Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በነሲብ መገመት በአድልኦ መፍረድ አይበቃም ወይ?

እነሆ መንገድ። ከቦሌ ወደ ገርጂ ልንጓዝ ነው። መንገዱና ልቡ አልስማማ ያለው መንገደኛ፣ ወዝ ለወዝ እየተሻሸ ሐሳብ ለሐሳብ እየተሸካከረ ወደ ሠልፉ ይነጉዳል። ‹‹የዚህ ሠልፍ መጨረሻ መቼ ይሆን?›› ትላለች ቀሚሷ አፈር ለአፈር እየተጎተተ ያስቸገራት ጠይም። ‹‹አይዞሽ! ቅርብ ግዜ ነው። ሰዓቱ ተቃርቧል። መምጫው ነው፤›› ይላታል ከኋላዋ ቁልቁል እያየ የሚከተላት ረዥም ጎልማሳ። ‹‹ገና ሳንደርስ? ምን ይሆን የሚመጣብን?” አለችው። ‹‹የዓለም መጨረሻ ነዋ! እኔ እኮ የዘመኑ ሰው ምን እንደነካው አላውቅም። አስታውሶ መርሳት ነው . . . ። አስቦ መርሳት ነው . . . ። ቀኑ እኮ አልቋል፣ . . . ›› ሲላት፣ ‹‹ቀኑማ ስላለቀ መሰለኝ ወደ ቤቱ የሚጓዘው ሠልፈኛ የበዛው። መምሸቱን ታዝበን መሰለኝ የተንጋጋነው፤›› አለችው።

‹‹እሱን ነው የምልሽ። እያዩ አለማየት፣ እየሰሙ አለመስማት የሚባል ነገር አለ። ይኼ እኮ ነው ያስቸገረን። ሁሉን ነገር የምር አርገን መቁጠር ነው እኮ ያበጣበጠን። ቀኑ ሲባል . . . የዋልነው ይመስለናል። ምሽቱ ሲባል . . . የሚጨልመው ሰማይ ይመስለናል። መሬቱ ሲባል . . . ይኼ የቆምንበት እንደ ገዛ ንብረታችን ካልቆጠርነው ብለን የምንንገታገትበት ይመስለናል። ወርቁ፣ ብሩ፣ ሀብቱ ዘለዓለማዊ ይመስለናል። በአጠቃላይ ቆመን መሄዳችን ከራሳችን ብቃት ይመስለናል። የሰው ልጅ ችግሩ እኮ ነገሮችን በቋሚነት ማሰቡ ነው። ስለዚህ ፀባችን ብዙ ነው። ዴሞክራሲ ያጣላናል፣ ሙቀት ያጣላናል፣ ብርድ ያጣላናል፣ ጥጋብ ያጣላናል፣ ጠኔ ያጣላናል። ፖለቲካውማ . . . ምኑ ይወራል?›› ብሎ ጎንበስ ሲል፣ ‹‹የእኔ ወንድም በዚህ ሠልፍ ላይ ፍልስፍና ሲጨመርበት ትንሽ ነውር አይመስልህም? እንኳን ከአቅም በላይ ሐሳብ ተጨምሮበት አንድ ሆዴን ለመሙላትም ናላዬ ዞሯል። ወረድ በልልኝ ፕሊስ፤›› ብላ ተከኮሳተረችበት። መለሎው ፈላስፋ ከአቀረቀረበት ቀና ብሎ ሰማይ ሰማይ ሲያይ ሠልፉ እየተሳበ ታክሲያችን ዘንድ ደረሰ። ተራው እስኪደርሰው የተረኛ ዕጣ ፈንታ ማንጋጠጥ ብቻ ነው የተባለ አይመስልም እስኪ አሁን?!

ጉዞ ጀምረናል። የታክሲ ፈላጊው ነዋሪ ሠልፍ ለዓይን ይታክታል። ትርክቱ አንዳንዴ ከቃላትና አቅም በላይ ነው። ትራንስፖርት ተቸግሮ በተሠለፈው ምስኪን ወገን ትይዩ የኑሮ ዳና ተሳክሮበት ልመናን መተዳደሪያው ያደረገው ደግሞ ሌላ ሠልፍ ሠርቷል። ከቁጣና ከግልምጫ ጋር ‘ታመጣለህ አታመጣም?’ በማለት ሰውን መድረሻ አሳጥተውታል። “ወይ ጉድ! መድረሻ አጣን እኮ እናንተ!” ይላሉ አንዲት ወይዘሮ በእጃቸው ያንጠለጠሉት ፌስታል ውስጥ ለማምሻ ሆድ የማይበቃ የቲማቲምና የሽንኩርት ሥፍር ይታያል። “በቃ እኮ የእኛ ኑሮ . . . ከእጅ ወደ አፍ ታውቃለህ . . . ” እያለ ከወይዘሮዋ ራቅ ብሎ ወደ መጨረሻ ወንበር የተሰየመ ጎልማሳ ፌስታላቸውን ለጓደኛው ይጠቁመዋል። ወይዘሮዋ ደግሞ፣ ‹‹ከሁሉ ብሶ ለምኖ የሚያድረው ብዛት? እነሱ ተሻሉ ከእኛ ልበል?” ብለው መነጫነጭ ጀመሩ። “እንግዲህ ምን ይደረጋል? ዓይነቱ ነው እንጂ እዚህ አገር ሁሉም ለማኝ ነው። የሳንቲም ምፅዋት አለመጠየቃችን እንጂ ሁላችን በደረጃችን የማንለምነው የለም፤›› አላቸው አመዛዛኝ ነኝ ባዩ ጎልማሳ። ከጎልማሳው አጠገብ የተሰየመ ወጣት ሳያስበው ንዴት አንዘረዘረው።

“ታዲያ እኛ እኮ የምንለምነው የራሳችን የሆነውን ነገር መልሱልን ብለን ነው። ፍትሕ፣ ነፃነትና ዴሞክራሲን ነው የምንማጠነው፤” ብሎ ሲነጫነጭ፣ “ሁሉን በአንድ ሙቀጫ የሚወቅጠው አይደል አገር እያጠፋ ያስቸገረን ንገረውማ ደህና አድርገህ፤” ይላል ሌላው። በዚህ መሀል ታክሲዋ ልትጭን ቆመች። ተረኞች ያለ ግርግር ገብተው በትርፍ ተቀመጡ። ቀረት ቀረት ያሉ ሠልፋቸውን ጠብቀው ወደኋላ ቀሩ። ይኼኔ ‹‹አይገርምም! በሠልፍ ተወልደን፣ በሠልፍ አድገን፣ ሳያልፍልን ማለፋችን? በዚህ ሳምንት ብቻ አራት አብሮ አደጎቼን ስቀብር!” እያለ ተንገበገበ። “ግፊያና አቋራጭ ናፋቂ ሆነን እንጂ፣ እንደ እኛ ያለ የሥነ ሥርዓት ተገዢ እንኳ አልነበረም፤›› የምትለው ደግሞ ወደ ጥግ በኩል ተወሽቃ የተሰየመች ደመግቡ ናት።  ንግግሯ በግልባጭ ማድረስ የፈለገው ማመልከቻ የቆጠረ ይመስላል። ዘመኑ የብሶት ማመልከቻ ሆኗላ!

ጋቢና ሁለት አብሮ አደግ ወጣቶች መንገድ አገናኝቷቸው ሰላምታ ይለዋወጣሉ። “ኮንግራ ብያለሁ። ባለፈው እኮ በፌስቡክ ሳይህ ነው ዘንድሮ እንደምትመረቅ ትዝ ያለኝ። እንዴት ነበር?” ይጠይቃል አንደኛው። “ምኑ? አጠያየቁ ግራ የገባው። “ምርቃቱ ነዋ? እንዴት አለፈ? አንተ ግን ትገርማለህ ሳትጠራኝ?›› ብሎ ወቀሳ ይጀምራል። “ሠርግ አደረግከው እንዴ? ዲግሪ እኮ ነው። ያውም የማያስበላ ዲግሪ . . . ›› እያለ አፀፋውን ሲመልስ እያጣጣለ፣ “ተው! ተው! እንደዚህማ አይባልም። ምንስ ቢሆን ይህቺ አገር እኛን ለማስተማር ያወጣችው ወጪ ቀላል አይደለም። ቢያንስ ምሥጋና ያስፈልጋታል፤” ሲለው ወዳጁ፣ “ኧረ ተው እንደማንተዋወቅ አትሁን። አንተና እኔ አብረን አልነበር እንዴ ዩኒቨርሲቲ የገባነው? አንተ ይኼው አሻፈረኝ ብለህ ጥለህ ወጥተህ ዛሬ በመካከላችን የአንድ ሚሊዮን ብር ካፒታል ርቀት ሰፍኖ ተገናኘን። ያልሰማሁ እንዳይመስልህ። ግን ጀግና ነህ ደስ ብሎኛል፤ ብሎ ትምህርቱን አቋርጦ ቀድሞ በሥራ ዓለም የተሰማራ ወዳጁን ማበረታታት ቀጠለ ተመራቂው።

 “ግን እኔ የምልህ? ምንድነው የምትሠራው?” ሲለው በጨዋታ መሀል፣ “አሁን ፋርዳ ወጣህ። በል ሰው እንዳይሰማህ ድምፅህን አጥፋ። ደግሞ የምንድነው የምትሠራው ብሎ ነገር አለ እንዴ? አንተ ስታስበው በሦስት ዓመት ውስጥ ምንም ዓይነት የአካዳሚ ሥልጠና ሳይኖረኝ ሚሊየን ልታቀፍ የምችልበት መንገድ ምን ሊሆን ይችላል?” ብሎ አተኩሮ አየው። “እንጃ አንተው ንገረኛ፤” ከማለቱ ተስፋ ቢሱ ባለዲግሪ፣ ያልተማረው ልማታዊ ቀበል አድርጎ፣ “የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ነዋ፤” ብሎት ከት ብሎ ሳቀ። ተሰርቄ እንጂ ሳቅማ ነበረኝ አለ አሉ ባለዲግሪው! ወያላው ሒሳብ መቀለብ ጀመረ። ከጋቢና አንስቶ መጨረሻ ወንበር ወደተቀመጡት ወጣቶች እስኪደር ፀጥታ ታክሲያቺን ውስጥ ሠፍፎ ነበር።

የወያላውም ሰዓት ያጥበረብር ነበር። “ፓ! ‘ራዶ’ ሰዓት አስረህ ነው ወያላነት የምትሠራው? የኢኮኖሚ ዕድገት ይሏችኋል ይኼ ነው፤” አለ መስኮቱን ታኮ ተጣቦ የተቀመጠ ቆብ የደፋ ወጣት። “ምን ታደርገዋለህ? አንዱ ሲንቀዠቀዥ አውልቆ ጥሎት ሄደና አነሳሁት። ግን አልሠራ ብሎ ያለፋኛል፤” ወያላው በንፅህና የልቡን ያወራል። “አይዞህ የአንተ ሰዓት ብቻ አይደለም የቆመው። የብዙዎች ዕድሜና ሰዓት አይሠራም፤” አዛውንቱ ናቸው መሀል ገብተው የሚቀኙት። “ሰው ሞባይል፣ ቁልፍ፣ ቦርሳ፣ . . .  ይጥላል እንጂ እንዴት የእጁን ሰዓት ታክሲ ውስጥ ጥሎ ይወርዳል? የማይመስል ነገር . . . አሉ ከአዛውንቱ፡፡ በስተግራ የተሰየመች ጥርሰ ፍንጭት አስተያየት ሰጠች። “ሰው ቀን ሲጥለው እንኳን የእጁን ሰዓት ራሱን ይጥል የለም ወይ? እንዴት ያለ ነገር ነው እንግባባ እንጂ?” አዛውንቱ ሊያቃኗት ይደክማሉ።

ከእሷ በስተግራ ያለው ደግሞ ከአጀንዳ ውጪ “ታክሲ ውስጥ የወደቀ ዕቃ ባለቤት እንደሌለው ተቆጥሮ ይወረሳል የሚል ማስታወሻ ተጽፎ ሊለጠፍልን ይገባል። አለበለዚያ እኮ ስናምናቸው የጣሉንን እያሰብን ጨርቃችንን ጥለን የምናብደው ታክሲ ውስጥ መሆኑ የማይቀር ነው፤›› ይላል፡፡ ወዲያ ደግሞ ባለቆቡ፣ “ሥልጣን ብይዝ መጀመሪያ የማቋቁመው የሰዓት ሚኒስቴር ነው፤” እያለ ይቀስቅሳል። “ምን ልታደርግ?” ባለፍንጭቷ በመገረም እያየችው። “የሚሠሩ ሰዓቶችን በሙሉ ሰብስቤ ለማስቆም ነዋ!” ብሎ ሲል ተሳፋሪዎች ተንጫጩ።  “ልማቱስ? የተጀመረው ሳያልቅ? ያሰብነው ሳይሳካ?” ብላ ወይዘሮ ስትቆጣ፣ “የቆመ ሰዓት በቀን ቢያንስ ሁለቴ እውነት ይናገራል። ዕድሜ ልክ የተዛባ አቆጣጠር፣ ሙስና፣ አድርባይነትና ማስመሰል እየተጫወቱብን ከመኖር በደቂቃ ዕድሜ ሀቅን ተሳልሞ ማለፍ አይሻለም?” ሲላት ቆቡን እያስተካከለ፣ “እንኳንም ሥልጣን አልኖረህ’ አልነው በልባችን። ሠርተንና ቆጥረን አልደርስበት ብንል ደግሞ ብለን ብለን ግዜን የሚያቆምልን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ስንመኝ አንገርምም? ወይ ሐበሻ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርቧል። ተብሎ ተብሎ ወሬው ሁሉ ወደማለቂያው አነጣጥሯል። ያ አሰላሳይ ረጂሙ ወጣት፣ “ጆሮ ያለው ይስማ ከማለት ሌላ ምን ይባላል?” ብሎ ሲያጉረመርም ከጎኑ የተሰየመው ጎልማሳ፣ “ወንድሜ ለመናገር የፈለግከው ካለ ለምን አትናገረውም? ይውጣልህ ተንፍሰው፤” አለው አባብሎ። “ግድ የለም አመሰግናለሁ። ‹እውነቱን ተናግሮ ከመሸበት ማደር› ብሎ ነገር ዘንድሮ አላስተማመነም፤” አለውና ዝም ሲል፣ “እውነት ምንድነው? ለመሆኑ እውነት ባለቤት አላት? ካላትስ ይኼ ሁሉ ነፃ አውጭ ነኝ ባይ፣ ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ እያለ የሚያደነቁረን፣ የፍትሕ ጠበቃ፣ የመብት ጠበቃ እንደ አሸን የሚፈላው በምን ምክንያት ነው? እውነት አንድ ከሆነ አፋችን ዕልፍ አዕላፍ የሆነው ለምንድነው? ማን ነው የሚታመነው? ማንስ ነው ጉድፍ የሌለው?” ብሎ የምሩን ተኮሳትሮ አየው። ወያላው ደንግጦ፣ “እንዴ ብላችሁ ብላችሁ ታክሲዬ ውስጥ የፓናል ውይይት ልትጀምሩብኝ ነው? የመጻፍና የመናገር ነፃነት ታክሲ ውስጥ ብቻ ነው የሚሠራው ያላችሁ ሰው አለ እንዴ?” ብሎ ተነጫነጨ።

እንዳልሰማ ሆኖ ቀውላላው ቀጠለ። “እሱን እኮ ነው የምልህ ወንድሜ። ዓለም ከዚህ በኋላ ደግ ነገር ታሰማናለች ብዬ አላስብም። ዝም ብዬ ሳስበው ከዚህ ወዲያ ከማንጋጠጥ በቀር በእጃችን ያለ መፍትሔ አይታየኝም። ይኼው አቶ ትራምፕ ከአየር ንብረት ውይይት ረግጠው ወጥተዋል። ዓለም መሪ ያጣች መርከብ ሆናለች። ነገሮች የሰከኑ ቢመስሉም ተሸፋፍነው እንጂ በርደው እንዳልሆነ ልባችን ያውቀዋል። ዓለምን ትተህ እኛ እዚህ ከሩብ ምዕተ ዓመታት በፊትና በኋላ የጻፍናቸውንና ያረቀቅናቸውን ሕጎች መተርጎምና ማስከበር አቅቶን ጭራሽ በሰዋሰው መጣላት ያምረናል። ቤት ያጣ ቤተኛ ሆነናል። ግብራችን ሴማ ባለው ሥርዓት መዳኘቱ ቀርቶ በግብር ይውጣና በአግቦ ግምት ይበየናል። ይፈረዳል፡፡ ይጫንብናል . . . ” እያለው ብዙ ሊያወራ ሲያስብ ወያላ መጨረሻ ብሎ በሩን በረገደው። ታክሲያችን ጥጓን ያዘች። ግብሩና አገባበሩ ምፅዓት ናፋቂ ያደረገው መንገደኛ የሞት ሞቱን ከተቀመጠበት እየተነሳ ዱብ ዱብ ብሎ ወረደ። በነሲብ መገመት በአድልኦ መፍረድ አይበቃም ወይ ያሰኛል፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት