Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየ40/60 የቤቶች መርሐ ግብርን በተመለከተ ይድረስ ለመንግሥት የበላይ አመራሮች በሙሉ

የ40/60 የቤቶች መርሐ ግብርን በተመለከተ ይድረስ ለመንግሥት የበላይ አመራሮች በሙሉ

ቀን:

በደነቀ ፀጋዬ አባይሬ

መንግሥት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ጉልህ የሆነ ተጨባጭ ሥራ እያከናወነ እንደቆየ ነባራዊ የሆነውን እውነታ በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ብንወስድ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አያሌ ዜጎቻችን የራሳቸው መኖሪያ ቤት ባለቤት የሆኑበትን እውነታ በአግባቡ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ ለበርካታ ወጣት ዜጎቻችንም መጠነ ሰፊ የሆነ የሥራ ዕድል እየፈጠረ መቆየቱ ገሃድ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ 40/60 የተባለውን የቤቶች ፕሮግራም በግንቦት 2005 ዓ.ም. «የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የ40/60 የቁጠባ መኖሪያ ቤቶች ልማት ፕሮግራም በአዲስ አበባ ከተማ የቤት ፈላጊዎች የምዝገባ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 21/2005 ዓ.ም.» ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግም ላይ ይገኛል፡፡ ይኼንንም የ40/60 ፕሮግራምን በዋነኛነት በተለያየ ደረጃ ላይ ሆነው እንዲያስፈጽሙ የሚከተሉት የባለድርሻ አካላት የባለቤትነት ድርሻ የተሰጣቸው መሆኑ በመመርያው ላይ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

  1. በአንቀጽ 17 የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር (አሁን የከተማ ልማትና ቤቶች)
  2. በአንቀጽ 18 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
  3. በአንቀጽ 19 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
  4. በአንቀጽ 20 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፐራይዝ

በአንቀጽ 21 ተጠቃሚ ደንበኛ የተባሉት ናቸው፡፡

- Advertisement -

እነዚህም ወገኖች በመመሪያው ላይ በግልጽ የተቀመጠ የየራሳቸው የሆነ ድርሻ ወይም ተግባርና ኃላፊነት አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግን ለየት ባለ መንገድ የመኖሪያ ቤቱን ውል በማስፈረምም ሆነ የመኖሪያ ቤቱን በኃላፊነት በማስረከቡ ላይ ዋነኛ ባለቤት እንደሆነ በመመርያው በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በዚህም መሠረት የ46/60 የቤቶች መርሐ ግብር ተጠቃሚ የሆኑት ዜጎች በሙሉ ከነሐሴ 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ከንግድ ባንክ ጋር ሕጋዊ የሆነ ውል አድርገዋል ማለት ነው፡፡ ይኼንንም እውነታ በአግባቡ ለመመልከት ካስፈለገ የአዋጁን አንቀጾች ማለትም በምዕራፍ አራት ሥር አንቀጽ 11 ላይ «የምዝገባ ሒደት» የሚለውን፣ አንቀጽ 13 ላይ «የቁጠባ ሒሳብ ስለሚዘጋበት ወይም ውል ስለሚፈርስበት ሁኔታ›› የሚለውን፣ አንቀጽ 16 ላይ «የቅድሚያ አወሳሰንና የቤት ማስተላለፍ ሥርዓት» የሚለውንና በክፍል አምሥት ሥር ደግሞ አንቀጽ 19 ላይ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተግባርና ኃላፊነት የሚሉትን ጉዳዮች ብቻ በአግባቡ መመልከት ይበቃል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በክፍል አምስት ሥር የሌሎቹን ባለድርሻ አካላት ተግባርና ኃላፊነቶችን በአግባቡ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ በመጀመርያ በመመርያው ላይ ምንም ዓይነት ቅሬታ ነገር የለብኝም፡፡ ይልቁንም መመርያው ዜጎችን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ፍትሐዊ የሆነ ሰነድ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ የመመርያውን አፈጻጸም በተመለከተ ግን መንግሥት ያወጣው መመርያ በአግባቡ ተግባራዊ እየሆነ አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ ይህም ችግር በአንድ ምሽት የተፈጠረ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከጠዋት ከማለዳው ጀምሮ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ፕሮግራሙ በእጅጉ የተጓተተ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግንባታው በተሳሳተ ዲዛይን እየተገነባ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይኼ ስህተት የተጀመረው በማን እንደሆነ በግልጽ ማወቅ ባይቻልም፣ በራሱ በባንኩ ተዘጋጅቶ በነበረው ብሮሸር ላይም በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የ40/60 ሕንፃ ፍሎር (ወለል) ዲዛይን ከመመርያው ጋር በእጅጉ የተገናዘበ አልነበረም፡፡

በተሳሳተው ዲዛይን ላይ በአንድ ፍሎር ላይ 6 አባወራዎች ብቻ እንደሚኖሩ ተደርጎ በመላ የተሳለ ነገርም ይመስል ነበር፡፡ በሒደትም ግንባታው ይኼንኑ መሠረት አድርጎ ሲካሄድ ነበር፡፡ በዚህም ስህተት ምክንያት በሰንጋ ተራና በክራውን ሆቴል አካባቢ ሕንፃዎቹ በወቅቱ ተገንብተው ማለቅ ቢችሉም፣ በተፈጠረው ስህተት ምክንያት ለባለዕድለኞች ሊተላለፍ የሚገባበት ጊዜ በእጅጉ ተጓቷል፡፡ ችግሩ ይኼ ብቻ አይደለም፡፡ ስለቤት ማስረከቡ ጉዳይ ዋናው የሚመለከተው አካል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስከ መጨረሻው ድረስ ምንም ዓይነት መግለጫ ሳይሰጥ የቆየ ከመሆኑም በላይ፣ ሌሎች ጉዳዩ የማይመለከታቸው ወገኖች በየራሳቸው ጊዜ እየተነሱ ‹የ40/60 መኖሪያ ቤት ለባለዕድለኞች በሚቀጥለው ወር ሊሰጥ ነው…› እያሉ የተጠቃሚዎችን ልብ  የሚያማልል መግለጫ ሲሰጡ ከርመዋል፡፡ ኮንትራክተሩ፣ የአዲስ አበባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ፣ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር . . . ወዘተ የየራሳቸውን መግለጫ ሲሰጡም ቆይተዋል፡፡

በመመርያው ላይ ግን ይኼ ዓይነቱ ሥልጣን ለእነዚህ አካላት አልተሰጠም፡፡ ይልቁንም ግንባታውን እንዲያፋጥኑ፣ ጥራቱን እንዲቆጣጠሩ፣ ግንባታው በታለመለት ዕቅድ መሠረት እንዲሳካ ጥረት እንዲያደርጉና ሌሎች ተጓዳኝ ኃላፊነቶችን እንዲወጡ ግልጽ ባለ መመርያ የየራሳቸው ሆነ ተግባርና ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ነገር ግን በሁለቱ ሳይቶች (በክራውንና በሰንጋ ተራ) የተገነቡት የ40/60 የጋራ መኖሪያ ሕንፃዎች መመርያው ከሚፈቅደው ውጪ እጅግ በጣም በተሳሳተ ዲዛይን ላይ ተመሥርተው 100 ካሬ ሜትር የሆነው ባለ 3 መኝታ ክፍል 150 ካሬ ሜትር፣ 75 ካሬ ሜትር የሆነው ባለ ሁለት መኝታ 124 ካሬ ሜትር፣ 55 ካሬ ሜትር የሆነው ባለ አንድ መኝታ 107 ካሬ ሜትር ሆነው እየተገነቡ ነበር፡፡ እነዚህ ባለድርሻ አካላት ስለዲዛይኑ መሳሳት አንድም ዓይነት መግለጫ ያልሰጡ ከመሆናቸውም በላይ፣ የእነሱ ተግባርና ኃላፊነት ባልሆነው የቤት ማስረከቡን ጉዳይ ራሳቸውን ቤት አስረካቢ በማድረግ አሰልቺ የሆነ መግለጫ ይሰጡ ነበር ማለት ነው፡፡ ይኼን ስል ግን መግለጫ መስጠት ኃጢያት ነው ለማለት ፈልጌ አይደለም፡፡ ይልቁንም በመመርያው መሠረት ኃላፊነታቸውን መወጣት ነበረባቸው ለማለት ነው፡፡ የባለ ዕድለኞቹን መኖሪያ ቤት በተመለከተ በዋነኛነት በመመርያው መሠረት በኃላፈነት መግለጫ መስጠት የነበረበት ንግድ ባንክ እንጂ ሌላ አካል ሊሆን አይገባውም ነበር፡፡

የመመርያውን አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ 9 በአግባቡ ብንመለከት ይኼንን እውነታ በግልጽ ያረጋግጥልናል፡፡ ንዑስ አንቀጽ 9፣ «ግንባታቸው የተጠናቀቁ ሕንፃዎችን እንደተረከበ የአምስት ዓመት የቁጠባ ውል ዘመኑን ሳይጠብቅ፣ የሚፈለግባቸውን የ40 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ ቁጠባ ያጠናቀቁ ተጠቃሚዎችን እንደ ተቀማጭ መጠናቸው መቶ በመቶ ቀጥሎ ወደታች በሚኖረው ቅደም ተከተል መሠረት የብድር ውል ይፈራረማል፣ የመኖሪያ ቤቱንም ያስረክባል፤» ተብሎ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ይኼ አሁንም በአግባቡ ሊታይ ይገባዋል፡፡

ሌላው በአግባቡ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ቢኖር ከባንኩ ጋር የተደረገው የውል ስምምነት ነው፡፡ የውል ስምምነቱ ሁሉንም ወገን በአግባቡ ሊገዛ ይገባል፡፡ የሁሉም ወገን ውል እኩል የሆነ መብት እንዳለው በግልጽ ሊታወቅ ይገባል፡፡ አንዱ ከአንዱ ሌላው ከሌላው ሊበልጥ ወይም ሊያንስ አይችልም፡፡ የአገሪቱ ሕግም ሁሉም ዜጋ እኩል ነው በማለትለ በግልጽ ያረጋግጣል፡፡ አንዱን ከፍ ሌላውን ደግሞ ዝቅ አያደርግም፡፡

ይሁን እንጂ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሰኔ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ስለ 40/60 ጉዳይ የተሰጠው መግለጫ ግን ፍትሐዊ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ይኼንን እውነታ ሁሉም ወገን በአግባቡ ሊመለከተው ይገባል፡፡ በመጀመርያ ከላይ በአጭሩ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የመኖሪያ ቤቱን ማስረከብ በተመለከተ መግለጫውን መስጠት የነበረበት አካል ባንኩና ባንኩ ብቻ መሆን ነበረበት፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተግባርና ኃላፊነት አይደለም፡፡ በመመርያው መሠረት የ40/60 ፕሮግራም የተጠቃሚዎች የውል ስምምነት የተፈጸመው ከባንኩ ጋር ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተግባርና ኃላፊነት በመመርያውን አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጾች በተለይም ደግሞ በንዑስ አንቀጽ 7 መሠረት «ተገንብተው የተጠናቀቁ ቤቶችን በገባው ውል መሠረት ለባንኩ ያስረክባል፤» የሚል ነው፡፡ በሰኔ 29 መግለጫ ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ምክትል ከንቲባ  ይኼንን መመርያ በግልጽ ሲሽሩት ተስተውሏል፡፡ በዚህ መግለጫ ላይ በግልጽ እንዳስቀመጡት ባለ አንድ መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎች በዚህ ዕድል ውስጥ አይካተቱም በማለት ፍትሐዊ ያልሆነ ውሳኔ ሰጥተዋል፡፡

ለመሆኑ ባለ አንድ መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎች በዚህ ዕድል ውስጥ መካተት አይችሉም የተባለበት ምክንያት ምን ይሆን? የመኖሪያ ቤቶቹ ዲዛይን በመመርያው ላይ ከተመለከተው መጠን ስፋት በላይ መስፋት (Over Size) መሆን ይሆን ምክንያቱ? ይኼ ከሆነ ደግሞ የምክትል ከንቲባው ያቀረቡት ምክንያት ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም የቤቶቹ መጠን መስፋት በአግባቡ ከተነሳ  ባለ ሁለትም ሆነ ባለ ሦስቱ መኝታ ክፍሎች በሙሉ ሰፊ ሆነው ስለተገነቡ ማለት ነው፡፡ ይኼ ግን የባለ አንድ መኝታ ክፍል ዕድለኞችን ብቻ ለይቶ ሊያስገልል አይችልም፡፡ መሰረዝ አለበት ከተባለ ደግሞ ሁሉም የዕጣ ዕድለኛ ወገኖች በሙሉ ሊሰረዙ ይገባል እንጂ፣ የባለ አንድ መኝታ ተመዝጋቢዎች ብቻ ተለይተው ፍትሐዊ ያልሆነ ውሳኔ ሊወሰንባቸው አይገባም፡፡

ይኼ ጉዳይ በአግባቡ ከታየ ለየት ያለ ትርጉምና ስሜት ሊፈጥር ይችላል፡፡ ለምን ቢባል መመርያው ለሁሉም ወገን እኩል ተደርጎ ተቀርጿል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን የተሰማው ግለ ሕግ የተላበሰው መግለጫ ሁሉም ዜጎች እኩል መሆን የለባቸውም የሚል ዓይነት አንድምታ ይሰጣል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አነስተኛ አቅም ያለው ወገን ከእነዚህ ሕንፃዎች (አካባቢዎች) ይራቅልን የሚል ዓይነት ስሜት ፈጥሯል፡፡ በአጠቃላይ አገላለጽ መንግሥት ለዜጎች በነፃነት የሰጠው ዕድል በዚህ ዓይነቱ የመልካም አስተዳደር ጉድለት (ኃላፊነት የጎደለው አሠራር) ምክንያት በጠራራ ፀሐይ ተቀምቷል ማለት ይቻላል፡፡

መንግሥት ለዜጎቹ የሚያደርገውን ድጋፍ ወደ ምሬት በመቀየር፣ ዜጎችን በመንግሥት ላይ ያልተገባ ቅሬታ እንዲፈጥሩ ማድረግ በእጅጉ ተገቢ አይደለም፡፡ ፈጽሞም ሊሆን አይገባውም፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በዚህ ዓይነቱ ፍትሐዊ ባልሆነ አሠራር ምክንያት ጠንካራ አቋም ሊኖረው ይገባ ነበር፡፡ ሽርፍራፊ ሳንቲሞችን ሳይቀር ተቆጣጥሮ የመላውን ደንበኞቹን ሀብት ግልጽ በሆነ ታማኝነት በመያዝ ለታላቅ ውጤትና ስኬት የሚያበቃው የኢትዮጵያ ንግድ ባንካችን፣ ሕግና ሕግን ብቻ አክብሮና አስከብሮ ሙያዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባ ነበር፡፡ በባንኩ የተቃናና ፍትሐዊ የሆነ አገልግሎትና ኃላፊነት ላይ አንዱ ልጅ ሌላው ደግሞ የእንጀራ ልጅ ሊሆን አይገባውም ነበር፡፡ አሁንም ይኼው ሀቅ በሁሉም ወገን ዘንድ በአግባቡ ሊታይ ይገባዋል፡፡

በአጠቃላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት አካላትም የመልካም አስተዳደር ጉድለት የታየበትን ይኼንነ ክስተት ቆም ብለው ሊመለከቱ ይገባቸዋል፡፡ ቆም ብለው መመልከትም ብቻ ሳይሆን በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው የተሟላ እርምት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ የፖሊሲ አፈጻጸም ላይ ችግር በፈጠሩ አካላት ላይም ተገቢ የሆነ ዕርምጃ ተወስዶ፣ ለኅብረተሰቡ ግልጽ ሊያደርጉ ይገባል እላለሁ፡፡ ቸር እንሰንብት፡:

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡    

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...