Sunday, May 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የ50 ሚሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ድርሻ የሚኖራቸው የቻይና ኩባንያዎች የቻይና ንግድ ሳምንት በተሰኘው ዓውደ ርዕይ እየተሳተፉ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የቻይና መንግሥት ይፋ ካደረገው ‹‹ዋን ቤልት ዋን ሮድ›› ከተሰኘውና አኅጉራትን እንደሚያስተሳስር ከሚነገርለት መጠነ ሰፊ የመሠረተ ልማት አውታር ዝርጋታ ዕቅድ ጋር የተገናኘው፣ የቻይና የንግድ ሳምንት የኢንቨስትመንትና የንግድ ዓውደ ርዕይ በአዲስ አበባ መካሔድ ጀምሯል፡፡ በዓውደ ርዕዩ እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉ ኩባንያዎች መሳተፋቸው ተነግሯል፡፡

 ማክሰኞ፣ ሰኔ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ የተከፈተው የቻይና ንግድ ሳምንት የኢንቨስትመንትና የንግድ ዓውደ ርዕይ፣ ከንግድ ግንኙነት ባሻገር የቻይናን የጎደፈ ስም የማደስ ዓላማም እንዳነገበ ተጠቅሷል፡፡ በመላው ዓለም የቻይና ዕቃዎች እርባናቢስ፣ በቶሎ የሚበላሹና የማያስተማምኑ እንደሆኑ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ የሰረፀ አመለካከት ተንሰራፍቷል ያሉት፣ ሚድል ኢስት ኢንተርናሽናል ግሩፕ የተባለው የዓውደ ርዕዮች አዘጋጅ ኩባንያ፣ የዓለም አቀፍ ዝግጅቶች ዳይሬክተር ሚሼል ሜሪይክ ናቸው፡፡ ሚሼል እንዳሉት ብቃት ያላቸውና የተመረጡ የቻይና ኩባንያዎች በሰታፉበት በቻይና የንግድ ሳምንት ተሳታፊዎች ታድመዋል፡፡ የቻይና ኩባንያዎችን ጨምሮ 400 ተሳታፊዎች በዓውደ ርዕዩ እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡

በኬንያ ሲካሔድ በቆየው የቻይና ንግድ ሳምንት ዓውደ ርዕይ፣ ከ35 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ ኢንቨስት በማድረግ የኬንያን የውጭ ኢንቨስትመንት መስክ የተቀላቀሉ እንዳሉ ይህም በዓውደ ርዕዩ ምክንያት በተፈጠረ ግንኙነት ሳቢያ እንደሆነ ያብራሩት ሚሼል ሜይሪክ፣ በኢትዮጵያም በዚሁ አኳኋን እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ሊያደርጉ የሚችሉ ኩባንያዎች መምጣታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

37 የቻይና ኩባንያዎች የተሳተፉበት ይህ ዓውደ ርዕይ ሐሙስ ሰኔ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ በዓውደ ርዕዩ የታደሙት በሙሉ በዘርፋቸው ተመርጠው የመጡና ከኢትዮጵያ ወገንም በዘርፍ የተመረጡ ይገኙበታል ተብሎ እንደነበር የፕራና ፕሮሞሽን ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነቢዩ ለማ ገልጸዋል፡፡

የዓውደ ርዕዩ አንዳንድ ጎብኚዎች ግን በዓውደ ርዕዩ የጠበቁትን እንዳላገኙ፣ የቀረቡትም ምርቶች ብዙም እንዳልማረካቸው የገለጹ ነበሩ፡፡ ስለ ጎብኚዎቹ አስተያየት ተጠይቀው ምላሽ የሰጡን አቶ ነብዩ፣ በዘርፍ በተለዩ መስኮች ላይ በማተኮር የተሰናዳ እንደሆነና ለዚሁም ሲባል የታዳሚዎች ቁጥር ውሱን እንዲሆን መደረጉን አቶ ነብዩ ተናግረዋል፡፡

በኢነርጂ፣ በኤሌክትሮኒክስ መሣሪዎች፣ በግንባታ ዕቃዎች፣ በማሽነሪዎች፣ በእርሻ መሣሪዎች፣ በኮስሞቲክስ፣ በማተሚያና ማሸጊያ ዕቃዎች፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍና በሌሎችም አምራችነት የተሠማሩ ኩባንያዎች በዓውደ ርዕዩ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ ኩባንያዎቹ ከ4,500 በላይ ልዩ ልዩ የፋብሪካ ውጤቶችን የሚያመርቱ እንደሆኑም ተጠቅሷል፡፡

በየዓመቱ በቋሚነት በአዲስ አበባ እንደሚዘጋጅ የሚጠበቀው ይህ ዓውደ ርዕይ፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ከኬንያ፣ ከጋና፣ ከሞሮኮ፣ ከኦማን፣ ከደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ከኢራን ባሻገር በኢትዮጵያም ዓመታዊ የቻይና የንግድ ሳምንት የተሰኘውን ዓውደ ርዕይ በማዘጋጀት እንደሚቀጥል አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ዓውደ ርዕይ የቻይና ኩባንያዎች ከሚፈጥሩት የኢንቨስትመንትና የንግድ ግንኙነት ባሻገር፣ የቻይናን ገጽታ በበጎ ጎኑ ለመገንባት ያለመ ነው የተባለ ሲሆን፣ ቻይና ርካሽና በቶሎ የሚበላሹ፣ የማይረቡ ምርቶችን ታመርታለች የሚለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ለመለወጥ የታሰበበት ነው ያሉት ሚሼል ሜይሪክ፣ ከዚህ ይልቅ ግን ቻይና እንደ ምርትና አገልግሎት ፈላጊው የመክፈል አቅም ለዚያ የሚመጥን ነገር እያቀረበች እንደምትገኝ መገንዘብ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

ከ16 ዓመታት በፊት በዱባይ የተመሠረተው ሚድል ኢስት ኢንተርናሽናል ኩባንያ፣ ዓውደ ርዕዮችን ከማዘጋጀት ባሻገር የንግድና የቱሪዝም መስኮችም ላይ የሚንቀሳቀስ ኩባንያ ነው፡፡ በአዲስ አበባ የተሰናዳውን የቻይና የንግድ ሳምንት ኩባንያው ከአገር በቀሉ ፕራና ፕሮሞሽን ጋር በመሆን አሰናድቶታል፡፡

ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የተመሠረተው ፕራና ፕሮሞሽን በአራት ወጣቶች የተቋቋመ ሲሆን፣ በጤና፣ በግብርና እና ምግብ፣ በዶሮ እርባታ እንዲሁም በቁም እንስሳት መስክ ያተኮሩ ዓውደ ርዕዮችን በማዘጋጀት ይታወቃል፡፡ ከዓውደ ርዕይ ዝግጅት ባሻገርም ዝግጅቶችን በገበያና ግብይት እንዲሁም በዝግጅት ማስተዳደር ሥራዎች ውስጥ እየተሳተፈ የሚገኝ ኩባንያ ነው፡፡

                                          

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች