Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበኦሮሚያ አማርኛን ከስንተኛ ክፍል?

በኦሮሚያ አማርኛን ከስንተኛ ክፍል?

ቀን:

በሮቤ ባልቻ

ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አገር ናት፡፡ ሕዝቦቿም እንደ ብዛትና ስፋታቸው የየራሳቸው ቋንቋዎችና ሌሎች ባህላዊ እሴቶች አሏቸው፡፡ እያንዳንዱ የሕዝብ ክፍል የየራሱ ቋንቋና ባህል ቢኖረውም፣ እንደ አገር አንድ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ መኖሩ ደግሞ አስፈላጊ ነው፡፡

ፌዴራላዊው የአወቃቀር ሥርዓት በኢትዮጵያ ከተዘረጋ በኋላ፣ አማርኛ ቋንቋ የጋራ መግባቢያ ሆኖ እንዲያገለግል በሕገ መንግሥቱ እንደገና ዕውቅናው ተረጋግጧል፡፡ ቀደም ሲልም በመላ አገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ ሲያገለግል የቆየው አማርኛ፣ ዛሬም አብዛኛውን ዜጋ በተሻለ ደረጃ ሊያግባባ እንደሚችል ታምኖበት በጋራ መግባቢያነቱ ቀጥሏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የአገሪቱ ሕዝቦችም የየራሳቸውን ባህልና ቋንቋ ከማሳደግ ጎን ብሔራዊ ቋንቋውንም መማርና ማወቅ ጠቀሜታ እንዳለው በአብዛኛው ተገንዝበውታል ለማለት ይቻላል፡፡ አንዳንዱ ክልል በአካባቢውም ጭምር በትምህርትና በሥራ ቋንቋነቱ እየተጠቀመበት ነው፡፡ ሌላው ክልል ደግሞ የትምህርትና የሥራ ቋንቋውን የራሱ (የብሔሩ) አድርጎ፣ አማርኛን በፌዴራል ቋንቋነቱ እየተገለገለበት ነው፡፡ ሁለቱም አማራጮች በሕዝቦች የጋራ ቤት፣ በአንድነት ውስጥ መከባበር፣ ሰላም፣ ፍቅርና አብሮነትን የሚያጠናክር አካሄድ ስለሆነ መልካም የሚባል ሐሳብ ነው፡፡

ከዚሁ መልካም ሐሳብ ጋር የሚስማማና ከሳምንታት በፊት በኦሮሚያ ክልል ትምህርት ዘርፍ የተሰጠ አንድ መግለጫ ለዚህ ጽሑፌ መነሻ ሆኖኛል፡፡

መግለጫው በክልሉ ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት የሚሰጥባቸው መጻሕፍት ያስገኙት ውጤት አጥጋቢ አለመሆናቸውን ያመለክታል፡፡ ይህም በመሆኑ መጻሕፍቱ የተሻለ ውጤት እንዲያገኙ የማሻሻያና የእርምት ዝግጅቶች እንደሚደረጉላቸው ይገልጻል፡፡ ከሞላ ጎደል የመግለጫው ፍሬ ሐሳብ በዚህ ዙሪያ  ያጠነጠነ ነው፡፡

ይህ የክልሉ ትምህርት ዘርፍ መግለጫ ሙያዊ አካሄድን የተከተለ በመሆኑ መልካም ነው ብዬዋለሁ፡፡ ሥራ ከተደራጀ በኋላ ሒደቱን ተመልክቶ የተገኘን ውጤት መገምገም፣ ድክመት የታየበትን ማረም፣ ማስተካከልና ማሻሻል በትምህርቱ ሙያ ዘርፍ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ የመማሪያ መጻሕፍቱ ክለሳ የሚታየው ከዚህ አኳያ ስለሆነ በጠንካራ ጎኑ ይገልጻል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ በክልሉ የትምህርት አሰጣጥ ካሪኩለም ላይ የሚስተዋሉ አንዳንድ ችግሮችም አብረው ቢታዩ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ለአማርኛ ቋንቋ ማስተማሪያነት የሚያገለግሉ መጻሕፍት፣ በባለሙያዎች ተገምግመው ውጤታቸው ደካማ መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ መከለሳቸው አግባብነት ያለው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ግን የአማርኛ ቋንቋ ትምህርትን በኦሮሚያ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከአምስተኛ ክፍል የሚያስጀምረው ካሪኩለምስ በልጆቹ ላይ ጫና አይፈጥርም ወይሐሕዝቦች አገር ነናት፡፡ሐ? አንድ ተማሪ (ሕፃን) በተወለደ በስድስተኛ ዓመቱ መደበኛ ትምህርት ቤት ይገባል ብለን ብናስብ፣ አምስተኛ ክፍል ሲገባ የ11 ዓመት ታዳጊ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ታዳጊ በ11 ዓመት ዕድሜው አዲስ ፊደልና ቋንቋ መማር መጀመር ማለት የሚከብድ ነገር ነው፡፡

‹‹ሕፃናት አንድን ቋንቋ ሳይጨናነቁ በቀላሉ መማርና መረዳት የሚችሉት ከስድስትና ከሰባት ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ቢማሩት ነው፤›› የሚሉ የቋንቋ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ‹አዲስና ሁለተኛ ቋንቋን በማንኛውም ዕድሜ ላይ ማጥናት ይቻላል› ብለው ይከራከራሉ፡፡ ምክንያታቸውም፣ በእያንዳንዱ የዕድሜ እርከን የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ስለሚያይ ችግር አያመጣም የሚል ነው፡፡ ሁሉንም ወገኖች የሚያቀራርባቸው አንድ ሐሳብ ግን አለ፡፡ በሕፃናንነት ተምረው የተለማመዱት ቋንቋ ለአነጋገር ዘይቤ (ፕሮናውንሴሽን) ችሎታ መዳበር ምቹና ጠቃሚ መሆኑን ይስማሙበታል፡፡ ሁለቱንም ነጥቦች ይዘው የሚከራከሩ የሙያ ሰዎች ሐሳብ አከብራለሁ፡፡ ምክንያቱም እነሱ የሚያነሷቸው ጉዳዮች እንደየኅብረተሰቡ የዕድገት ደረጃና የትምህርት መረጃ መሣሪያዎች መኖርና አለመኖር ውጤታቸው የሚለያዩ በመሆናቸው ነው፡፡

በአገራችን የትምህርት አሰጣጥ ሁኔታና የቋንቋው ልዩ ባህርይ ግን፣ በፌዴራል ቋንቋነት የሚያገለግለውን አማርኛ ሕፃናት ከጅምሩ ቢያጠኑት ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ፡፡ ቋንቋው የራሱ የሆነ ሆሄያት ያሉት በመሆኑ፣ በየትምህርት ቤቱ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ቢሰጥ፣ በረዥም ሒደት ማለትም እስከ ስምንተኛ ድረስ ሕግጋቱንና አጠቃቀሙን ይገነዘቡታል፡፡ የክልላቸውን ቋንቋ ለመማሪያ የመረጡ ሕዝቦች ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች እስከ ስምንተኛ ክፍል በራሳቸው ቋንቋ መማራቸው በበጎ ጎኑ የሚታይ ነው፡፡ ሕፃናትና ታዳጊዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸው ትምህርቱን በአግባቡ  እንዲረዱት ከማስቻሉም ሌላ፣ ለባህላቸው ዕድገትም ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ በተጨማሪ ግን ከመነሻው ሊጠኑ የሚገባቸውና በቋንቋ ዘርፍ የሚወሰዱ ትምህርቶች  የክልል ቋንቋ፣ አማርኛና እንግሊዝኛ ቢሆኑ ለተማሪዎቹ ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ፡፡

በዚህ በማነሳው ሐሳብ መሠረት በኦሮሚያ ክልልም አማርኛ በቋንቋነቱ ብቻ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ለሕፃናት መስጠቱ ቢታሰብበትና ካሪኩለሙ እንደገና ቢታይ መልካም ይሆናል፡፡ ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ለቋንቋው ማስተማሪያነት የሚያገለግሉ መጻሕፍት ውጤት ማጣትም ብቻውን የመጻሕፍቱ ችግር አይመስለኝም፡፡ የመጻሕፍቱ ድክመትና ችግር የተወሰነ ድርሻ ይይዛል ብዬ አስባለሁ፡፡ የመጻሕፍቱ አጥጋቢ አለመሆንና የመሻሻላቸው አስፈላጊነት እንዳለ ሆኖ ግን፣ ካሪኩለሙንም እንደገና መፈተሽ ከድግግሞሽ አሠራር ያድናል፡፡ ታዳጊዎች አሥር ዓመት ካለፋቸው በኋላ አዲስ ሆሄያትና ቋንቋ ከአምስተኛ ክፍል ከሚጀምሩ ልክ  እንደ እንግሊዝኛውና ኦሮሚኛው፣ አማርኛውንም ከአንደኛ ክፍል ቢጀምሩት ይቀላቸዋል፡፡ ይህ የግል አስተያየቴ ሆኖ፣ ትምህርቱ ከሚሰጥባቸው የገጠር አካባቢዎችም ለመረዳት የቻልኩት እውነት ነው፡፡ የትምህርት ቢሮው የተሻለ አሳማኝ ምክንያት ካለው ግን፣ የእኔ አስተያየት ብቻ የተሻለ አማራጭ ነው የሚል ግትር አቋም የለኝም፡፡

እዚህ ላይ ሕፃናት ቋንቋውን ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ቢማሩት ይሻላል የምለው፣ በክልሉ ቋንቋው በስፋት መነገር አለበት ከሚል መከራከሪያ ሐሳብ አይደለም፡፡ ተማሪዎችም ወደ ወጣትነት ዕድሜ ሲሸጋገሩ፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግባታቸው ይጠበቃል፡፡ በዚያ የሚገናኙት ከሁሉም ክልሎች ከሚመጡ ወጣቶች ጋር ነው፡፡ በተቋማቱም ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ በአማርኛም በቀላሉ መግባባት፣ ሐሳብ መለዋወጥ፣ መማማርና መደጋገፍ ይችላሉ፡፡

ሌላው በፌዴራል መንግሥት የሥራ ዘርፎች ውስጥ የዕድል ተጠቃሚ መሆንን ይመለከታል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል የተገኘ ተወላጅ፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከወጣ በኋላ ተመልሶ የሚያገለግለው በኦሮሚያ ክልል ብቻ አይደለም፡፡ እንደ ማንኛውም ዜጋ  በፌዴራል መንግሥቱ የሥራ መስኮች ባሉ ክፍት መደቦች ሁሉ ተወዳድሮ የዕድሉ ተሳታፊ የመሆን መብት አለው፡፡ ይህ ደግሞ ብቻውን የሚሰጥ አይደለም፡፡ በሥራው መስክ ብቁ ሠራተኛ ሆኖ ለመገኘት የፌዴራል ቋንቋውን መናገር፣ መጻፍና ሐሳብን በትክክል መግለጽ መቻል አንዱ መመዘኛ ነው፡፡ ይህንን መመዘኛ ለማሟላት ደግሞ ቋንቋውን በአግባቡ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሕፃናቱ የፌዴራል ቋንቋውን ከመነሻው ጀምሮ በቋንቋነቱ እንዲያጠኑት ካሪኩለሙን ማመቻቸት ጠቀሜታ አለው፡፡

አንድ ቋንቋ በሕዝቦች መካከል መግባቢያ ሆኖ ያገለግላል ስንል፣ ማኅበራዊ ጠቀሜታ ብቻ አለው ማለት አይደለም፡፡ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጎኑም ከፍ ያለ ነው፡፡ ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ኑሮአቸውን የመሠረቱ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሌሎች ብሔሮችና ሕዝቦች ይኖራሉ፡፡ ቀደም ሲል የተሠሩ ጥናቶች በእጄ ባይኖሩም፣ ከሌሎች ክልሎች በላቀ ሁኔታ ሌሎች ብሔሮችና ሕዝቦች የሚገኙበት ክልል ኦሮሚያ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት አለኝ፡፡ እነዚህ ሕዝቦች ታዲያ ቋንቋውን ይናገራሉ፣ በጽሑፍም ይገለገሉበታል፡፡ ከፊሉ በተለይም ትምህርት ያለው በዚህ ችሎታ ተርታ ሳይመደብ አይቀርም፡፡ ቋንቋውን መናገርና መጻፍ እስከቻሉ ድረስ ደግሞ፣ በክልሉ አመራር ውስጥ በፖለቲካው የመሳተፍ፣ በሚወጡ ክፍት የሥራ መደቦች ሁሉ የመወዳደርና የመቀጠር መብት አላቸው፡፡ በርካቶች በኦሮሚያ ክልል የመቀጠር መብት አላቸው፡፡ በርካቶች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ መሥፈርቱን አሟልተው መብታቸውን በመጠቀም ላይ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ይህ የዜግነት መብታቸው ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ተወልደውና አድገው (የብሔሩ ተወላጆችም ሊሆኑ ይችላሉ) ኦሮሚኛ መናገርም ሆነ መጻፍ የማይችሉ አሉ፡፡ የክልሉን ቋንቋ መናገርና መጻፍ የማይችል አካል ደግሞ፣ ቋንቋውን ማወቅ አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት የሥራ መስክ ሁሉ መሳተፍ አይችልም ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ ከአሥር ዓመታት በፊት ሁለት ወጣቶች በአንድ የግል ጋዜጣ ላይ ያቀረቡትን ቅሬታ ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡

ሁለቱ ወጣቶች ከአዳማ ከተማ የላኩትን ቅሬታ በወቅቱ የነበረ አንድ ጋዜጣ አትሞታል፡፡ ወጣቶቹ 12ኛ ክፍል ማጠናቀቃቸውን ያወሱና ለዕጩ መምህርነት ለመወዳደር ወደ ትምህርት ቢሮው ሄደው ሲያመለክቱ፣ ቋንቋ ባለመቻላቸው ብቻ ዕድሉን መነፈጋቸው እንዳሳዘናቸው ይገልጻሉ፡፡ እዚህ ላይ የግንዛቤ ጉድለት እንዳለ እንመለከታለን፡፡ ትምህርት ቢሮው ማስታወቂያውን ያወጣው በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን ለማሠልጠን ነው፡፡ ሥልጠናው የሚሰጠው በእንግሊዝኛና በኦሮሚኛ ሆኖ ሠልጣኞቹ ሲመረቁ በኦሮሚኛ ቋንቋ የተዘጋጀውን ካሪኩለም መሠረት አድርገው እንዲያስተምሩ የታሰቡ ናቸው፡፡ ስለዚህ ቋንቋውን መናገርና መጻፍ የማይችሉ የአዳማ ወጣቶች፣ እዚያ በመወለዳቸው ብቻ ወደ መምህራን ማሠልጠኛው ለመግባትና ለመመዝገብ ማሰባቸው የግንዛቤ ችግር እንዳለ ያሳያል፡፡

ወጣቶቹን ያስታወስኩት አንዳንዶቻችን የውጭ ቋንቋዎችን ለማጥናት የምናቅደውን ያህል፣ ለአገራችን ቋንቋዎችና እውቀት ትኩረት አለመስጠታችን ትክክል አለመሆኑን ለማንሳት ፈልጌ ነው፡፡ ዛሬ ዓረብኛ፣ ማንዳሪን (የቻይና ቋንቋ) እና ሌሎችንም ለመማር ብዙዎች ፍላጎት ያሳያሉ፡፡ ቢቻል ሁሉንም የዓለም ቋንቋ ማወቅ ጥሩ ነውና ፍላጎታቸውና አከብራለሁ፡፡ ነገር ግን ለማጥናት የቻልነውን ያህል የአገር ውስጥ ቋንቋዎችንም ለማወቅ መጣር ብልህነት ይመስለኛል፡፡

የአገር ውስጥ ቋንቋዎች እንዲያድጉና ዜጎች ከአማርኛም ውጪ፣ በሌሎችም መግባባት እንዲችሉ ጥረቱ የቋንቋዎች ባለቤቶች (ብሔር አባላት) ብቻ መሆን የለበትም፡፡ አንዳንድ ባለሀብቶችም ጥናት ላይ ተመሥርተው የአገር ቋንቋዎች ትምህርት ቤቶች ቢከፍቱ የሚያከስራቸው አይሆንም፡፡

ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ኢንቨስት ለማድረግ፣ የተለያዩ ሥራዎች ለመሥራትና ኑሮአቸውን ለመመሥረት የሚፈልጉ ሕዝቦች የኦሮሚኛ ቋንቋ ለመማርና ለመረዳት ጥረት ቢያደርጉ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ፡፡ ይህ ሥራቸውንና ማኅበራዊ ሕይወታቸውን ቀላል እንደሚያደርግላቸው ይታመናል፡፡

በአጠቃላይ ቋንቋ የመግባቢያ መሣሪያ ነው ስንል ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ባህርይውን ከግምት በማስገባት ነው፡፡ ‹‹በኦሮሚያ ክልል የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ካሪኩለም ቢፈተሽና የቋንቋ ትምህርቱ ከአንደኛ ክፍል የሚጀመርበት ሁኔታ ቢመቻች›› የምለውም ከዚህ እሳቤ በመነሳት ነው፡፡ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ካሰበው የመጻሕፍቱ ክለሳ ጋር ተደምሮ ይህ የተሻለ ውጤት ያመጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኦሮሚኛ ለሚማሩ ተማሪዎችም ሆነ በአማርኛ ለሚማሩ ደረጃውን የጠበቀና ተመጣጣኝ የኦሮሚኛ ቋንቋ ትምህርት መስጠቱ ተገቢ ነው፡፡ በኦሮሚያ ከተሞች የአንደኛ ደረጃ ትምህርት በኦሮሚኛና በአማርኛ ቋንቋዎች የመሰጠቱን ያህል፣ በኦሮሚኛ የማይማሩት ከደረጃው ዝቅ ያለ የኦሮሚኛ ቋንቋ ችሎታ እንዳይኖራቸው ጥረትና ጠንካራ አመራር ይጠይቃል፡፡ ከአንድ ክልል ተምረው የሚወጡ ተማሪዎች ከፊሉ ጠንካራ የኦሮሚኛ ችሎታ አዳብሮ ሲወጣ፣ ሌላው ቋንቋውን በአግባቡ መጠቀምና ራሱንም መግለጽ አለመቻሉ አሳሳቢ ነው፡፡ ስለዚህ በአማርኛ ቋንቋ የሚማሩ ተማሪዎችም ቢሆኑ፣ ኦሮሚኛን በቋንቋነቱ በአግባቡ ተምረው ብቁ ሊሆኑ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ የተማሪዎቹ የግል ጥረትና ፍላጎት ትልቅ ድርሻ ቢኖረውም፣ የትምህርት ቤቶች አመራርና ክትትልም ወሳኝነት አለው፡፡ ቋንቋዎቻችንን በአግባቡ መጠቀም፣ ማዳበርና የትምህርት ይዘታቸውን ገምግሞ ማረም ተገቢ ነው፡፡

በቋንቋዎቻችን መነጋገር፣ መደማመጥና መወያየት ወደ መግባባት ያሸጋግራል፡፡ መግባባት የቻለ ሕዝብ ደግሞ በመከባበር ወደ ጠንካራ ኅብረት ይደርሳል፡፡ ቋንቋዎቻችን ወደዚህ ሁሉ የሚያደርሱን ድልድዮች ናቸውና የቻልነውን ያህል ብናጠናቸውና ብንገለገልባቸው ጠቀሜታው ለሁላችንም ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 ሐሕፃናት አንድን ቀቋንቋ ሰሳይሕ

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...