጡን ይገልጻል፡፡

ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አላየንስ ከኤግዚም ባንክ በተገኘ ብድር በሱዳን የሚገኘውን ማሽኩር ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ለማካሄድ ውል ቢገባም፣ ግንባታው ለሰባት ዓመታት በመጓተቱ ውሉ መቋረጡ በተጻፈለት ደብዳቤ ተገልጿል፡፡

ይህ የሱዳን ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ተነጥቆ ለኬይ ቦቬት ኢንጂነሪንግ  ሊትድ መስጠቱም ተገልጿል፡፡ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት በዝቅተኛው አዋሽ ተፋሰስ በአፋር ክልል ለ50 ሺሕ ሔክታር መሬት የሚለማ የሸንኮራ አገዳ ይጠቀማል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች