Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበፈጠራ ሥራዎች ሕጋዊ መብት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥር አነስተኛ ነው ተባለ

በፈጠራ ሥራዎች ሕጋዊ መብት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥር አነስተኛ ነው ተባለ

ቀን:

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በ2009 ዓ.ም. 388 የፓተንት የምዝገባ ጥያቄዎች ቀርበውለት ለ102ቱ ሰርተፍኬት መስጠቱንና ከእነዚህም መካከል ሦስቱ በኢትዮጵያውያን የተያዙ መሆናቸውን አስታወቀ፡፡ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን በሕግ የማስጠበቅ ባህሉ አለመዳበሩም በፈጠራ ሥራዎች ረገድ ሕጋዊ መብት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥር አነስተኛ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል ተብሏል፡፡

የፓተንት መብቶች በውጭ አገር ዜጎች ሊያዙ የቻሉበትን ሁኔታ አስመልክቶ የጽሕፈት ቤቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ስንታየሁ ታደሰ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፓተንት ምዝገባ መስፈርቶች ለአገር ውስጥ የፈጠራ ባለሙያዎች ከባድ መሆናቸው የፓተንት መብቶች በአብዛኛው በውጭ ዜጎች እንዲያዙ ምክንያ ሆኗል፡፡

አንድ የፈጠራ ሥራ ባለሙያ ሕጋዊ የፓተንት መብት ጥበቃ ለማግኘት ፈጠራው በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ መሆን፣ ተግባራዊነቱ፣ ተፈጻሚነቱና ፈጠራዊ ብቃቱ ተመርምሮ መረጋገጥ እንዳለበት የተናገሩት አቶ ስንታየሁ፣ ‹‹ባደጉ አገሮች አንድ የፈጠራ ሥራ የሚሠራው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ሥር በበርካቶች ርብርብ ነው፡፡ ብዙ ዕውቀት ፈሶበት ትልቅ በጀት ተይዞለት ነው፡፡ እኛ አገር የሚሠሩ አብዛኛዎቹ ፈጠራዎች በግለሰብ ደረጃ ናቸው፤›› በማለት የአገር ውስጥ የፈጠራ ባለሙያዎችን የሚያበረታታ አሠራር ብዙም አለመለመዱ በፓተንት የመብት ጥበቃ ሥር የተቀመጡ መስፈርቶችን አሟልቶ ለመሥራት የሚቸገሩበት ሁኔታ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡ 

አብዛኛዎቹ ግለሰቦች ከሚያዩዋቸው ችግሮች በመነሳት ለችግሮቹ መፍትሔ ይሆናሉ የሚሏቸውን ፈጠራዎች ቀድመው በነበሩት ላይ በማከል መጠነኛ ማሻሻያ ያደርጋሉ፡፡ ለዚህም አዲስ ለጨመሩት ፈጠራ ብቻ የግልጋሎት ሞዴል (utility model) መብት ያገኛሉ፡፡ አገር ውስጥ  ያልነበረ ነገር ግን በሌላው ዓለም ፓተንት ለተሰጠውና የጥበቃ ጊዜው ያለፈበትን ወደ አገር ለሚያስገቡም የአስገቢ ፓተንት ይሰጣቸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ፈጣሪዎች ከፓተንት ይልቅ በእነዚህ የመብት ጥበቃዎች እንደሚካተቱ ከቀረበው ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

‹‹ፈጠራው በግልጋሎት ሞዴል ወይም በፓተንት ይመዝገብልኝ የሚሉት ራሳቸው ባለቤቶቹ ናቸው፡፡ እኛም በዚህኛው ሞዴል መመዝገብ አለበት ብለን አንወስንም፡፡ ግን አማራጮቹን እንነግራቸዋለን፡፡ ከዚህ ተነስተው ፈጠራቸው በምን ሞዴል ይመዝግብ የሚለውን ይወሰናሉ፤›› ብለዋል አቶ ስንታየሁ፡፡

የንግድ ምልክት፣ ኮፒራይት፣ ኢንዱስትሪያዊ ንድፍና ፓተንት ዋና ዋናዎቹ የአዕምሯዊ ንብረት ዘርፎች ናቸው፡፡ ፓተንት ለአንድ አዲስ የፈጠራ ሥራ ወይም ከዚህ ቀደም በነበረ ፈጠራ ላይ ለተደረገ አዲስ የማሻሻያ ሥራ የሚሰጥ መብት ነው፡፡ ለተወሰነ ጊዜ የሚያገለግል ሕጋዊ የጥበቃ መብት ሲሆን፣ የጥበቃ ጊዜው እስኪያልቅ ድረስም ከባለቤቱ ፈቃድ ውጪ ፈጠራውን በሕገወጥ መንገድ ጥቅም ላይ እንዳይውል ጥበቃ ይደረግለታል፡፡

በሌላው ዓለም የፓተንት መብት ጸንቶ የሚቆየው ጥበቃ ለማግኘት ማመልከቻው ከገባበት ጊዜ አንስቶ ለ20 ዓመታት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ግን መብቱ የሚቆየው ማመልከቻው ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ በሚኖሩት 15 ዓመታት ነው፡፡  ባለመብቱ መብቱን የማከራየት፣ የመሸጥ፣ በውርስ የማስተላለፍ፣ በጋራ የመገልገል መብት ይኖረዋል፡፡ ይሁንና ንግድ ነክ ባልሆኑ ተግባራት አንዲሁም ፓተንት የተሰጠበት ፈጠራ ለሳይንሳዊ ምርምርና ሙከራዎች ዓላማ የሚውል ከሆነ የባለመብቱን ፈቃድ መጠየቅ ሳያስፈልግ መጠቀም እንደሚቻል የፓተንት ምንነትና የመብት ጥበቃው በኢትዮጵያ በሚል በአቶ ስንታየሁ የተዘጋጀው ሰነድ ያሳያል፡፡

ኢትዮጵያውያን የፈጠራ ሥራ ባለሙያዎች የሚገጥማቸውን ችግር ለመቅረፍም የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ጽሕፈት ቤቱ የ2009 ዓ.ም. በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ባቀረበበት ወቅት ተነግሯል፡፡

ጽሕፈት ቤቱም በግልጋሎት ሞዴል ዘርፍ 845 ሰርተፍኬት መስጠቱን፣ ከእነዚህም ውስጥ 834ቱ በኢትዮጵያውያን የተያዙ መሆኑን፣ እንዲሁም ለ2,665 የአገር ውስጥና ለ5,080 የውጭ አገር ተቋማት የንግድ ምልክት ሰርተፍኬት መስጠቱን፣ 758 የኢንዱስትሪያል ዲዛይንና 145 አስገቢ ፓተንት ሰርተፍኬትም መስጠቱን አስታውቋል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ደንቡ ከተዘጋጀበት ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በቅጂ መብት 966 ሰርተፍኬት መስጠቱም ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...