[የክቡር ሚኒስትሩ የአክስት ልጅ ስልክ ደወለችላቸው]
- ሄሎ፡፡
- ሄሎ ጋሼ!
- ማን ልበል?
- እንዴ ድምፄን ረሳኸው?
- ሴትዮ ስልኩን ልዘጋው ነው፡፡
- የእታባ ልጅ ነኝ ጋሼ፡፡
- እንዴ ከየት ተገኘሽ ዛሬ?
- ብዙ ጊዜ ልደውል አስባለሁ ግን ሥራ ይበዛብሃል እያልኩ ነው፡፡
- ለነገሩ አሁንም ቢዚ ነኝ፡፡
- አውቃለሁ ጋሼ፡፡
- ምን ፈልገሽ ደወልሽ?
- አንድ ነገር ላማክርህ ብዬ ነው፡፡
- ምንድን ነው የምታማክሪኝ?
- ውጭ እንዴት ልሂድ ልልህ ነው?
- ያው በደላላ ነዋ፡፡
- እኔማ በጣም ስለመመረኝ በእግሬ ልጀምረው ነው፡፡
- ምን ሆነሽ ተማረርሽ?
- ሁሉ ነገር ያማርራል፡፡
- ሥራ እየሠራሽ አይደል እንዴ?
- እሱማ ለነገሩ ጀማምሬ ነበር፡፡
- ታዲያ ምን ጎደለሽ?
- በቃ ምቀኛ መንግሥት ካለ መሥራት አይቻልም፡፡
- እየተሳደብሽ እኮ ነው?
- ምን ላድርግ ወድጄ አይደለም፡፡
- ምን ገጠመሽ?
- ያው ቡና ጠጡ ብዬ ትንሽ ንግድ ቢጤ ጀምሬ ነበር፡፡
- እሺ?
- እና ትንሽ እንቀሳቀስ ነበር፡፡
- ስለዚህ አንቺና ልጅሽን ነፃ አውጥተሻል ማለት ነው?
- እሱማ በሚገባ፡፡
- ታዲያ አሁን ምን ገጠመሽ?
- ግብር የሚሉት ጣጣ፡፡
- በግብር ቀልድ የለም፡፡
- መጀመሪያ ማን ሲያስቀልድህ ጋሼ?
- እንዴት?
- በግብር ያማርሩሃል እንጂ አያስቀልዱህም፡፡
- አልገባኝም?
- ይኸው በቀን ሁለት ሺሕ ብር ትሸጫለሽ ብለው አመጡብኝ፡፡
- ምን?
- ቁጥር አያውቁም ስልህ?
- ከቡና በቀን ሁለት ሺሕ ብር?
- አይገርምህም ጋሼ?
- እኔም አሁኑኑ ነው የምጀምረው፡፡
- ምኑን?
- ኑ ቡና ጠጡ!
[የክቡር ሚኒስትሩ የወንድም ልጅ ደወለላቸው]
- ሄሎ ጋሼ፡፡
- እንዴት ነህ ጎረምሳው?
- አለሁ ጋሼ፡፡
- ምነው ድምፅህ?
- ምን ባክህ ሙዴ ተከንቶ ነው፡፡
- አንተ ልጅ ይኼን ቋንቋ ተው አልተባልክም?
- በቅርቡ የሥራ ቋንቋ ሊሆን ይችላል ብዬ ነው፡፡
- ይኼን ፖለቲካህን እዛው፡፡
- ጋሼ በጣም ተማርሬያለሁ፡፡
- ምነው?
- ሱቄን መቼም ታውቃታለህ?
- ያቺ የክብሪት ቤት የምታክለው?
- ጎሽ ጋሼ፡፡
- ምን ሆነች?
- አሁን እዛ ቤት በቀን ሰባት ሺሕ ብር ይሸጣል?
- ምን አልከኝ?
- በቀን ሰባት ሺሕ ትሸጣለህ አሉኝ እኮ ነው የምልህ?
- ምን ትቀልዳለህ?
- እውነት ጋሼ፡፡
- በእርግጥ ስንት ትሸጣለህ?
- ሦስትም፣ አራትም አንዳንዴ እስከ አሥርም ይደርሳል፡፡
- እ. . .
- መንግሥት ግን ያለ ግብር አያውቅም እንዴ?
- እና አሁን ምን ልታደርግ ነው?
- እኔማ ልመልሰው እያሰብኩ ነው፡፡
- ምኑን?
- የንግድ ፈቃዴን፡፡
- በቃ እኔ መፍትሔ አለኝ፡፡
- ምን ልታደርግ?
- እኔ እወስደዋለሁ፡፡
- ምኑን?
- ንግድ ፈቃዱን!
[የክቡር ሚኒስትሩ የእህት ልጅ ስልክ ደወለችላቸው]
- ሄሎ ጋሼ፡፡
- እሺ አንቺ ሞልቃቃ፡፡
- እንዴት ነህ ጋሼ?
- ዛሬ ግን እንዴት ነው የዘመድ ስልክ በዛብኝ?
- ማን ደውሎልህ ነበር?
- የአጎትሽ ልጅም ደውሎልኝ ነበር፡፡
- እኔ እንኳን አንድ ነገር ልጠይቅህ ፈልጌ ነው፡፡
- ምን ልጠይቂኝ?
- ይኼ ግብርና ምናምን የሚሉት ነገር ምንድነው?
- የምን ግብርና ነው?
- ይኼ ገቢዎች የሚሉት ድርጅት ነዋ፡፡
- ግብር ማለትሽ ነው?
- አዎን ጋሼ፡፡
- ምን ሆንሽ አንቺ ደግሞ?
- ያው ቦሌ ላይ ሞባይል ቤት እንዳለኝ ታውቃለህ?
- ከአንቺ አይደል እንዴ አይፎን የገዛሁት?
- በቃ እየውልህ ጋሼ እኔ ብራንድ አይፎን ብቻ ነው የምይዘው፡፡
- እሺ?
- እና ይኸው ግብርና ምናምን ሊያመጡብኝ ነው፡፡
- ግብር ነው የሚባለው አልኩሽ እኮ፡፡
- ለመሆኑ በቀን ስንት ገመቱብሽ?
- እኔ ጋ አልመጡም ግን ጓደኞቼን 20 ሺሕ ምናምን ብለዋቸዋል፡፡
- ምን?
- እና ጋሼ አስቁማቸው፡፡
- በቃ አስቆማቸዋለሁ!
[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ስልክ ደወሉ]
- አቤት፡፡
- ምን ለመሆን ፈልጋችሁ ነው ግን?
- ማለት?
- ሰላም አትፈልጉም እንዴ?
- ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ዋልሽ መሰለኝ?
- እናንተ ትመስሉኛላችሁ ፀረ ሰላሞቹ?
- ሴትዮ እየተሳደብሽ ነው?
- ሐሳባችሁ ግራ አጋብቶኝ ነው እኮ?
- የምን ሐሳብ?
- ይኸው ሰው ከሳዑዲ ዓረቢያ እንዲመጣ ትማፀናላችሁ?
- ሰው አገር እንዳይሰቃዩ ነው እኮ፡፡
- ታዲያ እኔ እዚሁ ለእነሱ የሥራ ዕድል ፈጠርኩ፡፡
- እሱማ ጥሩ ነገር ነው ያደረግሽው፡፡
- ይኸው መንግሥት ግን እየበጠበጠኝ ነው፡፡
- እንዴት ማለት?
- ፀጉር ቤቴ ሊዘጋ ነው፡፡
- ለምን?
- ሠራተኞቹም ሊበተኑ ነው፡፡
- ማን አባቱ ነው የሚበትናቸው?
- የተጠየኩት ግብር ነዋ፡፡
- አልገባኝም?
- በቀን ሰባት ሺሕ ትሠሪያለሽ ነው ያሉኝ፡፡
- ታዲያ እንደዛ ከተሠራበት ለምን ሁሉም አይከፍቱም?
- እኔ ምን አውቅላቸዋለሁ?
- ተያቸው አሁን የመጡት በእንትኔ ነው፡፡
- በምንህ?
- በህልውናዬ!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ደላላ ደወለላቸው]
- ክቡር ሚኒስትር ሰሞኑን ከትልልቅ ሰዎች ጋር ስገናኝ ነበር፡፡
- በምን ጉዳይ?
- ለአገሪቱ ዕድገት ወሳኝ ነገር ላይ ስወያይ ነበር፡፡
- ምን ዓይነት ነገር ነው?
- ሱፐር ኮምፒዩተር ይባላል፡፡
- ምንድነው እሱ?
- ኮምፒዩተር ነው፡፡
- ታዲያ ኮምፒዩተር አለን አይደል እንዴ?
- ይኼኛው ሱፐር ነዋ፡፡
- እህ. . .
- ያው ዘመኑ የአይቲ አይደል?
- በትክክል እንጂ፡፡
- ስለዚህ ይኼን ኮምፒዩተር አገሪቷ መግዛት አለባት፡፡
- ምን እናደርግበታለን ግን?
- የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዳታ በሙሉ ይቀመጥበታል፡፡
- በጣም አሪፍ፡፡
- ዋናው ነገር እሱ አይደለም፡፡
- ታዲያ ምንድነው?
- ከግዥው ከፍተኛ ኮሚሽን እናገኝበታለን፡፡
- እውነት?
- አዎ ኮሚሽናችን ውጭ እንዲቀመጥ ተስማምቻለሁ፡፡
- በምን?
- በዶላር!
[ክቡር ሚኒትሩ ኮምፒዩተሩን ገዝተው የአይቲ ክፍል ኃላፊውን አስጠሩት]
- አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንድ ኮምፒዩተር አስገዝቻለሁ፡፡
- አለዎት አይደል እንዴ?
- ለእኔ አይደለም፡፡
- ታዲያ ለማን ነው?
- ለአገሪቷ፡፡
- ለአገሪቷ?
- አዎን ለአገሪቷ፡፡
- ምን ሊያደርግላት?
- ስማ ለዚህች አገር መስዋዕትነት መክፈላችንን ታውቃለህ?
- እሱማ ሁላችንም ከፍለናል፡፡
- እኛ እኮ አጥንታችንን ከስክሰን ደማችንን አፍስሰናል፡፡
- አውቃለሁ፡፡
- ስለዚህ እቺ አገር በጠላት እንድትጠቃ አልፈልግም፡፡
- ማን ሊያጠቃት ነው?
- የዚህ ዘመን ጦርነት እኮ በኮምፒዩተር ሆኗል፡፡
- እና ምን እያሉኝ ነው?
- ይኸው ተመልከተው፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ሱፐር ኮምፒዩተሩ የተጫነበትን ኮንቴይነር ፎቶ በስልካቸው አሳዩት]
- እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- የምን ቀልድ ነው?
- እና ኮምፒዩተሩ ተገዝቷል?
- እህሳ፡፡
- እኔንና ሌሎች የአይቲ ባለሙያዎችን ሳያማክሩ?
- አንተን ማን አለቃ አደረገህ?
- ምን?
- ይኼ እኮ የዕድገታችን መገለጫ ነው፡፡
- ይህ ዕድገት ሳይሆን. . .
- እ. . .
- ብክነት ነው!
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
- አቤት ክቡር ሚኒስትር?
- ወዳጃችን ያደረገውን ሰማህ?
- ማን ነው ወዳጃችን?
- ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ነዋ፡፡
- ምን አደረገ?
- የኅብረቱን ስብሰባ እየተከታተልክ አይደለም እንዴ?
- ኧረ ነው፡፡
- ይኸው አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ከብቶችን ለገሰ እኮ፡፡
- ለግድቡ ነው?
- አንተ ደግሞ ሰፋ አድርገህ አስብ እንጂ?
- እ. . .
- ለኅብረቱ ነው፡፡
- እሱንማ ሰምቻለሁ፡፡
- ከብቶቹ በሰላም እንዴት እንደሚመጡ ሳስብበት ነበር፡፡
- ምን አሉኝ?
- ሎጂስቲክስ ላይ የሚሠራ ዘመድ አለኝ፡፡
- እሺ?
- እሱ እዚህ ድረስ ያመጣቸዋል፡፡
- እሺ?
- እዚህ ሲደርሱ የሚጠበቃቸው እረኛ አዘጋጅቻለሁ፡፡
- ማንን?
- አንድ ጥሩ እረኛ ዘመድ አለኝ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎም ግን ያስፈልግዎታል፡፡
- ምን?
- እረኛ!