Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበርኖስ እና መላወሻ

በርኖስ እና መላወሻ

ቀን:

በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች መደበኛው ክረምት ተያይዞታል፡፡ የዝናብ ኮቴ በመሰማቱ ቁርና ቅዝቃዜውም በርትቷል፡፡ ኅብረተሰቡ አለባበሱንም ከክረምት ጋር ሲያስማማ ይታያል፡፡ ‹‹በክረምት በርኖስክን አታውል ከቤት›› የሚል ብሂል አለ፡፡ ከጥቁር በግ ፀጉር የሚሠራው በርኖስ የተሠራው ለሙቀት ስለሆነ ለክረምት ተጠቀምበት የሚል ምክር ለመስጠት የሚውል ብሂል እንደሆነ ይታመናል፡፡

በርኖስ በሰሜን ሸዋና በጎጃም የሚታወቅ ሀገረሰባዊ ልብስ ነው፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በሰሜን ሸዋ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች ባደረገው የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ምዝገባና ቆጠራ (ኢንቬንቶሪ) ላይ ከተመለከታቸው ባህላዊ እሴቶች መካከል የወንዶች ልብስ የሆነው ‹‹በርኖስ›› እና የሴቶች ልብስ ‹‹መላወሻ›› ይገኙባቸዋል፡፡

በርኖስ

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በርኖስ በበግ ፀጉር የሚሠራና በካባ መሰል ቅርጽ ተዘጋጅቶ የሚለበስ ሀገረሰባዊ ልብስ ሲሆን፣ በአብዛኛው የሚለበሰው በጣም ቀዝቃዛና ደጋማ በሆኑ አካባቢዎች ነው፡፡ በርኖስ የእጅ ማስገቢያ እጅጌ እንዲሁም በቀኝ ትከሻ በኩል ወደላይ ቀጥ ብሎ የወጣና እንደጌጥ የሚያገለግልና የመሣሪያቸውን አፈሙዝ ደግፎ በመያዝ አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ በርኖስ በጥንት ጊዜያት በቀዝቃዛና በደጋማ አካባቢዎች የሚለበስ የዘወትር ልብስ የነበረ ሲሆን፣ በሌሎች የማኅበረሰቡ አካባቢዎች ግን ተጨማሪ አገልግሎት አለው፡፡ በዚህም መሠረት በሠርግ ጊዜ ሴቷ ሙሽራ ለወላጆቿ ቤት ወደ ወንዱ ቤተሰብ ስትሄድ የምትለብሰው ልብስ ሲሆን፣ በሙሽራውም የክብር ልብስ በመሆን ያገለግላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በርኖስ ወንዶች/አባቶች በሐዘን ጊዜ የሚለብሱና ሐዘን እንደገጠማቸው የሚያመለክት ሲሆን፣ በጎጃም ማኅበረሰብ አንድ ሰው በርኖስ ገልብጦ በውስጠኛው መልክ ከለበሰ ሐዘን እንደደረሰበትና የቅርብ ዘመዱን በሞት እንደተነጠቀ ያመለክታል፡፡

በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ በርኖስ የሚለበሰው በሽምግልና ወቅት፣ ለጋብቻ ጥየቃ ጊዜ፣ በክብረ በዓላት ወቅት/ጥምቀት፣ ገና፣ ፋሲካ፣ በለቅሶ ወቅት፣ በተለይም ትልልቅ ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ በአጠቃላይ በክብር ቦታዎች ላይ የክብር መገለጫ ሆኖ የሚለበስ ነው፡፡ በአካባቢው ማኅበረሰብ በርኖስ የሚለብሱት አዛውንቶች፣ ታዋቂ ወንዶችና የትልልቅ ሰዎች ባለቤት፣ ለልጆቻቸው አርአያ መሆን የቻሉ ጨዋ ሴቶች ሲሆኑ፣ ወጣቶች አይለብሱም፤ እንዲለብሱም አይፈቀድም፡፡ ወንዶቹና ሴቶቹ የሚለብሱት በርኖስ ልዩነቱ አሰፋፉ ላይ ብቻ ነው፡፡ አሠራሩ ግን ተመሳሳይ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የለቅሶ ጊዜ አለባበስን በተመለከተ የውስጡ ወደላይ ተገልብጦ እጀታው ታጥፎ ሲሆን፣ በደስታ ጊዜ ግን በትክክለኛ መልኩ በኩል እጀታው ብቅ ብሎ ይለበሳል፡፡ ከዚህ ሌላ በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ አንድ ሐዘን የደረሰበት ሰው ሐዘንተኛ መሆኑን ለመግለጽ በርኖሱን ገልብጦ በመልበስ ይታወቃል ሲሉ መረጃ ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡

በርኖስ እንዴት ይዘጋጃል?

የበርኖስ ሥራን ለመሥራት በጥሬ ዕቃ አቅርቦት የሚመረጠው የጥቁር ጠቦት በጎች ብቻ መሆኑ፣ የበጎቹ የጸጉር ቁርጥ ወይም ሽለታ የመጀመሪያ ብቻ መሆኑና ሁለተኛ ቁርጥ አለመሆኑ ነው፡፡

ከዚህ ሌላ በርኖሱ ከተሸመነ በኋላ አረጋገጡ ከባና ዝግጅት መለየቱ ነው፡፡ ይኼውም የበርኖሱን የመጀመሪያ የሽመና ሥራ ወይም ሽክሽክ ጸጉሩ እንዲደፍንና እንዲለሰልስ በሚል ለመጀመሪያ ጊዜ ለሁለት ቀናት ያህል ሳይቋረጥ ይረገጣል፡፡ ከዚህ በኋላ በቀጥታ ለአገልግሎት ከመዋሉ በፊት አልጋ ወይም ቁርበት ስር እስከ አንድ ወር ድረስ ተነጥፎ ይቆያል፡፡ ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ለሦስት ቀናት ያህል በድጋሚ ተከልሶ ይረገጣል፡፡

በዚህ ሁኔታ ተረግጦ ጸጉሩ ከለሰለሰ በኋላ ፀሐይ ላይ እንዲደርቅ ይደረጋል ከደረቀ በኋላ እየተቀደደ ቅርጹን በማውጣት በዶሮ ላባ ይሰፋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ስፌቱ ካለቀ በኋላ በ‹መሀራረብ› ጃኖ መልክ ክር ዙሪያውን በመቀምቀም ለአገልግሎት ይውላል፡፡ የበርኖስ ሥራ ላይ ወንዶቹም ሆነ የየራሳቸው ተሳትፎ አላቸው፡፡

ሴቶቹ የበጉን ጸጉር በማባዛት ወይም መፈታታት፣ በመፍተል፣ በማዳወርና የመሳሰሉት ወንዶች ደግሞ በጎቹ ከማጠብ ጀምሮ በመሸመን፣ በውኃ ዘፍዝፎ በመርገጥ፣ በርኖሱን ቅርጹን ጠብቆ ሰፍቶ ለአገልግሎት እስኪውል ድረስ ባለው ሒደት ተሳትፎ አላቸው፡፡ የበርኖስ ሥራ ካባና ሥራ የሚለየው የሚለበስበት ጊዜ የተለየ መሆኑ ነው፡፡

‹‹መላወሻ››

በማንኛውም የኀብረተሰብ ክፍል ሴቶቹም ሆኑ ወንዶቹም የየራሳቸው የአለባበስ ሥርዓት አላቸው፡፡ ከዚሁ ጋር የሥራ፣ የቤት፣ የክትና የአደባባይ ልብሶች ተብለው እንደየሁኔታው ተለይተው የሚለበሱ ልብሶችም ይኖራሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በመንዝ ማኅበረሰብም ‹‹መላወሻ›› የሴቶች የክትና  የክብር ልብስ ተብሎ የሚታወቅ እንደሆነ መረጃ ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡

መላወሻ እንደ ዝተትና ባና ተመሳሳይ የሽመና ቁሳቁስና የአሸማመን ወይም የአሠራር ሥርዓት አለው፡፡ የመላወሻ ዕደ ጥበብ ውጤት ከሌሎች የዕደ ጥበብ ውጤት የሚለየው የበጎቹ የፀጉር ሁኔታ ነው፡፡ ሥራውን ለማከናወን ከሕፃናት በቀር በየደረጃው ያሉ ሴቶችም ሆነ ወንዶቹ ይሳተፋሉ፡፡

በዚህ ሥራ የሴቶቹ ተሳትፎ ፀጉርን ማብዛት፣ መፍተል፣ ማዳወርና መንደፍ ይሆናል፡፡ ወንዶቹ በበኩላቸው በጉን በማጠብ፣ የበጉን ፀጉር በመሸለት ወይም በመቁረጥ፣ በመሸመን፣ በመርገጥና በመገተር ወይም በመወጠር ይሳተፋሉ፡፡ የመላወሻ ሥራ ዕውቀት የተገኘው እንደባናና ዝተት ሥራ ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣ ከቤተሰብና ከሙያው ባለቤቶች ሙያውን በመልመድና በመቅሰም እንደሆነ መረጃ ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡

የመላወሻ ዕደ ጥበብ ውጤት የሴቶች ብቻ የክት ልብስ ሲሆን፣ አለባበሱ እንደጉርድ ቀሚስ ዙሪያውን በመቀነት ሰብስቦ በማሰርና ከላይ እንደ አላባሽ ጥለት ያለው ነጠላ በትከሻና ትከሻቸው ነጥሎ፣ እንደሁኔታውም በሐዘን ወቅት ጥለቱን አዘቅዝቆ በመልበስ እንደሆነ መረጃ ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...