Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የምግብ አምራቾች ቅደመ ምዝገባን የሚደነግግ ረቂቅ መመርያ እየተዘጋጀ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ምግብ ማቀናበሪያዎች መመርያው እንዲስተካከል ባሏቸው ነጥቦች ላይ ሐሳብ አቅርበዋል

የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ሰሞኑን ባዘጋጀው መድረክ የምግብ አምራቾች በምግብ አቀነባባሪነት ለመመዝገብ ከመጠየቃቸው በፊት ሊያሟሉ ይገባቸዋል የተባሉ ዝርዝር ነጥቦችን የሚደነግግ ረቂቅ መመርያ ለውይይት አቅርቧል፡፡

ባለሥልጣኑ ባለፈው ሳምንት በጠራው የውይይት መድረክ ወቅት ይፋ የተደረገው ረቂቅ መመርያ፣ ምግብ አምራቾች ፈቃድ ከማግኘታቸው በፊት ሊያሟላ ይገባቸዋል በማለት የዘረዘራቸውን መጠይቆች ከአዋጅ ቁጥር 661/2002 እንዲሁም ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 299/2006 ጋር በማዛመድ አቅርቧል፡፡ ‹‹የምግብ ማምረቻ ተቋማት የቅድመ ፈቃድ መመርያ›› የተሰኘው አዲሱ ረቂቅ መመርያ፣ ምግብ አምራቾችን በአምስት ምድብ በማስቀመጥ ትርጓሜ ሰጥቷቸዋል፡፡ ለልዩ የምግብ ንጥረ ነገር ፍላጎት የሚዘጋጁ ምግቦች አምራች፣ በከፍተኛ ደረጃ ለብልሽት ተጋላጭ ምግቦች አምራች፣ የዝቅተኛ ደረጃ ለብልሽት ተጋላጭ ምግቦች አምራች፣ አነስተኛ ምግብ አምራች እንዲሁም ከፍተኛ ምግብ አምራች በማለት መድቧቸዋል፡፡

በዚህ መሠረት ልዩ የምግብ ንጥረ ነገር ፍላጎትን ለማሟላት የሚዘጋጁ ምግቦች አምራች የሚባሉት በልዩ የቅንብር ሁኔታ ለተለዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚቀርቡ ሆነው ተጨማሪ ምግብ፣ የጨቅላ ሕፃናት ምግቦች፣ የታዳጊ ሕፃናት፣ የጨቅላና ታዳጊ ሕፃናት ማሟያ ምግብ፣ ምግብ ንጥረ ነገር እጥረት ለተጎዱ ሰዎች የሚቀርቡ እንዲሁም ጤናቸው በተለያዩ በሽታዎች ምክንያት ለተጎዳ ሰዎች ታስበው የሚመረቱና ከዚህ ዓይነት ምግቦች ጋር ተመሳሳይ ምግቦችን የሚያመርቱ በዚህ መስክ ተደልድለዋል፡፡  

በከፍተኛ ደረጃ ለብልሽት ተጋላጭ ምግቦች አምራች የሚባሉት ተቋማት ከምግቦቹ ተፈጥሯዊ ይዘት አንፃር በቀላሉ ለበሽታ አምጪ ተዋስያን ዕድገት ተስማሚ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ የወተት፣ የወተት ተዋፅኦ፣ የሥጋና የሥጋ ውጤቶች፣ ዓሣና የባህር ምግቦች፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ውጤቶችና ሌሎችንም የሚያመርቱ ድርጅቶች የሚጠቃለሉበት ይህ ምድብ ሲሆን፣ በዝቅተኛ ደረጃ ለብልሽት ተጋላጭ ምግቦች አምራቾች የተባሉት ደግሞ የሚያመርቷቸው የምግብ ይዘቶችና ባህርያት ለበሽታ አምጪ ተዋስያን ዕድገት የማይመቹ እንደ አልኮል መጠጦች፣ እንደ ጥራጥሬ፣ የሻይ ቅጠል፣ ቡና እና ቅመማ ቅመም፣ ዘይትና ቅባት፣ ስኳር፣ ማር ስታርች፣ የባልትና ውጤቶች፣ ኮምጣጤ፣ እርሾና ሌሎች ተመሳሳይ የምግብ ዓይነቶች የሚያመርቱ ሁሉ በዝቅተኛ ደረጃ ለብልሽት ተጋላጭ የሆኑ ምግቦች አምራቾች ተብለዋል፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ሁለቱ የምግብ አምራቾች ላይ የቀረቡ የማሻሻያ ጥያቄዎች ቢኖሩም በተለይ በአነስተኛና በከፍተኛ ምግብ አምራችነት የተመደቡት ላይ የተቀመጡት ትርጓሜዎች ላይ አንኳር ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ይኸውም አነስተኛ የምግብ አምራች ተብለው የተደለደሉት ማቀናበሪዎች የሚጠየቁት ካፒታል ከግማሽ ሚሊዮን ብር በታች የሆኑና ከ50 ሰው በታች የሰው ኃይል እንዲኖራቸው የሚጠይቅ በመሆኑ የማሻሻያ ጥያቄ ቀርቦበታል፡፡

ከፍተኛ የምግብ አምራቾች በአንፃሩ ካፒታላቸው ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ እንዲሁም በሥራቸው የሚተዳደረው የሰው ኃይል ከ50 ሰው በላይ የሆኑ ከፍተኛ ምግብ አምራቾች ተብለው በረቂቅ መመርያው መቅረባቸው ተቀባይነት አላገኘም፡፡ አብዛኞቹ ተሳታፊዎች በመመርያው በዚህ አግባብ የቀረበው መጠይቅ፣ በምግብ የማምረት አቅም መጠን ላይ እንዲመረኮዝና የቀረበው የግማሽ ሚሊዮን ብር የካፒታል አቅም በገንዘብ መሆኑ ቀርቶ በሚመረተው የምግብ መጠን ብዛት አምራቾች እንዲፈረጁ ተዋዋዮቹ ጠይቀዋል፡፡ የምግብ ደኅንነትን ለማስፈን ካፒታል ዋናው መጠይቅ መሆን የለበትም ብለዋል፡፡

በመመርያው ክልል ተሻጋሪ አምራቾችን እንደሚመለከት ሲያስቀምጥ፣ ክልል ተሻጋሪ አይደሉም ተብለው የሚለዩት በምን ይዳኛሉ ያሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ ክልል የማይሻገሩ ኩባንያዎች ተብለው የሚጠቀሱት አምራቾቹ ቢሆኑም ምርቶቻቸው ግን ክልል መሻገራቸው የማይቀር በመሆኑ፣ ይህ የመመርያው አተረጓጎም እንዲሻሻል ጥያቄ ቀርቧል፡፡ በመመርያው መካተት ሲገባቸው አልተካተቱም ከተባሉት ውስጥ የሚጠቀሱት ደግሞ የአካባቢ ደኅንነት ባለሙያዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር የምግብ ቸርቻሪዎችና አከፋፋዮች በእሴት ሰንሰለቱ ውስጥ ጉልህ ሚና ቢኖራቸውም፣ በመመርያው ውስጥ አለመካተታቸውም እንዲታይ ተጠይቋል፡፡ ምግብ አምራቾች ያመረቱት ምርት በሥርጭት ወቅት ለሚገጥመው ችግርና ብልሽት አምራቾችን ተጠያቂ የሚያደርግ አካሔድ ያለው መመርያ በመሆኑ ይሻሻል በማለት ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

ምግብ በሚመረትበት አካባቢ ለምግብ ብክለት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ እንደ ሲሚንቶ ማምረቻ ያሉ ፋብሪካዎች በሚከፈቱበት ወቅት፣ ከምግብ ደኅንነት መሥፈርት አኳያ የግንባታ ፈቃድ ሰጭ፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲሁም የመሬት አስተዳደር አካላት እንዲህ ያለውን የአመራረት ሒደት በሚገባ ሊያጤኑ እንደሚገባና ይህ አካሔድም እንዲስተካከል ጥያቄ ቀርቧል፡፡ በቆሻሻ አወጋገድ፣ በተለይም ቆሻሻ መቃጠል እንደሚኖርበት የሚጠይቀው የመመርያው ክፍል እንዲሻሻል ተወያዮቹ ሲጠይቁ፣ ካቀረቧቸው መከራከሪያዎች አንዱ ማቃጠል ብክለትን እንደሚያባብስ የጠቀሱበት አካሔድ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር ለሠራተኞች የደንብ ወይም የማምረቻ አልባሳት ስቴራላይዝ ማድረግንም መመርያው የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ይህ አግባብ አይደለም ያሉት አምራቾች ስቴሪያላዝ የሚደረግባቸው ማሽኖች ምግብ ለማቀነባበር ከሚተከለው ፋብሪካ ያልተናነሰ ወጪ ስለሚጠይቁ፣ ከዚህ ይልቅ በእጥበትና በመሳሰሉት መንገዶች ንፅህናቸውን ማስጠበቅ የሚቻሉባቸው ስልቶች በመመርያው እንዲቀርቡ የጠየቁም አልታጡም፡፡

በቡድን ተከፋፍለው ባደረጉት ውይይት ከተለያዩ የምግብ ማምረቻ ኩባንያዎች ተወክለው የተሰባሰቡ ሰዎች ባደረጉት ውይይት፣ እነዚህን ሌሎችም መሠረታዊ ያሏቸውን ማሻሻያዎች በረቂቅ መመርያው እንዲካተቱላቸው ጠይቀዋል፡፡ ባለሥልጣኑ በበኩሉ ለውይይት ባቀረበው ረቂቅ መመርያ ላይ የተነሱትን ነጥቦች በግብዓትነት በማካተት እንደሚያስተካክል አስታውቋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የምግብ ምዝገባ አፈጻጸም መመርያ የተባለ ረቂቅ ሰነድም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ይሁንና መመዝገብ ሳያስፈልጋቸው ለሽያጭ መዋል ይችላሉ ተብለው የተለዩ የምግብ ዓይነቶችም በመመርያው ተዘርዝረዋል፡፡

በአገር ውስጥና በውጭ የተመረቱ፣ ተጠቃሚው ጋር ከመድረሳቸው በፊት በአምራቹ የታሸጉ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን የሚያመርቱ ተቋማት፣ ምርቶቻቸውን ማስመዝገብና ማሳወቅ እንዳለባቸው መመርያው ይጠይቃል፡፡ ለሰብዓዊ ዕርዳታ፣ ለግለሰብ ጥቅም፣ ለሳይንሳዊ ምርምሮች፣ ለተለያዩ ሆቴሎችና ምግብ አምራች ድርጅቶች እንደ ግብዓትም ሆነ እንደ ጥሬ ዕቃነት ጥቅም ላይ የሚውሉ፣ በ24 ሰዓታት ውስጥ ጥቅም ላይ መዋል የሚኖርባቸው፣ በልዩ ሁኔታ ለተለዩ የኅብረሰተቡ ክፍሎች ጥቅም ላይ የሚውሉትን ምግቦች ምዝገባ ሳያስፈልጋቸው ለገበያ መዋል የሚችሉ መሆናቸውን ባለሥልጣኑ በረቂቅ ሕጉ አስፍሯል፡፡ እነዚህ መመርያዎች ማሻሻያ ከተደረገባቸው በኋላ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚደረጉ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች