ገብረክርስቶስ ሰሎሞን በላቸው አብዛኛውን የሥነጥበብ ጊዜውን የሚያሳልፈው በራሱ የጥበብ መደብር ነው፡፡ መቶ ሠላሳ ዓመታትን ባስቆጠረችው አዲስ አበባ ጥንታዊ ማዕከል፣ ከፒያሳ ማህል ወደ ጣይቱ ሆቴል በሚወስደው መንገድ ከዕውቅ የስጦታ ዕቃዎች መደብሮች ባንዱ የጥበብ ገበታውን ይዟል፡፡
መደብሩ ውስጥ ለገበያ የቀረቡ የዕደጥበብና ሥነጥበብ ሥራዎች ብቻ አይደሉም የሚገኙት፤ ለዘመናት ሠዓሊው ገብረ ክርስቶስና ቤተሰቦቹ የሰበሰቧቸውን የጥበብ ሀብቶች ይገኙበታል፡፡
የአባቱን የሰሎሞን በላቸው የጥበብ ዱካ ብቻ ሳይሆን የአያቱን በላቸው ይመር ጎሹ ጭምር ተከትሏል፡፡ ምንም እንኳ በወጣትነቱ የነበረው የሙዚቃ ዝንባሌ በዙላ ክለብ የነበረው ጨዋታውን ትቶ እንደ አያቱና እንደ አባቱ ከሥዕል ገበታው ላይ ተቆናጧል፡፡ ከድምፃዊነት ወደ ሠዓሊነት ለዚያውም ትውፊታዊውን የኢትዮጵያ አሣሣል ጥበብን ተቆናጦ ዘልቋል፡፡
እንደ አባቱና አያቱ ገብረክርስቶስ በሠዓሊነት እንዲተጋ ወላጁ መገፋፋታቸው አልቀሩም፡፡ የገብረክርስቶስ አያት በ19ኛ ምዕት ዓመት መገባደጃ ከተነሱት ግንባር ቀደም ሠዓልያን ዝነኛ የነበሩት በላቸው ይመር፣ ትውልዳቸው የሚነሳው ከጎጃም ጠቅላይ ግዛት ብቸና አውራጃ፣ የጠም አቦ አጥቢያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ታሪክ በተለይ የሚወሱበት የንግሥተ ሳባ ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ያደረገችው ጉዞና ቀዳማዊ ምኒልክን ስለመውለዷ የሚያሳየው ሥዕላዊ ተረካቸው ነው፡፡ የሠዓሊ ገብረክርስቶስ አያትና አባት ሌላው የሚጠቀሱበት በወራሪዎቹ ጣሊያውያን ላይ በዓድዋ ጦርነት የተገኘውን ድል በሚያሳዩበት ሥዕሎቻቸው ነው፡፡
በሥዕሉ ጐልተው ከሚታዩት ከጠቅላይ አዝማቹ ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ በተጨማሪ አዝማቾች፣ መካከል ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ራስ መንገሻ፣ ራስ አሉላ፣ ራስ አባተ፣ ደጃዝማች ባልቻ ይጠቀሳሉ፡፡ ከአዝማሪዎች መካከልም አዝማሪ ፃዲቄ እየሸለለችና እየፎከረች ስታዋጋ የሚያሳይ ሥዕልም የዘመኑ ትሩፋት ነው፡፡
አዝማሪዎች ለኢትዮጵያ ሠራዊት ይሰጡት የነበረው ወኔ ቀስቃሽ አዝመራ ጉልህ ነበር፡፡ ስለነዚያ አዝማሪዎች ቤርክሌይ ከጉዞው ጋር አያይዞ የጻፈው የሚጠቀስ ነው፡፡
«. . . በሠራዊቱ መሀል አዝማሪዎችም አብረው ይዘምታሉ፡፡ በዚያ ሁሉ ሁካታ አዝማሪዎቹ ዘማቹን እያጫወቱ ይሄዳሉ፡፡ አብሮአቸው የሚጓዘው ሠራዊትም ለአዝማሪዎቹ ግጥም ይነግሩዋቸዋል፡፡ አዝማሪዎቹ የደከመውን በግጥም እያበረታቱ ይጓዛሉ፡፡» በዚያን ጊዜ ነው አዝማሪ ፃዲቄ፡-
‹‹ወንድሜ ራበህ ወይ? ወንድሜ ጠማህ ወይ
አዎን የናቴ ልጅ እርቦህ ጠምቶሃል
ታዲያ የናቴ ልጅ አዳኝ ወፍ አይደለህም ወይ?
ግፋ ብረር ወደፊትህ ሂደህ ጠላትህን አትበላም ወይ?
ግፋ ወደፊት ከበዓሉ ቦታ ፈጥነህ ድረስ
የምታርደውን ሥጋ የማቆራርጥልህ እኔ ነኝ
ግፋ የናቴ ልጅ ውሃ ጠምቶሃል
ጠጅ ብታጣ ደሜን እንድትጠጣ እሰጥሃለሁ›› እያለች እየሸለለችና እየፎከረች ያዋጋችው፤ በላቸው ይመር ጎሹም በሥዕሉ ገበታ ያኖረው፡፡
በ1940ዎቹ አጋማሽ በላቸው ይመር በከፈቱት የራሳቸው ስቱዲዮ ሥራቸውን ሲያከናውኑ በእንጦጦ በሚገኙት አብያተ ክርስቲያናትም በሥዕሎች በማስዋብ በኩል ከሌሎች ጋር ተሳትፈዋል፡፡
‹‹አንዳንድ የታወቁ የኢትዮጵያ ሠዓሊዎች አጭር የሕይወት ታሪክ 1862-1950 ዓ.ም. Short Biographics of Some Well-Know Ethiopian Artists 1869-1957›› በሚል ርዕስ በታዬ ታደሰ በተዘጋጀው መደበል ላይ በቀዳሚነት የተጠቀሱት በላቸው ይመር ናቸው፡፡ 1862 ዓ.ም. ሠዓሊ በላቸው የተወለዱበት ዓመት በመሆኑ ከ19ኛው ምዕት ዓመት አጋማሽ ወዲህ ላለው የኢትዮጵያ የሥዕል ታሪክ መነሻም ሆነዋል፡፡
የ1933 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ልዩና ታሪካዊ ዓመት ነው፡፡ ወራሪው የፋሺስት ጣሊያንን ሠራዊት ከአምስት ዓመታት ተጋድሎ በኋላ የተወገደበት፣ የሚያዝያ 27 ቀን የድል ብሥራት የታወጀበት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡
የዓድዋውን ድል በጥበባቸው የዘከሩት ሠዓሊው በላቸው፣ ለሁለተኛው የጣሊያን ጦርነት በድል መጠናቀቅም በቡሩሻቸው ዳሰውታል፡፡ በመዝሙረ ዳዊት የሚገኘውን ‹‹ኢትዮጵያ ታበጽህ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር›› (ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች) ከሥዕሉ አናት ሆኖ፣ እግዚአብሔር ከሰማያት ላይ ሆኖ ንግሥቱ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ብጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማን ይዛና እጆቿን ዘርግታ ሥዕሉ ያሳያል፡፡ በግራና ቀኝ በአደይ አበባ ቀንበጦች ሥር የኢትዮጵያና ፋሺስት ጣሊያንን ለማስወገድ ከኢትዮጵያ ጎን የተሰለፈችው የብሪታኒያ ሰንደቅ ዓላማዎች ይታያሉ፡፡ በተራሮች ራስጌ ብቅ ያለችው ባለጋሻዋ ፀሐይ አናት ላይም ‹‹የብሪታኒያ ፀሐይ ለኢትዮጵያ እንዳበራች›› የሚል ጽሑፍ፣ እንዲሁም በሰንደቅ ላይ በተሰቀለው ዓላማ ‹‹ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› (የአሸናፊው አንበሳ ነገድ የሆነው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) የሚል ጽሑፍ ከፈረሰኛው ጊዮርጊስ ጋር ተሸልሟል፡፡ ሰንደቅ ዓላማውን የያዘው ዘውድ የደፋ አንበሳ ነው፡፡
የ1952 ዓ.ም. መካተቻ ጳጉሜን 5 ቀን ለኢትዮጵያ ብሎ ለአህጉሪቱ አፍሪካ ልዩ ነበረች፡፡ በኦሊምፒክ ታሪክ ጥቁር አፍሪካዊው አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ በሮም ኦሊምፒክ የማራቶንን ድል የተቀዳጀበት፡፡ ከአራት ዓመት በኋላም አበበ ቢቂላ በቶኪዮ ዳግመኛ በማራቶን ድል መታ፡፡ በኦሊምፒክ ታሪክ የመጀመሪያው በተከታታይ ድል ያስመዘገበ ተብሎ በወርቅ ቀለም ተጻፈለት፡፡ የገብረክርስቶስ አባት ጠቢቡ ሰሎሞንም በትውፊታዊው ቁርጥራጭ ያሣሣል ጥበብ፣ የአበበ ቢቂላን የድል ጉዞ ከልደቱ እስከ ዕድገቱ የክብር ዘበኛ ሕይወቱ ጭምር ባካተተ በገበታው አቅርቦታል፡፡
ባለ 28 ክፍሉ የአበበ ቢቂላ ገበታ ሕፃኑ አበበ ከወላጆቹ ጋር፣ በልጅነቱ ገና ሲጫወት፣ ለእናቱ በሩጫ ሲላላክ፣ በሬ ጠምዶ ሲያርስ፣ አረም ሲያርም፣ የክብር ዘበኛ ሠራዊት በወታደርነት ሲቀጠር፣ በደብረ ዘይት መንገድ ሲሮጥ፣ በሮምና ቶኪዮ ኦሊምፒክ ድል ሲያደርግ፣ አዲስ አበባ በድል አድራጊነት ሲመለስ፣ የነበረው አቀባበል፣ ‹‹መኩሪያ›› የተባለው የጃንሆይ አንበሳ ለአበበ አቀባበል ሲያደርግለት፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሲሸልሙት ወዘተ. ያሳያል፡፡
በአያት ተጀምሮ በአባት የቀጠለው የገበታ አሣሣል፣ ገብረክርስቶስም ቀጥሎበታል፡፡ በኢትዮ ኤርትራ የ1990 ዓ.ም. ጦርነት ዘምቶ በተሰዋ ወጣት ላይ ተመሥርቶ ሠርቶታል፡፡
ሠዓሊ ገብረክርስቶስ እንደሚለው የገበታውን ሥዕል እንዲሥል ያሳሰበችው ሆላንዳዊቷ ሳም ሳም ናት፡፡ ከላሊበላ የተመለመለው ወጣት በጦርነቱ ሕይወቱ ያልፋል፡፡ በቁርጥራጭ የሥዕል ገበታ ገብረ ክርስቶስ እንደ ሳባና ሰሎሞን፣ እንደ አበበ ቢቂላ አሣሣል ታሪክ ፈጥሮለት ሣለው፡፡ እንደርሱ አገላለጽ፣ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ታሪኩ የተባለ አንድ ወጣት ተማሪ ከላሊበላ ተመልምሎ ይሄዳል፡፡ አባቱ ጥበቃ ናቸው፡፡ ያገሩን ሰው ተሰናብቶ ሲሄድ፣ በቴሌቪዥን ሲነገር እህቱ ከጦር ሜዳ የተላከላትንና የታንክ መካኒክ መሆኑን የሚገልጸውን ደብዳቤ ስታነብ ያሳያል፤ ጦርነቱ ያልቅና ዘማቾች ሲመለሱ ታሪኩ ወሬው የለም፡፡ አንድ ማለዳ ጥይት እየተተኮሰ መርዶ ሲነገር፣ እህቱ ተላጭታ፣ ሐዘን ተቀምጠው፣ የላሊበላ ካህናት ፍታት ሲያደርጉ፣ መንግሥት ካሳ ሲከፍል የገበታው ሥዕል ያሳያል፡፡
ገብረ ክርስቶስ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ ባሻገር ዘመናዊውን ያሣሣል ጥበብ በአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት (በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘው) በመቅሰም በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡
በእቴጌ እጅጥበብ ትምህርት ቤት (የዕደጥበባት ማዕከል) የቀሰመው ትምህርትም ለጥበባዊ ሥራው አስተዋጽኦ አድርጎለታል፡፡ የአዲስ አበባ ሆቴሎችና የቀድሞው ቱሪዝም ኮሚሽንና ‹‹አእማድ›› ይባል የነበረው የአነስተኛ እንዱስትሪዎች ማስፋፊያ ድርጅት (ያሁኑ አነስተኛና ጥቃቅን) ከሥራዎቹ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በሸክላ ሣህን ላይ የታተሙትና በገበያ ላይ ያሉት የነገሥቱ ሳባና ሰሎሞን ምስሎች የገብረክርስቶስ ትሩፋት ናቸው፡፡
በ1970ዎቹ መጀመሪያ የራሱን ሥራ መሥራት በጀመረበት ጊዜ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንስ ከነጥበበ ተርፉ፣ ተሰመ በቀለ ጋር ዐውደ ርዕይ አሳይቷል፡፡
ፒያሳ በሚገኘው ስቱዲዮው/መደብሩ የውጭ ቱሪስቶችን ቀልብ መግዛቱ አልቀረም፡፡ ኢትዮጵያውያንን ቢጎበኙትም መግዛቱ ላይ ግን እምብዛም ናቸው ይላል፡፡ አብዛኞቹ ገዥዎች የውጭ አገሮቹ ጎብኚዎች ናቸው፡፡
በመደብሩ የሚሸጣቸው የሌሎች ሠዓሊዎችም ሥራዎች አሉት፡፡ ከገብረ ክርስቶስ ስብስቦች አንዱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከዊንስተን ቸርችል ጋር በ1937 ዓ.ም. በተገናኙበት ጊዜ የተነሱት ፎቶ በሥዕል የተቀናበረው ነው፡፡
በ1862 ዓ.ም. ተወልደው በ1960 ዓ.ም. ያረፉት ሠዓሊ በዓላቸው ይመር ጎሹ፣ ያላቸውን የፈጠራ ችሎታ ያንፀባረቁባቸው በርከት ያሉ ሥራዎችን ትተዋል፡፡ ከዓድዋ ጦርነትና ከንግሥተ ሳባ ጉዞ በተጨማሪ፣ የአውሬ ማኅበር፣ የአይጥና ድመት ጋብቻ፣ የጌዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፣ የሐረር ቅድስት ሥላሴ፣ ኢትዮጵያ እጆቿን ዘርግታ፣ የመተማ ጦርነት ይገኙበታል፡፡ አንዳንዶቹ ሥራዎቻቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ይገኛሉ፡፡
አባቱ ሰሎሞን በላቸው ከአባቱ በላቸው ይመር ባገኘው ትምህርት ከሠራቸው ሥዕሎች መካከል ፈርኦን ሙሴን ሲያሳድድ፣ የዓድዋ ጦርነት፣ ዳዊት በበገና ይገኙበታል፡፡ የሰሎሞን ወንድም ግርማ በላቸውም እንዲሁ ሠዓሊ ነበር፡፡
‹‹አያቴ በልጅነቱ ጎንደር ሄዶ ቤተክርስቲያንን እያገለገለ ሥዕል ተማረ፤ አዲስ አበባም መጥቶ በሙያው አገለገለ፡፡ ሥዕል ሸጦ መኖር እንደሚቻል ያስተማረ አያቴ በላቸው ይመር ነው፤›› የሚለው ሠዓሊ ገብረክርስቶስ፣ የቀደምት ሠዓሊዎች ብላታ እምአዕላፍ ኅሩይ፣ አገኘሁ እንግዳ፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታና የመምህሩ ዳንኤል ጧፌ ሥዕሎች በእጁ ይገኛል፡፡
ከሃይማኖት፣ ከባህልና ከታሪክ ጋር የተያያዙትን ሥራዎች የሚያመርቱት የገብረ ክርስቶስ እጆች አሁንም አልቦዘኑም፡፡ በሊዮናርዶ ዳቪንቺ የተሣለው ‹‹የመጨረሻ ራት›› መነሻ ሆኖት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐዋርያቱ ጋር ያሳለፈበትን የጸሎተ ሐሙስ ምሽት በኢትዮጵያ ባህላዊ አሣሣል አቅርቦታል፡፡
‹‹ያድዋ ጦርነትን አያቴም፣ አባቴም ሠርተውታል፤ ያያቴን ኮፒ በማድረግም ለየት ባለ መልኩ ሠርቸዋለሁ፤››የሚለው ገብረክርስቶስ፣ ከአያት በአባት በኩል እርሱ ዘንድ የደረሰው የሥዕል ጥበብ የወለዳቸው ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት እንደ ሙያ አልያዙትም፡፡ አንደኛው ልጃቸው በሙያው ባይኖርበትም ዝንባሌ አለው፤ ለስሜቱ ይሠራል፡፡
ሠዓሊ ገብረክርስቶስ የቅርብ ትዝብቱን እንዲህ ገልጾታል፡፡ ‹‹የራሳችን የሥዕል አሠራር ዘዴ አለን፡፡ የጥንቶቹ ቤተ ክርስቲያኖች እየፈረሱ አዳዲስ እየተሠሩ ሲመጡ የጥንት የሥዕል አሻራቸውን በመተው ነው፤ ታሪካችንን እየረሳን ነባሩን ሥዕል እያጣነው ነው፡፡ የውጪው ሥዕል እየተቀዳ ከታሪካችን ጋር እየተጣላን ነው፤ መስተካከል አለበት፡፡››